Wednesday, 14 May 2014

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ተካሔደ


Holy Synod opening prayerዛሬ፣ ረቡዕ ግንቦት ፮ ቀን የሚጀመረው የ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት በትላትናው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተካሒዷል፡፡
በትላንትናው ዕለት ከቀኑ ፲ ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው በዚኹ የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት የተሰበሰቡ ከሠላሳ በላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል፤ በሥርዓተ ጸሎቱ መክፈቻና መዝጊያ የቤተ ክርስቲያኑ የደወል ድምፅ ለደቂቃዎች ተሰምቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ‹‹ሑሩ ወመሀሩ›› በሚል ርእስ በጽሑፍ የተዘጋጀ ትምህርት የሰጡት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ናቸው፡፡
His Grace Abune Garima‹‹ኹላችንንም ከየአህጉረ ስብከታችን ሰብስቦ ስሙን በመቀደስ፣ ቃሉን በመስማት ዓመታዊ ስብሰባችንን በጸሎት ለመጀመር ላበቃን አምላካችን እግዚአብሔር ‹ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐነ እስከ ዛቲ ሰዓት› ብለን እናመሰግነዋለን›› በማለት ትምህርታዊ ጽሑፋቸውን የጀመሩት ብፁዕነታቸው÷ በቅዱስ ሲኖዶሱ እየተጠናና እየተመከረበት የሚወጣው ሕግና ደንብ ለእምነታችን ህልውና፣ ለኅብረተሰባችን ማኅበራዊ አገልግሎት ዋስትና የሚሰጥ ስለኾነ ለሕጉ ተገዥዎች መኾን እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስን ምንነትና አጀማመር፣ ቤተ ክርስቲያንን በመምራትና በመጠበቅ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ ስላሳለፋቸው ውሳኔዎችና የሥልጣን ልዕልናው እንዲሁም ከወቅቱና ከመጪ ኹኔታዎች አንጻር የሚጠበቅበትን አባታዊ ሓላፊነትና ውሳኔዎቹን በማስፈጸም ረገድ ካህናትና ምእመናን ያላቸውን ድርሻ ብፁዕነታቸው በትምህርታዊ ጽሑፋቸው በስፋት አብራርተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት በፓትርያርክ ሰብሳቢነት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለመወሰን የሚደረግ የሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ መኾኑን ብፁዕነታቸው ገልጸው፣ ከጥንት ጀምሮ ጸንቶ የመጣውን የአበው ሐዋርያት፣ የአበው ሊቃውንት ትምህርተ ሃይማኖት ያለምንም ለውጥ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሓላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያን የሥልጣነ ክህነት ባለሥልጣን መኾኑንና ውሳኔውም የመጨረሻና ይግባኝ እንደሌለው ብፁዕነታቸው አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ50 ሚልዮን በላይ ተከታይ ምእመናን፣ ከ500‚000 በላይ ካህናት፣ መዘምራንና ዲያቆናት፣ ከ60‚000 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያንና ከ1000 በላይ ገዳማት እንዳሏት የጠቀሱት ብፁዕነታቸው÷ ሃይማኖትና ምግባር እንዲጸና፣ አገር እንዲቀና፣ የተቸገረ ወገን እንዲረዳ ቅዱስ ሲኖዶሱ በየጊዜው እየተሰበሰበ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች በሥራ ለመተርጎም የኹሉንም ጥረት እንደሚጠይቅና ለዚኽም ክህነታዊ አገልግሎቱ ወቅቱን የዋጀ እንዲኾንና የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በግንባር ቀደምነት አባታዊ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment