Saturday, 31 May 2014

የቤተ ክህነቱ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ ፡ Cynical Intellectual Atmosphere

                                                              
                                                              በታደሰ ወርቁ ተጻፈ
  • ዛሬ ሊቃውንቱ የቤተክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና ቤተክርስቲያን አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች፡፡

(አንድ አድርገን ግንቦት 23 2006 ዓ.ም)፡- በዚህ ዐውድ(Context)ምሁር የምለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሊቅነታቸውን ያስመሰከሩ ፤ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጥናትና ምርምር አድርገው የጥናት ወረቀቶቻቸውን ያበረከቱ ፤ መጻሕፍትን ያሳተሙትን ጭምር ነው፡፡ በጥቅሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በአዕምሮ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ነው፡፡

በዚህ መልኩ ያስቀመጥናቸው ሊቃውንት ቁጥር በአንጻራዊነት እያደገ ቢሄድም በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመኑ ውስጥ ቀድሞ የነበራቸው ቦታና የኑሮ ደረጃ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹም ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያኒቱ  አገልግሎታቸውን እየሰጡ ቢሆኑም  በአሁን ጊዜ በቤተ ክርስቲኒቱ ውስጥ እንደሚታየው የቀድሞውን የመንፈስ ልዕልና እና ሐሳባዊ መሪነት አጥተዋል፡፡ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ከማድረግ በተረፈ ምሁር የሚያሰኛቸውን ተግባር የሚፈጽ አሉ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡

በተለያዩ አዝማናት የቀሰሙትን በጎ እውቀት ከምእመኑ ሕይወትና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ግንኙነት ያለው ፤ የምእመኑንና የቤተ ክርስቲያኒቱን የአግልግሎት ሕይወት ለመቀየር የሚውል መሆኑ ቀርቶ ዝም ብሎ የኑሮ መደጎሚያ ብቻ አድርጎ መውሰድ በእጅጉ ይታይባቸዋል፡፡ይህ ደግሞ እውቀትን ለእውነትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረት እምነት ፤ ቀኖናና ትውፊት ወገንተኛ መሆን ቀርቶ የበለጠ ዋጋ ለከፈለ የጥፋት ኃይል ሁሉ በሚፈለገው ዓይነት ተለክቶና ከሐሰት ጋር ተለውሶ የሚሸጥ ሸቀጥ አድርታል፡፡


ሊቃውንቱ ‹‹እኔ ንጹሕ ነኝ ፤ ምንም አልሆንም ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሙያተኛ ነኝ ፤ ሥራዬን እየሠራ ነው” በሚል ራሳዊ አቋም መንጋውን የተኩላ ሲሳይ አድርገውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የ‹‹አጉራ ዘለሎችና ጆቢራዎች›› መፈልጫ እንድትሆን ፈቅደዋል የሚሉ ወቀሳዎችም ይቀርቡባቸዋል፡፡ ወቀሳውም የደረት ንግግር አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሁኔታውን ክፉና ጨለማ የሚያደርገው ምሁራኑ አሁን ያሉበት ደካማ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማሻሻል ያላቸው ወኔ እና የሌሎች እህት አብያተ-ክርስቲያናት ምሁራን አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድባቸው ጊዜ ስናሰላ ነው፡፡

በቤተክርስቲያኒቱ ትምህርተ መሠረት የሊቃውንት ድርሻ ‹‹የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው›› መሆንም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ታላቅነት በድርሻቸው ሲታደሉት በደካማነታቸውና በሓላፊነት ሽሽታቸው ብርሃንነታቸውን ወደ ጨለማ ፤ ጨውነታቸውን ወደ አልጫነት በመለወጣቸው ኃላፊነታቸውንና ብርኩናቸውን አውጥነው የጣሉ ይመስላሉ፡፡

በእርግጥ ብዙዎች የምሁርነታቸውን ሚና በሚገባ መደላደል(Stabilization) እንዳልተጫወቱ አሳምረው ያውቁታል፡፡ዕውቀታቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔ ሰጪ አካል ለመምከር አለመቻሉንም ሁሉም ይረዱታል፡፡ ውሳኔ ሰጪዎቹም የ‹‹ሊቃውንት ምክር›› ብለው ሲጠይቁ የሚያገኙት እውነቱን ሳይሆን ሊቃውቱ ውሳኔ ሰጪውን አካል ያስደስተዋል ብለው የሚያስቡትን ‹‹እውነት›› ብቻ እንደሆነም ይገነዘባሉ፡፡
አሁን ባለው የቤተ-ክህነቱ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝነው የእነኚህ ኃይሎች(የውሳኔ ሰጪው እና የምሁራን) በተናጠል መዳከም ብቻ ሳይሆን ይህንን ድክመት በመገንዘብ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲባል በጋራ ለመሥራት አለመቻላቸውና የመሥራም ፍላጎት ፍንጭ አለመታየቱ ነው፡፡

የሁለቱም ኃይሎች እርስ በእርስ የጎሪጥ መተያየት ፤ ቅንነት በተሞላውና ገንቢ በሆነ መልኩ መተቻቸት አለመቻል ወይም ለመደጋገፍ አለመመሞከር ተቋሟን ‹‹የነጋ አድርሶች›› ስብስብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ሕግ የሚጣስላቸውና ሕግ የሚጣስባቸው ሰዎች ጥርቅምም እንድትሆን አብቅቷታል፡፡

ይልቁንም በጽንፈኛነት የአንዱን ድክመት ማጉላትና ይህን የጽንፈኛነትን አቋም በየጎራው በማስተጋባት ‹‹እኔ የበለጠ አሳቢ ፤ ከእኔ የተለየው ሁሉ ግን የቤተክርስቲያ አጥፊ ነው›› ብሎ በመኩራራት እና በዚህም እንጀራ ለመጋገር መሞከር በእጅጉ የሚዘወተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቢያንስ በግል ደረጃ የግብዝነትና የአድርባይነት (Opportunist) መገለጫ ፤ ሲያልፍ ደግሞ ቤተ ክርስቲያቱን ሊጎዳ የሚችል እኩይ ድርጊት ነው፡፡  

ይህ ሁሉ የእውቀትና የሞራል ተገናኝ ቀጠናዎች(Inter-Zone) የሚያመጡትን የሥነ ልቡና ቀውስ ለመከላከል በሚመስል ሁኔታ በቤተ-ክህነቱ ሊቃውንተ ዙሪያ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ(Cynical Intellectual Atmosphere) የተንሰራፋ ይመስላል፡፡ 

ነገሮችን በዕውቀትና በሃይማኖት ከመጋፈጥ ይልቅ ፍጹም ሥር በሰደደ ወሬና ሐሜት ማለፍ ፤ አጥፊ የቤተ-ክህነቱን ሹማምንት እነርሱ ሳያውቁ በየመሸታ ቤቱ ወይም አንድ አይነት ሀሳብ በሚያስቡ ቡድኖች  መካከል ማማት ፤ የሚደረጉ ጥረቶች መጨረሻ መጥፎ ይሆናሉ ብሎ ማመን ፤ ለለውጥ ሳይጥሩ ሌላው የሚያደርገውን የለውጥ ጥረት ማጣጣል ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ክፉና ጎጂ ክስተት እንዳይመጣ ‹‹ አኔ ምን ማድረግ አለብን?›› ብሎ በመጠየቅ በምሁርነት ማድረግ የሚገባቸውን ከማድረግ ይልቅ ክፉ ነገር ሲመጣ ‹‹አላልኳችሁም›› ብሎ በጨለምተኛ ምሁርነት መመጻደቅ የቤተ-ክህነቱ ምሁራዊ ድባብ የሆነ ይመስላል፡፡በቤተ ክርስያኒቱ ደረጃ ውድቀት ሊያመጡ የሚችሉ መሠረታዊ ችግሮችን እያዩና እየተገነዘቡ  ለምእመኑ እይታና ውይይት ማቅረብ ምሁራዊ ግዴታ ከመሆኑ በላይ የኦርቶዶክሳዊነት ግዴታ ሳይሆን እንደ የዋህነትና አላዋቂነት የሚቆጠሩበት ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ ያለበት ቤተክህነት ባለፉት በ22 ዓመታት ውስጥ ያፈራን ይመስላል፡፡

ከዚህ ቢብስም በምዕመኑ ፊት ትክክለኛ የሆነውንና የሚመስለን ነገር መናገር በተለይም ይህን ነገር መንግሥትን የሚጎነትል ከሆነ አንድም የተናገርነው ጀብደኝነት አሊያም ‹‹ ሰውየው የመንግሥት ሰላይ ሳይሆን አይቀርም›› ተብሎ የሚያስጠረጥር ደረጃ ላይም እየተደረሰ ነው፡፡

እንዲህ አይነቱን ምሁራዊ ጨለምተኝነት ለተጣለባቸው ፍርሃትና ስንፍና መደበቂያ የሚያደርጉት ብዙዎች ናቸው፡፡በዚህ ምክንያት እውነተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቅነት ስሜት ጠፍቶ ምሁርነቱ ርካሽና የማይከበር እየሆነ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል የምሁርነቱ ደረጃ እየወረደ ፤ በሌላ በኩል የቆራጦቹ ቤትና የነጻዎቹ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን እየተዋረደች ትገኛለች፡፡ እነዚህ ምሁራን ‹‹ሆዷን ለቆረጣት የራስ ሕመም መድኃኒት የማዘዝ›› ያህል እየታየባቸው ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተደራርቦ የፈጠረው ‹‹የምሁራዊ ቅሌት›› ስሜት ሊቃውንቶቻችን በቤተ-ክህነቱ ውስጥ በጉልህ የሚታዩትን መሠረታዊ ችግሮች(የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ፤ የቤተሰብ አስተዳደር እጦት ፤ ሙስናና ጎጠኝነት) የሚያሳዩ መስታወቶች ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት ፤ ሥርዓተ አምልኮ ሐዋርያዊ ትውፊትና አስተዳደራዊ ድርጁነት ቀጣይነት የሚጠቁሙ ዘመን ተሻጋሪ ኃይል መሆናቸው ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡

እንደ ማኛው ተራ ምዕመን በቤተ-ክህነቱ ‹‹ገዥ መደቦች›› አድርጉ የተባሉትን ሁሉ በተንበርካኪነት (submissive) የሚያደርጉ ፤ ባሳለፍነው ዘመነ ፕትርክና እንደታየው የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት በቤተ-ክህነቱ ‹‹ገዥ መደብ›› ጎን የመቀመጥ ክብር መቀዳጀትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ ለራሳቸውና ለሊቅነታቸው ብዙ ክብር የሌላቸው ፤ አቅመ ቢስ የቀንድ አውጣ ኑሮ ነዋሪዎች ናቸው የሚለው የብዙዎች አስተያየት እየሆነ ይገኛል፡፡

ሊቃውንቶቻችን የቤተ-ክህነቱ ፖለቲካ ሳበዳቸው ‹ገዥዎች› ጋር ሲርመጠመጡ መቃናት የሚገባው ሁሉ ይበልጥ እየጎበጠ መሄዱና ቤተ-ክርስቲያኒቱም የምትተማመንበት የታሪክ ምስክርና ታጋይ መጥፋቱም በጉልህ ታይቷል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ‹‹ነጻ የወጣ ነፍስ›› የሌላቸው እስኪመስል ድረስ ሕሊናው ላይ አንጥፈው ተቀምጠዋል፡፡

እርግጥ ከላይ የጠቀስኳቸው በሊቃውንቶቻችን ዘንድ የሚታዩት ምሁራዊ ጨለምተኝነት እና ክትያው(Consequences) እነዚህ ሊቃውት በሚኖሩባቸውና በሚሠሩባቸው አካባቢዎች በሚደርስባቸው ቤተ-ክህነታዊ ‹‹ገዥ መደብ›› እና ‹‹መንግሥታዊ›› ገዥ መደቦች ነን ባዮች ተጽዕኖ ምክንያት የመጡና ከፍተኛ አስዋጽኦ ያደረጉባው እንደሆኑ አይካድም፡፡

ይሁንና እንደ ጥንቶቹ ሊቃውንት ነጻ ምሁራዊ ድባብ በሌለበትም የቤተ ክርስቲያቱ ማኅጠነ ልቦና(Think Thank) በመሆን ምእመኑን በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሐሳብ መርተው በሚፈለገው የሞራልና የመንፈስ ልዕልና ማብቃት ባለመቻላቸው ከወቀሳ አይድኑም፡፡

ዛሬ ቤተ ክርስቲያ ከእነሱ የበለጠ አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና፡ ለዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰረታዊ ችግሮች ‹‹ ያለ አቡነ ተክለሃይማኖት ያለ አቡነ ፍሊጶስ ደብረ ሊባኖስ ምንድን ነች ? ያለ አቡነ እየሱስ ሞዐ ያለ አቡነ ክርስቶስ ሞዐ ደብረ ሀይቅ ምንድን ነች ? ያለ አቡነ ኤዎስጣቲዎስ ያለ አቡነ ፊሊጶስ ደብረ ባዚን ምንድን ነች ? ›› ያሰኙንን አይነት ሊቃውንት አጥብቀን እንፈልጋለን ፡፡ 
ሊቀ ካህናት ማንትሴን ፤ ሊቀ ስዩማን እገሌን ፤ መጋቢ ሐዲስ ፤ መጋ ብሉይና ሊቀ ማእመራንን እንትናን እናከብራቸዋለን ፡፡ ለዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን ደዌ መድኀኒት መሆን ካልቻሉ ክእነርሱ ይልቅ መድኀኒት መሆን የቻለውን ጨዋን እንመርጠዋለን፡፡
እንዲህ ካለ ምሁራዊ ጨለምተኝነት ወጥታችሁ በቦታሁ ተገኝታችሁ ቢሆን ኖሮ ያልጠገገውንና ከቶውንስ በላይ በላዩ የሚጨማመርበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁስል እኛም በየጋዜጣው ፤ በየመጽሔቱና በየብሎጉ የምንሞጫጭር የቤተ ክርስቲያን ልጆች በየብዕራችን ባንጓጉጠው ደስ ይለን ነበር፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ውኃንም ድንጋዩ ስለሚያጮኽው›› ጥሩ ትንፋሽ ለመሳብ ፋታ አልተገኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያቱና ምእመኑ ተራ በተራ አንድ ጊዜ በመሐል አገር ፤ ሌላ ጊዜ በደቡብ ፤ አንድ ጊዜ በሰሜን ሌላ ጊዜ በምእራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በገዛ እረኞቻቸው ሲወጉና ሲደሙ ብዕር አብሮ ይጮኻል፡፡ ያ የእረኞች አጥቂነት የባለቅኔውን ፤ የደራሲውን ፤ የፖለቲከኛውን ፤ የምሁሩን አንጀት ያላውሳል፤ ሐሞቱን ፤ የቀረች ውሳኔን ይነካካል፡፡ ያስጮኻል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱን እያጠፋ ያለው መዋቅር አርበድባጅ (Shock detachment) ቡድንም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ፤ ክብርንና ሉዓላዊነት  እየተፈታተነና ከዚህ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ (አንዳንዶችን) ያደረሰው ቤተ ክርስቲያቱን ለመጠበቅ ፤ ለመንከባከብ ፤ ለማዳን የምሁራን ቆራጥነት የማጣት ጉዳይ ነው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ጥንካሬና ችሎታ ላይ እንዳንተማመን በብዛት የምናየው በሲኖዶስ በኩል ችሎታ ማጣትንና ችሎታ ካላቸው የሊቃውንት ኃይል ጋር የበለጠ እየተለያየ መሄዱን ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውጪ ባሉ አደረጃጀቶች ላይ እምነታችንን እንዳናሳርፍ የቤተ-ክህነቱን አርበድባጅ ቡድን መቋቋም ቀርቶ በራሱ ለመቆም የሚችል አደረጃጀት ያለበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ይህን ሁኔታ ለማስቀረት የቤተ-ክህነቱ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ መቀየሩ ወሳኝነት አለው፡፡ መቀየር ማለት ሊቃውንቱ በቤተ- ክርስቲያኒቱ የመሠረተ እምነት ፤ የሥርዓተ አምልኮና ትውፊት መፋለሶች ላይ እውቀትን መሠረት ያደረገ ሂሳዊ አስተሳሰብ በነጻነት ማራመድ ፤ የቤተክህነቱን መዋቅራዊ አርበድባጅ ቡድን ያለ አንዳች መሸማቀቅ መገሰጽ ፤ ቤተ ክርስያኒቱ ያለችበት ነባራዊ እውነታ ከአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ተገንዝቦ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ማለት ነው፡፡
እናም በዚህ መልኩ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባቡ እንዲለወጥ ከተፈለገ ቅዱስ ሲኖዶስ ይከተል የነበረውን ኋላ ቀር አሰራር ለውጦ ፤ ከትንሽ ቡድን ጉጠኝነት (Sectarianism) ወጥቶ ፤ የተለያዩ ምሁራን አቅፎ እና የፖሊሲ ማውጣት ላይ አማክሮ ምእመኑን ለሚፈልገውበጎ አላማ የሚያነሳሳበት መንገድ መቀየስ አለበት ፡፡ ይህ ነው ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቀው ‹‹ኦርቶዶክሳዊነት››፡፡
በሊቃውንት በኩል ደግሞ ከላይ የጠቀስኩትን ፤ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ከልቡ ወስዶ ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ በድብቅና በሹክሽክታ ሳይሆን በግልጽና ሓላፊነት በሚሰማው መልክ በመሳተፍ ፤ ያሉትን መንፈሳዊ የትምህርት ተቋሞቻችንን እያጠናከረ ፤ የሌሉና የሚያስፈልጉትን እየፈጠረ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት መብቱን በቀናኢነት የሚጠብቅ ፤  ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣ መሆን ይገባዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት ልንማጸን የምፈልገው ወደ ኋላ ተመልካችነቱን አቁመውና ረስተው በወደፊቱ ላይ ያተኩሩ ዘንድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሲባል ካለፈው ታሪካችን ሳንማርና ሳንታረም ዘግቶና ለማኅደር አስረክቦ አይደለም፡፡
ባለፉት 22 ዓመታት የሚያሳፍርና ለአድማጭ ግር የሚያሰኝ የታሪክ ሸክም የተፈጸመ ይመስለናል፡፡ የወደፊቱን ተመልካች (Future Oriented) ሊቃውንቶቻችን እነዚህን የታሪክ ሸክም ነቁጥ በምራዊ ቅኝት ሊያሳዩን ይገባል፡፡ በጥናትና ምርምር ታግዘው ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል ? የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁኔታዎች አሁን ባሉበት አቅጣጫ ከቀጠሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምን መልክ ይኖራቸዋል? በጎ ለውጥ ለማጣት ቅዱስ ሲኖዶስ ካህናቱና ምእመኑ አንዳድ የአቅጣጫ ማስካካከያዎችን በአንድት ቢያደርጉ በቤተ ክርስቲያቱ የሚታየው ለውጥ ምንድነው? ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ ከሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን ፤ ከአገልጋዮችና ምዕመናን ምን ይጠበቃል ? ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ፤ ቤተ ክርስቲያቱ ካለችበት አዙሪት ለመውጣት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚዘጋጅ እውነተኛ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ››  ምሁራዊ መኅበረሰብ እንዲዳብር መታገል የሚጠበቅባቸው ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

Tuesday, 27 May 2014

በማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ረቂቅ የፓትርያርኩና የምልዓተ ጉባኤው ልዩነት ተካሯል፤ ለመሥራት ተቸግሬአለኹ ያሉት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከፓትርያርኩ ረዳት ሓላፊነት ለመልቀቅ ጠይቀዋል



Holy Synod in session
  • ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከጨለማው ቡድንና ፖለቲከኞች ጋራ የመከሩበትን የራሳቸው ያልኾነ የተልእኮ ሐሳብና አጀንዳ የተቃወሟቸውን የምልዓተ ጉባኤውን አባላት ‹‹በገንዘብ የተገዛችኹ›› እያሉ በመዝለፍ ቅዱስ ሲኖዶሱን ተዳፍረዋል፡፡
  • አቡነ ማትያስ ለአጥኚ ኮሚቴው የላኩት ባለ24 አንቀጽ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች ሳይቀነሱና ውይይት ሳይደረግባቸው በደንቡ ካልተካተቱና ረቂቁ በሌላ ኮሚቴ ዳግመኛ ካልታየ በሚል አጀንዳውን በራሳቸው አቋም ብቻ ለመቋጨት ያደረጉት ሙከራ በፍጹም አንድነት በቆሙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተቃውሞ ውድቅ በመደረጉ በመተዳደርያ ደንቡ ማሻሻያ ላይ የሚደረገው የምልዓተ ጉባኤው ውይይት ይቀጥላል፡፡
  • ከድንጋጌዎችና ግዴታዎቹ ውስጥ፡- የማኅበሩ ፈቃድ በየዓመቱ እንዲታደስ፣ ማኅበሩ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዳይሰበሰብና ቢሮ እንዳይከፍት፣ የሠራተኞቹ ቅጥርና ምደባ በመንበረ ፓትርያርኩ እንዲካሔድ፣ አባላቱ በግልም በቡድንም በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥራና በሰንበት ት/ቤቶች ጉዳይ እንዳይገቡ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
  • የአጥኚ ኮሚቴው አብላጫ አባላት፣ የፓትርያርኩን የድንጋጌዎችና ግዴታዎች መመሪያ ‹‹ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔና የደንብ ማሻሻያ አቅጣጫ ጋራ የማይሔድ›› በሚል ያልተቀበሉት ሲኾን ማኅበሩ በበኩሉ በተለይ በፈቃድ ዕድሳት ረገድ የተነሣው ሐሳብ ‹‹አገልግሎቱን ለማስቆም የሚደረግ አካሔድ ነው፤›› ብሏል፡፡
  • ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የመሥራት አቅሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ፣ በቤተ ክርስቲያናችንም እየሠራ ባለው ሥራ ኹሉ አብያተ ክርስቲያናትን፣ አድባራትንና ገዳማትን በስፋት እየጠቀመ ያለ፣ በምሁራን የታቀፈ ኹለንተናዊ ዝግጅት ያለው ማኅበር ስለኾነና ብዙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ በመኾኑ ራሱን የቻለ ድርጅታዊ መዋቅር ሊዘጋጅለት እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡›› /የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጥኚ ኮሚቴውን ባቋቋመበት የግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ውሳኔው የሰጠው የደንብ ማሻሻያ አቅጣጫ/
Holy Synod04
  • በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሓላፊነታቸው በአርኣያነት የሚጠቀስ ጥረት ባደረጉበት የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ሳቢያ ከፓትርያርኩ ጋራ ውስብስብ ችግር ውስጥ እንደገቡና አብረው ለመሥራት እንደሚቸገሩ በምልዓተ ጉባኤው መካከል ቆመው የተናገሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹አባቶቼ፣ አሰናብቱኝ›› ሲሉ ምልዓተ ጉባኤውን ጠይቀዋል፤ ምልዓተ ጉባኤው እንደሚነጋገርበት ይጠበቃል፡፡
  • ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መልቀቂያ ያቀረቡበትን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ለመከፋፈል እየተጠቀሙበት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡
Holy Synod07
የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ በቅርቡ ባረፉት ብፁዕ አቡነ ቶማስ ቦታ÷ ምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት÷ ተዛውረዋል፤ በምትካቸው የአኵስም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩትና የመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም የበላይ ጠባቂ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሰላማ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት መመደባቸው ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 17 May 2014

ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ



  • ‹‹የፓትርያርኩን ሥልጣን ይገድባል›› በሚል ተተችቷል
  • ‹‹አመራራቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ነው›› /የሕግ ረቂቁ/
  • ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚያስተላልፉት በብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ይኾናል
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፬፻፵፰፤ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
His Holiness Abune Mathias with thier Graces the Archbishopsየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ፓትርያርኩ የተጣለባቸውን አባታዊ ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችሉ የሚያግዝ እንደራሴ እንደሚመደብ በሚገልጽና የፓትርያርኩን ሓላፊነትና ተጠያቂነት በጉልሕ የሚያሳዩ አንቀጾችን ባካተተ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ ላይ እየተወያየ እንደኾነ ተገለጸ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በ1991 ዓ.ም. ያወጣችውንና ስትገለገልበት የቆየችውን ሕግ ከሌሎች ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋራ በማጣጣም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ከነባራዊ ኹኔታዎች ጋራ በማገናዘብ ያሻሽላል የተባለው የሕግ ረቂቅ ለውይይት የቀረበው ቅዱስ ሲኖዶሱ የትንሣኤ በዓል በዋለ በኻያ አምስተኛው ቀን በሚያካሒደውና ባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ የምልዓተ ጉባኤው ስብሰባው ላይ ነው፡፡
patriarch Ab Mathiasከምልዓተ ጉባኤው ኻያ ሦስት የመነጋገርያ አጀንዳዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የቀረበውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጎች፣ ደንቦችና ልማዳዊ አሠራሮች ኹሉ ይገዛል የተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁ÷ ርእሰ አበውና ለካህናቷና ለምእመናንዋ ኹሉ መንፈሳዊ አባት በመኾን በማናቸውም ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያኒቱን የመወከል ሥልጣን እንዳላቸው በሕጉ ለተገለጸው ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚሾም በአንቀጽ 24 ላይ ማስፈሩ ተመልክቷል፡፡
ለፓትርያርኩ እንደራሴ የመመደብ አስፈላጊነት፣ ‹‹ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን የተጣለበትን ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችል የሚያግዝ›› መኾኑን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ተገልጧል፡፡ እንደራሴው የሚመደበው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ምርጫ ሲኾን ለምርጫው ሦስት ዕጩዎች በፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጥቆማ ተለይተው እንደሚመረጡ፣ የሚመረጠውም አንድ አባት በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ በእንደራሴነት እንደሚመደብ ተጠቅሷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ቀኖናና ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለአድልዎ የማስተዳደር ሓላፊነት ላለባቸው ለፓትርያርኩ በእንደራሴነት የሚመረጠው ሊቀ ጳጳስ በአባትነት የሚመራው ሀገረ ስብከት ወይም በማእከል የሚገኝ የሥራ ሓላፊነት ያለው ቢኾንም በሕጉ የተመለከተውን መመዘኛ ማሟላት እንደሚገባው ተገልጧል፤ መመዘኛው ከ50 – 60 ዓመት የዕድሜ ገደብ የሚያስቀምጥ ሲኾን የአስተዳደር ችሎታና የመንፈሳዊ አመራር ልምድን፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ ዕውቀት አጣምሮ መያዝን እንደሚጠይቅ ተዘርዝሯል፡፡
‹‹ግለሰባዊ የሥልጣን ፈላጊነት ስሜት የሚገንበት፣ የፓትርያርኩን ሥልጣን የሚጋፋና መካሠስን የሚያበረታታ ነው›› በሚል አንቀጹን የተቃወሙ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ ምደባው አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም እንደራሴው በፓትርያርኩ ጥቆማ ብቻ መመረጥ እንዳለበት የቃሉ ትርጉም እንደሚያስገደድ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
የአህጉረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች በአንጻሩ፥ የእንደራሴው ምደባ፣ ፓትርያርኩ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩትን የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላትና የሥራ ክፍሎች በማቀናጀት በአዲስ መልክ ለማቋቋም በሌሎች አንቀጾች ከቀረቡት የረቂቁ ሐሳቦች ጋራ ተዳምሮ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት በማድረግ ላይ ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር መጠናከር የራሱ አስተዋፅኦ ያለው በመኾኑ እንደሚደግፉት መግለጻቸው ተነግሯል፡፡
ከሥልጣን አኳያም እንደራሴው ቅዱስ ፓትርያርኩን በዕለት ተዕለት ሥራውና በመንፈሳዊ አገልግሎቱ ከማገዝ ውጭ ‹‹ለቅዱስ ፓትርያርኩ ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ የሚጋራው የተለየ ሓላፊነት አይኖረውም፤›› በሚል በረቂቁ የሰፈረውን አንቀጽ በመጥቀስ እንደራሴው ፓትርያርኩን በቅርበት የመደገፍ እንጂ የመጋፋት ሚና እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
ተጠያቂነትን በተመለከተም ፓትርያርኩን ጨምሮ ኹሉንም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፡-
  • ቤተ ክርስቲያኒቱን በበላይነት ለሚመራውና ለሚጠብቀው እንዲኹም ቤተ ክርስቲያኒቱን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ላለው ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ በማድረግ፣
  • በሕይወት ባሉበት ጊዜ ኹሉ ቋሚ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረትና ሌላም የገንዘብ ማስገኛ ምንጭ እንዳይኖራቸው፣ በስጦታም ኾነ በውርስ የሚያገኙት ሀብት በሞት በሚለዩበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ንብረት እንደሚኾንና በስጦታም ኾነ በውርስ ለሦስተኛ ወገን እንደማይተላለፍ በማረጋገጥ
  • እያንዳንዳቸው በተሾሙበት ቀን የፈጸሙትን የመሐላ ቃል አፍርሰው ሃይማኖትን ቢያፋልሱ፣ ቀኖና ጥሰው ቤተ ክርስቲያኒቱን ቢያስነቅፉ፣ በአስተዳደር በደልና በአመራር ጉድለት የካህናቱንና የምእመናኑን አመኔታና ተቀባይነት ቢያጡ በማስረጃ ተደግፎ በሚቀርብ ክሥና ቅሬታ የሚጠየቁበት፣ ለመታረም ፈቃደኛ ካልኾኑም ከሓላፊነታቸው የሚገለሉበት ሥርዓት በረቂቁ በመካተቱ፣ በፓትርያርኩ አልያም በወቅታዊ እይታ ላይ ብቻ የታጠረ ረቂቅ እንዳልኾነ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩ በዋናነት የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አመራር በማጠናከር ልዕልናዋንና ክብሯን፣ አንድነቷንና ሥርዓቷን ከማስጠበቅ አንጻር ሊታይ ይገባል የሚሉት የሥራ ሓላፊዎቹ፡- ምልዓተ ጉባኤው የሕግ ማሻሻያ ረቂቁን በጥልቀት በማዳበር ከፍተኛው መንፈሳዊ፣ ሕግ አውጭና አስተዳደራዊ አካል የኾነው የቅዱስ ሲኖዶሱ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም የማይገሠስበት፣ ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬም እንደቀድሞው ልዕልናዋና ክብሯ፣ አንድነቷና ሥርዓቷ የሚጠበቅበት፣ ሃይማኖታዊና ልማታዊ ሥራን በመሥራት የመሪነት ሚናዋን የምታጠናክርበት መሣርያ አድርጎ እንደሚያጸድቀው እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ በዓላት ላይ እንዳስፈላጊነቱ እየተገኘ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጠው እንዲሁም በብዙኃን መገናኛ መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፈው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ እንደሚኾን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ መስፈሩ ተጠቅሷል፡፡

Share this:

‹‹መንግሥት በማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይችልም›› /ኢንጅነር ታደለ ብጡል/


(ሎሚ መጽሔት፤ ቅጽ ፫ ቁጥር ፻፮፤ ከግንቦት ፰ – ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
ሎሚ፡- እንደሚታወቀው እርስዎ በቤተ ክህነት አካባቢ ብዙ አስተዋፅኦዎችን አበርክተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በቤተ ክህነቱ አካባቢ ብዙ ተደማጭነት አልዎት ይባላል፡፡ ቤተ ክህነት ስላለችበት ኹኔታና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ተያይዞ ስለሚነሡ ‹‹ወሬዎች›› የሚሉን ነገር ካለ?
lomi ginbot magazineኢ.ር ታደለ፡- ቤተ ክህነታችን ወደድንም ጠላንም ማንም ምን ይበል የኢትዮጵያ አንድነት ምሶሶ ነች፡፡ ከምን አንጻር? ግብረ ገብነትን በመስበክ፣ ትምህርት በማስተማር፣ ሥነ ጽሑፍን በማበርከት፣ የሀገር ኩራት የኾኑትን ቅርሶች በመጠበቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ እግረ መንገዳችንን አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙበት ስፍራ ኹሉ አገር በቀል ዛፎች፣ አበቦችና ንጹሕ አየር መኖሩ ሌላው የቤተ ክርስቲያናችን ትሩፋቶች ናቸው፡፡
ትላልቆቹ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተንጣለለ ቤት እየኖሩ፣ ሚልዮኖች በሚያወጡ መኪናዎች እየሔዱ ቤተ ክርስቲያናችን ግን በልመና መተዳደር አይኖርባትም፡፡ በተለይ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ድኻዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ቅ/ሲኖዶሱ ይህ ኹኔታ የሚለወጥበትን መንገድ ማስተካከል አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለኝ፡፡
መስቀል፣ ጸናጽል፣ መጻሕፍትንና ሌሎችም ቅርሶች እየተሰረቁ ሲሸጡ ተገኝተዋል፡፡ ዋናው ምክንያቱ የንቃተ ኅሊና ውሱንነት፣ የመተዳደርያ ደመወዝ ማነስና ሰብአዊ ደካማነት መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሰፊ መሬት ከምትገነባው ሕንፃና ከምእመናኑ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ላይ በቂ ደመወዝ ልትሰጣቸው ይገባል፡፡
በየክፍለ ሀገሩ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የመቀደሻ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ስለሌላቸው፣ ክብካቤ በማጣታቸው ካህናቱ በመንገድ ዳር ጨርቅ አንጥፈውና ዣንጥላ ዘርግተው መለመናቸው እንዲቀር ቅ/ሲኖዶሱ አትኩሮት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ችግር መቅረፍ ያለበት የቤተ ክህነታችን አመራር አካል ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ቀድሞም ከመተቸት አልተቆጠብኹም ነበር፡፡ አኹን ከብዙኃን መገናኛ እንደሰማኹት አዲሱ ፓትርያርካችን ይህን የመሰለ ጉድለት መኖሩንና መስተካከል ይገባዋል ማለታቸውን ሰምቻለኹ፡፡ እኔ አሜሪካን አገር ቆይቼ ስለመጣኹ ከአዲሱ ፓትርያርካችን ጋራ ገና የመተወዋወቅ ዕድል አላገኘኹም፡፡ በቅርቡ ግን ቀጠሮ ወስጄ ላነጋግራቸው እፈልጋለኹ፡፡ ያለኝን ቅሬታ ምንም ሳልደብቅ የመንገር ሐሳብ አለኝ፤ የሚሉትን ሰምቼ እነግርሃለኹ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የጥላቻ ዘመቻ እየተካሔደ ነው፡፡ እንደምታውቀው የሌሎች ሃይማኖቶች በየቦታው ሕንፃ እየገነቡና እየገዙ ሰውን ይሰብካሉ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ወጣቶች ደግሞ ዝም ብለው ከጧት እስከ ማታ በመለፍለፍ ሳይኾን የራሳቸውን ገንዘብ ከደወመዛቸው በማዋጣት ቤተ ክርስቲያን ከልመና የምትድንበትን መንገድ ተከትለዋል፡፡ ሥነ ሥርዓት ባለው መንገድ ምእመናኑ ሳይደክሙና ሳይሰለቹ ጸሎት እንዲካሔድ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ለሃይማኖታቸው ካላቸው ቀና ሐሳብ በመነሣት ቤተ ክርስቲያናችን እየጠነከረች እንድትሔድ ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ማድረግ የተሳናቸው ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳንን ለማዳከም ይሞክራሉ፡፡ መልካም ተግባሩን ለማጣጣል የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚነዛው ወሬ የጥላቻ ወሬ ነው፡፡ ጥላቻ ደግሞ የትም አያደርስም፡፡ ማንም ሲለፈልፍ ቢውል የትም አይደርስም፡፡
የራሳቸውን እምነት ከማራመድ ውጭ አንድም የማኅበረ ቅዱሳን አባል ከሌላ የማኅበረ ቅዱሳን አባል ጋራ ተጣላ የሚል መረጃ የለም፡፡ እነኚኽ ልጆች ለምን ራሳቸውን ችለው ቆሙ ከሚል ቅናት በስተቀር አንድም ሌላ ጥፋት አልፈጸሙም፡፡
ሰሞኑን እንደሰማኹት በቅርቡ ስብሰባቸውን አግደዋቸዋል፡፡ ይኼ ነውር ነው! በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አትሰበሰቡም ማለት አይችልም፡፡ ይኼ ስሕተት ነው፤ ምክንያቱም ይህ ድርጊት በሃይማኖት ጣልቃ መግባት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ስብሰባ ማካሔድ የዜጎች መብት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ርግጥ ለመሰብሰብ ፈቃድ በሚያስፈልግበት ቦታና ጊዜ ፈቃድ መጠየቅ ይጠበቃል፤ ግን ምንም ችግር የማይፈጥር ስብሰባ እንዳይካሔድ መደረጉ አግባብነት የለውም፡፡
ምናልባት ይህን ድርጊት የፈጸሙት ማኅበረ ቅዱሳንን ለማውገዝና ለማስጠላት የሚሞክሩቱ ሳይኾኑ አይቀሩምና እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው የሚል መልእክቴን አስተላልፍልኝ፡፡
About these ads

Wednesday, 14 May 2014

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ተካሔደ


Holy Synod opening prayerዛሬ፣ ረቡዕ ግንቦት ፮ ቀን የሚጀመረው የ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት በትላትናው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተካሒዷል፡፡
በትላንትናው ዕለት ከቀኑ ፲ ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው በዚኹ የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት የተሰበሰቡ ከሠላሳ በላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል፤ በሥርዓተ ጸሎቱ መክፈቻና መዝጊያ የቤተ ክርስቲያኑ የደወል ድምፅ ለደቂቃዎች ተሰምቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ‹‹ሑሩ ወመሀሩ›› በሚል ርእስ በጽሑፍ የተዘጋጀ ትምህርት የሰጡት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ናቸው፡፡
His Grace Abune Garima‹‹ኹላችንንም ከየአህጉረ ስብከታችን ሰብስቦ ስሙን በመቀደስ፣ ቃሉን በመስማት ዓመታዊ ስብሰባችንን በጸሎት ለመጀመር ላበቃን አምላካችን እግዚአብሔር ‹ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐነ እስከ ዛቲ ሰዓት› ብለን እናመሰግነዋለን›› በማለት ትምህርታዊ ጽሑፋቸውን የጀመሩት ብፁዕነታቸው÷ በቅዱስ ሲኖዶሱ እየተጠናና እየተመከረበት የሚወጣው ሕግና ደንብ ለእምነታችን ህልውና፣ ለኅብረተሰባችን ማኅበራዊ አገልግሎት ዋስትና የሚሰጥ ስለኾነ ለሕጉ ተገዥዎች መኾን እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስን ምንነትና አጀማመር፣ ቤተ ክርስቲያንን በመምራትና በመጠበቅ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ ስላሳለፋቸው ውሳኔዎችና የሥልጣን ልዕልናው እንዲሁም ከወቅቱና ከመጪ ኹኔታዎች አንጻር የሚጠበቅበትን አባታዊ ሓላፊነትና ውሳኔዎቹን በማስፈጸም ረገድ ካህናትና ምእመናን ያላቸውን ድርሻ ብፁዕነታቸው በትምህርታዊ ጽሑፋቸው በስፋት አብራርተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት በፓትርያርክ ሰብሳቢነት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለመወሰን የሚደረግ የሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ መኾኑን ብፁዕነታቸው ገልጸው፣ ከጥንት ጀምሮ ጸንቶ የመጣውን የአበው ሐዋርያት፣ የአበው ሊቃውንት ትምህርተ ሃይማኖት ያለምንም ለውጥ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሓላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያን የሥልጣነ ክህነት ባለሥልጣን መኾኑንና ውሳኔውም የመጨረሻና ይግባኝ እንደሌለው ብፁዕነታቸው አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ50 ሚልዮን በላይ ተከታይ ምእመናን፣ ከ500‚000 በላይ ካህናት፣ መዘምራንና ዲያቆናት፣ ከ60‚000 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያንና ከ1000 በላይ ገዳማት እንዳሏት የጠቀሱት ብፁዕነታቸው÷ ሃይማኖትና ምግባር እንዲጸና፣ አገር እንዲቀና፣ የተቸገረ ወገን እንዲረዳ ቅዱስ ሲኖዶሱ በየጊዜው እየተሰበሰበ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች በሥራ ለመተርጎም የኹሉንም ጥረት እንደሚጠይቅና ለዚኽም ክህነታዊ አገልግሎቱ ወቅቱን የዋጀ እንዲኾንና የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በግንባር ቀደምነት አባታዊ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

Friday, 2 May 2014

ሰበር ዜና – ማኅበረ ቅዱሳን በጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አያያዝና አጠባበቅ ላይ ለዛሬ የጠራውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የተፈቀደው ጥናታዊ ጉባኤ በፓትርያርኩ ውሳኔ ተከለከለ


mahibere kidusan
  • ዛሬ ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 – 11፡00 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም አዲሱ አዳራሽ ‹‹ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ዓይነትና የይዘት ትንተና እንዲሁም አያያያዝና አጠባበቅ›› በሚል ርእስ የተጠራው የጥናት ጉባኤ ክልከላ መንሥኤ ‹‹የሥልጣን ተዋረድንና የዕዝ ሰንሰለትን ባልተከተለ መልኩ በቀጥታ የአድባራትንና የገዳማትን አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ስብሰባ መጥራት›› የሚል ነው፡፡
  • ለጥናታዊ ጉባኤው የተጠሩት የገዳማትና አድባራት አለቆች ቤተ መዘክር ያላቸው ሦስት አብያተ ክርስቲያን ብቻ መኾናቸውን የገለጹት የጉባኤው አስተባባሪዎች በበኩላቸው÷ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች፣ ምሁራንና እንግዶች ጥሪ ያደረገው ዕቅዱና አስፈላጊነቱ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቀርቦ ከተመከረበትና ከተፈቀደ በኋላ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
  • ፓትርያርኩ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተጠሪ የኾነበትን አሠራር በመሻር ማንኛውንም ስብሰባዎቹንና ጉባኤዎቹን ኹሉ ያለልዩ ጽ/ቤታቸው ፈቃድ እንዳያካሒድ ከሕጉ ውጭ በቀጥታ ለማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት በላኩት የልዩ ጽ/ቤታቸው ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
  • የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የጥናታዊ ጉባኤውን መከልከል በተመለከተ በቀጥታ ለማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት ደብዳቤ ለመጻፍ የተገደደው፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ስለጉባኤው እንደሚያውቁና ዝግጅቱም የአሠራር ክፍተት እንደሌለበት ለልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊ በማሳወቅ ሊታገድ እንደማይገባው በመከራከራቸው ነው፡፡
  • ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የዋናውን መሥሪያ ቤት ማለትም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መምሪያዎችና ድርጅቶች ጨምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚገኙትን የሥራ ዘርፎች ኹሉ በበላይነት የማስተዳደር ሥልጣንና ተግባር የሚሰጠው ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ነው፡፡ በዚኽ ረገድ የፓትርያርኩ ሓላፊነት በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማቸው የማስተላለፍ፣ በተግባር ላይ መዋላቸውንም መከታተልና መቆጣጠር ነው፤ ፓትርያርኩ የሚፈጽሟቸው ተግባራት ካሉም ዓበይትና የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ ያረፈባቸው መኾን እንደሚገባቸው ተደንግጓል፡፡
  • በፓትርያርኩና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሥራ አለመግባባቶች እየተባባሱ የመጡ ሲኾን መንሥኤውም÷ በአማሳኞችና ጎሰኞች የሚመከሩት ፓትርያርኩ የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ጨምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የሥራ ዘርፎች በቀጥታ የመምራትና የማስተዳደር ሓላፊነት ያለባቸውን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በመጋፋት የጀመሩት አካሔድ ነው፡፡
  • ፓትርያርኩ የሚመለከታቸውንና የማይመለከታቸውን ዐውቀውና ለይተው በብቃት የመምራት አቅም ያጡትን ያኽል በዙሪያቸው የከተሙ አማሳኞችንና ጎጠኞችን መሸጋገርያ ያደረገውን ውጫዊ ተጽዕኖ በቀጥታ ተቀብሎ ለማስፈጸም የሚታይባቸው ፍጥነትና ታዛዥነት በእጅጉ እንዲናቁና እንዲጠሉ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
*                           *                              *
  • ጥናታዊ ጉባኤው÷ ማኅበረ ቅዱሳን በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማት፣ ዕድገት፣ ታሪክ፣ ቅርስና መሰል አርእስተ ጉዳዮች ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይም ወጣት ምሁራንን ለማበረታታትና በተቻለው ኹሉ ለመርዳት፤ ሃይማኖታቸውን የሚጠብቁ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚከባከቡና ሀገራቸውን የሚወዱ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በተጣለበት ሓላፊነት መሠረት ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ተያያዥነት ባላቸው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ለማከናወን ባቋቋመው የጥናትና ምርምር ማእከል በየኹለት ወሩ የሚካሔድ መደበኛ መርሐ ግብር ነው፡፡
  • የማኅበሩ የጥናትና ምርምር ማዕከል በየኹለት ወሩ የሚያካሒደው መደበኛ ጥናታዊ መድረክ አካል የኾነውና የሚመለከተው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ዝርዝር ይዘቱን ከአንድ ወር በፊት በጋራ ውይይት ጭምር እንዲያውቀው ተደርጎ የተጠራው ጥናታዊ ጉባኤ፣ በጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ዓይነትና የይዘት ትንተና እንዲኹም ጥበቃ ላይ ያተኮረ መኾኑ የመርሐ ግብሩ መግለጫ ያመለክታል፡፡ms1971
  • ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ ‹‹ዜና መጻሕፍተ ብራና›› በተሰኘውና በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በተካሔደው ሦስተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጥናት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ጽሑፋቸው እንደገለጹት÷ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍታችን ገበታቸው የወርቅ የኾነ፣ የብርዓቸው አጣጣልና የብራናቸው ንጽሕና፣ የቅርፃቸው ማማርና ውበት ሲመለከቱት በእውነት የእነርሱን መልክና ቅርፅ የኑሮ ቤት አድርጎ መኖር እንጂ በዚኽ ዓለም በሥጋዊ ኑሮ ታስሮ መኖርን አያስመኙም፡፡
  • ከቅዱሳን ገድላትና ድርሳት ባሻገር አያሌ ‹የቴዎሎጊያ እና ፊሎሶፊያ› ሀብት ያካበቱት ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት በይዘታቸው ‹‹እግረ ኅሊና ያልደረሰበት፣ የአእምሮ ክንፍ ያልበረረበት የተሸሸገ ጥበብና ያልተሞከረ ስውር ፍልስፍና›› የተካበተባቸው ናቸው ያሉት ሊቁ÷ ያልተከፈተውን የዕውቀት ጎዳና፣ ዓይን ያላየውን ዦሮ ያልሰማውን በጥበበኞች ያልታሰበውን ብልሃትና ሥነ ጥበብ መፈለግና መሻት ፈልጎም ማግኘትና አግኝቶም በፍሬውና በመልኩ መጠቀም ከአኹኑ ትውልድ የሚጠበቅ አዲስ አለኝታ፣ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ የምሥራች መኾኑን አመልክተዋል፡፡Ge'ez 1
  • የተማረው ትውልድ የጠፋባትን የወርቅ ቀለበት ለማግኘት ባጡ፣ ቆጡ፣ ማዘንቱ፣ ማቶቱ ሳይቀር ኹሉንም በጥንቃቄ እያገላበጠች የምትፈልገውን ልባም ሴት መምሰል እንዳለበት ሊቁ በጽሑፋቸው መክረዋል፡፡ የበሬ ቆዳው በገዛ ሞራው እንዲለፋና እንዲለሰልስ የሀገራችን መልክና ቅርፅ በገዛ ሥነ ጽሑፋችንና ቅርፃችን ማሣመር እንድንችልና በዝግ ቤት ከየቤተ መቅደሱ ምህዋርና ከዋሻ ውስጥ ወይም ከመንደርና ደንበኛ ካልኾነ ዕቃ ቤት ተደብቆ ትውውቁ ከሌሊት ወፍና ከአይጥ መንጋ ጋራ የኾነውን የአባቶቻችንን ሥነ ጽሑፍ እያሠሥንና እየመረመርን ለተከታዩ ትውልድ እንድናቆይም በጥናታቸው አደራ ብለው ነበር፡፡
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች የበጀት እጥረትንና የሰው ኃይል ውሱንነትን በመጥቀስ ተግባራቸውን ማከናወንና የታሰበውን ለውጥና ውጤት ማምጣት እንደተሳናቸው ሰሞኑን በአስተዳደር ጉባኤው ላይ ቀርቦ ከተገመገመው የስድስት ወር ዕቅድ ክንውን ሪፖርታቸው በተረዳንበት ኹኔታ ያልነበሩና የሌሉ ለመኾን የተቃረቡትን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍታችን ላይ ያተኮረው ጥናታዊ ጉባኤ የተከለከለበት ዋነኛ ምክንያት ታድያ፣ በልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ እንደተመለከተው ዝግጅቱን ካለማወቅ አልያም የዝግጅት ሒደቱ የሥልጣን ተዋረድንና የዕዝ ሰንሰለት አልተከተለም ከሚለው የተለመደ የማሰናከያ ስልት ጋራ በርግጥም የተያያዘ እንዳልኾነ ግልጽ ነው፡፡
  • የልዩ ጽ/ቤቱ የክልከላ ውሳኔ ከታወቀበት ከትላንት ቀትር ጀምሮ ደብዳቤውን እያሰራጩ የሚገኙት በፓትርያርኩ ዙሪያ በአማካሪነትና ረዳትነት ስም ከተጠጉት እነንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ የዓላማና የጥቅም ግንኙነት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት አማሳኞቹ እነኃይሌ ኣብርሃ መኾናቸው ሲታይ የክልከላ ውሳኔው ምንጭ፣ የአብነት መምህራን ሀገር አቀፍ ጉባኤ ከታገደበት የካቲት ወር ጀምሮ የተጠናከረውና ማኅበሩን ብሎም ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም ልዩ ተልእኮ ባላቸው ባለሥልጣናት ጭምር ተደግፎ የቀጠለው ጫና ስለመኾኑ ግልጽ ያደርገዋል፡፡
  • የማኅበሩ አመራር ስለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የክልከላ ደብዳቤ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ መምከሩ የተገለጸ ሲኾን በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት የጽሑፍ ምላሽ እንደሚሰጥ ተመልክቷል፤ የጎሰኝነት ሰለባ በመኾንና ለአማሳኞች ሽፋን በመስጠት በበታች ሠራተኞች ዘንድ ሳይቀር ክፉኛ እየተናቁና እየተጠሉ በመጡት ፓትርያርክ ዙሪያ የተኮለኮሉትን ጥቅመኞች የማጋለጥ እንቅስቃሴም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እየተገለጸ ይገኛል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ዓመታዊ ስብሰባው የማኅበሩን ተጠሪነት ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር አውጥቶ በጊዜያዊነት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያደረገበት ውሳኔ፤Holy Synod 2004 Ginbot annual meeting decision on Mahibere Kidusan
የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ በመተላለፍ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የፈቀዱትን የማኅበሩን ጥናታዊ ጉባኤ የከለከሉበትና ለወደፊቱም ማኅበሩ የልዩ ጽ/ቤቱን ፈቃድ ሳያገኝ ስብሰባ ማካሔድ እንደማይችል ያሳሰቡበት ደብዳቤ፤pat ban

የማኅበራችን አገልግሎት የክርስቲያናዊ ግዴታችን አካል ነው

አትም ኢሜይል
 ሚያዚያ 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ክርስቲያኖች የተጠሩት በክርስቶስ እንዲያምኑ በስሙም እንዲጠመቁ ብቻ አይደለም፤ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የፍቅርና የርኅራኄ ሥራ ለሰዎች ሁሉ እንዲሠሩም ነው፡፡ “ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” /ፊል 1÷29/ ያለው የሐዋርያው ቃሉ ይሄንን ያመለክተናል፡፡ ይኸውም የመንፈስ ፍሬዎችን ይዘን እንድንገኝ የታዘዝንበት ነው፡፡ /ገላ 5÷22/

በዚያም ላይ ተመሥርተን ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለነፍሳችን ድኅነት መልካሙን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ሰዎች ቢራቡ ማብላት፣ ቢጠሙ ማጠጣት፣ ቢታረዙ ማልበስ፣ ቢታሰሩ መጠየቅ … ወዘተ ሁሉ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑ የፍቅርና የቸርነት ሥራዎች ናቸው፡፡ ይሄንን ለማድረግም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኖ መጠመቅ ብቻ በቂ ነው፡፡ የተጠመቅነውም ይሄንን የፍቅርና የቸርነት ሥራ ሠርተን በእግዚአብሔር ፊት እንድንከብር ነውና፡፡

በዚህም ምክንያት የማኅበራችን የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ላለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ ለሆኑት ጊዜያተ ይሄንን እምነት በመያዝ በየገዳማቱ ላሉ አባቶች፣ በየአብነት ትምህርት ቤቶቹ ላሉ ሊቃውንት በተቸገሩት ነገር ሁሉ በመድረስ ክርስቲያናዊ ምግባረ ሠናይ ተግባራትን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ አባላቱ በሙያቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ሁለንተናዊ ተግባራትን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚፈጸመው ግን የአምልኮ አካል ሆኖ እንጂ በዓለማዊ፣ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች እንደሚፈጸም ከምድራዊ ሥልጣንና ከዕለት ጉርስ አንጻር የሚታይ አገልግሎት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በእንዲህ ዓይነት መንገድ የሚፈጸሙ መንፈሳዊ ተግባራትን ምንነትን ሲያመለክት እንዲህ ማለቱ አይረሳም “ንጹሕ የሆነ፤ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።” /ያዕ. 1÷27/

ከልዩ ልዩ ማኀበራዊ አገልግሎቶች በመለስ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ለመናፍቃን ጥያቄዎች ሊቃውንቱን ምንጭ አድርጎ መልስ በመስጠት ፍጹም መንፈሳዊ ተግበራትን ሲፈጽምም ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ የሚሠራባቸው መንገዶችም ጊዜውን የዋጁ ሆነው በሰፊ መዋቅር ይከናወኑ እንጂ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በቅዱሳን ስም በተሰባሰቡ የሰንበቴና የጽዋ ማኅበራትም እንደየዘመኑ ሁኔታ ሲፈጸም የቆየ ነው፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በአቅራቢያቸው ባሉ አጥቢያዎች ተሰባስበው በቃለ እግዚአብሔር በመማር በሰብእናቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አድገው ከሥነ ምግባራዊ ችግሮች ተጠብቀው ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ እንዲሆኑ ያተጋል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም ተመርቀው በሙያቸው በልዩ ልዩ የሥራ ሓላፊነቶች ላይ ሲቀመጡ ቤተክርስቲያንን በሙያቸው በየአጥቢያው እንዲያገለግሉ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሓላፊነቶች ግን ከክርስቲያናዊ ግዴታ የሚመነጩ እንጂ ከተራ ሥጋዊ ምኞትና ዓለማዊ ሐሳብ የመነጩ አይደሉም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉም የቤተክርስቲያን አካላትና ምእመናን ቢሆንም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ የፍቅርና የቸርነት ሥራን በመሥራት ሕያዊት የሆነችው ነፍስ የምትድንበትን ሥራ በጋራም በተናጠልም እንዲያከናውኑ የሚሻ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ያሉ የመንፈሳዊ ማኅበራት ተግባራት ሁሉ ከዚህ አንጻር ሊታይ ይገባል፡፡ እነዚህ ተግባራት በጎ ተግባራት ናቸው፡፡ ለነፍሳችን መዳን ወሳኝ ናቸው፡፡ በጎ መሆናቸውን ካወቅን ደግሞ ሌሎች አካላት ተደሰቱም አልተደሰቱም ሳንፈጽም የምንተወው ነገር አይደለም፡፡ “እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነውና።” /ያዕ 4÷17/፡፡

ስለዚህ ማንኛውም ወገን እውነታዎችን ፈሪሃ እግዚአብሔር በተሞላበት መነጽር እንዲመለከት እየጠየቅን፤ የማኅበሩ አገልግሎት በመክሊቱ አትርፎ ከመገኘት የመነጨ ዓለማዊ ያልሆነ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መሆኑን በውል ማጤን ይገባዋል፡፡ አገልግሎቱን ቤተ ክርስቲያን ባለችበት በመላው ዓለም እንዲሠራ ፈቃድ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስና አባቶች በጸሎትና ምክር ማገዛቸው እንዳለ ሆኖ ወደፊትም አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሊያደርጉ የሚችሉ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል፡፡

የማኀበሩ አባላትም የምንሠራው በስሙ ተጠምቀን አምነን የተከተልነው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ መነሻ አድርገን መሆኑን ሁልጊዜም በማሰብ በሚመጡ ፈታኝ ነገሮች ሁሉ ሳንፈራ ሳንደነግጥ በአገልግሎታችን ልንጸና ይገባል፡፡ “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብለን የገባንላትን ቃል ጠብቀን ለእኛና ለመላው ሕዝብ ነፍስ መዳን የምናደርገውን ትጋት እናጠናከር እንላለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር