Friday, 2 May 2014

የማኅበራችን አገልግሎት የክርስቲያናዊ ግዴታችን አካል ነው

አትም ኢሜይል
 ሚያዚያ 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ክርስቲያኖች የተጠሩት በክርስቶስ እንዲያምኑ በስሙም እንዲጠመቁ ብቻ አይደለም፤ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የፍቅርና የርኅራኄ ሥራ ለሰዎች ሁሉ እንዲሠሩም ነው፡፡ “ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” /ፊል 1÷29/ ያለው የሐዋርያው ቃሉ ይሄንን ያመለክተናል፡፡ ይኸውም የመንፈስ ፍሬዎችን ይዘን እንድንገኝ የታዘዝንበት ነው፡፡ /ገላ 5÷22/

በዚያም ላይ ተመሥርተን ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለነፍሳችን ድኅነት መልካሙን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ሰዎች ቢራቡ ማብላት፣ ቢጠሙ ማጠጣት፣ ቢታረዙ ማልበስ፣ ቢታሰሩ መጠየቅ … ወዘተ ሁሉ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑ የፍቅርና የቸርነት ሥራዎች ናቸው፡፡ ይሄንን ለማድረግም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኖ መጠመቅ ብቻ በቂ ነው፡፡ የተጠመቅነውም ይሄንን የፍቅርና የቸርነት ሥራ ሠርተን በእግዚአብሔር ፊት እንድንከብር ነውና፡፡

በዚህም ምክንያት የማኅበራችን የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ላለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ ለሆኑት ጊዜያተ ይሄንን እምነት በመያዝ በየገዳማቱ ላሉ አባቶች፣ በየአብነት ትምህርት ቤቶቹ ላሉ ሊቃውንት በተቸገሩት ነገር ሁሉ በመድረስ ክርስቲያናዊ ምግባረ ሠናይ ተግባራትን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ አባላቱ በሙያቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ሁለንተናዊ ተግባራትን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚፈጸመው ግን የአምልኮ አካል ሆኖ እንጂ በዓለማዊ፣ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች እንደሚፈጸም ከምድራዊ ሥልጣንና ከዕለት ጉርስ አንጻር የሚታይ አገልግሎት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በእንዲህ ዓይነት መንገድ የሚፈጸሙ መንፈሳዊ ተግባራትን ምንነትን ሲያመለክት እንዲህ ማለቱ አይረሳም “ንጹሕ የሆነ፤ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።” /ያዕ. 1÷27/

ከልዩ ልዩ ማኀበራዊ አገልግሎቶች በመለስ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ለመናፍቃን ጥያቄዎች ሊቃውንቱን ምንጭ አድርጎ መልስ በመስጠት ፍጹም መንፈሳዊ ተግበራትን ሲፈጽምም ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ የሚሠራባቸው መንገዶችም ጊዜውን የዋጁ ሆነው በሰፊ መዋቅር ይከናወኑ እንጂ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በቅዱሳን ስም በተሰባሰቡ የሰንበቴና የጽዋ ማኅበራትም እንደየዘመኑ ሁኔታ ሲፈጸም የቆየ ነው፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በአቅራቢያቸው ባሉ አጥቢያዎች ተሰባስበው በቃለ እግዚአብሔር በመማር በሰብእናቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አድገው ከሥነ ምግባራዊ ችግሮች ተጠብቀው ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ እንዲሆኑ ያተጋል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም ተመርቀው በሙያቸው በልዩ ልዩ የሥራ ሓላፊነቶች ላይ ሲቀመጡ ቤተክርስቲያንን በሙያቸው በየአጥቢያው እንዲያገለግሉ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሓላፊነቶች ግን ከክርስቲያናዊ ግዴታ የሚመነጩ እንጂ ከተራ ሥጋዊ ምኞትና ዓለማዊ ሐሳብ የመነጩ አይደሉም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉም የቤተክርስቲያን አካላትና ምእመናን ቢሆንም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ የፍቅርና የቸርነት ሥራን በመሥራት ሕያዊት የሆነችው ነፍስ የምትድንበትን ሥራ በጋራም በተናጠልም እንዲያከናውኑ የሚሻ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ያሉ የመንፈሳዊ ማኅበራት ተግባራት ሁሉ ከዚህ አንጻር ሊታይ ይገባል፡፡ እነዚህ ተግባራት በጎ ተግባራት ናቸው፡፡ ለነፍሳችን መዳን ወሳኝ ናቸው፡፡ በጎ መሆናቸውን ካወቅን ደግሞ ሌሎች አካላት ተደሰቱም አልተደሰቱም ሳንፈጽም የምንተወው ነገር አይደለም፡፡ “እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነውና።” /ያዕ 4÷17/፡፡

ስለዚህ ማንኛውም ወገን እውነታዎችን ፈሪሃ እግዚአብሔር በተሞላበት መነጽር እንዲመለከት እየጠየቅን፤ የማኅበሩ አገልግሎት በመክሊቱ አትርፎ ከመገኘት የመነጨ ዓለማዊ ያልሆነ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መሆኑን በውል ማጤን ይገባዋል፡፡ አገልግሎቱን ቤተ ክርስቲያን ባለችበት በመላው ዓለም እንዲሠራ ፈቃድ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስና አባቶች በጸሎትና ምክር ማገዛቸው እንዳለ ሆኖ ወደፊትም አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሊያደርጉ የሚችሉ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል፡፡

የማኀበሩ አባላትም የምንሠራው በስሙ ተጠምቀን አምነን የተከተልነው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ መነሻ አድርገን መሆኑን ሁልጊዜም በማሰብ በሚመጡ ፈታኝ ነገሮች ሁሉ ሳንፈራ ሳንደነግጥ በአገልግሎታችን ልንጸና ይገባል፡፡ “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብለን የገባንላትን ቃል ጠብቀን ለእኛና ለመላው ሕዝብ ነፍስ መዳን የምናደርገውን ትጋት እናጠናከር እንላለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment