- ‹‹የፓትርያርኩን ሥልጣን ይገድባል›› በሚል ተተችቷል
- ‹‹አመራራቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ነው›› /የሕግ ረቂቁ/
- ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚያስተላልፉት በብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ይኾናል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ፓትርያርኩ የተጣለባቸውን አባታዊ ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችሉ የሚያግዝ እንደራሴ እንደሚመደብ በሚገልጽና የፓትርያርኩን ሓላፊነትና ተጠያቂነት በጉልሕ የሚያሳዩ አንቀጾችን ባካተተ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ ላይ እየተወያየ እንደኾነ ተገለጸ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በ1991 ዓ.ም. ያወጣችውንና ስትገለገልበት የቆየችውን ሕግ ከሌሎች ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋራ በማጣጣም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ከነባራዊ ኹኔታዎች ጋራ በማገናዘብ ያሻሽላል የተባለው የሕግ ረቂቅ ለውይይት የቀረበው ቅዱስ ሲኖዶሱ የትንሣኤ በዓል በዋለ በኻያ አምስተኛው ቀን በሚያካሒደውና ባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ የምልዓተ ጉባኤው ስብሰባው ላይ ነው፡፡
ከምልዓተ ጉባኤው ኻያ ሦስት የመነጋገርያ አጀንዳዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የቀረበውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጎች፣ ደንቦችና ልማዳዊ አሠራሮች ኹሉ ይገዛል የተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁ÷ ርእሰ አበውና ለካህናቷና ለምእመናንዋ ኹሉ መንፈሳዊ አባት በመኾን በማናቸውም ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያኒቱን የመወከል ሥልጣን እንዳላቸው በሕጉ ለተገለጸው ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚሾም በአንቀጽ 24 ላይ ማስፈሩ ተመልክቷል፡፡
ለፓትርያርኩ እንደራሴ የመመደብ አስፈላጊነት፣ ‹‹ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን የተጣለበትን ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችል የሚያግዝ›› መኾኑን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ተገልጧል፡፡ እንደራሴው የሚመደበው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ምርጫ ሲኾን ለምርጫው ሦስት ዕጩዎች በፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጥቆማ ተለይተው እንደሚመረጡ፣ የሚመረጠውም አንድ አባት በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ በእንደራሴነት እንደሚመደብ ተጠቅሷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ቀኖናና ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለአድልዎ የማስተዳደር ሓላፊነት ላለባቸው ለፓትርያርኩ በእንደራሴነት የሚመረጠው ሊቀ ጳጳስ በአባትነት የሚመራው ሀገረ ስብከት ወይም በማእከል የሚገኝ የሥራ ሓላፊነት ያለው ቢኾንም በሕጉ የተመለከተውን መመዘኛ ማሟላት እንደሚገባው ተገልጧል፤ መመዘኛው ከ50 – 60 ዓመት የዕድሜ ገደብ የሚያስቀምጥ ሲኾን የአስተዳደር ችሎታና የመንፈሳዊ አመራር ልምድን፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ ዕውቀት አጣምሮ መያዝን እንደሚጠይቅ ተዘርዝሯል፡፡
‹‹ግለሰባዊ የሥልጣን ፈላጊነት ስሜት የሚገንበት፣ የፓትርያርኩን ሥልጣን የሚጋፋና መካሠስን የሚያበረታታ ነው›› በሚል አንቀጹን የተቃወሙ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ ምደባው አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም እንደራሴው በፓትርያርኩ ጥቆማ ብቻ መመረጥ እንዳለበት የቃሉ ትርጉም እንደሚያስገደድ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
የአህጉረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች በአንጻሩ፥ የእንደራሴው ምደባ፣ ፓትርያርኩ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩትን የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላትና የሥራ ክፍሎች በማቀናጀት በአዲስ መልክ ለማቋቋም በሌሎች አንቀጾች ከቀረቡት የረቂቁ ሐሳቦች ጋራ ተዳምሮ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት በማድረግ ላይ ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር መጠናከር የራሱ አስተዋፅኦ ያለው በመኾኑ እንደሚደግፉት መግለጻቸው ተነግሯል፡፡
ከሥልጣን አኳያም እንደራሴው ቅዱስ ፓትርያርኩን በዕለት ተዕለት ሥራውና በመንፈሳዊ አገልግሎቱ ከማገዝ ውጭ ‹‹ለቅዱስ ፓትርያርኩ ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ የሚጋራው የተለየ ሓላፊነት አይኖረውም፤›› በሚል በረቂቁ የሰፈረውን አንቀጽ በመጥቀስ እንደራሴው ፓትርያርኩን በቅርበት የመደገፍ እንጂ የመጋፋት ሚና እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
ተጠያቂነትን በተመለከተም ፓትርያርኩን ጨምሮ ኹሉንም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፡-
- ቤተ ክርስቲያኒቱን በበላይነት ለሚመራውና ለሚጠብቀው እንዲኹም ቤተ ክርስቲያኒቱን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ላለው ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ በማድረግ፣
- በሕይወት ባሉበት ጊዜ ኹሉ ቋሚ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረትና ሌላም የገንዘብ ማስገኛ ምንጭ እንዳይኖራቸው፣ በስጦታም ኾነ በውርስ የሚያገኙት ሀብት በሞት በሚለዩበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ንብረት እንደሚኾንና በስጦታም ኾነ በውርስ ለሦስተኛ ወገን እንደማይተላለፍ በማረጋገጥ፣
- እያንዳንዳቸው በተሾሙበት ቀን የፈጸሙትን የመሐላ ቃል አፍርሰው ሃይማኖትን ቢያፋልሱ፣ ቀኖና ጥሰው ቤተ ክርስቲያኒቱን ቢያስነቅፉ፣ በአስተዳደር በደልና በአመራር ጉድለት የካህናቱንና የምእመናኑን አመኔታና ተቀባይነት ቢያጡ በማስረጃ ተደግፎ በሚቀርብ ክሥና ቅሬታ የሚጠየቁበት፣ ለመታረም ፈቃደኛ ካልኾኑም ከሓላፊነታቸው የሚገለሉበት ሥርዓት በረቂቁ በመካተቱ፣ በፓትርያርኩ አልያም በወቅታዊ እይታ ላይ ብቻ የታጠረ ረቂቅ እንዳልኾነ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ በዓላት ላይ እንዳስፈላጊነቱ እየተገኘ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጠው እንዲሁም በብዙኃን መገናኛ መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፈው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ እንደሚኾን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ መስፈሩ ተጠቅሷል፡፡
No comments:
Post a Comment