- የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢና ወጪ ኦዲት እስከ ግንባታው ፍጻሜ መዘግየቱ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ ተፈጻሚነት አዳጋች እንደሚያደርገውና የግንባታው ሒደት ምርመራም ከግንባታው መጠናቀቅ በኋላ እንዲኾን መታዘዙ የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ እንደሚያሥነሳ የገለጹ ምእመናን፣ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ያስተላለፈውን ትእዛዝ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
- የኦዲት ምርመራው እንዲዘገይ ከድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ ጋራ እንደተስማሙ አስመስለው ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ያስረዱት ብርሃኔ መሐሪ፣ በአድራሻ ለፓትርያርኩ በግልባጭ ደግሞ ለድሬዳዋ ሀ/ስብከት ጽ/ቤትና ለሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በጻፉት ይዘቱ የተለያየ ደብዳቤ÷ ‹‹ማን እንደሚመራው የማይታወቅ ሲኖዶስ ግራና ቀኙን ሳያጣራ በግብር ይውጣ ያስተላለፈው ነው›› በሚል ቋሚ ሲኖዶሱ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ያስተላለፈውን ውሳኔ ማጣጣላቸው ተዘግቧል፡፡
- የደብሩን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በብቸኝነት የሚያዝዙበት መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ፣ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የበላይ ሓላፊነት የሚመራው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ከፓትርያርኩ እንደተሰጠው በተገለጸ መመሪያ መሠረት የኦዲት ምርመራውን እስከ ግንባታው ፍጻሜ በማዘግየቱ ዝርፊያውን ያጋለጡ ተሟጋች ምእመናን ‹‹ምንም አታመጡም›› በሚል እየተሳለቁባቸው ነው፤ የደብሩ አስተዳዳሪንም ‹‹በአቋም ወደ እኛ የማትመጣ ከኾነ እናበርሃለን›› ሲሉ ዝተውባቸዋል፡፡
- መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ከጥቅመኞቹ የሕንፃው ተቋራጭ ኤፍሬም ተስፋዬ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ኢንጅነር ሰሎሞን ካሳዬ ጋራ በመኾን በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤቱ እንዲተላለፍ ያደረጉት ለሙስናና አማሳኞች ሽፋን የሚሰጠው ትእዛዝ፣ የሀ/ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አሳዝኗል፤ የከተማውን ምእመናን አበሳጭቷል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ምእመናኑን ዛሬ በጉዳዩ ላይ እንደሚያወያዩ ተጠቁሟል፡፡
- ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ÷ ከሀ/ስብከቱ፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት በተውጣጡ ተወካዮች አማካይነት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የገቢና ወጪ ሒሳብ ኦዲትና የግንባታ ሒደቱ ምርመራ ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ለማስፈጸም ብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች የሚመረጡባቸውን አግባቦች በማዘጋጀት ላይ የነበሩ ሲኾን የምርመራ ሪፖርቶቹ እስከ ሚያዝያ ፲፱/፳፻፮ ዓ.ም. ተጠናቅቆ እንዲቀርብ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡
- የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ማስፈጸም ያለበት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ከመዝባሪዎች ጋራ የመከረበትን ትእዛዝ ሳይኾን የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ መኾን እንደሚገባው ያሳሰቡት የደብሩ ምእመናን፣ ትእዛዙ ‹‹የፓትርያርኩ ፀረ ሙስና አቋም በተግባር የተፈተነበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
- የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በአድራሻ ለሀ/ስብከቱ በግልባጭ ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ ትእዛዙን ያስተላለፈበት ደብዳቤ ትላንት በደብሩ አስተዳዳሪ በንባብ በተሰማበትና የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ፓትርያርኩ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ መሻር እንደማይችሉ የገለጹት ምእመናኑ እንዳስጠነቀቁት÷ የኦዲት ምርመራው በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት የማይፈጸም ከኾነ በደብሩ ሕንፃ ግንባታ ስም የሚካሔዱ ማንኛውንም የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴዎች በማገድ ለመንግሥት አቤት ይላሉ፡፡
* * *
- በጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ዊነር ኮንስትራክሽን ከተባለው ደረጃው ከማይታወቅ የአቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ተቋራጭ ጋራ በተያዘ ውል፣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ በ2 ዓመት ጊዜና በ2‚984‚562.51 ሚልዮን ብር ወጪ መጠናቀቅ ነበረበት፡፡ ከውለታ ጊዜው ውጭ ለ6 ዓመታት የዘገየውና 8 ሚልዮን ብር የፈጀው የግንባታ ሒደት ግን ከ70 – 80 በመቶ ብቻ እንደተፈጸመ የተመለከተው፡፡
- የግንባታ ፈቃድ እና ደረጃው በተለየ መሐንዲስ ቁጥጥር ተደርጎበት የማያውቀው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ÷ ሥራው ከዲዛየኑ ውጭ ስለመከናወኑ፣ ምእመናን በዐይነት የሚያበረክቷቸው አስተዋፅኦዎች (ቆርቆሮ፣ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ አሸዋ) በአግባቡ ተተምነው ገብተው ወጪ እንደማይደረጉ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ለቅ/ገብርኤል ክብረ በዓል በግንባታው ስም የሚሰበሰበው ከፍተኛ ገቢ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን በብቸኝነት ከሚቆጣጠሩትና የግል ኢንቨስትመንታቸውን በማጧጧፍ ላይ ካሉት ብርሃኔ መሐሪ በቀር በሚመለከተው አካል በትክክል እንደማይታወቅ በኅዳር ወር ፳፻፭ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተሠየመው አጣሪ ልኡክ ለቅ/ሲኖዶሱ ባቀረበው ሪፖርት ተረጋግጧል፡፡
- ቋሚ ሲኖዶሱ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢና ወጪ እንዲሁም የግንባታው ሒደት በብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ለሦስተኛ ጊዜ የተሠየመው የጠቅ/ቤ/ክህነቱ አጣሪ ልኡክ ባቀረበለት ሰፊ ሪፖርት ላይ የተመሠረተ ኾኖ ሳለ፣ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ከግንባታው ፍጻሜ በፊት እንዳይካሔድ ማዘዙ በርግጥም የፓትርያርኩ የፀረ ሙስና አቋም ከኹኔታዎች ጋራ የሚጋሽብ ለመኾኑ የሚያመላክትና በመግለጫዎች የሚናገሩለትን ቆራጥነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ አይቀርም፡፡
- የድሬዳዋ ሀ/ስብከትን ከአዲስ አበባ ኾነው ለሁለት ዓመታት የመሩትና በሕንፃው ግንባታ ዙሪያ ሲቀርቡ ለቆዩት የምእመናን ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚጋፋውን የኦዲት ምርመራ የሚያዘገየውን ትእዛዝ በፊርማቸው ወጪ ያደረጉት በፓትርያርኩ መመሪያ ነው ቢባልም ወቀሳንና ተጠያቂነትን የሚያስቀርላቸው አይኾንም፡፡ – ‹‹ብፁዕ አባታችን፣ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል እየተፈጸመ የሚገኘው ከባድ ወንጀል ሕዝበ ክርስቲያኑን እያስቆጣ ከመምጣቱም ባሻገር ብፁዕ አባታችን ይህን እየሰሙና እያወቁ ምነው ዝም አሉ ብሎ ሕዝቡ እንዲያስብ አድርጎታል፡፡… ›› /የደብሩን ወቅታዊ ጉዳይ ለማሳወቅ ምእመናኑ በኅዳር ፳፻፬ ዓ.ም. ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ከጻፉት አቤቱታ የተወሰደ/
No comments:
Post a Comment