የአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ካህናቱንና ምእመናኑን እያነጋገረ ነው
- ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲያገልግሉ ብቻ ሳይሆን በትምህርትና በተግባራዊ ልምምድ ለከፍተኛ ክብርና ማዕርግ እንዲበቁም ትሠራለች
- ገዳማት እና አድባራት የልማት ፈንድ ያቋቁማሉ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰሞኑን ለሀ/ስብከቱ ባለድርሻ አካላት ለውይይት ያቀረበው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ካህናቱንና ምእመናኑን እያነጋገረ ነው፡፡ የጥናት ሰነዱን እንደማይቀበሉት የሚገልጹ ወገኖች፡- ‹‹ጥናቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያልተሳተፉበትና በውይይት ያልዳበረ በመኾኑ በገለልተኛና ልምድ ባላቸው ምሁራን ይሰናዳ፤ ከነባሩ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዐዋዲ ጋራ የሚጋጭና የሚጣረስ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ጥናቱ ‹‹ነባሩን ሠራተኛ በማፈናቀል በስመ ዲግሪና ዲፕሎማ ዕውቀት የሌለውን በመዋቅሩ ውስጥ በመሰግሰግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር ያለመ ነው፤›› የሚሉት እኒሁ ወገኖች፣ ‹‹የአጥኚው አካል ማንነት በግልጽ አይታወቅም፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ሥልጣን ያለውን የፓትርያርኩን ሥልጣን ይጋፋል፤›› የሚሉ ተቃውሞዎችን በመዘርዘር አቤቱታቸውን ለፓትርያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አቅርበዋል፡፡
ተቃዋሚዎቹ በአደረጃጀትና አሠራር ትግበራው በሚመጣው ለውጥ ተጠቃሚ የኾኑትን ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደማይወክሉ ለኢትዮ – ምኅዳር የተናገሩ የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች በበኩላቸው፣ የተጀመረው የለውጥ ሒደት በሐቅ ላይ ባልተመሠረተ፣ ቅንነት በጎደለውና ደረጃውን ባልጠበቀ የአቋም መግለጫ ወደኋላ እንደማይመለስ በመግለጽ ተቃውሞውን አስተባብለዋል፡፡
የጥናቱ መነሻ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኃይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ የተሰጠው ውሳኔ መኾኑን ሓላፊዎቹ አስታውሰዋል፤ጥናቱን ያካሄደው የባለሞያ ቡድንም በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በኾኑት አቡነ እስጢፋኖስ መዋቀሩንና ሥራውን ከመጀመሩ በፊትም በፓትርያርኩ ፊት ቀርቦ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አልፎ ለሌሎች አህጉረ ስብከትም የሚያገልግል የአሠራር ጥናት በማድረግ አደረጃጀቶችንና መመሪያዎችን እንዲያዘጋጅ አባታዊ መመሪያ መቀበሉን ገልጸዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ በአንድ ሀገረ ስብከትና በአንድ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ከተወሰነ በኋላ ከሐምሌ 2005 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለሦስት ወራት የተመራበትንና ቋሚ ሲኖዶስ ያጸደቀውን ጊዜያዊ መዋቅር የሠራው የባለሞያ ቡድኑ፣ በፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ ላይ ተመሥርቶ በረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው የቅርብ ክትትል እየተደረገለት በቀጣይ ባከናወነው ጥናት÷ ክህነታዊ አገልግሎትንና ስብከተ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ፣ ወጥነት ያለው የሰው ሀብት አስተዳደርና ዘመኑን የዋጀ የፋይናንስ አሠራር ለመዘርጋትና በልማት ራስን ለመቻል የሚያበቃ 13 ጥራዞች ያሉት ሀገረ ስብከት አቀፍ መዋቅርና አደረጃጀት ሰነድ አርቅቆ ጥቅምት 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ማቅረቡ ተገልጦአል፡፡
ጥናቱ በባለሞያ ቡድኑ ገለጻ ታግዞ በስላይድ የቀረበለት የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም ዐይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውለው ይኹንታና የአፈጻጸም አቅጣጫ እንደሰጠበት ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት ቁጥራቸው ከ2700 በላይ የኾኑ የሀ/ስብከቱ የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ የሰባት ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ መሪዎች፣ የ169 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና ምእመናን ተወካዮች ከኅዳር 17 – ታኅሣሥ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. በተለያዩ ዙሮች በንቃት እንደተወያዩበት ሓላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ የውይይት መድረኮቹ፣ ‹‹ጥናቱ በይዘቱ እንዲዳብርና በአቀራረቡ እንዲስተካከል ግብአት የሚኾኑ ትችቶችና አስተያየቶች የተገኙበት አሳታፊ ብቻ ሳይሆን ሳይዘገይ ጸድቆ እንዲተገበር ብዙኃኑ አገልጋይና ሠራተኛ በአማካይ እስከ 96 በመቶ ድጋፍ በመስጠት ግፊት ያደረገበትም ነበር፤›› ብለዋል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያኑም ይኹን በቃለ ዐዋዲ ደንቡ፣ የሁሉም አህጉረ ስብከት ማዕከል የኾነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው ልዩ ደንብና መመሪያ እንደሚተዳደር መደንገጉን የጠቀሱት ሓላፊዎቹ የጥናት ሰነዱን በሲኖዶሱ አባላት እየታየ ከሚገኘው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ጋራም ለማገናዘብ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ኹሉ አኳያ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ወሳኝ አካል የኾነው ሲኖዶሱ በምልአተ ጉባኤ ስብሰባው ባስተላለፈው ውሳኔና የውሳኔው አስፈጻሚ የኾኑት ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ መሠረት÷ ዕውቅና ባለው፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በተውጣጣና ቤተ ክርስቲያኒቱን በጥልቀት በሚያውቅ የባለሞያ ቡድን አዲስ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነድ መዘጋጀቱ የሚጥሰው ሕግና ደንብ የለም በማለት የሕግና ደንብ ጥሰት እንዳለ የተሰነዘረውን ተቃውሞ ተከራክረዋል፡፡
የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጡ ‹‹ነባሩን ሠራተኛ በማፈናቀል በስመ ዲግሪና ዲፕሎማ ዕውቀት የሌለውን በመዋቅሩ ውስጥ በመሰግሰግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር ያለመ ነው፤›› ስለሚለው ተቃውሞ ኢትዮ – ምኅዳር የጠየቃቸው የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች÷ ‹‹በጥናቱ የሀ/ስብከቱ የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ችግሮች መነሻ ተደርገዋል፤ ዋና ተልዕኮውና መሠረታዊ ተልዕኮውን የሚደግፉ ተግባራት በዝርዝር ተለይተዋል፤ መዋቅሩ ከዚህ አንጻር ያሠራል ወይስ አያሠራም በሚል አመቺነቱና እንከኑ ተገምግሞ በስምምነት የሚወሰን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሰነዱ የሚታየው ተቋማዊ መዋቅር የመጨረሻ መልክ ከመያዙ በፊት ብዙ አማራጮች እየቀረቡ መፈተሹን ያስረዱት ሓላፊዎቹ ለውይይት የቀረበው መዋቅር የቤተ ክርስቲያናችን ዋነኛ ተልዕኮ የኾነው ሐዋርያ አገልግሎትዋ እየሰፋ እንዲሄድ፣ የተሻለ የልማት ዕድል ተፈጥሮ የበለጠ ገቢ በማግኘት ሐዋርያዊ አገልግሎትዋን ለማስፋፋትና ለማጠናከር እንዲቻል የተመቻቸበት በመኾኑ ከፍተኛ የአገልጋይ ቁጥር እንደሚያበቃ የተናገሩት ሓላፊዎቹ÷ ያለውን አገልጋይ በሥልጠና የማብቃት፣ በትምህርት ራሱን እንዲያሳድግ የማበረታታት፣ የመደልደልና የማሸጋሸግ ሥራ ይሠራል እንጂ ትርፍ ነው ተብሎ የሚፈናቀል ሰው አይኖርም ብለዋል፡፡
ሀ/ስብከቱ በጥቅምት ወር መጨረሻ ባካሄደው የሦስት ወራት የጊዜያዊ መዋቅሩ አፈጻጸም ግምገማ በየገዳማቱና አድባራቱ ካለው ከፍተኛ የሰው ኃይል ክምችት አንጻር በተለያየ ምክንያት ከሥራ ተፈናቅለው ካልተመደቡ ሠራተኞች በስተቀር ላልተወሰነ ጊዜ የአዲስ ሠራተኛ ቅጥር እንዲቆም መወሰኑም በሥራ ላይ ያለውን አገልጋይ ሰፊ የሥራ ዕድል በሚፈጥረው በአዲሱ ተቋማዊ መዋቅር አደረጃጀትና የሥራ መደብ ዝርዝር መሠረት በመለስተኛ ሥልጠና ጭምር እያበቁ ለመደልደል ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳለ ሓላፊዎቹ በምላሻቸው ጠቅሰዋል፡፡
የሀ/ስብከቱ ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በአገልግሎት ስፋትና በልማት አቅም እርስ በርስ እየተወዳደሩ ወደ ደረጃ አንድ የሚያድጉበት አምስት ደረጃዎችና ደረጃዎቹ የሚለዩባቸው መመዘኛዎች መዘጋጀታቸው ተገልጧል፤ አምስቱም ደረጃዎች የየራሳቸው መዋቅር፣ በሞያና በቁጥር የተለያየ የሰው ኃይል ምደባና የደመወዝ ስኬል ያላቸው ሲኾን ቤተ ክርስቲያኑ እንደሚገኝበት ደረጃና እንደሚሰጠው የአገልግሎት ስፋት የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ትመና የቤተ ክህነቱን ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጋራ በአቻ ንጽጽር በመመዘን ተገቢው ትኩረትና ደረጃ እንዲሰጠው ተደርጎ መሠራቱም ተመልክቷል፡፡
‹‹የሰው ኃይል ትመናው÷ ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት የሥራን ጥራት ከማሳደግ አንጻር የአገልጋዩ ዝቅተኛ የትምህርት፣ የሥራ ልምድና የክሂሎት ዝግጅት የታየበት ነው፤ የደመወዝ ስኬል ጥናቱ÷ ከቢሮ ሥራ ይልቅ ለካህናቱ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት የካህናቱን ኑሮ ለማሻሻል፣ ሊቃውንቱ ትኩረት አግኝተው ተተኪ ለማፍራት እንዲችሉ በልዩ ኹኔታ የሚበረታቱበት ነው፤›› ይላሉ ለኢትዮ – ምኅዳር አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የባለሞያ ቡድኑ አባል፡፡
ባለሞያው አያይዘውም ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲያገልግሉ ብቻ ሳይሆን በትምህርትና በተግባራዊ ልምምድ ለከፍተኛ ክብርም እንዲበቁ እንደምትሠራ ገልጸዋል፤ ከዚህም አንጻር ልዩ ተሰጥኦና ላቅ ያለ ችሎታ ያላቸው አገልጋዮች ወደ ታችና ወደ ጎን ለተሻለ ዕድል የሚበቁበትና የሚበረታቱበት የደረጃ ዕድገት፣ የዝውውርና ሹመት፣ የክፍያና ምዘና፣ የጤና ክብካቤ ሽፋንና የጡረታ ዋስትና ሥርዐት የሚወሰንበት የአገልጋዮች ማስተዳደርያ ፖሊሲ፣ መመሪያና ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ለየዘርፉ የተጠኑት የሥራ ማኑዋሎች መለስተኛ ክሂል (semi-skilled) ያለው አገልጋይ በቀላል ሥልጠና ሊተገብራቸው የሚችላቸው ናቸው፤›› ያሉት ባለሞያው፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የለውጥ አመራር ዕቅድና በአገልጋዩ አቅም መካከል የሚታዩ ክፍተቶች በየጊዜው እየተለዩ የሚሞሉባቸው የአቅም ግንባታዎች(የሥልጠና) ዐይነቶች ከማስፈጸሚያ መመሪያው ጋራ በሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲው በዝርዝር መቀመጣቸውን አብራርተዋል፡፡
የገዳማትና አድባራት የልማት ፈንድ
በተያያዘ ዜና÷ የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራት ልማትን በማስፋፋት ሐዋርያዊ አገልግሎትን በዘላቂነት ለማከናወን የሚያስችል ሀብትና ንብረት የሚያፈሩበት የልማት ፈንድ ሊያቋቁሙ መኾኑን የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሰበካ ጉባኤ ከሚሰበስቡት አስተዋፅኦ ጋራ በልማት መስኮች ለሚያገኙት ገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ለኢትዮ ምኅዳር ያስታወቁት የሀ/ስብከቱ ምንጮች÷ ገዳማትና አድባራት በአንድ የበጀት ዓመት መጨረሻ ለመደበኛ አገልግሎት ከሚመደበው በጀትና መጠባበቂያው ከሚተርፈው ገንዘብ ስድሳ በመቶውን (60%) የልማት ፈንድ እንዲያቋቁሙበት የሚያስችል ጥናት በሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
እንደምንጮቹ ገለጻ በጥናቱ መሠረት፣ ሀገረ ስብከቱና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ካለው የተጣራ የባንክ ሒሳብ ተቀማጭ ገንዘብና የአጭር ጊዜ ተሰብሳቢ ገንዘብ ውስጥ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት መደበኛ ወጭዎችን ለመሸፈን የሚያስፈልገውን ገንዘብ መጠባበቂያ አድርገው ካስቀመጡ በኋላ ከሚተርፈው ዓመታዊ ቀሪ ገንዘብ ውስጥ ስድሳ በመቶውን የልማት ፈንድ እንዲያቋቁሙበት ታስቧል፡፡
የልማት ፈንዱ÷ የልማት ተቋማትን በማቋቋምና በማስፋፋት የካህናትንና ሊቃውንትን የኑሮ ኹኔታ የማሻሻልና አብያተ ክርስቲያናቱን ከልመና የማውጣት፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ከመደገፍ ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የምግባረ ሠናይ ድርጅቶች በቋሚ የገንዘብ ምንጭነት በማገልገል የምግባረ ሠናይ ተግባራትን በስፋት የማከናወን በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮ የኾነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በከተማና በገጠር የማስፋፋትና የማጠናከር አስፈላጊነት እንዳለው የሀ/ስብከቱ ሌላው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ አካል የኾነው የልማት ሥራዎችና የምግባረ ሠናይ ተግባራት ፖሊሲና መመሪያ ረቂቅ ያስረዳል፡፡
ፖሊሲው ለልማት ተቋማቱ ባስቀመጣቸው መርሖዎች መሠረት÷ በተቋማቱ ምሥረታና ማስፋፋት ወቅት ለቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊ አገልግሎት እንደ ግብዓት የሚያገልግሉ ዕቃዎችን ለማምረትና ለማከፋፈል ቅድሚያ መሰጠት ይገባዋል፡፡ ተቋማቱ የሚያመርቷቸውና የሚያከፋፍሏቸው ንዋያተ ቅድሳት፣ የኅትመት ውጤቶች፣ የምስል ወድምፅ ሥራዎችና የመሳሰሉት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ሥርዐት፣ ከማኅበረሰቡ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ትውፊት አንጻር ታሳቢ መደረጋቸው መፈተሽና መረጋገጥ እንደሚኖርበትም ተመልክቷል፡፡
ፖሊሲው ‹‹የተፈቀዱ›› የሚላቸው የልማት ተቋማት ለብዝኃ ሕይወት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ በዕውቀቱ የበለጸገ፣ በሥነ ምግባሩ የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው በመርሖው አስቀምጧል፡፡ ከተቋማቱ ዝርዝር ውስጥም፡- ኮሌጆችና ማሠልጠኛዎች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅት በማቋቋም የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት መስጠት፣ ክሊኒኮችንና ፋርማሲዎችን በማቋቋም የሕክምና አገልግሎት መስጠትና መድኃኒቶችን ማከፋፈል፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ ለአገልግሎትና ኪራይ የሚውሉ ሕንጻዎችን መገንባትና ማከራየት፣ ከውጭ የሚገቡ ንዋያተ ቅድሳትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማዳንና ሥርዐትና ትውፊት የጠበቁ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ የግብርና ውጤቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ፣ የፋይናንስ ተቋም አክስዮን፣ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድና ቦንድ መግዛት የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ገዳማትና አድባራት በራሳቸው አልያም በመቀናጀት ተቋማቱን መመሥረት እንደሚችሉ በመርሖው የተገለጸ ሲኾን ቅንጅቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አጥቢያዎች ጋራ፣ አጥቢያዎች ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጋራ እንዲሁም ሀ/ስብከቱና አጥቢያዎቹ ከሌሎች አህጉረ ስብከትና አጥቢያዎቻቸው ጋራ ሊከናወን የሚችልበት የፕሮጀክት አጸዳደቅና አተገባበር ሥርዐት መካተቱ ተገልጧል፡፡ የልማት ተቋማቱ የሚተዳደሩት በቦርድ ሲኾን የቦርዱ ተጠሪነትም ላቋቋማቸው አካል (በአጥቢያ ደረጃ ከኾነ ለአጥቢያው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ) እንደኾነ ታውቋል፡፡
በልማት ፈንዱ የሚቋቋሙና የሚስፋፉ ተቋማት፣ ካህናትና ሊቃውንት ከመደበኛ ተግባራቸው በተጨማሪ እንደየዝንባሌያቸው በተለያዩ ክሂሎቶች እየሠለጠኑ እንዲሠማሩ በማስቻል የሥራ ዕድል እንደሚፈጠሩላቸው፣ በአገልግሎታቸውም እንዲበረቱ ተገቢውን በማሟላት አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉላቸው ታምኖባቸዋል፡፡ የልማት ተቋማቱ ወደፊት ሀገረ ስብከቱ ከምእመናን አሰፋፈር አኳያ እንደአስፈላጊነታቸው እያየ ከሚተክላቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋራም አንጻራዊ መስፋፋት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በቁጥር 169 ለሚደርሱት የመዲናዪቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሰራጨው ቅጽ እየሰበሰበው የሚገኘው የአገልጋዮች ጠቅላላ መረጃ÷ ገዳማቱና አድባራቱ ልዩ ልዩ ክህሎት ያላቸው አገልጋዮች እንዳሉባቸው በምንጮቹ መረጃ ተመልክቷል፡፡ ይህም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በየደረጃቸው ከተዘረጋላቸው ተቋማዊ መዋቅርና አደረጃጀት አኳያ የተሠራላቸው የሥራ መደቦች መዘርዝር መንፈሳዊ ዕውቀትን ከዘመናዊው ሞያ ጋራ በአቻ ንጽጽር በማስቀመጥ ከሚያቅፈው በርካታ የሰው ኃይል በተጨማሪ በሒደት አገልጋዮችን በብዛት ለማፍራትና ለማሰማራት ያስችላል የሚል እምነት እንደተጣለበት ተዘግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment