- ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከጨለማው ቡድንና ፖለቲከኞች ጋራ የመከሩበትን የራሳቸው ያልኾነ የተልእኮ ሐሳብና አጀንዳ የተቃወሟቸውን የምልዓተ ጉባኤውን አባላት ‹‹በገንዘብ የተገዛችኹ›› እያሉ በመዝለፍ ቅዱስ ሲኖዶሱን ተዳፍረዋል፡፡
- አቡነ ማትያስ ለአጥኚ ኮሚቴው የላኩት ባለ24 አንቀጽ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች ሳይቀነሱና ውይይት ሳይደረግባቸው በደንቡ ካልተካተቱና ረቂቁ በሌላ ኮሚቴ ዳግመኛ ካልታየ በሚል አጀንዳውን በራሳቸው አቋም ብቻ ለመቋጨት ያደረጉት ሙከራ በፍጹም አንድነት በቆሙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተቃውሞ ውድቅ በመደረጉ በመተዳደርያ ደንቡ ማሻሻያ ላይ የሚደረገው የምልዓተ ጉባኤው ውይይት ይቀጥላል፡፡
- ከድንጋጌዎችና ግዴታዎቹ ውስጥ፡- የማኅበሩ ፈቃድ በየዓመቱ እንዲታደስ፣ ማኅበሩ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዳይሰበሰብና ቢሮ እንዳይከፍት፣ የሠራተኞቹ ቅጥርና ምደባ በመንበረ ፓትርያርኩ እንዲካሔድ፣ አባላቱ በግልም በቡድንም በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥራና በሰንበት ት/ቤቶች ጉዳይ እንዳይገቡ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
- የአጥኚ ኮሚቴው አብላጫ አባላት፣ የፓትርያርኩን የድንጋጌዎችና ግዴታዎች መመሪያ ‹‹ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔና የደንብ ማሻሻያ አቅጣጫ ጋራ የማይሔድ›› በሚል ያልተቀበሉት ሲኾን ማኅበሩ በበኩሉ በተለይ በፈቃድ ዕድሳት ረገድ የተነሣው ሐሳብ ‹‹አገልግሎቱን ለማስቆም የሚደረግ አካሔድ ነው፤›› ብሏል፡፡
- ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የመሥራት አቅሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ፣ በቤተ ክርስቲያናችንም እየሠራ ባለው ሥራ ኹሉ አብያተ ክርስቲያናትን፣ አድባራትንና ገዳማትን በስፋት እየጠቀመ ያለ፣ በምሁራን የታቀፈ ኹለንተናዊ ዝግጅት ያለው ማኅበር ስለኾነና ብዙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ በመኾኑ ራሱን የቻለ ድርጅታዊ መዋቅር ሊዘጋጅለት እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡›› /የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጥኚ ኮሚቴውን ባቋቋመበት የግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ውሳኔው የሰጠው የደንብ ማሻሻያ አቅጣጫ/
- በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሓላፊነታቸው በአርኣያነት የሚጠቀስ ጥረት ባደረጉበት የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ሳቢያ ከፓትርያርኩ ጋራ ውስብስብ ችግር ውስጥ እንደገቡና አብረው ለመሥራት እንደሚቸገሩ በምልዓተ ጉባኤው መካከል ቆመው የተናገሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹አባቶቼ፣ አሰናብቱኝ›› ሲሉ ምልዓተ ጉባኤውን ጠይቀዋል፤ ምልዓተ ጉባኤው እንደሚነጋገርበት ይጠበቃል፡፡
- ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መልቀቂያ ያቀረቡበትን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ለመከፋፈል እየተጠቀሙበት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡
የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ በቅርቡ ባረፉት ብፁዕ አቡነ ቶማስ ቦታ÷ ምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት÷ ተዛውረዋል፤ በምትካቸው የአኵስም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩትና የመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም የበላይ ጠባቂ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሰላማ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት መመደባቸው ተጠቁሟል፡፡
No comments:
Post a Comment