Saturday, 17 May 2014

‹‹መንግሥት በማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይችልም›› /ኢንጅነር ታደለ ብጡል/


(ሎሚ መጽሔት፤ ቅጽ ፫ ቁጥር ፻፮፤ ከግንቦት ፰ – ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
ሎሚ፡- እንደሚታወቀው እርስዎ በቤተ ክህነት አካባቢ ብዙ አስተዋፅኦዎችን አበርክተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በቤተ ክህነቱ አካባቢ ብዙ ተደማጭነት አልዎት ይባላል፡፡ ቤተ ክህነት ስላለችበት ኹኔታና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ተያይዞ ስለሚነሡ ‹‹ወሬዎች›› የሚሉን ነገር ካለ?
lomi ginbot magazineኢ.ር ታደለ፡- ቤተ ክህነታችን ወደድንም ጠላንም ማንም ምን ይበል የኢትዮጵያ አንድነት ምሶሶ ነች፡፡ ከምን አንጻር? ግብረ ገብነትን በመስበክ፣ ትምህርት በማስተማር፣ ሥነ ጽሑፍን በማበርከት፣ የሀገር ኩራት የኾኑትን ቅርሶች በመጠበቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ እግረ መንገዳችንን አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙበት ስፍራ ኹሉ አገር በቀል ዛፎች፣ አበቦችና ንጹሕ አየር መኖሩ ሌላው የቤተ ክርስቲያናችን ትሩፋቶች ናቸው፡፡
ትላልቆቹ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተንጣለለ ቤት እየኖሩ፣ ሚልዮኖች በሚያወጡ መኪናዎች እየሔዱ ቤተ ክርስቲያናችን ግን በልመና መተዳደር አይኖርባትም፡፡ በተለይ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ድኻዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ቅ/ሲኖዶሱ ይህ ኹኔታ የሚለወጥበትን መንገድ ማስተካከል አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለኝ፡፡
መስቀል፣ ጸናጽል፣ መጻሕፍትንና ሌሎችም ቅርሶች እየተሰረቁ ሲሸጡ ተገኝተዋል፡፡ ዋናው ምክንያቱ የንቃተ ኅሊና ውሱንነት፣ የመተዳደርያ ደመወዝ ማነስና ሰብአዊ ደካማነት መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሰፊ መሬት ከምትገነባው ሕንፃና ከምእመናኑ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ላይ በቂ ደመወዝ ልትሰጣቸው ይገባል፡፡
በየክፍለ ሀገሩ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የመቀደሻ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ስለሌላቸው፣ ክብካቤ በማጣታቸው ካህናቱ በመንገድ ዳር ጨርቅ አንጥፈውና ዣንጥላ ዘርግተው መለመናቸው እንዲቀር ቅ/ሲኖዶሱ አትኩሮት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ችግር መቅረፍ ያለበት የቤተ ክህነታችን አመራር አካል ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ቀድሞም ከመተቸት አልተቆጠብኹም ነበር፡፡ አኹን ከብዙኃን መገናኛ እንደሰማኹት አዲሱ ፓትርያርካችን ይህን የመሰለ ጉድለት መኖሩንና መስተካከል ይገባዋል ማለታቸውን ሰምቻለኹ፡፡ እኔ አሜሪካን አገር ቆይቼ ስለመጣኹ ከአዲሱ ፓትርያርካችን ጋራ ገና የመተወዋወቅ ዕድል አላገኘኹም፡፡ በቅርቡ ግን ቀጠሮ ወስጄ ላነጋግራቸው እፈልጋለኹ፡፡ ያለኝን ቅሬታ ምንም ሳልደብቅ የመንገር ሐሳብ አለኝ፤ የሚሉትን ሰምቼ እነግርሃለኹ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የጥላቻ ዘመቻ እየተካሔደ ነው፡፡ እንደምታውቀው የሌሎች ሃይማኖቶች በየቦታው ሕንፃ እየገነቡና እየገዙ ሰውን ይሰብካሉ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ወጣቶች ደግሞ ዝም ብለው ከጧት እስከ ማታ በመለፍለፍ ሳይኾን የራሳቸውን ገንዘብ ከደወመዛቸው በማዋጣት ቤተ ክርስቲያን ከልመና የምትድንበትን መንገድ ተከትለዋል፡፡ ሥነ ሥርዓት ባለው መንገድ ምእመናኑ ሳይደክሙና ሳይሰለቹ ጸሎት እንዲካሔድ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ለሃይማኖታቸው ካላቸው ቀና ሐሳብ በመነሣት ቤተ ክርስቲያናችን እየጠነከረች እንድትሔድ ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ማድረግ የተሳናቸው ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳንን ለማዳከም ይሞክራሉ፡፡ መልካም ተግባሩን ለማጣጣል የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚነዛው ወሬ የጥላቻ ወሬ ነው፡፡ ጥላቻ ደግሞ የትም አያደርስም፡፡ ማንም ሲለፈልፍ ቢውል የትም አይደርስም፡፡
የራሳቸውን እምነት ከማራመድ ውጭ አንድም የማኅበረ ቅዱሳን አባል ከሌላ የማኅበረ ቅዱሳን አባል ጋራ ተጣላ የሚል መረጃ የለም፡፡ እነኚኽ ልጆች ለምን ራሳቸውን ችለው ቆሙ ከሚል ቅናት በስተቀር አንድም ሌላ ጥፋት አልፈጸሙም፡፡
ሰሞኑን እንደሰማኹት በቅርቡ ስብሰባቸውን አግደዋቸዋል፡፡ ይኼ ነውር ነው! በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አትሰበሰቡም ማለት አይችልም፡፡ ይኼ ስሕተት ነው፤ ምክንያቱም ይህ ድርጊት በሃይማኖት ጣልቃ መግባት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ስብሰባ ማካሔድ የዜጎች መብት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ርግጥ ለመሰብሰብ ፈቃድ በሚያስፈልግበት ቦታና ጊዜ ፈቃድ መጠየቅ ይጠበቃል፤ ግን ምንም ችግር የማይፈጥር ስብሰባ እንዳይካሔድ መደረጉ አግባብነት የለውም፡፡
ምናልባት ይህን ድርጊት የፈጸሙት ማኅበረ ቅዱሳንን ለማውገዝና ለማስጠላት የሚሞክሩቱ ሳይኾኑ አይቀሩምና እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው የሚል መልእክቴን አስተላልፍልኝ፡፡
About these ads

No comments:

Post a Comment