Friday, 2 May 2014

ሰበር ዜና – ማኅበረ ቅዱሳን በጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አያያዝና አጠባበቅ ላይ ለዛሬ የጠራውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የተፈቀደው ጥናታዊ ጉባኤ በፓትርያርኩ ውሳኔ ተከለከለ


mahibere kidusan
  • ዛሬ ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 – 11፡00 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም አዲሱ አዳራሽ ‹‹ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ዓይነትና የይዘት ትንተና እንዲሁም አያያያዝና አጠባበቅ›› በሚል ርእስ የተጠራው የጥናት ጉባኤ ክልከላ መንሥኤ ‹‹የሥልጣን ተዋረድንና የዕዝ ሰንሰለትን ባልተከተለ መልኩ በቀጥታ የአድባራትንና የገዳማትን አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ስብሰባ መጥራት›› የሚል ነው፡፡
  • ለጥናታዊ ጉባኤው የተጠሩት የገዳማትና አድባራት አለቆች ቤተ መዘክር ያላቸው ሦስት አብያተ ክርስቲያን ብቻ መኾናቸውን የገለጹት የጉባኤው አስተባባሪዎች በበኩላቸው÷ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች፣ ምሁራንና እንግዶች ጥሪ ያደረገው ዕቅዱና አስፈላጊነቱ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቀርቦ ከተመከረበትና ከተፈቀደ በኋላ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
  • ፓትርያርኩ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተጠሪ የኾነበትን አሠራር በመሻር ማንኛውንም ስብሰባዎቹንና ጉባኤዎቹን ኹሉ ያለልዩ ጽ/ቤታቸው ፈቃድ እንዳያካሒድ ከሕጉ ውጭ በቀጥታ ለማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት በላኩት የልዩ ጽ/ቤታቸው ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
  • የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የጥናታዊ ጉባኤውን መከልከል በተመለከተ በቀጥታ ለማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት ደብዳቤ ለመጻፍ የተገደደው፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ስለጉባኤው እንደሚያውቁና ዝግጅቱም የአሠራር ክፍተት እንደሌለበት ለልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊ በማሳወቅ ሊታገድ እንደማይገባው በመከራከራቸው ነው፡፡
  • ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የዋናውን መሥሪያ ቤት ማለትም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መምሪያዎችና ድርጅቶች ጨምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚገኙትን የሥራ ዘርፎች ኹሉ በበላይነት የማስተዳደር ሥልጣንና ተግባር የሚሰጠው ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ነው፡፡ በዚኽ ረገድ የፓትርያርኩ ሓላፊነት በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማቸው የማስተላለፍ፣ በተግባር ላይ መዋላቸውንም መከታተልና መቆጣጠር ነው፤ ፓትርያርኩ የሚፈጽሟቸው ተግባራት ካሉም ዓበይትና የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ ያረፈባቸው መኾን እንደሚገባቸው ተደንግጓል፡፡
  • በፓትርያርኩና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሥራ አለመግባባቶች እየተባባሱ የመጡ ሲኾን መንሥኤውም÷ በአማሳኞችና ጎሰኞች የሚመከሩት ፓትርያርኩ የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ጨምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የሥራ ዘርፎች በቀጥታ የመምራትና የማስተዳደር ሓላፊነት ያለባቸውን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በመጋፋት የጀመሩት አካሔድ ነው፡፡
  • ፓትርያርኩ የሚመለከታቸውንና የማይመለከታቸውን ዐውቀውና ለይተው በብቃት የመምራት አቅም ያጡትን ያኽል በዙሪያቸው የከተሙ አማሳኞችንና ጎጠኞችን መሸጋገርያ ያደረገውን ውጫዊ ተጽዕኖ በቀጥታ ተቀብሎ ለማስፈጸም የሚታይባቸው ፍጥነትና ታዛዥነት በእጅጉ እንዲናቁና እንዲጠሉ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
*                           *                              *
  • ጥናታዊ ጉባኤው÷ ማኅበረ ቅዱሳን በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማት፣ ዕድገት፣ ታሪክ፣ ቅርስና መሰል አርእስተ ጉዳዮች ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይም ወጣት ምሁራንን ለማበረታታትና በተቻለው ኹሉ ለመርዳት፤ ሃይማኖታቸውን የሚጠብቁ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚከባከቡና ሀገራቸውን የሚወዱ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በተጣለበት ሓላፊነት መሠረት ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ተያያዥነት ባላቸው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ለማከናወን ባቋቋመው የጥናትና ምርምር ማእከል በየኹለት ወሩ የሚካሔድ መደበኛ መርሐ ግብር ነው፡፡
  • የማኅበሩ የጥናትና ምርምር ማዕከል በየኹለት ወሩ የሚያካሒደው መደበኛ ጥናታዊ መድረክ አካል የኾነውና የሚመለከተው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ዝርዝር ይዘቱን ከአንድ ወር በፊት በጋራ ውይይት ጭምር እንዲያውቀው ተደርጎ የተጠራው ጥናታዊ ጉባኤ፣ በጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ዓይነትና የይዘት ትንተና እንዲኹም ጥበቃ ላይ ያተኮረ መኾኑ የመርሐ ግብሩ መግለጫ ያመለክታል፡፡ms1971
  • ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ ‹‹ዜና መጻሕፍተ ብራና›› በተሰኘውና በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በተካሔደው ሦስተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጥናት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ጽሑፋቸው እንደገለጹት÷ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍታችን ገበታቸው የወርቅ የኾነ፣ የብርዓቸው አጣጣልና የብራናቸው ንጽሕና፣ የቅርፃቸው ማማርና ውበት ሲመለከቱት በእውነት የእነርሱን መልክና ቅርፅ የኑሮ ቤት አድርጎ መኖር እንጂ በዚኽ ዓለም በሥጋዊ ኑሮ ታስሮ መኖርን አያስመኙም፡፡
  • ከቅዱሳን ገድላትና ድርሳት ባሻገር አያሌ ‹የቴዎሎጊያ እና ፊሎሶፊያ› ሀብት ያካበቱት ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት በይዘታቸው ‹‹እግረ ኅሊና ያልደረሰበት፣ የአእምሮ ክንፍ ያልበረረበት የተሸሸገ ጥበብና ያልተሞከረ ስውር ፍልስፍና›› የተካበተባቸው ናቸው ያሉት ሊቁ÷ ያልተከፈተውን የዕውቀት ጎዳና፣ ዓይን ያላየውን ዦሮ ያልሰማውን በጥበበኞች ያልታሰበውን ብልሃትና ሥነ ጥበብ መፈለግና መሻት ፈልጎም ማግኘትና አግኝቶም በፍሬውና በመልኩ መጠቀም ከአኹኑ ትውልድ የሚጠበቅ አዲስ አለኝታ፣ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ የምሥራች መኾኑን አመልክተዋል፡፡Ge'ez 1
  • የተማረው ትውልድ የጠፋባትን የወርቅ ቀለበት ለማግኘት ባጡ፣ ቆጡ፣ ማዘንቱ፣ ማቶቱ ሳይቀር ኹሉንም በጥንቃቄ እያገላበጠች የምትፈልገውን ልባም ሴት መምሰል እንዳለበት ሊቁ በጽሑፋቸው መክረዋል፡፡ የበሬ ቆዳው በገዛ ሞራው እንዲለፋና እንዲለሰልስ የሀገራችን መልክና ቅርፅ በገዛ ሥነ ጽሑፋችንና ቅርፃችን ማሣመር እንድንችልና በዝግ ቤት ከየቤተ መቅደሱ ምህዋርና ከዋሻ ውስጥ ወይም ከመንደርና ደንበኛ ካልኾነ ዕቃ ቤት ተደብቆ ትውውቁ ከሌሊት ወፍና ከአይጥ መንጋ ጋራ የኾነውን የአባቶቻችንን ሥነ ጽሑፍ እያሠሥንና እየመረመርን ለተከታዩ ትውልድ እንድናቆይም በጥናታቸው አደራ ብለው ነበር፡፡
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች የበጀት እጥረትንና የሰው ኃይል ውሱንነትን በመጥቀስ ተግባራቸውን ማከናወንና የታሰበውን ለውጥና ውጤት ማምጣት እንደተሳናቸው ሰሞኑን በአስተዳደር ጉባኤው ላይ ቀርቦ ከተገመገመው የስድስት ወር ዕቅድ ክንውን ሪፖርታቸው በተረዳንበት ኹኔታ ያልነበሩና የሌሉ ለመኾን የተቃረቡትን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍታችን ላይ ያተኮረው ጥናታዊ ጉባኤ የተከለከለበት ዋነኛ ምክንያት ታድያ፣ በልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ እንደተመለከተው ዝግጅቱን ካለማወቅ አልያም የዝግጅት ሒደቱ የሥልጣን ተዋረድንና የዕዝ ሰንሰለት አልተከተለም ከሚለው የተለመደ የማሰናከያ ስልት ጋራ በርግጥም የተያያዘ እንዳልኾነ ግልጽ ነው፡፡
  • የልዩ ጽ/ቤቱ የክልከላ ውሳኔ ከታወቀበት ከትላንት ቀትር ጀምሮ ደብዳቤውን እያሰራጩ የሚገኙት በፓትርያርኩ ዙሪያ በአማካሪነትና ረዳትነት ስም ከተጠጉት እነንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ የዓላማና የጥቅም ግንኙነት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት አማሳኞቹ እነኃይሌ ኣብርሃ መኾናቸው ሲታይ የክልከላ ውሳኔው ምንጭ፣ የአብነት መምህራን ሀገር አቀፍ ጉባኤ ከታገደበት የካቲት ወር ጀምሮ የተጠናከረውና ማኅበሩን ብሎም ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም ልዩ ተልእኮ ባላቸው ባለሥልጣናት ጭምር ተደግፎ የቀጠለው ጫና ስለመኾኑ ግልጽ ያደርገዋል፡፡
  • የማኅበሩ አመራር ስለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የክልከላ ደብዳቤ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ መምከሩ የተገለጸ ሲኾን በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት የጽሑፍ ምላሽ እንደሚሰጥ ተመልክቷል፤ የጎሰኝነት ሰለባ በመኾንና ለአማሳኞች ሽፋን በመስጠት በበታች ሠራተኞች ዘንድ ሳይቀር ክፉኛ እየተናቁና እየተጠሉ በመጡት ፓትርያርክ ዙሪያ የተኮለኮሉትን ጥቅመኞች የማጋለጥ እንቅስቃሴም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እየተገለጸ ይገኛል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ዓመታዊ ስብሰባው የማኅበሩን ተጠሪነት ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር አውጥቶ በጊዜያዊነት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያደረገበት ውሳኔ፤Holy Synod 2004 Ginbot annual meeting decision on Mahibere Kidusan
የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ በመተላለፍ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የፈቀዱትን የማኅበሩን ጥናታዊ ጉባኤ የከለከሉበትና ለወደፊቱም ማኅበሩ የልዩ ጽ/ቤቱን ፈቃድ ሳያገኝ ስብሰባ ማካሔድ እንደማይችል ያሳሰቡበት ደብዳቤ፤pat ban

1 comment:


  1. Werena hamet astelegn...lemin memenanun tebetebitalachu merja kale sinodos lay akirbe endiwegez madereg newu . kalebeleza sibket teresto siele kidusan sile emebetachin ,..........tetachu yesewu hamet lay yetesemarchu sewoch Egizeabheren feru. Ene eterateralehu enate rasachu tadiso protestant satihono atkerum ...Betekiristiyan higia siriat eyalat higina siriat endelelat yemitadergu tada enate yetewahido lijoch nachu . betu balabet alewuna zim belu ! ላይ ቤተ ክርስቲያን የማናት?

    ReplyDelete