Monday, 13 January 2014

የአ/አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ተቃዋሚዎች ገዳማቱንና አድባራቱን አይወክሉም ‹‹ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት የተረቀቀው ሕግ ወደ ኋላ አይመለስም፤ መሥመሩን አይለቅም›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/


(አዲስ አድማስ ) ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ /ስብከት ለመዋቅርና አሠራር ለውጥ በባለሞያ ያካሔደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት እንቃወማለን የሚሉ ውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች አይወክሉንም ሲሉ የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ልዩ ልዩ አገልጋዮችና ምእመናን ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡ ለዘመናት የቆየው የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና የሥራ ሒደት ከነበረው ተስፋፍቶ፣ የወቅቱን አሠራርና ሥልጣኔ የዋጀ ኾኖ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔና በፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በባለሞያዎች መዘጋጀቱንና ረቂቁ ወደ ታች ለግምገማ ወርዶ እንደተወያዩበት አስተዳዳሪዎቹና አገልጋዮቹ ጠቅሰዋል፡፡

የግምገማው ሪፖርት በሀ/ስብከቱ ተጠናቅሮ የሚቀርብለት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ሳይታወቅ በሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ስም ‹‹በውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች›› በጥናቱ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞና በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ የሚሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ÷ ‹‹ከመሥመር የዘለለ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ አንድነትና ጥቅም እየደከሙ ያሉትን ብፁዓን አባቶች በመድፈር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰድቦ ለሰዳቢ አጋልጧታል፤›› ብለዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በአምስት ሺሕ የአስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ፊርማ አስደግፈው ማቅረባቸውን የገለጹት በመቶዎች የሚቆጠሩ እኒህ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች፣ /ስብከቱ እያካሔደው በሚገኘው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹ወሳኝ አባት›› እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡
ከቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ውጭ በኾኑ፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና ጠባየ ብልሹነት ባለባቸው ውስን ሰዎች ሳቢያ ምእመኑ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዲያመራ እየተደረገ በመኾኑ ጉዳዩ አንገብጋቢ መኾኑን በመጠቆም፣ ‹‹በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ የሚደረግ የስም ማጥፋት ዘመቻና ሰድቦ ለሰዳቢ የመስጠት ሕገ ወጥ ተግባር›› መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከማስጠበቅ ጋራ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአባቶችን ክብር ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ የሚችል ጠበቅ ያለ ሕግ ማውጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡ የጥያቄ አቅራቢዎቹን አቤቱታ ያዳመጡት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ ኹሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመኾናቸው የኹሉንም ሐሳብ የመስማት ሓላፊነት ቢኖርባቸውም በተቃዋሚዎቹ በኩል የተሰማው ሕገ ወጥና ግብረ ገብነት የጎደለው ንግግር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰዋል፤ አኹን ደግሞ በተረጋጋ መንገድ ስለቀረበው የአስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ጥያቄ አመስግነዋል፡፡
በባለሞያዎች የቀረበው የሀ/ስብከቱ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቅ ወደኋላ የሚመለስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ፓትርያርኩ ገልጸው፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና፣ ለሃይማኖት መጽናት የሚጠቅመውን ሐሳብ ኹሉ ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የዘመኑ ምሁራን የተካተቱበት በቁጥር 9 - 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቁን ዳግመኛ እንዲያዩት መቋቋሙን ለጥያቄ አቅራቢዎቹ ያስታወቁት አቡነ ማትያስ፣ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲኖራት የተዘረጋው ሕግ ረቂቅ መሥመሩን እንደማይለቅ አረጋግጠውላቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment