Wednesday, 1 January 2014


 




  
ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወጡ (ያፈነገጡ) ሰዎች የሚመለሱት እንዴት ነው? አትም ኢሜይል
 መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዲ/ን ያረጋል አበጋ

፩. የቤተ ክርስቲያን ምንነት፣ ዓላማና ተልእኮዎች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው በአጭር ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ አካል ስትሆን፣ አማንያን ደግሞ የተለያዩ የአካል ክፍሎቿ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለቤቷና መሥራቿ እግዚአብሔር ሲሆን ከእግዚአብሔር ጋር መንፈሳዊ ኅብረትና ግንኙነት ያላቸው መንፈሳውያን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ አንድ ሰው በሃይማኖትና በምሥጢራት አማካይነት ወደዚህች ጉባኤ ሲገባ የዚህ ጉባኤ (ኅብረት) አካል ሆኖ ይሠራል፡፡ ሐዋርያው “ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው” በማለት ያስረዳው ይህን ነው፡፡ 1 ቆሮ. 1፡9 እንዲሁም “ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም” የሚለው ቃል ይህን የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እሳቤ ያሳያል። ኤፌ. 2፡19-22 ይህች እግዚአብሔር የመሠረታት ጉባኤ (ማኅበር) ቀዳማዊት ናት፤ “ተዘከር ማኅበረከ ዘአቅደምከ ፈጢረ - አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን አስብ” ያለው ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 73፡2
የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መሠረት ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ ሃይማኖት ደግሞ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አንድና ብቸኛ እውነት ነው፡፡ ሐዋርያው “ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት እንዴት መኖር እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው” ያለው ለዚህ ነው፡፡ 1 ጢሞ. 3፡15 ይህ የቤተ ክርስቲያን አምዷ (ምሰሶዋ) የሆነው እውነትና ሃይማኖት ካልተጠበቀ ወይም ችላ ከተባለና እግዚአብሔር ከገለጠው እውነት ጋር እንሸቃቅጠው ከተባለ ቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋ ስለማይፈቅድላት እንዲህ ያለ ነገር መቀበል አትችልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረቷ እና ዓምዷ እውነት ነውና፡፡

፪. የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ባሕርያት

ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን እርሷነቷን ለመግለጽ የሚያገለግሉ አራት መሠረታዊ ባሕርያት አሏት፡፡ እነዚህም ቅድስት፣ አሐቲ (አንዲት)፣ ሐዋርያዊት እና ኩላዊት (ጉባኤያዊት) ናት የሚሉት ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዓላማዎችና ተልእኮዎች የሚመነጩትና የሚቀዱት ከዚህ መሠረታዊ ባሕርይዋ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ጽሑፍ በርእሱ ወደ ተነሣው ጉዳይ ላይ ለማተኮር ስንል የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት የሚለውን መሠረታዊ ጉዳይ አሁን አንዳስሰውም፡፡


፫. የቤተ ክርስቲያን ዓላማና ተግባር
ቅድስት፣ አሐቲ፣ ሐዋርያዊትና ኩላዊት የሆነችው የልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ዓላማዎችና ተልእኮዎች በዋናነት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠውን የመዳን ምሥጢር መግለጥ፣ ሰዎችን ማዳን
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠውን የመዳን ጸጋ ሰዎች አውቀውና ተረድተው ይጠቀሙበት ዘንድ የምሥራቹን ለዓለም (ለሰዎች) ሁሉ የምትናገር ናት፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዋናው ተልእኮዋም ጌታችን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ የሰጣት ታላቅ አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ. 28፡19-20 ሰዎች ይህን የወንጌል ጥሪ ተቀብለው ለመዳን የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያደርጉ ታስተምራለች፣ ያመኑትን ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ቅዱሳት ምሥጢራትን ትፈጽምላቸዋለች፡፡ በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ይሆናሉ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ከሆኑት ሁሉ ጋር ኅብረት ይኖራቸዋል፡፡ “ . . . ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ 2 ቆሮ. 5፡20፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደጉ ሳምራዊ በመንገድ ላይ ቆስሎ ወድቆ ለተገኘው ሰው ያደረገለት ነገሮች - ማዘኑ፣ ዘይትና ወይን በቁስሉ ላይ ማፍሰሱና ከዚያም በራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ስፍራ ካደረሰውና ከጠበቀው በኋላ በዚያ አሳድሮ በማግሥቱ ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና “ጠብቀው፣ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ” አለው ተብሎ የተገለጸውን አገልግሎት - በዚህ ዓለም በኃጢአትና በክህደት ለቆሰሉ ሁሉ ታደርግ ዘንድ የተሰጠች ሐኪም ቤት ናት። ሉቃ. 10፡30-35 በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮዋ ሰዎች እንዲድኑ መርዳት (ማስተማር፣ ማጥመቅ፣ ማቁረብ . . . ) ነው፡፡ ሌላው ተግባሯና ድርጊቷ ሁሉ ከዚህ የሚመነጭና የዚህ አጋዥና ደጋፊ ነው፡፡
2. ምእመናንን፣ ሃይማኖትን፣ እና ምሥጢራትን መጠበቅ
ገና ያላመኑትን ማስተማሯና መስበኳ እንዳለ ሆኖ በዚህ ላይ ወደ ድኅነት መስመር የገቡትን፣ በመዳን መንገድ ላይ ጉዞ የጀመሩትን ደግሞ ትጠብቃለች፡፡ ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን “ጠቦቶቼን ጠብቅ” እንዳለው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያስረዳ የመንፈስ ልጁን ጢሞቴዎስን “አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ” ይላል፡፡ 1 ጢሞ. 5፡21 በድጋሜም “ዕቀብ ማኅፀንተከ ሠናየ በመንፈስ ቅዱስ ዘኅዱር ላዕሌከ - መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ” ይላል 2 ጢሞ. 1፡14፡፡
እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ለሰዎች የተሰጠውን የመዳኛና መቀደሻ መንገድ የሆነውን ሃይማኖትና እውነት፣ እንዲሁም እነዚህ የሚፈጸሙበትንና የሚገለጡበትን ምሥጢራትን (Mysteries) መጠበቅ ተግባሯና ተልእኮዋ ነው፡፡
3. የጠፉትን መፈለግ
ልጆቿ የሆኑ ምእመናን የሚሰማሩት ተኩላ በበዛበት ዓለም በመሆኑ ከመንጋው መካከል በግልጽ ተኩላ የሆኑም፣ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችም የሚያስቀሯቸው በጎች አይጠፉም፡፡ በራሳቸው ስንፍናና ድካም የሚጠፉም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ በምንም ምክንያት ይሁን የጠፉባትን ልጆቿን ትፈልጋለች፡፡ እስኪመለሱላት ድረስም ዕረፍት አይኖራትም፡፡ ፈሪሳውያንና ጻፎች በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ “ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል፣ ከእነርሱም ጋር ይበላል” ብለው እርስ በርሳቸው ባንጐራጐሩ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ነገራቸው፡- “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው?” ሉቃ. 15፡2-4፡፡
እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምሳሌ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጠፉ ልጆቿን መልሳ እስክታገኛቸው ድረስ ዕረፍት እንደማይኖራትና አጥብቃ ከመፈለግ እንደማትቦዝን ሲያስተምረን እንዲህ አለ፡- “ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤቷንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆቿንና ጐረቤቶቿን በአንድነት ጠርታ፡- የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች። እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።” ሉቃ. 15፡8-10 ይህን ሁሉ አጠቃልሎ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና” በማለት ነግሮናል፡፡ ሉቃ. 19፡10 የክርስቶስ አካሉ የሆነችው ቤተ ክርስቲያንም አንዱ ተልእኮዋ የጠፉትን መፈለግና ሕይወት ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የምትችለውን ሁሉ ማድረግ ነው፡፡
4. ስለ ሁሉም ጸሎትና ምልጃ ማቅረብ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የምትገኝ ድልድይ እንደ መሆኗ ሌላው ተግባሯ ስለ ፍጥረታት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትና ምልጃ ማቅረብ ነው፡፡ ይህም “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው” ተብሎ የተሰጣት ተግባር ነው፡፡ 1 ጢሞ. 2፡1-4 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሊጦኑ፣ በዘይነግሡ፣ በመስተብቁዑ፣ በእንተ ቅድሳቱ፣ በመሳሰለው ጸሎት ሁሉ ስለ ዝናማት፣ ስለ ወንዞች፣ ስለ ነፋሳት፣ ስለ ፍሬ ምድር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ መንገደኞች፣ ስለ ተማረኩ ሰዎች፣ ስለ ታመሙ ሰዎች፣ ወዘተ ወደ እግዚአብሔር የምትማልደው ስለዚህ ነው፡፡
፬. ማውገዝ ለምን አስፈለገ?
በመጀመሪያ ማውገዝ ምንድን ነው? ማውገዝ ማለት አንድ ሰው በሃይማኖትና በምሥጢራት አማካይነት የቤተ ክርስቲያንን ጸጋ ከተቀበለና አካል መሆን ከጀመረ በኋላ ቀድሞ ያመነውን ሲክድ፣ የቤተ ክርስቲያን አካላትን አንድ ከሚያደርገው ከሃይማኖትና ከእውነት ዐምድ ሲያፈነግጥ ያን ጊዜ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ከአሁን በኋላ የእኔ አካል አይደለህምና ወደፈለግኸው ሂድ፣ ከእኔ ጋር ግን ኅብረትና አንድነት የለህም” ብላ የምታሰናብተው ማሰናበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እሥራትም ሆነ ግርፋት አትፈርድም፣ ይህ የምድራውያን ፍርድ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ሰማያዊና መንፈሳዊ የእግዚአብሔር ጉባኤ እንደ መሆኗ የአንድነቷ መሠረት ከሆነው ከሃይማኖት የወጣውን እርሱ ራሱ ክዶ የወጣ ስለሆነ ያንኑ በግልጽ በመግለጥ ልጇና አባሏ አለመሆኑን በይፋ ለሁሉም ታሳውቃለች፡፡
ውግዘት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍላጎቷም፣ ዓላማዋም አይደለም፤ ማውገዝ የግድ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚመጣ ነገር ነው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ “ሰዎችን መጥራት፣ መመገብና መጠበቅ እንጂ መፍረድ የቤተ ክርስቲያን ድርሻ አይደለም” ይላል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍላጎቷና ምኞቷ እንኳን ወደ ውስጧ የገቡት ቀርቶ ገና ያልቀረቡትም እንዲቀርቡና እንዲድኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተግባራዊ ዓለም ሲታይ ከገቡ በኋላ የሚወጡ፣ ካመኑ በኋላ የሚክዱ፣ ከቀረቡ በኋላ የሚርቁ አልጠፉም፡፡ ስለዚህ ማውገዝ ከሰውነት አካላት መካከል የታመመና ሌላውን የሚበክል አካል ቢኖር ያ አካል የሰውነት ክፍል ሆኖ መቀጠሉ ለሰውዬው ሕይወት አደጋ የሚሆን ሲሆን ይቆረጥ እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡
አንዱን የጠፋውን በግ - የሰውን ልጅ - ለመፈለግ እስከ መስቀል ሞት ድረስ የተቀበለው መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን አካል ከሆኑ በኋላ ከእምነቷና ከሥርዓቷ ስለሚያፈነግጡ ሰዎች ምን ማድረግ እንደሚገባ እንዲህ በማለት በግልጽ አስተምሮናል፡-
“ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ” ማቴ. 18፡15-17፡፡
ተመክሮ የማይሰማና የማይመለስ ከሆነ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ተነግሮ አሁንም የማይመለስ ከሆነ፣ በመጨረሻ ያለው አማራጭ “ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ” እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ማለት አረመኔና ቀራጭ በቤተ ክርስቲያን ከምሥጢራቷና ከጸጋዋ ሱታፌ እንደሌላቸው ሁሉ እርሱም እንደዚያ ይሆናል፣ ክርስቲያን ከተባለ በኋላ አረመኔ ይባላል፣ ከቤተ ክርስቲያን የወጣ፣ ከጸጋዋና ከሁሉ ነገሯ የተለየ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እንደዚሁም በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ሠርቶ የነበረውን ሰው ቀኖና ሊሰጡትና ከመካከላቸው ሊለዩት ሲገባ እነርሱ ግን ምንም ያልሆነ ይመስል ዝም ብለው ሰውዬውን በመካከላቸውይዘው፣ ከዚያም አልፎ እንዲያ ያደረገው ሰው በመጸጸት ፋንታ ዝም ሲሉት ጊዜ የተወደደለት መስሎት የራሱን ደጋፊዎችና አንጃዎች ወደ ማሰባሰብና ወደ ማደራጀት ደረጃ ደርሶ ስለ ነበር ቅዱስ ጳውሎስ ጠንከር ያለ መልእክት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ልኮላቸዋል፡፡ ይህን የተመለከተው ቃል እንዲህ ይላል፡-
“በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል፣ የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፣ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ” 1 ቆሮ. 5፡1-7፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም በሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ምን ያህል ጠንቃቆች መሆን እንደሚገባን ሲናገር “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።” በማለት አርቀን እንድናጥርና እንድንጠነቀቅ አስተምሮናል፡፡ 2ኛ ዮሐ. 9-11 ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፣ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፣ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፣ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ” በማለት ነግሮናል ሮሜ 16፡18፡፡
፭. የማውገዝ ምክንያቶች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መናፍቃንን የምታወግዝባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ምእመናንን እንዳይበክሉ ለመጠበቅ
ኑፋቄ ደዌ ነው፣ በሽታ ነው፡፡ ስለዚህ በኑፋቄ በሽታ የተለከፈውና የታመመው ሰው “ታምመሃል፣ ታከምና ዳን” ሲሉት “አይ፣ እኔ ጤነኛ ነኝ፣ ምንም ችግር የለብኝም” የሚል ከሆነ የሃይማኖት በሽታውን ወደ ሌሎች እንዳያዛምትና አንዲቷን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያንን) እንዳይበክል ለመከላከል ሲባል ከማኅበረ ምእመናን እንዲለይ (እንዲወገዝ) ይደረጋል፡፡ አንድ ሰው ከአካሉ ውስጥ በጠና የታመመና የማይድን መሆኑ የተረጋገጠ አካል ቢኖረው፣ አለመዳኑ ብቻ ሳይሆን የዚያ አካል በሽታ ወደ ሌላው የሰውነት ክፍል የሚዛመትና የሰውዬውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥለው ከሆነ ሐኪሞች ብቸኛው መፍትሔ ያን አካል መቁረጥና ማውጣት መሆኑን ይነግሩታል፡፡ ሐኪሞች እንዲያ የሚሉት የሰውዬውን አካል ጠልተውት ወይም ሰውዬውን ለመጉዳት ብለው ሳይሆን የሰውዬውን ሕይወት ለመታደግ፣ ሌላው አካሉ እንዳይመረዝ ለማዳን ሲሉ የሚያደርጉት የርኅራኄ ሥራ ነው፡፡ በሽተኛውም ገንዘቡን አፍስሶና ይደረግ ዘንድ ፈቃደኛነቱን በፈርማው አረጋግጦ አካሉን ወደ ማስቆረጥ የሚሄደው ሕይወቱን ለማቆየት ካለው ጽኑ ምኞት የተነሣ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በኑፋቄ በሽታ ላይድኑ የታመሙ ሰዎች ዝም ቢባሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት ምእመናንን ስለሚበክሉ የግድ እያዘኑ እንደሚቆረጠው አካል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እያዘነች አውግዛ ትለያቸዋለች፡፡
እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት ከነዓን ሊገቡ ዮርዳኖስን ተሻግረው ኢያሪኮን በተአምራት በእጃቸው አሳልፎ ሲሰጣቸው በኢያሪኮ ካለው ሀብትና ንብረት ምንም ዓይነት ነገር እንዳይወስዱ “እርም ነው” ብሎ እግዚአብሔር ነግሯቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከመካከላቸው አንድ አካን የተባለ ሰው እርም የሆነውን ነገር በመንካቱ ምክንያት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ተለያቸው፡፡ በአሕዛብ ፊትም ድል ተነሡ፣ ብዙ ሰዎችም ተገደሉባቸው፣ ከዚህም የተነሣ ብዙ ሐዘን ደረሰባቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ኢያሱ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ስላደረገው ነገር ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይናገራል፡-
“. . . ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም አለ። ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው? እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፡-ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም እስራኤል በድሎአል፣ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፣ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም።”
ችግሩንና የችግሩን ምክንያት እንዲህ ከነገራቸው በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ደግሞ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፡-
“ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፣ እስራኤል ሆይ፣ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፣ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና እስከ ነገ ተቀደሱ። . . .”
ኢያሱና ሕዝቡ ስለዳረጉት ደግሞ እንዲህ ይላል፡-
“ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩንም፣ ካባውንም፣ ወርቁንም፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፣ በሬዎቹንም፣ አህያዎቹንም፣ በጎቹንም፣ ድንኳኑንም፣ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጧቸው። ኢያሱም፡- ለምን አስጨነቅኸን? እግዚአብሔር ዛሬ ያስጨንቅሃል አለው፡፡ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፣ በእሳትም አቃጠሏቸው፥ በድንጋይም ወገሯቸው። በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፣ እግዚአብሔርም ከቍጣው ትኵሳት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ” ኢያ. 7፡1-26፡፡
እንግዲህ ይህ የሚያስተምረን ነገር በአንድ ሰው በአካን እርም የሆነውን ነገር መንካት ምክንያት መላው ሕዝብ መጨነቁንና እግዚአብሔርም ከማኅበረ እስራኤል መለየቱን ነው፡፡ አካን ሲወገድ ደግሞ ተለይቷቸው የነበረው አምላካቸው እንደገና አብሯቸው ሆነ፡፡ በሃይማኖት ላይ የሚጨምርም ሆነ የሚቀንስ ሰው ከባድ እርም መንካቱ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን ሰው አብራ ይዛ ጸጋ እግዚአብሔርንም ልትሰጥና ልትጠብቅ አትችልም፤ ስለዚህ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ካጣራች በኋላ ትለያቸዋለች፡፡ ይህም ማኅበረ ምእመኑ እግዚአብሔር እንዳይለየውና ጸጋ እግዚአብሔር እንዳይርቀው ያደርጋል፡፡
ገንዘባቸውን ከሸጡ በኋላ ሰርቀው አስቀርተው ወደ ምእመናን አንድነት እንገባለን ብለው የነበሩት ሐናንያና ሰጲራ የተባሉት ባልና ሚስቶች በመንፈስ ቅዱስ የተቀሰፉትም ለዚህ ነበር፡፡ የሐዋ. 5፡1-11 ድርጊታቸው ያላቸውን ሁሉ እየሸጡ በሐዋርያት እግር ሥር እየጣሉ “ይህ የእኔ ነው” ይህ የአንተ ነው” ሳይባባሉ በአንድነት ይኖሩ ለነበሩት ምእመናን መጥፎ አብነት እንዳይሆኑ ገና ከበሩ ላይ ሐናንያና ሰጲራን ቀስፏቸዋል፡፡ እንዲህ ያለው መጥፎ እርሾ ጥቂትም እንኳ ቢሆን ብዙውን ሊጥ ሊያቦካ ይችላልና፤ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ያላቸው ለዚህ ነበር። ማቴ. 16፡5 በእርሾ እየተለወሰ የማይቦካ ዱቄት የለምና፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ “የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው፣ ፍርድንም ያመለክታል” በማለት እንዲህ ኑፋቄያቸው ግልጽ የሆነውና የታወቀውን ሰዎች ዝም ማለት እንደማይገባና መፍረድ (ማውገዝ) እንደሚገባ ይናገራል፡፡ 1 ጢሞ. 5፡24-25 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱን ሐሰት ማለት ስለሚገባት፣ ብርሃንን ከጨለማ መለየት ስላለባት በራሳቸው ጊዜ እውነትንና ብርሃንን የተውትን ትለያቸዋለች፡፡ ይህም ክፉዎች መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን እንዳይውጧት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡
በአራተኛው መቶ ዓመት መጨረሻና በአምስተኛው የመጀመሪያ አጋማሽ የነበረው የሰሜን አፍሪቃው አውግስጢኖስ የተለያየ ዓይነት በሆኑ በብዙ መናፍቃን ተከብቦ ነበር፡፡ እርሱም ይመለሱ እንደ ሆነ በማለት ከእነርሱ ጋር ውይይትን ደጋግሞ ሞከረ፣ ሆኖም ግን ውጤት እንደ ሌለው ተመለከተ፡፡ ከሂደቱም የምእመናን እምነት ለመጠበቅ መናፍቃንን አውግዞ ከመለየት ውጭ ሌላ መፍትሔ የለም አለ፡፡ ይህንም ሲያስረዳ እንዲህ አለ፡-
“የማይስማማ ነገር ወደ ሰውነታችን ሲገባ ያ ነገር በትውኪያ ካልወጣ በስተቀር ውስጣችን ሰላምና ጤና እንደማያገኘው ሁሉ፣ መናፍቃንም እስካልተተፉ ድረስ ቤተ ክርስቲያን ጤና አታገኝም፡፡ ከሕይወታዊ ባሕርዩ ጋር ከማይሄድ ከማንኛውም ባእድ ነገር ጋር አለመስማማትና እስኪወጣለት ድረስ ዕረፍት ማጣት የሕይወት ባሕርይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ውስጣችን ወደ ራሱ ሊያዋሕደው የማይችለው ማንኛውም ነገር ጋር ይጋጫል፣ ያ ባእድ ነገር እስከሚወጣ ድረስም ይታወካል፣ ይታመማል፡፡ መናፍቃንም ለቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ናቸው፡፡” ቅ. አውግስጢኖስ፣ 1ኛ ዮሐ. 2፡19 (ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ) የሚለውን ሲተረጉም
ኑፋቄን ዝም ብለን እንታገሠው፣ አብሮ ይኑር ማለት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እና ኑፋቄ አንድ ናቸው ወደ ማለት ይወስዳል፤ ወይም ደግሞ ጥንቱንም በመካከላቸው ያን ያህልም የጎላና መሠረታዊ የሆነ ልዩነት የለም ማለት ይመስላል፡፡ ስለሆነም ሐዋርያዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንዲጠበቅ ብቻም ሳይሆን ከኑፋቄ ጋር ምንም ዓይነት ኅብረትና አንድነት የሌለው መሆኑ ይገለጥና ይታወቅ ዘንድ የተለየ አስተሳሰብ ይዘው ብቅ የሚሉ ወገኖችን ወደሚመስሏቸው እንዲሄዱ እንጂ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የእነርሱ አስተሳሰብ ተቀባይነትና ቦታ እንደ ሌለው መግለጫና ማሳወቂያ መንገድም ነው፡፡ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?” ተብሏልና፡፡ 2 ቆሮ. 6፡14-15 ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ልጆቿ በኑፋቄ በሽታ እንዳይያዙባት ስትል የኑፋቄ ተሐዋስያን የያዙትን መናፍቃንን በውግዘት እንዲለዩ ታደርጋቸዋለች፡፡
ከተለዩ (ከተወገዙ) በኋላም እናት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ልብ እንዲሰጣቸውና ወደ ሕይወት እንዲመለሱ ትጸልይላቸዋለች፡፡ በመውጣታቸውም ታዝናለች፡፡ ምንም እንኳ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ቢለዩም እንደ ሰብአዊ ፍጡርነታቸውና እንደ ሰውነታቸው ክፉ እንዳያገኛቸው የምትችለውን ለማድረግ ፈቃዷ ነው፡፡
2. ለራሱ ለሰውዬው ጥቅም ሲባል
ቤተ ክርስቲያን መናፍቃንን የምታወግዛቸው ለራሳቸው ለመናፍቃኑ ጠቀሜታ ስትልም ነው፡፡ መወገዝ ለሚወገዘው ሰው ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንደኛው፡- ሰውዬው ራሱን የሚያይበት እድል ለመስጠት ነው፡፡ የያዘውን ኑፋቄ በማሰራጨት ላይ ተጠምዶ ያለ ሰው ምን እያደረገ እንደሆነ ቆም ብሎ ራሱን የሚያይበት ዕድል ላያገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን “ይሄ አስተምህሮህና ድርጊትህ ትክክል አይደለም፣ ተመለስ፣ ተስተካከል” ስትለው ልብ ከገዛ መልካም፣ ተጠቀመ ማለት ነው፡፡ ያ ካልሆነም በመጨረሻ ሲወገዝ አሁንም ድርጊቱ ስህተት መሆኑ በይፋ እየተነገረው በመሆኑ እልከኝነት ካላሸነፈው በስተቀር የድርጊቱን ስህተትነት ለመረዳትና ራሱን ለማየት ሰፊ ዕድል ይሰጠዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ተወግዞ እንዲለይ የወሰነበትን የቆሮንቶስ ሰው ስለ ውግዘቱ ምክንያት (ለምን እንደዚያ እንደ ወሰነበት ሲናገር) እንዲህ ያለው ለዚህ ነበር፡-
“እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” 1 ቆሮ. 5፡5፡፡
ስለዚህ የውግዘቱ ዓላማ ማጥፋት ሳይሆን ማዳን ነበር ማለት ነው፤ “መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” በማለት ዓላማውን ተናገረ፡፡ እንዲሁም “በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት” አለ፡፡ 2 ተሰ. 3፡14-15 የሚወገዘው (የተወገዘው) ሰው እንደ ጠላት ሊቆጠር አይገባውም፣ ሆኖም ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን የወጣና የተለየ መሆኑንና ያም ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ እንዲገነዘብ ማድረግ ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ መናፍቃንን ዝም ማለትና “ተዋቸው” በማለት በኑፋቄ ሲበላሹ እያዩ ዝም ማለት ፍቅር ሳይሆን ጥላቻ ነው፣ እነዚያን ሰዎች መጥቀም ሳይሆን መጉዳት ነው፤ ያውም በሥጋ ሳይሆን በነፍስ መጉዳት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አዳም በበደለ ጊዜ ከዕፀ ሕይወት እንዳይበላ ከልክሎታል፣ እንዲህ በማለት፡-
“እግዚአብሔር አምላክም አለ፡- እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፣ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፣ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፣ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” ዘፍ. 3፡22-24፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከሃይማኖት ወጥቶ ከፈጣሪው ተጣልቶ ባለበት ሁኔታ የተቀደሰ ከሆነው ነገር ሁሉ (ከዕፀ ሕይወት፣ ከገነት፣ ወዘተ) የከለከለውና ወደዚያም እንዳይደርስ ዘግቶ ያስጠበቀበት አዳምን ስለ ጠላው አልነበረም፡፡ ከእግዚአብሔር በላይ ሰውን የሚወድድ ማን አለ ሊባል ነው? አዳምን የከለከለው ከፍጹም ፍቅሩና ከቸርነቱ የተነሣ ነበር እንጂ ከክፋት አልነበረም፡፡ ስለሆነም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ከሃይማኖት የወጡ ከሥርዓት ያፈነገጡ ሰዎችን እስኪመለሱ ድረስ ከምሥጢራቷና ከአንድነቷ የምትለያቸው ከእናትነት ፍቅሯ የተነሣ ነው፡፡ ይልቁንም ጭካኔና ፍቅር የለሽነት የሚሆነው ኑፋቄያቸውን እያዩ በግድ የለሽነት ዝም ማለት ነው፡፡ መናፍቅነት የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማያስወርሱ ታላላቅ ኃጢአቶች አንዱ ነውና፣ “. . . መናፍቅነት . . . አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ገላ. 5፡21፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፣ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤ ከእነዚያም እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው፥ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው።” 1 ጢሞ. 1፡19-20 ለሰይጣን አሳልፎ የሰጣቸው “እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ነው” አለ፡፡ የጠፋው ልጅም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በተወለደበትና ባደገበት በአባቱ ቤት ያለው መልካም ነገር ሁሉ ስልችት ባለውና ከዚያ ወጥቶ መሄድ በፈለገ ጊዜ አባቱ አልከለከለውም፡፡ ነገር ግን ወደ ሌላ አገር ከሄደ በኋላ የደረሰበት ረሃብና መከራ ሌላው ቢቀር ቢያንስ በአባቴ ቤት እንጀራ ጠግበውና ተርፏቸው ከሚያድሩት ከባሮቹ እንደ አንዱ ልሁን ብሎ ወደ ልቡ ተመለሰ፤ ከዚያም ወደ አባቱ በንስሐ ተመለሰ፡፡ አባቱ ከመጀመሪያውኑ እንዳይሄድ ከልክሎት ቢሆኖ ኖሮ ምናልባት የአባቱ ቤት መልካም ነገር ከተሰደደ በኋላ እንደ ታየው ሆኖ ላይታየው ይችል ነበር፡፡ መውጣቱና መቸገሩ ግን በአባቱ ቤት ያለውን መልካም ነገር በንጸጽር እንዲመለከት አድርጎታል፡፡ መናፍቃንም በቤቷ ሲኖሩ የጸጋዋ ጣዕም ካልገባቸው ተወግዘው ሲወጡና በባዕድ አገር (በሌላ ሁኔታ) ሲባዝኑ ያጡት ጸጋ ምንነት በፊታቸው ወለል ብሎ ሊታያቸው ይችላል፡፡ ይህ ባይሆንም ችግሩ የራሳቸው የሰዎቹ ነው፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ ራሳቸውን የሚያዩበትን ዕድል መስጠቱ ከራሳቸው እልከኝነትና ስንፍና የተነሣ ሁሉም ላይጠቀምበት ቢችልም ምን ጊዜም ቢሆን በተሰጠው ነገር የሚጠቀመው ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው እና ወደ ልቡ የሚመለስ ሰው ስለሆነ እንደዚህ ላሉት ሰዎች ዕድሉን ማግኘቱ ይጠቅማቸዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ የሚያመካኙበት ሰበብ ያጣሉ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም እንዲህ ይላል፡- “ኩላዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ታላቅና ገነት ናት . . . እናም ማንም ቢሆን በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዲያብሎስ የኑፋቄ ትምህርት ተበክሎና ታሞ ከተገኘ . . . አዳም ከጥንቷ ገነት እንደ ተባረረ ሁሉ እርሱም ከዚህችኛዋ ገነት - ከቤተ ክርስቲያን ይባረራል፡፡”


ሁለተኛው ጠቀሜታ ብዙዎችን በማጥፋት ባለ ብዙ ዕዳ እንዳይሆን ስለሚከለክለውና ስለሚረዳው፣ ኃጢአቱና ዕዳው እንዳይጨምር በግድም ቢሆን ስለሚጠቅመው ነው፡፡ “እስመ ዘሞተሰ ድኅነ እምገቢረ ኃጢአት - የሞተ ሰው ኃጢአት ከመሥራት ድኗል” በማለት እንደ ገለጸው የሞተ ሰው ቢያንስ ከዚያ በኋላ ኃጢአት ከመሥራት ነጻ ወጥቷል፡፡ ሮሜ 6፡7 እንደዚሁም በኑፋቄው ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የተወገዘ (የተለየ) ሰው ሌሎችን በኑፋቄው መርዝ እየበከለ በማቁሰልና በመግደል በብዙዎች ደም ተጠያቂና ባለ ዕዳ እንዳይሆን ይረዳዋል፡፡ ሰዎችን መግደል ማለት ቁሳዊ በሆነ ነገር መምታትና የማይቀረውን ሞት ማምጣት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከዚህም በላይ ሊቀር ይችል የነበረውን ሞተ ነፍስን በኑፋቄ ምክንያት ሰዎችን ከእግዚአብሔር እንዲለዩ ማድረግ እጅግ በጣም ከባድ ዕዳ ነው፡፡ ስለዚህ ተወግዞ ሲለይ ስለሚታወቅበትና ለብሶት የነበረው የበግ ለምድ ስለሚገፈፍ ምእመናን ስለሚያውቁት ይጠነቀቃሉ፣ ይርቁታል፡፡ በዚህም በኃጢአት ላይ ኃጢአት እንዳይጨምርና ዕዳው እንዳይበዛበት ይረዳዋል፡፡
3. ለሌሎችም ትምህርት እንዲሆን
በሃይማኖት ላይ የሚጨምርም ሆነ የሚቀንስ መናፍቅ በተገቢው ጊዜ ትክክለኛ የሆነ እርማት ካልተሰጠውና ዝም የሚባል ከሆነ ሌላውም እንደዚያ እያደረገ ላለመቀጠሉ ምንም ዓይነት ዋስትና አይኖርም፡፡ ስለዚህ ችግሩ በዚያ በአንዱ መናፍቅ ብቻ ተወስኖ አይቀርም፣ እርሱ ምንም ሳይባል ዝም ሲባል ያዩ ሌሎችም እንደ እርሱ ኑፋቄያቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ልባቸው መትከልና ማሳደግ ይጀምራሉ፡፡ የመጀመሪያው ዝም ሲባል ያዩት ሌሎቹም “እገሌ ምን ተደረገ?” እያሉ ልባቸው እየደነደነ፣ በኃጢአት ላይ ኃጢአት እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ወዳለ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ከመጀመሪያው በሃይማኖት ላይ ባእድ ነገር (ኑፋቄ) የሚያመጣውን ሰው የሚመለስ ከሆነ በምክርና በቀኖና፣ አልመለስም ካለ ደግሞ በውግዘት መለየት የግድ ይሆናል፡፡ ይህም ለሌሎች መገሠጫና መጠንቀቂያም ይሆናል፡፡
እንዲህ ካልተደረገ ቤተ ክርስቲያን የመናፍቃንና የግዴለሾች መሰባሰቢያ የምትመስላቸው፣ ትዕግሥቷንና ዝምታዋን እንደ አለማወቅ ወይም ከእነርሱ ጋር እንደ መስማማት የሚቆጥሩና በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ የሚሄዱ ሰነፎች ሊበዙ ይችላሉ፡፡ ከላይ ያነሳነው የሐናንያና የሰጲራ ቅጣት በዚህ አንጻርም የሚታይ ነው፡፡ በእነርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ስላደረገው ቅጣት ሲናገር “ጴጥሮስም፦ የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፣ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው፣ አንቺንም ያወጡሻል አላት። ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች፣ ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኟት፣ አውጥተውም በባሏ አጠገብ ቀበሯት” ይልና የዚያ ቅጣት ውጤት ምን እንደ ነበር ሲናገር “በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ” ይላል፡፡ የሐዋ. 5፡9-11 የእነርሱ መቀጣት በሌሎች ዘንድ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጽሙ ተግባራዊ ማስጠንቀቂያ ሆነ፡፡ እንኳን የመንፈሳዊ አሠራር፣ የዚህ ዓለም አሠራርም ቢሆን የሕግና የቅጣት መሠረታዊ ዓላማው ሰዎችን መጉዳት ሳይሆን ማስተማርና ማስጠንቀቅ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-
“ትንሽ በሆኑ ነገሮች ላይ በጊዜው ጊዜ ተገቢውን ቁጣ አለመቆጣታችን የደረሱብንና የሚደርሱብን ጥፋቶችና ምስቅልቅሎች ምክንያት ነው፤ ጥቃቅን ስህተቶች በጊዜው ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ ሳይደረግባቸው ስለሚታለፉ ታላላቆቹ ስህተቶች እየተንኳተቱ ይመጣሉ፡፡ ሰውነታችን ላይ ቁስል ሲወጣ ዝም ብለን ብንተወው መመረዝንና ሞትን ሊያስከትል እንደሚችለው ሁሉ በነፍስም ችላ የሚባሉ ስህተቶችና ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ለታላላቆቹ ክፉ ነገሮች በር ይከፍቱላቸዋል፡፡ . . . ነገር ግን ከአምላካዊ አስተምህሮ ለማፈንገጥና ትንሽ የሆነ ነገር ለመለወጥ የሚሞክሩት ሰዎች ገና ከመጀመሪያው ተገቢው ተግሣጽ ተሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለው የኑፋቄ ወረርሽኝ አይወለድም ነበር፣ ቤተ ክርስቲያንንም እንዲህ ያለ ማዕበል አይይዛትም ነበር፤ በኦርቶዶክሳዊ እምነት ትንሽ የሆነ ነገር እንኳ የሚለውጥ ሰው በሁሉም ነገረ ሃይማኖት ላይ ጥፋት ያስከትላልና፡፡” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ትርጓሜ መልእክተ ጳውሎስ ኀበ ሰብአ ገላትያ)
ለዚህ ነው ሐዋርያው “ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው” ያለው፡፡ 1 ጢሞ. 5፡20 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ሊሆኑ የተጠሩ ሰዎች ጉባኤ (አንድነት) ናት እንጂ በክህደት ለመኖር፣ በኑፋቄያቸው ለመቀጠል የወሰኑ የተንኮለኞች ዋሻ አይደለችምና፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አጥርና ቅጥር በኑፋቄ እንዳይፈርስና የመዳን ምሥጢር እንዲጠበቅ ለማድረግ ሲባል ባእድ ነገር ይዘን ካልገባን ሞተን እንገኛለን የሚሉትን ማራቅና መጠበቅ የግድ ይላል፡፡ እንድ ሰው “በራሱ ማንነትና መሠረታዊ ምንነት ዙሪያ ድንበርና ወሰን የማያበጅና እነዚያን ያበጃቸውን ድንበሮችም የማይጠብቅ ማንኛውም ቡድን ማንነቱንና ህልውናውን ለረጂም ጊዜ ጠብቆ መዝለቅና መኖር አይችልም” ያለው ለዚህ ነው፡፡
ከዚህም ጋር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መናፍቃንን የምታወግዘው በነገረ ሃይማኖት በሳል እውቀት ለሌላቸው ልጆቿ ለማስጠንቀቅ፣ “እንዲህ የሚለው . . . ኑፋቄ ነው፣ የእኔ እምነትና ትምህርት አይደለምና ተጠንቀቁ” ለማለት ነው፡፡ የኑፋቄውን ምንነት ለመግለጥ፣ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተለየ መሆኑን በይፋ ለመግለጥና ለማሳወቅ ነው፡፡ አንድ የነገረ ሃይማኖት ምሁር “ኑፋቄዎችና መናፍቃን ሊወገዙ የሚገባበት ምክንያት በውስጡ እውነት የሚመስሉ ነገሮች ስላሉትና የዋሃን ክርስቲያኖችን ወደ ስህተት ሊመራ የሚችል ስለሆነ ነው” ብሏል፡፡ ጠርጠሉስ የተባለው ሊቅም “መናፍቃን ደካማዎች የሆኑትን ያሳስታሉ፣ ታናናሾችን ያናውጻሉ፣ የተማሩትን ደግሞ ያታክታሉ፣ ያጭበረብራሉ” ብሏል፡፡
የታላቁ የቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ አባትና መካሪው የነበረው የፔሉዚየሙ ቅዱስ ኤስድሮስም ስለ መናፍቃን እንዲህ ይላል፡- “ዓሣ አጥማጆች መንጠቆውን ዓሣዎችን በሚስብ ነገር እንደሚሸፍኑትና ከዚህም የተነሣ ዓሣዎቹን እንደሚይዟቸው፣ መናፍቃንም ከተንኮላቸው የተነሣ ክፉ ትምህርታቸውንና የተበላሸ አረዳዳቸውን በመንፈሳዊነትና በአስመሳይነት በመሸፈን ሞኞችንና የማያስተውሉትን በማጥመድ ወደ መንፈሳዊ ሞት ይወስዷቸዋል፡፡” ስለዚህም ምእመናን ልጆቿ አስመሳዮች በሆኑ መናፍቃን እንዳይታለሉባት ለመጠበቅ መናፍቃን የሆኑትን ትለያቸዋለች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በመልክእቱ እንዲህ ሲል በጽኑ ያሳሰበው ለዚህ ነው፡- “ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፣ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዝዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ” 1 ጢሞ. 1፡3-4፡፡
4. በሰማይ (ኋላ) ላለው (ለሚገለጠው) የኃጥአን ከጻድቃን መለየት ማሳያ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት ወካይና መገለጫ ናት፡፡ ስለዚህ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ተቀላቅሎና ተመሳስሎ መግባት እንደ ሌለ ሁሉ በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያንም የዚያ ወካይና መገለጫ እንደ መሆኗ የእርሷ ወገኖች ያልሆኑትን ትለያቸዋለች፡፡ እግዚአብሔር ስለሚያደርው መለየት በተለያዩ ምሳሌዎችና ሁኔታዎች ተገልጾአል፡፡ ለአብነትም፡-
  • “አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል” ይላል፡፡ ማቴ. 25፡32-33
  • “መንሹም በእጁ ነው፣ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፣ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፣ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ማቴ. 3፡12
  •  “የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። ማቴ. 7፡23
  • “ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና፡- ወዳጄ ሆይ፥ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ” ማቴ. 22፡11-13፡፡
በተጨማሪም በአንድ ማሳ ላይ በነበሩት በእንክርዳዱና በስንዴው መለየት መስሎም አስተምሯል፡፡ ስለሆነም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ጉባኤያትን እያደረገች መናፍቃንን የምታወግዘው ለዚህ ነው፡፡
5. የሰጠችውን ሀብት ለመንሣት
መናፍቃን የሆኑትን ቀድሞ ስትቀበላቸውና ልጆቿ ስታደርጋቸው፣ ከዚያም ባለፈ በአገልግሎት ስታሰማራቸውና ዲያቆናት ካህናት አድርጋቸው ከነበረ በዚያ ጊዜ የሰጠቻቸውን ስጦታና የፈጸመችውን ለማጠፍና ከዚያ በኋላ ልጆቿ አለመሆናቸውንና እነርሱ የሚያደርጉት ማንኛውም ነገራቸው እርሷን እንደማይመለከታት በዐዋጅ ለማሳወቅ ነው፡፡ በዚህም ሰጥታቸው የነበረውን መብትና ጸጋ ሁሉ በአደባባይ ታነሳለች፡፡ ይህ በዚህ ዓለም ባሉ እንደ ወታደራዊ ባሉ ተቋማትም ይፈጸማል፡፡ አንድ የጦር ሠራዊት አባል ወይም ባለ ሥልጣን ከተሰጠው አደራና ኃላፊነት ጋር የማይሄድ፣ አገርንና ሕዝብ የሚጎዳ ድርጊት ከፈጸመ በይፋ መዓርጉና ክብሩ ይገፈፋል፡፡


፮. መናፍቃን ከቤተ ክርስቲያን የሚለዩት መቼ ነው?
አንድ ምእመን በቤተ ክርስቲያን የሚኖረው በእውነትና በሃይማኖት እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ያን እምነትና እውነት ሲክድና ሌላ ባእድ ነገር ውስጥ ሲገባ ግን ያን ጊዜውኑ ከቤተ ክርስቲያን ራሱን በራሱ ያወጣል፤ በራሱ ድርጊት ራሱን ከድኅነት ውጭ ያደርጋል፡፡ ሐዋርያው “ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት ነው” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ያን የእውነት ዓምድ የማይይዝ ሰው በራሱ ይለያል፡፡ ባለቤቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ብሎ ያስተማረን ይኸው ነው፡፡ ዮሐ. 3፡36 ያላመነ ሰው ያን ጊዜውኑ የራሱ አለማመን ፈርዶበታል፡፡
እንዲሁም “መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ” ሲል ይህን ያመለክታል፡፡ ቲቶ 3፡10-11 ኑፋቄን (መለያየትን) የሚያነሣ ሰው በራሱ ላይ የፈረደው ያን ጊዜ ነው፡፡
አዳም ከእግዚአብሔር የተለየውና ራቁቱን የሆነው ከገነት እንዲወጣ በተፈረደበት ጊዜ ሳይሆን ከዚያ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን ንጹሕ እምነት በዲያብሎስ ስብከት በለወጠና ባበላሸ ጊዜ ነበር፡፡ ለዚህ ነበር እግዚአብሔር ወደ እነርሱ ከመምጣቱ በፊት አስቀድሞ ራቁታቸውን እንደሆኑ በማወቃቸው የበለስ ቅጠል ሰፍተው ያገለደሙት፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው ከቤተ ክርስቲያን የሚለየውን ነገር የሚያደርገው ራሱ ነው፡፡ ራሱን ከእግዚአብሔርና ከቤተ ክርስቲያን ያልለየን ሰው ማንም ሊለየው አይችልም፡፡ ራሱን የለየን ሰው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ሰጪ አካላት በተለያዩ ምክንያቶች (መናፍቅነቱን ባለማወቅ፣ ወይም ሰውዬው ኑፋቄውን ሰውሮ እያጭበረበረ በመኖሩ፣ ወይም በሌሎች ሰብአዊ ምክንያቶች) ከቤተ ክርስቲያን በውግዘት ሳይለይ ቢቀር እንኳ እርሱ አስቀድሞ ራሱን የለየ ስለሆነ ከሰዎች ፍርድ ማምለጡ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመለየት አያድነውም፡፡ እንዲህ በማድረግ ከሰዎች ፍርድ ማምለጥ ለሰማያዊ ሕይወቱ አንድም የሚጠቅመው ነገር የለም፣ ይልቁንም ከላይ እንዳየነው ይጎዳዋል እንጂ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የምትለየው ቀድሞውንም ራሱን በኑፋቄው የለየውን ሰው ነው፡፡
እንደ አንድ ማሳያ የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስን እና የአርዮስን ሁኔታ በአጭሩ ማስታወስ እንችላለን፡፡ ፲፯ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ከማረፉ በፊት (ያረፈው በ፫፻፲፩ ዓ. ም. ነው) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደደ ልብስ ለብሶ በራእይ ታየው፡፡ ያን ጊዜ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለህምን? ልብስህን ማን ቀደደው? አለው፡፡ ጌታችንም “አርዮስ ሰጠጣ ለልብስየ ወፈለጠኒ አምአቡየ ወእምእመናን ዘአጥረይክዎሙ በደምየ - አርዮስ ከባሕርይ አባቴ ከአብ ለየኝ፣ በደሜ ከቤዠኋቸው ከምእመናንም ለየኝ” አለው፡፡ ከዚያም ጌታችን ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስን አርዮስ የማይመለስ መናፍቅ ስለሆነ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይቀበለውና አውግዞ እንዲለየው ነገረው፡፡
እንግዲህ አርዮስ ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ራሱ ባመነጨው ኑፋቄው የተለየው ከዚያ አስቀድሞ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህም ከቅዱስ ጴጥሮስ ዕረፍት በፊት ማለት ነው፡፡ ሆኖም አርዮስ በጉባኤ የተወገዘው ግን ከተፍጻሜተ ሰማዕት ከቅዱስ ጴጥሮስ ዕረፍት ከአሥር ዓመት በኋላ በእስክድርያው ፓትርያርክ በቅዱስ እለእስክንድሮስ ሰብሳቢነት በ፫፻፳፩ ዓ. ም. በእስክንድርያ በተካሄደ ጉባኤ ነበር፡፡ ሆኖም ምንም እንኳ አርዮስ በጉባኤ ሳይወገዝ ከአሥር ዓመት በላይ ቢቆይም እርሱ ግን ራሱን ከቤተ ክርስቲያን ከለየና የወይን ግንድ ከሆነው ከጌታ ራሱን ቆርጦ ከጣለ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ በእምነት ያፈነገጠና የወጣ ሰው በጉባኤ ቢወገዝም ባይወገዝም ራሱን በራሱ የቆረጠና የለየ፣ በራሱ የተወገዘ ነው፡፡ ልዩነቱ እንደ ታወቀበትና ያልታወቀበት ሌባ ወይም ወንጀለኛ ነው፡፡ ወንጀልን የፈጸመ ሰው ፖሊስ ቢይዘውም ባይይዘውም፣ ፍርድ ቤት ቢፈርድበትም ባይፈርድበትም ወንጀለኛነቱ አይለወጥም፡፡ ሆኖም ሲያዝና ሰፈረድበት ለራሱም ለኅብረተሰቡም ጠቀሜታው የጎላ ነው፤ ከዚያ ባለፈ የሰውዬውን ጥፈተኛነት ግን አይለውጠውም፡፡
፯. መናፍቃን የሚወገዙት እንዴት ነው?
የመናፍቃን አወጋገዝ ሂደት እንደ ኑፋቄው ዓይነት ነው፡፡ የኑፋቄው ዓይነት ምንድን ነው? የሚለውን ማጤን ይገባል፡፡ ይህም:-
  • የታወቀ ኑፋቄ፣ እና
  • እንግዳ ዓይነት ኑፋቄ
የታወቀ ኑፋቄ - ስንል
ሀ. ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር ተቃርኖው ግልጽና የማያሻማ የሆነ ኑፋቄ፣ እና
ለ. ከዚያ በፊት በአካባቢያዊም ሆነ በዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የተወገዘ ኑፋቄ ማለታችን ነው፡፡
እንዲህ ያለ ኑፋቄ ይዞ ለሚነሣ ሰው አዲስ ነገረ ሃይማኖታዊ ውይይትና ውሳኔ አያስፈልገውም፡፡ የአርዮስን ኑፋቄ ይዞ ለሚነሣ ግለሰብም ሆነ ቡድን የኒቅያ ጉባኤ በየጊዜው ሲሰበሰብ አይኖርም፤ የንስጥሮስን ኑፋቄ ይዞ ለሚነሣም እንዲሁ የኤፌሶን ጉባኤ በየጊዜው አይሰበሰብም፡፡ በቀደመው ውግዘት እስከ ዕለተ ምጽአት የሚነሡት ሁሉ ተወግዘዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ግልጽ ተቃርኖ የያዘ ኑፋቄ ሁሉ በአጠቃላይ የተወገዘ ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ኑፋቄ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም ያን ኑፋቄ የሚያራምደው ግለሰብ በትክክል ያን ኑፋቄ መያዝ አለመያዙን፣ የሚመለስ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከተረጋገጠ በኋላ ያ ሰው ከቤተ ክርስቲያን መለየቱ (ማውገዙ) በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ወይም በአገረ ስብከት ደረጃ ሊፈጸም ይችላል፡፡
እንግዳ ዓይነት ኑፋቄ ሲባል ደግሞ በግልጽ ስህተቱ ይህ ነው ለማለት ቀላል ያልሆነና ጉዳዩን ከቤተ ክርስቲያን እምነት አንጻር በጥንቃቄ መመዘን የሚያስፈልገው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን የኑፋቄውን ምንነት፣ ነገረ ሃይማኖታዊ አንድምታውን፣ ጥልቀቱንና ስፋቱን በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህን የሚያደርጉትም በሳል የሆነ ነገረ ሃይማኖታዊ እውቀት ያላቸው ሊቃውንት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔውን የሚሰጠው የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

፰. መናፍቃን እንዴት ይመለሱ?

ከቤተ ክርስቲያን በኑፋቄ ተወግዘው (ይፋዊ በሆነ ውግዘትም ሆነ ራሳቸውን በኑፋቄ በመለየታቸው) የተለዩ ሰዎች እንዲመለሱ የቤተ ክርስቲያን ናፍቆቷና ምኞቷ ነው፡፡ እንዲወገዙ የሚደረገውም ከላይ እንዳየነው ለራሳቸው ለሰዎቹ ጥቅም ሲባል፣ ነፍሳቸው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን እንድትድን ለመርዳት ሲባል እንጂ እንዲጠፉ አይደለም፡፡ ስለሆነም የመመለሳቸው ዜና ታላቅ የምሥራች ነው፣ ከዚህ የበለጠ ደስታም የለም፡፡ ጌታችን በትምህርቱ የጠፋው ልጅ ሲመለስ ስለሆነው ነገር ሲናገር እንዲህ አለ፡- “አባቱ ለአገልጋዮቹ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፣ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር፡፡” ሉቃ. 15፡22-24 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድ የጠፋ ልጇ ሲመጣ እንዲህ ደስ ይላታል፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በሰማይ ንስሐ ስለሚገባ አንድ ኃጥእ ደስ ይሰኛሉ፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችና ተግባሮችም አሉ፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን ከመጠበቅ አንጻር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ መናፍቃን የነበሩ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንመለሳለን ሲሉ ሊደረጉ የሚገባቸው ዋና ዋና ጥንቃቄዎችና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፡-
1. መመለሳቸው (ተመልሰናል ማለታቸው) የእውነት ነው? ከልብ ነው? ወይስ ለስልትና ለዘዴ ነው?
ቤተ ክርስቲያን እስካሁን በተጓዘችባቸው ዘመናት ሁለቱም ዓይነት ሰዎች በየጊዜው ሲገጥሟት ነበር፤ እነዚህም በአንድ በኩል በእውነት ተጸጽተው የሚመለሱ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ከልባቸው ሳይመለሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተመልሰው በመግባት ብዙ ምእመናንን ለመበረዝና ለማታለል ያመቻቸው ዘንድ በተንኮል ተመልሰናልና ተቀበሉን የሚሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ተመልሰናል ስላሉ ብቻ ዝም ብሎ መቀበል የዋህነት ሳይሆን ጅልነት ስለሆነ በሚገባ ማጣራትና መጠንቀቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
በኒቅያ ጉባኤ በቅዱሳን አባቶች ተወግዞ የተለየው አርዮስና የኑፋቄ ጓደኞቹ የተለያዩ ሰዎችን በመላክና በውስጥ ለውስጥ በሠሩት የፕሮፓጋንዳ ሥራ በመጨረሻ ላይ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አርዮስን ከፈረደበት ከግዞቱ እንዲወጣና ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣ አደረገው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም እምነቱን በጽሑፍ እንዲያቀርብ አዘዘው፡፡ አርዮስም በፊት የፈጠራቸውን የኑፋቄ ቃላትና ሐረጎች ሁሉ፣ እንዲሁም የተወገዘባቸውን የክህደት አንቀጾች ሁሉ ለጊዜው ወደ ጎን ትቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ያሉና ማንም ሰው ሊቀበላቸው የሚችላቸውን ነገሮች ብቻ ጽፎ “በፊትም ቢሆን ከዚህ የተለየ ሃሳብም ሆነ እምነት አልነበረኝ፣ አሁንም የማምነው ይህን ነው” በማለት ፈርሞ፣ በመሐላ አጽንቶ ሰጠው፡፡ ያ አርዮስ ጽፎ የሰጠው አንቀጸ እምነት እነርሱ (አርዮሳውያን) በፈለጉት መንገድ ሊተረጉሙትና የያዙትን አርዮሳዊ እብደት በቀላሉ በማያጋልጥ መልኩ በፈሊጥ ተሸፍኖ የቀረበ ማታለያ ነበር፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ግን እንዲያ ሲያደርግ ሲያየው አርዮስ በእውነት የተመለሰና ኦርቶዶክሳዊ የሆነ መሰለው፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አርዮሳውያን የነበሩ ጳጳሳት አርዮስ በይፋ መጀመሪያ በተወገዘበት በእስክንድርያ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባና ከምሥጢራት እንዲካፈል የሚል ደብዳቤ ንጉሡ እንዲጽፍላቸው አደረጉና ያን ደብዳቤ ከዛቻና ከማስፈራሪያ ጋር ወደ ቅዱስ አትናቴዎስ ወደ እስክንድርያ እንዲላክ አደረጉ፡፡ ለየአብያተ ክርስቲያናቱም አርዮስና ጓደኞቹ ኦርቶዶክሳውያን መሆናቸውን ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ የመሰከረላቸው ስለሆነ፣ በሲኖዶስም የተወሰነ በመሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ወደ ሱታፌ ምሥጢራት ይቀበሏቸው ዘንድ በጥብቅ የሚያሳስብ ደብዳቤ በፍጥነት ላኩ፡፡ የአርዮስ ቀኝ እጅ የነበረው አውሳብዮስ ዘኒቆምድያ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በደብዳቤው ላይ ቅዱስ አትናቴዎስን “ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመለሱ የሚፈልጉትን ሁሉ የማትቀበል ከሆነ እኔ ራሴ ሰው ልኬ ከመንበርህ አወርድሃለሁ” የሚል ዛቻ እንዲላክበት አደረገ፡፡ ብዙ ጊዜ ከታሪክ ስናይ መናፍቃን የፖለቲካ ሰዎችንና ባለ ሥልጣናትን በመዘወርና ከጎናቸው በማሰለፍ በኩል ጠንካሮችና የተሳካላቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ግን “የክርስቶስ ጠላት የሆነው አርዮስና ኑፋቄው ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ኅብረት የላቸውም” በማለት በጉባኤ የተወገዘውን አርዮስን በንጉሥ ቀላጤ አልቀበልም አለ፡፡ የቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ከአርዮሳዊ ክህደት አቀንቃኞችና ደጋፊዎች ጋር የገባው እልህ አስጨራሽ ትግል በዚህ ሁኔታ እየጠነከረ ሄደ፡፡ ከመንበሩ ስድስት ጊዜ እንዲሳደድና ከአርባ አምስት ዓመት ዘመነ ፕትርክናው አሥራ ሰባት ዓመቱን ያህል በስደትና በእንግልት እንዲያሳልፍ ያደረገው ይህ የአርዮሳውያን ተንኮልና ዘመቻ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አርዮሳውያን ያን ንጉሡ ከግዞት መመለሱን እንደ መልካም ካርድ በመጠቀም ከዚያ ቀጥሎ በነበሩት ሃምሳ ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ሲያውኳትና ሲፈትኗት ኖረዋል፡፡ ነገሥታትን ሳይቀር ከጎናቸው እያሰለፉ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳትንና ካህናትን ከየመናብርታቸውና አብያተ መቃድሳቸው እያሳደዱ እነርሱ ሲፈነጩባቸው ኖረዋል፡፡ ነገሩ የማታ የማታ እውነት ይረታ ሆነ እንጂ፡፡
ስለዚህ ዛሬም እንመለሳን የሚሉት ሰዎች በትክክል ከልባቸው ነው? ወይስ እንደ ግብር አባቶቻቸው እንደ አርዮሳውያን ውስጥ ገብተው ለመበጥበጥ ነው? የሚለውን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ “ታሪክ የሚያስተምረው ሰዎች ከታሪክ አለመማራቸውን ነው” የተባለው እንዳይደርስብን ማሰብ ይገባል፡፡ “በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህ እንጂ ገደሉን ሳታይ” እንደ ተባለውም እንዳይሆን እያንዳንዱ ምእመን፣ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ሊያስቡበትና ተገቢውን ነገር ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
2. ጉዳዮችን በቡድን ወይም በጅምላ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰው ደረጃ መመልከትና መለየት፣
እንመለሳለን የሚሉትን ወገኖቻችንን ጉዳያቸውን በእያንዳንዳቸው ማየትና ማጥናት ይገባል እንጂ በጅምላ ከዚህ ወዲያ ወይም ከዚያ መለስ ብሎ ማድረግ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር የሚፈርደው በእያንዳንዱ ሰው እንጂ በቡድን ወይም በጅምላ አይደለም፤ “እስመ አንተ ትፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ - አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ታስረክበዋለህና” እንደ ተባለ፡፡ መዝ. 61፡ እንዲሁም “እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ተብሏልና። ሮሜ 14፡12 ስለሆነም እያንዳንዱን በየግለሰቡ ጥፋቱ ምን አንደ ነበር፣ ለምን እመለሳለሁ እንዳለ፣ ወዘተ በዝርዝር ማጥናትና መወሰን ይገባል እንጂ “እነ እገሌ” በሚል የጅምላ ንስሐ የለምና ይህን ማስታወሱም ተገቢ ነው፡፡
3. ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ (እንዲያፈነግጡ) ያደረጓቸውን ምክንያቶች በሙሉ እንዲዘረዝሩ ማድረግና መመዝገብ፣
አንድ ሰው ዳነ ሲባል ታምሞ የነበረ መሆኑ፣ ተመለሰ ሲባል ደግሞ ወጥቶ ወደ ሌላ ሄዶ የነበረ መሆኑን ያጠይቃልና እንመለሳለን የሚሉት ሰዎች እያንዳንዳቸው ቀድሞ እንዲወጡ ያደረጋቸው ምክንያት ምን እንደ ነበረ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በሽታውን ደብቆ እንዲሁ አክሙኝ እንደሚል ሰው መምሰል ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ግን እንመለሳለን ለሚሉት ሰዎችም፣ ለማኅበረ ምእመናኑም ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡ ያን ኑፋቄ እንደገና ሲያስተምሩ ቢገኙ ማንነታቸውን በግልጽ ለመለየት ይጠቅማል፤ አለበለዚያ “ሞኝን እባብ ሁለት ጊዜ ነከሰው” (መጀመሪያ ሲያይ፣ ሁለተኛ ደግሞ ሲያሳይ) እንደ ተባለው ይሆናል፡፡
4. መመለሳቸውን፣ እንዲሁም ከምን ዓይነት ስህተት እንደ ተመለሱ ለሕዝቡ በይፋ መነገር ይኖርበታል፡፡
መናፍቃን ሲመለሱ በጓዳና ለሌሎች በማይታወቅ ሁኔታ ሳይሆን በግልጽ፣ ምእመናን ሁሉ በሚሰሙበትና በሚያውቁበት መድረክ በይፋ መሆን አለበት፡፡ በፊት የካዱትና ቤተ ክርስቲያንን ያሳጡትና የነቀፉት በይፋ እንደ ነበር ሁሉ ሲመለሱም በይፋ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ስለ መናፍቃን አመላለስ በጻፈው ቀኖና ላይ እንዲህ ይላል፡-


“በማንኛውም መንገድ ቢሆን ከኑፋቄ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመለሱ ሰዎች ምእመናን ባሉበት መሆን አለበት፤ ወደ ምሥጢራት ሊቀርቡ የሚገባቸውም እንዲህ ባለ ይፋዊ ሁኔታ ካለፉ በኋላ ብቻ ነው፡፡” ቀኖና ዘቅዱስ ባስልዮስ፣ ቁ. 1
እንዲህ ካልሆነ ብዙ ችግር ያስከትላል፡፡ እንዲህ ማድረግ ለአጭበርባሪዎችና ለተንኮለኞች መጠቀሚያ ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ ነገ ተመልሰው ያንኑ ዓይነት ችግር እንዳይፈጥሩ በይፋ መነገሩ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ አለበለዚያ ውስጥ ውስጡን ምእመናንን እየበከሉ ላለመቀጠላቸው ዋስትና አይኖርም፡፡ መመለሳቸው በይፋ ከተደረገ ግን የቀድሞ ኑፋቄያቸውን እናስተምራለን ቢሉ እንኳ “ተመልሰናል ብላችሁ አልነበረምን? የቀድሞ ስህተታችንን ትተናል ብላችሁ አልነበረምን?” ብሎ ለመጠየቅና በቶሎ ማንነታቸውን ለማወቅ ይረዳል፡፡
5. ከጥንት ጀምሮ የተነሡ የተለያዩ የኑፋቄ መሪዎችንና ዋና ዋና መናፍቃንን በጥንቃቄ ከተዘረዘሩ በኋላ ማውገዝ ይገባቸዋል፣
የሚመለሱ መናፍቃን በእውነት ከመናፍቃን የተለዩና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋር የተዋሐዱ ስለ መሆናቸው አንዱ ምስክር የሚሆነው ከቀድሞ ጀምሮ የተነሡ ዋና ዋና የኑፋቄ አመንጪዎችን በይፋ ማውገዝ ነው፡፡ ስለሆነም በጥንቃቄ በተዘጋጀ የመናፍቃን ዝርዝር ላይ እነዚያን መናፍቃን ማውገዝና ለዚህም መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡
6. እስከ ዛሬ ድረስ በስብከቶቻቸውና በመጻሕፍት ያስተማሯቸውንና የጻፏቸውን የኑፋቄ ትምህርቶች ሁሉ ቀድሞ ኑፋቄው ከተላለፈበት ልሳን ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ እንዲያወግዙና ስህተት መፈጸማቸውን ተቀብለው ከአሁን በኋላ እንደዚያ ዓይነት የስህተት ትምህርት እንደማያስተምሩ በጽሑፍ ቃል መግባት ይኖርባቸዋል፡፡
የስህተት ትምህርቱን በመጽሐፍ ወይም በቪሲዲ ወይም በካሴት እና በመሳሰለው ያስተላለፈ ሰው ስህተቱን ሲያምንና ወደ እውነት ሲመለስ የቀደመውን አስተምህሮውን ስህተትነት መግለጽ የሚገባው በዚያው የስህተት ትምህርቱን ባስተላለፈበት መንገድ (ልሳን - ሚዲያ) ነው፡፡ አለበለዚያ ተደራሽነቱ ተመጣጣኝ አይሆንም፡፡ የስህተት ትምህርቱን በመጽሐፍ የጻፈ ሰው በቃሉ “አጥፍቼ ነበር፣ አሁን ተመልሻለሁ” ቢል መመለሱንና የቀድሞውን አስተምህሮውን ስህተትነት ማመኑን የሰሙት በተናገረበት ጊዜና ቦታ የሚገኙት ሰዎች ብቻ ናቸው፤ ሌሎቹ ግን በመጻሕፍት የተጻፈውን ኑፋቄውን እንጂ በቃል የተናገረውን የሚያውቁበት መንገድ የለም፡፡ እንዲሁም በቃሉ ብቻ “ያ ቀድሞ ያልሁት ስህተት ነው” ብሎ ቢናገር ያ ነገር ከአንድ ትውልድ ያለፈ ሊታወስና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ሊጠቀስ አይቻልም፣ መጽሐፉ ግን ለዘመናት ትውልድን እየተሻገረ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
ስለሆነም በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች አንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመለስ ሰው ቀድሞ የስህተት ትምህርቱን ካስተማረበት የሚዲያ ዓይነትና ተደራሽነት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ መግለጽ ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለብዙዎች መሰናከያ አድርጎ ያስተማረው እንክርዳድ መበከሉን እየቀጠለና ትውልድ እየተሻገረ ስለሚሄድ ስለ አንዱ ሰው መመለስ እንደምንጨነቀው ሁሉ ይህ ሰው በኑፋቄ ትምህርቱ ስላጠፋቸው ስለ ብዙዎቹም ማሰብ የግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ያ ሰው ያጠፋቸውን የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ረስተን ለአንዱ ብቻ የተጨነቅን መስሎን የምናደርገው ነገር ውስጡ ወይ አለመረዳት ወይም ደግሞ ሌላ ነገር እንዳይሆን ማሰብ ይገባል፡፡
7. በእርሱ የኑፋቄ ትምህርት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የወጡትን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ይኖርበታል፡፡
ኑፋቄውን በማስተማሩ ምክንያት ለብዙዎች ከቤተ ክርስቲያን መውጣት ምክንያት የሆነና በነፍሳቸው እንዲሞቱ ያደረገ ሰው ሲመለስ በመጀመሪያ እነዚያ ያጠፋቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ይኖርበታል፡፡ መርቅያን የተባለው መናፍቅ ብዙ ሰዎችን ካጠፋና የራሱን አንጃ መሥርቶ ከኖረ በኋላ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ በኑፋቄው ተጸጽቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ልመለስ ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከሁሉም አስቀድሞ በመጀመሪያ ማድረግ እንዳለበት የነገሩት ነገር ቢኖር ወደ ስህተት የመራቸውን ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመልስ ነበር፡፡ ያን ለማድረግ በመሯሯጥ ላይ እያለ ታመመና ሞተ፡፡ ይህ በየዘመናቱ እንመለስ ሲሉ በነበሩ ሰዎች ላይ ሲፈጸም የኖረ ቀኖና ነው፡፡ ሽዎችን አጥፍቶ አንድ እርሱ ብቻ ቢመለስ እግዚአብሔር ስለ ጠፉት ስለ ብዙዎቹ ግድ የለውምን? እንዲህ የሚያደርጉትንስ ዝም ብሎ ይመለከታቸዋልን? ስለዚህ ይህን ጉዳይ መዘንጋት አይገባም፣ ለመጥፋታቸው ምክንያት የሆኗቸውን ሰዎች (በእነርሱ ምክንያት የጠፉትን ሁሉንም ለይቶ ማወቅ ባይቻልም እንኳ) ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግና መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡


8. እያንዳንዳቸውን በኦርቶዶክሳዊ መንገድ የሚመራቸው በነገረ ሃይማኖት በሳል የሆኑ አባቶችን መመደብ፣
ኦርቶዶክሳዊነት ከሁሉም በላይ እሳቤው፣ መንፈሱ እንዲገባቸውና እንዲሠርጻቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርቷን ሳያውቁ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤና እይታ እንዲሁም መንፈስ ሳይኖራቸው በሌላ ቅኝት መንፈስ የኖሩ ሰዎች እንደ መሆናቸው እንመለስ ስላሉ ብቻ አብሯቸው የኖረውና የሠረጻቸው የኑፋቄ ትምህርትና መንፈስና እንዲሁ በአንድ ጊዜ ውልቅ ብሎ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የያዛቸው የኑፋቄ መንፈስ እንዲለቃቸው፣ እርሾው ጭልጥ ብሎ እንዲጨለጥላቸው ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ጀምበር የሚፈጸም አይደለም፡፡ ጌታችን “ዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት - ይህ ዓይነት አብሮ አደግ ክፉ መንፈስ ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም” እንዳለ፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሃይማኖታዊ መንፈስንና እይታን፣ ኦርዶክሳዊ አስተምህሮንና በአጠቃላይ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ምን እንደሆነ በበሰለ እውቀት፣ በእውቀት ብቻም ሳይሆን በሕይወት የሚያስተምራቸው በሳል አባት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቆዳ በማውለቅና ልብስ በመቀየር ብቻ ከኑፋቄ ወደ ኦርቶዶክሳዊነት መመለስ አይቻልም፡፡
ባለፉት የቅርብ ጊዜያት (በ1990ዎቹ ዓመታት) በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ካጣራ በኋላ በሃይማኖት ችግር (በተሐድሶነት) የተጠረጠሩትን ወደ አንዳንድ ቦታዎች ሄደው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማሩ ተብሎ ነበር፡፡ ከእነዚያ ለቀኖና ተብለው ከተላኩት መካከል ግን አጋጣሚውን ሌላ ጥፋት ለመሥራት እንደ ምቹ አጋጣሚ የተጠቀሙበት ነበሩ፡፡ ከዚህም የተነሣ እየተማሩ ይቆዩ ተብለው ከተላኩት መካከል ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን አባቶች አስክደው ወደ እነርሱ የጥፋት መንገድ ለማስገባት የተጠቀሙበት ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ የፕሮቴስታንታዊ ትምህርቶችን በተለያዩ መንገዶች ለማስፋፋት ሲሞክሩ የተደረሰባቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ ያን ጊዜ እንደ ተደረገው እንዲሁ ሁለት ሁለት እያደረጉ ወደ ሆነ ገዳም ወይም ቦታ መላክ ብቻውን ሰዎቹን አይለውጣቸውም፡፡ ስለዚህ በዚህም ከፍተኛ ሥራና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” እንደሚባለው እንዳይሆን፡፡
9. የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የሚቀበሉ ስለ መሆናቸው ግልጽና ጠንቃቃ የሆነ ቃለ ጉባኤ አዘጋጅቶ እንዲፈርሙ ማድረግ
ይህም አስፈላጊ ነው፡፡ የሰው ነገር ነገ የሚሆነው ስለማይታወቅ ለወደፊቱም ጥሩ መሠረትና ማስረጃ፣ ምስክርም ይሆን ዘንድ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮና ሥርዓት ያለ አንዳች ቅሬታ የሚቀበሉ ስለመሆናቸው ቃለ ጉባኤ ተይዞ በሚዘጋጅ ወረቀት ላይ መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡
10. ቀኖና መስጠት - (በመድረክ ላይ ይቀጥላሉ ወይስ አይቀጥሉም?)
ይህ ለአባቶች የሚተው ጉዳይ ቢሆንም እዚህ ላይ ያነሣነው እንዲሁ ለትምህርት ያህል ግን አስፈላጊነቱን ሳይጠቅሱ ማለፍ አይገባም በሚል ነው፡፡ እንዲያውም ፍትሐ ነገሥታችን ለሌላው ሰው ክህደት ምክንያት የሚሆን ሰው ሲመለስ ቀኖናው ከበድ ያለ እንዲሆን ያዝዛል፡-
“ወለዘኢአከሎ ክሕደቱ ባሕቲቱ እስከ ያወጽኦ ለካልኡ እምሃይማኖቱ ወኮነ ምክንያተ ለክህደቱ ይኩን ንስሓሁ ፈድፋደ - የራሱ ክህደት ብቻ አልበቃው ብሎ ባልንጀራውን ከሃይማኖቱ እስኪያወጣው ድረስ ለመካድ ምክንያት ቢሆን ንስሓው ጽኑዕ ይሁን፡፡” አንቀጽ ፳ ቁ. ፯፻፷
ከዚሁም ጋር ገና ተመለስን እንዳሉ “በዚያው በለመድነው ማስተማራችንን እንቀጥላለን፣ ከመድረክ አንወርድም የሚሉ ከሆነም ሌላ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ አንድ ሰው ቀኖናውን ሳይጨርስ እንዲያ ማድረግ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ አንድ በኑፋቄ የነበረ ሰው እንዲሁ “ተመልሻለሁ” ስላለ ብቻ በውስጡ የነበረው ኑፋቄ በአንድ ጊዜ በተአምራት በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት አይሞላም፡፡ ስለዚህ በመድረክ እቀጥላለሁ ካለ የሚያስተምረው ያንኑ ከመመለሱ በፊት ሲያስተምረው የነበረውን የቀድሞ የስህተት ትምህርት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ከየት ያመጣል? ጌታችን “ኄር ብእሲ እምሠናይ መዝገበ ልቡ ያወጽኣ ለሠናይት ወእኩይሰ ብእሲ እምእኩይ መዝገበ ልቡ ያወጽኣ ለእኪት እስመ እምተረፈ ልብ ይነበብ አፍ - በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና፣ መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል” እንዳለ፡፡ ሉቃ. 6፡45
ታዲያ በኑፋቄ የኖረና ልቡ በዚያ ተሞልቶ፣ ከዚያ ውስጡን ከሞላው ኑፋቄ ለሌሎችም ሲናገር የኖረ ሰው ተመልሻለሁ ስላለ ብቻ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና መንፈስ በአንድ ጊዜ ውስጡ ይመላበታልን? ይኽ ጌታችን ካስተማረው ትምህርት ጋር የማይሄድ ስለሆነ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ተመልሰናል የሚሉት ሰዎች መመለሳቸውና ንስሐቸው የእውነት መሆን አለመሆኑ የሚገለጥበትና የሚፈተንበት አንዱ መንገድም ይኽ ነው፤ የተመለሱት በእውነት ከሆነ ግድ እናስተምር፣ በመድረክ እንቀጥል አይሉም፤ ነገር ግን የተንኮልና የስልት ከሆነ መድረኩ ላይ ካልቀጠልን ብለው የሙጥኝ ይላሉ፡፡
በዚህም ላይ አንድ በእውነተኛ መንፈስ ንስሐ የሚገባ ሰው በመጀመሪያ የሚያሳስበው ነገር እግዚአብሔርን በመበደሉ ይቅር እንዲለው፣ በደሉና ንስሓው እንጂ አሁንም መድረክ ላይ የመቀጠሉ ጉዳይ ሊሆን አይገባውም፡፡ እንመለስ የሚሉ ሰዎች ጭንቀታቸው መድረክ ላይ ስለ መዘመራቸውና ስለ መስበካቸው ከሆነ ጉዳዩ ዓላማን በውጭ ሆኖ ማስፈጸም ስለማይመች ወደ ውስጥ ገብቶ ተሐድሷዊውን ዓላማ ለማስፈጸም የአስገቡኝ ጥያቄ እንጂ የመመለስና የንስሐ ጥያቄ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይኼ የድርድር እንጂ የንስሓ መንገድ አይደለም፡፡ የእንመለሳለን ጥያቄው ትኩረቱ በመድረክ ላይ ስለ መዘመርና ስለ መስበክ ከሆነ ጉዳዩ በእውነትም የእድሜ ማራዘሚያና የተንኮል ስልት እንጂ በቅንነት የተደረገ የእንመለሳለን አካሄድ ሆኖ አይታይም፡፡
11. የሚደረጉትን እያዳንዳቸውን ነገሮች ሁሉ በከፍተኛ ጥንቃቄና ማስተዋል ማድረግ
የጠፉትን መቀበል ተገቢና መልካም ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሂደት የሚደረጉት እያንዳንዳቸው ነገሮች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቷ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ያላት ቁርጠኝነትና ድርጊቶቹ በኅብረተሰቡ ሥነ ልቡናዊና ሃይማኖታዊ አረዳድና መንፈስ ላይ ሸርሻሪ መሆን አለመሆናቸውን መጠየቅና በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ መናፍቃን የነበሩትን መቀበል የቤተ ክርስቲያንን እምነት መሸርሸር ተደርጎ እንዳይታይ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ አለበለዚያ አንዱን እገነባለሁ ሲሉ ሌላውን ማፍረስ እንዳይሆን፡፡
እነዚህ ነገሮች በሚሆኑበት ጊዜ የሕዝቡን አረዳድና ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ገና ለገና ለወደፊቱ ይጠቅማል በማለት በጊዜው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ውሳኔና ድርጊት ውስጥ መግባት አደገኛ ነው፡፡ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አርቆ ማየት ያስፈልጋል፣ ጭምብሎቻቸውን ገልጦ ትክክለኛ ማንነታቸውንና አደጋውን መረዳትና መለየት ያስፈልጋል፡፡
“ሰላም ሰላም” በሚል ቃል ብቻ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያንን ውሳጣዊ ሰላም፣ እንዲሁም ጊዜያዊ ችግር የፈታንና ያቃለልን ሲመስለን ለወደፊቱ ችግር እያወሳሰብንና እያቆላለፍን እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርብ ጊዜ በዘመናችን ከስድስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ በሆነችው በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሆነውን አሳዛኝ ነገር ልንረሳው አይገባንም፡፡ በዋናነት በአንግሊካን ፕሮቴስታንት ቸርች (በእንግሊዝ ቤ/ክ) ቀያሽነትና አስፈጻሚነት በውስጣቸው ተፈልፍለው ያደጉት ተሐድሶዎች ገና ከመጀመሪያው ጉዳዩን የተረዱ አባቶችና ምእመናን ለይተው የማውገዝና የማጥራት ሥራ ሊሠሩ ሲሉ ተሐድሶዎቹ የእንመለሳን፣ የአስታርቁን ሽምግልና በተለያዩ ሰዎች በኩል ይልኩባቸው ነበር፡፡ በሽምግልናው ይሳተፉ የነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲሁ በሽፍኑ እርቅ ማን ይጠላል፣ ሰላም ምን ክፋት አለው በሚሉ መሸፈኛዎች የተታለሉና ምን እያደረጉ እንደሆኑ የማያውቁ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አስታረቁ ተብለው ስም ለማሰርና ጀብድ እንደ ሠሩ ለመቆጠር ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸውን በአስታራቂነት ጎራ ሲመድቡ እነርሱ ከሌሎቹ የተሻሉ አስተዋዮችና ያላከረሩ ብልሆች እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዋናዎቹ ከጀርባ ሽማግሌዎቹን የሚልኳቸውና በሽምግልናውም ውስጥ ዋናውን ሥራ ይሠሩ የነበሩት ጥቂቶቹ ግን ዓላማው ገብቷቸው ተሐድሶዎቹ በደንብ ሳይጠነክሩና ሳይጎለምሱ፣ ብዙዎችን ወደ እነርሱ ጎራ ሳይለውጡ እንዳይወጡ እንደ እድሜ ማራዘሚያ ስልት ለመጠቀም ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ሳይወገዙ “እርቅ”፣ “ይቅርታ፣ “ንስሐ” እየተባለ ውስጥ ውስጡን ብዙ ካህናትንና ምእመናንን ከመለመሉና ከቀሰጡ በኋላ ራሳችንን የቻልንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለው ሲያስቡ መላዋን ቤተ ክርስቲያን መቆጣጠር ስላልቻሉ በይገባኛል የቤተ ክርስቲያኒቱን ነገር ሁሉ በፍርድ ቤት ተካፍለው ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውስጡን ተሐድሶ ያደረጓቸውን ካህናትና ምእመናን ይዘው በመውጣት የራሳቸውን የተሐድሶ ቤተ እምነት መሥርተዋል፡፡ እነዚህም “ማር ቶማ ቸርች” ይባላሉ፡፡ ምሥራቃዊ ፕሮቴስታንትም (Oriental Protestant) ይሏቸዋል፡፡ እርቁንና ሽምግልናውን እየተቀበሉ ተወግዘው እንዳይለዩ ሲደግፉና ሓሳብ ሲሰጡ፣ በጊዜው ጊዜ ተወግዘው እንዲለዩና ምእመናን እንዲያውቋቸው ለማድረግ ይጥሩ የነበሩ ጳጳሳትንና ምእመናንን እየለመኑና እያግባቡ “እርቅ፣ ሰላም፣ አንድነት” በሚሉ ቃላት ተታለው ሲያታልሉ የነበሩት ጳጳሳትና ምእመናን ግን የኋላ ኋላ ጥቅም የሌው ጸጸት ብቻ ነበር ያተረፉት፡፡ ነገሩ ጅብ ከሄደ ሆነባቸው፡፡
ስለሆነም ይህ ጉዳይ አንድ ጊዜ ከመቁረጥ በፊት አሥር ጊዜ፣ ካስፈለገም ከዚያም በላይ፣ መለካት የሚያስፈልገው ጠንካራ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁ በይሁን ይሁን፣ በምናለበት፣ ያለ ማስተዋልና ያለ አርቆ ማሰብ የሚደረግ ነገር በኋላ በእግዚአብሔርም ዘንድ፣ በትውልድም ዘንድ ያስጠይቃልና መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ይኼው የሕንድ ቤተ ክርስቲያን የደረሰባትን አሳዛኝ ነገር እኛ እያዘንን እንደምንጠቅሰው፣ ሌላውም ዛሬም ወደፊትም እንደ አሳዛኝ ታሪክ ማሳያ እያደረገ እንደሚጠቅሰው ሁሉ የእኛ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን በዚህ ጉዳይ ላይ ከፊታችን የሚሠሩት ሥራም በበጎም ሆነ በክፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ግን በአስተዋይነት የተሠራ መልካም ሥራ ሆኖ በበጎ ታሪክነትና በአስተማሪነቱ የሚጠቀስ ይሆን? ወይስ በስህተትና “በእነርሱ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ” በሚል ማስፈራሪያነት? ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ግን ከአፍንጫ ሥር ያለውንና ከፊት የቀረበውን ብቻ አሽትቶና አይቶ የሚወሰን ሳይሆን ወደ ኋላ ከዘመነ ሐዋርያት አንሥቶ የነበረው ታሪከ ቤተ ክርስቲያንና አስተምህሮን፣ አሁን ደግሞ ያለንበትን ጠቅላላና ዝርዝር ተጨባጭ ሁኔታ፣ ወደፊትም በእግዚአብሔርና በትውልድ ያለብንን ኃላፊነት ታሳቢ ያደረገ ቀኖናዊ ሂደት ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፣ እንዲኖርም እንፈልጋለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም ናትና እያንዳንዳችንም ችላ ሳንል፣ “እንዳረጉ ያድርጉት፣ እኔ ምን አገባኝ” ሳንል የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ቀኖናዊነት በጠበቀና ባገናዘበ መልኩ የየድርሻችንን እንወጣ፡፡
  • “ከወዳጆችህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጠላቶችህም ጋር እንኳ ሳይቀር በሰላም ኑር፤ ነገር ግን እንዲህ የምልህ ካንተ ከግል ጠላቶችህ ጋር እንጂ ከእግዚአብሔርና ከቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ጋር አይደለም፡፡”አንድ ገዳማዊ አባት ለአንድ በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ላይ ለነበረ ሌላ አባት ከጻፈው መልእክት ላይ የተወሰደ
  •  “ሰውን ከእግዚአብሔር ከሚለየው አጉል ሰላም ይልቅ ከእግዚአብሔር የማይለየው ጦርነት ይሻላል፤ ስሜታዊ ከሆነና ለቤተ ክርስቲያን ዘለቄታዊ ጉዳት ከሚኖረው ስምምነትና አንድነት ይልቅ ስለ ሃይማኖት መጠበቅ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ የሚኖረውና ለዚህ ሲባል የሚሆን አለመስማማት ይሻላል፡፡”
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ትምህርት 2፡82

 

 

No comments:

Post a Comment