Wednesday, 26 March 2014

ቤተ ክህነቱን ከሙሰኞችና ከጎሰኞች የማጥራት ዘመቻው ይሳካ ይሆን?! Posted by DejeS ZeTewahedo

March 25, 2014



(ደጀ ሰላም፣ መጋቢት 14/2006 ዓ.ም፤ ማርች 24/2014/ PDF በፍቅር ለይኩን):- ባለፈው ሳምንት ‹‹የፓትርያርኩ የለውጥ ተስፋዎች ወዴት ገቡ?›› በሚል አቶ መብራቱ መርሳ የተባሉ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ በቤተ ክህነቱ ተቋም የተንሰራፋውን ሙሰኝነትንና ጎጠኝነትን በተመለከተ የተማፅኖ ጦማራቸውን በሪፖርተር ጋዜጣ በኩል ለቅዱስ ፓትርያርኩ ይደርስ ዘንድ አቅርበው ነበር፡፡ እኚህ ግለሰብም ባቀረቡት የተማፅኖ ደብዳቤያቸው ዋና አሳብም፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ የነገሠውን አድር ባይነት፣ ዘረኝነት/ጎጠኝነትና ሙስና ለማጥፋት በአደባባይ ቃል የገቡበትን ዘመቻቸውን አጠንክረው እንዲቀጥሉበትና ፍሬውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚጠይቅ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ የአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የበርካታዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪዎች፣ አባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን የቀን ተሌት ብርቱ ምኞትና ተማፅኖ ነው፡፡ እኚህ ሰው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ወደ ፕትርክና መንበር በመጡ ማግሥት የቤተ ክህነቱን ተቋም ከጎጠኞችና ከሙሰኞች ለማጥራት የገቡት ቃል ተግባራዊ ኾኖ ለማየት የነበራቸው ምኞት ከዓመት በኋላ የተጠበቀውን ያህል ዘመቻው ስኬት ባለማሳየቱና የለውጡም ሂደት በመንቀራፈፉ ሥጋት ቢጤ ገብቷቸው ይመስላል ይህን የተማፅኖ ደብዳቤ ለፓትርያርኩና ለሚመሩት የቤተ ክህነት ተቋም ለማድረስ የወደዱት፣ የተገደዱት፡፡
የእኚህ ግለሰብ ‹‹የለውጥ ያለኽ›› ተማፅኖ ጦማር በርካታዎችን የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶችን፣ አገልጋዮችንና ምእመናን የሚወክል እንደሆነ ነው በግሌ የማምነው፣ የምቀበለውም፡፡ የብዙዎች የአባት ያለኽ፣ የመሪ ያለኽ፣ የፍቅር ያለኽ፣ የእውነት ያለኽ፣ የፍትሕ ያለኽ፣ የበጎነት ያለኽ፣ የቅንነት ያለኽ፣ የመንፈሳዊነት ያለኽ፣ የለውጥ ንፋስ ያለኽ ጩኸትና አቤቱታ የቤተ ክህነቱን ተቋምና የአገሪቱን ሰማይ ክፉኛ ካደፈረሰው ሰንብቷል፣ ከራርሟልም፡፡
እውነተኛ የኾኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች፣ መንፈሳዊ መሪዎች፣ አገልጋዮችና ምእመናንም፣ አምላክ ሆይ ዝምታህ እስከ መቼ ነው?!፣ በቅዱስ መቅደስህ አደባባይ በትእቢትና በድፍረት እየተንጎማለሉ መሠውያህን በድሆች ዕንባና ደም የሞሉ ክፉዎችን የምትታገሳቸው እስከ መቼ ነው?!፣ በአፍቅሮተ ንዋይ አቅላቸውን የሳቱ፣ በክቡር ደምህ በዋጃኻቸው በጎችህ/በመንጋዎችህ ላይ በዋጋ የሚደራደሩ ይሁዳዎች- ምንደኞችና ነጋዴዎች ላይ የተግሣጽህ፣ የቁጣህ ጅራፍህ መቼ ነው የሚነሳው?!፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በዘርና በጎሳ የሚለያዩና የሚከፋፍሉ ዘረኞችና ጎጠኞችስ መቼ ነው ክፉ ዘራቸው የሚመክነው?!
የወንጌልን እውነት ቃል የሚሸቃቅጡ፣ መንፈሳዊ ሕይወትንና ስኬትን በግፍ በተከማቸ የዓመፃ ገንዘብና በዓለማዊ ሀብት የሚለኩ፣ የእግዚአብሔርን ስጦታ እንደ ስምኦን መሰሪ በገንዘብ ገዝተው በመቸርቸር ሀብትና ዝናቸውን ሰማይ ለማድረስ ዓውደ ምሕረቱን ያረከሱ አስመሳይ ነጋዴዎችና ምንደኞችስ ስለምን ቤትህን አጣበቡት?!፣ በቅድስናህ መቅደስ ላይ የሚዘባበቱ ፌዘኞችስ እስከ መቼ ሕዝብህን በሽንገላ ቃል ያባብሉታል፣ በክፉ ሥራቸውስ ያሰጨንቁታል፣ ያሰቃዩታል፣ ያስለቅሱታል?!
ስለ ሕዝብ መከራና ሰቆቃ፣ በየቀኑ እየፈራረሱ ስላሉ በክቡር ደምህ ስለዋጃኻቸው መቅደሶችህ/ሕዝበ ክርስቲያን ግድ የሚለውና በፈረሰው ቅጥር በኩል የሚቆም ነቢይ ኢሳይያስ ወዴት ይገኝ ይሆን?!፣ በመቅደስህ አጥር ስር ስለወደቁ የምድሪቱ ጎስቋሎችና መፃጉዎች፣ በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ በቤተ መቅደስ ደጃፍ ስለሚያነቡ የዋኃን ሕፃናትና እናቶቻቸውስ ማን ነው ግድ የሚለው?!፣ ሕዝብህ በየቀኑ እየፈረሰ፣ እየተናደ ባለበት፣ የአንተን ቤት በዕብነ በረድና በከበሩ ድንጋዮች አንሠራለን፣ እነገነባለን የሚሉ ግብዞችንና ሙሰኞችንስ የሚገሥጻቸው ማን ይሆን?!
ነገሥታትንና መሪዎችን በአደባባይ የሚገጥሙ፣ ስለ ክፋታቸው፣ ኃጢአታቸውና በደላቸው ፊት ለፊት የሚገሥጹ፣ ስለ እውነትና ፍትሕ የሚቆሙ መንፈሳዊ ዐርበኛ የኾኑ ባህታውያን ዮሐንሶች ወዴት አሉ?!፣ ሕዝብን ከአስጨናቂው የፈረዖን አገዛዝ ነፃ የሚያወጡ፣ በሕዝባቸውና በወገናቸው ፍቅር የነደዱ የዘመናችን ሙሴዎችስ አድራሻቸው ወዴየት ነው?!፣ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ዕንባቸውን እያፈሰሱ ‹‹አቤቱ የኾነብንን አስብ፣ ስለ ቅዱስ ስምህ ስትልም ዘመናችን አድስ!›› የሚሉ ኤርምያሶችን ከወዴት እናገኝ ይሆን በማለት ብዙዎች በተማፅኖ ዕንባቸውን እንደ ራሄል ወደ ጸባዖት፣ ወደ አርያም እየረጩት ነው፡፡
ምድሪቱን በከደነው በዚህ ሁሉ ዋይታ፣ ጩኸትና ሰቆቃ መካከል እጅግ ወደ ተከበረው መንፈሳዊ መንበር፣ ሥልጣንና ኃላፊነት የመጡት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በሹመታቸው ማግሥት ሙሰኝነትንና ጎሰኝነትን አልታገሥም፡፡ ይህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ የልጆቻችን ብርቱ ጩኸትና ዋይታ ወደ ጆሮዬ ደርሷል እናም ጊዜው የለውጥ ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች፣ መንፈሳዊ አገልጋዮችና ልጆቻችን ጋር በመሆን ለለውጥ እንሠራለን፣ እንደክማለን በማለት የብዙዎችን ልብና ስሜት ከፍ አደርገውት ነበር፡፡ በዚሁ መንፈሳዊ ቆራጥነትና ትጋትም የተወሰዱ የብዙዎችን ልብ በተስፋና በሐሤት የሞሉ አንዳንድ የለውጥ ዕርምጃዎችም ነበሩ ማለት ይቻል ይመስለኛል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ቅዱስ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተንሰራፋውን የጎጠኝነትና የሙሰኝነት ችግሮች መኖራቸውን አምነው መቀበላቸው አንድ የለውጥ ዕርምጃ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ‹‹በቅጡ ተለይቶ የታወቀ ችግር በከፊል እንደተፈታ ይቆጠራል፡፡›› እንዲሉ፡፡ ሲቀጥልም ፓትርያርኩ እነዚህ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን በትክክል ለይቶ ከማስቀመጥና ባለፈም ተግባራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የለውጥ ዕርምጃው በአምላካችን ረዳትነት ፍሬ እንዲያፈራ እናደርጋለን በማለት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ለብዙዎች ብሩሕ የለውጥ ተስፋን የፈነጠቀ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ለአብነትም ያህል ፓትርያርኩና ቅዱስ ሲኖዶሱ በበዓለ ሲመትና በሌሎች ክብረ በዓላት ሰበብ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪና የተንዛዛ ድግስና ውዳሴዎች እንዲቀሩ ማድረጋቸው፣ በድግስ ሰበብና በበዓላት ሽርጉድ ኪሳቸውን የሚያደልቡ ሙሰኞችን በሩ እንዲዘጋባቸው አድርጓል፡፡ በዚህም በውድ ስጦታዎችና ገጸ በረከቶች ሰበብ፣ እጅ የመጠመዘዝ ያህል ድብቅ አጀንዳቸውንና ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚተጉና የሚሯሯጡ አስመሳዮችና ሙሰኞችም ቀኑ እንዲጨልምባቸው ኾኗል፡፡
ሌላውና በተለይም በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚገባው የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ በቤተ ክህነቱ አስተዳደር ሥራ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት፣ መንፈሳዊ ትጋት፣ በጎነትና ቅንነት የሚንጸባረቅበት ሙያዊ/ፕሮፌሽናል አሠራር እንዲኖርና ለማድረግ ከመነጋገር አንስቶ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ልጆችና ምሁራን የተሳተፉበት ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅር አደረጃጀትና የአሠራር መመሪያ ጥናት›› ሰነድ ቀርቦ ሰፋ ያለ ተከታታይ ውይይቶች የተደረገበት የዛን ሰሞኑ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ሠራተኞችና መንፈሳዊ አባቶች የተሳተፉበት ጉባኤ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ይህን የለውጥ ትግበራ ጥናት ሰነድን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ይህ ዳጎስ ያለ ጥናትም በቁጥር ጥቂት የማይባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የኾኑ ምሁራንና ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በገንዘብ ሲሰላም ቤተ ክርስቲያኒቱን በመቶ ሺኅዎች የሚገመት ወጪን ከማውጣት የታደጋት በብዙ ድካምና በብርቱ ጥንቃቄ የተዘጋጀ የጥናት ሰነድ እንደሆነ ነው አብዝቶ የተነገረለት፡፡
በዚህ የጥናት ሰነድ ላይም በየደረጃው ተከታታይ የኾኑና ውጤታማ ነበሩ ሊባሉ የሚችሉ ውይይቶች ተደርጎባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጉባኤው ላይ ይህን የመዋቅር አደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነድ በምን መልኩ ሥራ ላይ ልናውለው እንችላለን የሚለው ላይ በተነሡ አንዳንድ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የተነሳ የተለያዩ ቡድኖች ጎራ ለይተው የቃላት ጦር ሲማዘዙ፣ ሲጠዛጠዙ ታዝበናል፡፡ አሁንም የቃላት ጦርነቱ፣ መወራረፉና መጎነታተሉ እንደቀጠለ ነው፡፡ በአንፃሩም ችግሩንና ቀውሱን ከቤተ ክህነቱ ክልል በማውጣት በስውርም ኾነ በግልጽ እየታየ ያለ ሌላ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ያለው ጠንካራ ግፊት እንዳለ የሚከራከሩ ድምፆች ደግሞ እዚህም እዛም እየተሰሙ ናቸው፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚቆረቆሩ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ምሁራንን በሥሩ አሳባስቦ የያዘው ማህበረ ቅዱሳን ለዚህ የለውጥ ዕርምጃ የበኩሉን ዕገዛና ጥረት ለማድረግ ደፋ ቀና ቢልም፣ ማኅበሩ ያቀረበው የዳጎሰ የጥናት ሰነድ ሁሉንም የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪዎችና አባቶች ባስማማ መልኩ ተቀባይነት አግኝቶ የለውጥ ትግበራውን ዕውን ለማድረግ ዕንቅፋት እንደገጠመው ግን በግልጽ እየተስተዋለ ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ይህ የጥናት ሰነዱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተዛማጅ የኾኑ እንቅስቃሴዎቹም ከሰሞኑን እክል እንደገጠማቸው ሰምተናል፣ ታዝበናልም፡፡ ለአብነትም የአብነት መምህራንን በተመለከተ የጠራው አገር አቀፍ ጉባኤ መታገዱ የሰሞኑን በርካታዎችን ያሳዘነ ዜና ሆነ ማለፉን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሰሞኑን፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በባይሎጂና በኬምስትሪ ምሩቃን አትመራም፡፡›› የሚለው መረርና ከረር ያለ ውስጠ ወይራ ንግግራቸው በማኅበሩ ማንነትና አቋም ላይ ያነጣጠረና ጥርጣሬያቸውንም ገሃድ ያወጣ ንግግር እንደሆነ ነው ብዙዎች ሲናገሩ የተደመጡት፡፡
የኾኖ ኾኖ ፓትርያርኩ በአደባባይ ያወጁትንና ቃል የገቡለትን ቤተ ክህነቱን ተቋም ከሙሰኞችና ከጎጠኞች እናጻዳለን ዘመቻቸውም ኾነ ለዚሁ የለውጥ ዘመቻ ያግዛል በሚል በማኅበረ ቅዱሳን ያቀረበው የጥናት ሰነድ የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ ምን ይኾናል የሚለውን በእርግጠኝነት ለመናገር ግን አሁንም በትዕግሥት መጠበቅ የሚያስፈልግ ነው የሚሉ በርካታ ታዛቢዎች አልጠፉም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ ክህነቱ ተቋም ትልቁና ዋንኛ ችግሩ የሚጀምረው ከላይ ከመንፈሳዊ መሪዎቹ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አካባቢ መንፈሳዊ ሕይወትና መንፈሳዊ ቆራጥነት/ቅንዓት መጥፋቱ በቤተ ክህነቱ ተቋም ለተከሰተው የዚህ ሁሉ ምስቅልቅልና ቀውስ ዋንኛው ምክንያት እንደኾነ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በከፋ የሞራል ውድቀትና ዝቅጠት ውስጠ የተዘፈቁ፣ ምድራዊ ሀብትና ዝና የሚያንኾልላቸው፣ የለየላቸው ሙሰኞችና ጎሰኞች ከላይ እስከ ታች በተሰገሰጉበት የቤተ ክህነቱ ተቋም ውስጥ ለውጥን ለማምጣት መንገዱ አልጋ በአልጋ ይኾናል ተብሎ አይታሰብም፣ አይጠበቅምም፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲንከባለል የቆየ ይህ የተወሳሰበው የቤተ ክህነቱ ተቋም ችግሮች በአንድ ጀምበር ይፈታሉ ብሎ ማሰብም የዋኽነት ነው፡፡ እናም ለውጡን ዕውን ለማድረግ ከሚያስፈልገው ትዕግሥትና ቁርጠኝነት ባሻገር የክርስትና ሃይማኖት ዓምድና መሠረት የኾኑት ፍቅር፣ በጎ ሕሊና፣ ቅንነትና ታማኝት እንዲኖሩ የግድ ይላል፡፡ መሰሪነት፣ አድር ባይነት፣ አጎብዳጅነትና ግብዝነት በነገሡበትና መንፈሳዊነት ፈፅሞ እየተሰደደበት ባለበት ተቋም ውስጥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች ፍቅርና ኅብረት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ህልውና፣ የመንፈስ አንድነትና ሰላም ቀዳሚና ዋና አጀንዳ ሊኾን በተገባው ነበር፡፡
ከሁሉም በፊት ፍቅርንና መንፈሳዊ አንድነትን ለማምጣት ፈቃድም ኾነ አቅም ያነሰው የቤተ ክህነቱ ተቋም ጋሪውን ከፈረሱ በማስቀደም ጉልበቱንና አቅሙን በከንቱ እያባከነ ነው በማለት የሚተቹ ብዙዎች ናቸው፡፡ የቤተ ክህነቱ ተቋምም ኾነ መሪዎች በእውነትም ሊያሳስባቸውና ሊያስጨንቃቸው የሚገባው ቀዳሚው ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አንድነትና ሰላም መሆን ነበረበት፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች ወይም የቤተ ክህነቱ ተቋም ወሳኝና ቀዳሚ አጀንዳ የአንድ ሰሞን ብቻ ወሬና ግርግር ኾኖ ማለፉና አሁን አሁን ደግሞ ከእነ መፈጠሩም የመረሳቱ ነገር ለመኾኑ መቅደም ያለበት የትኛው ነው ‹‹ሰላምና አንድነት ወይስ …›› የሚል ጥያቄን በተደጋጋሚ እያስነሳ ነው፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአንድነትና የሰላም ጉዳይ የሚያሳስባቸው በርካታዎችም የፓትርያርኩም ኾነ የቤተ ክህነቱ ተቋም የለውጥ እንቅስቃሴ የቤቱ መሠረት ተነቃንቆ እያለ ጣርያውና ግድግዳው እንዳይፈረስ ከሚታገል የዋኽ ሰው ጋር በማመሳሰል የሚያቀርቡ ታዛቢዎች አልጠፉም፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ኾኖ በማያውቅ ለሦስት ተከፍላ፣ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ፣ ሕጋዊው ሲኖዶስ፣ ገለልተኛ በሚል የተለያዩ፣ የተከፋፈሉና ተገለባባጭና አድር ባይ የኾኑ ፖለቲከኞች እንደሻቸው የሚጠመዙዟቸው አባቶች ልዩነታቸውን በሰላም ፈተው ወደ አንድነት መምጣት እስካልፈቀዱ ድረስ፣ ለቤተ ክህነቱ የምንመኘው እውነተኛውና ተግባራዊው ለውጥ ህልም ነው ሲሉ አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ ዛሬ ከዳር እስከ ዳር መነጋገሪያ የኾነው ሙሰኝነትም ኾነ ጎጠኝነት የቤተ ክህነቱ ለገባበት ቀውስና የሞራል ውድቀት አንድ ወይም ጥቂቱ መገለጫ እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ችግር ጥልቅ፣ የተወሳሰበና ዕድሜ ጠገብ ነው፡፡ መፍትሔውም ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም ግድ የሚላቸው፣ ለእግዚአብሔርና ለቤቱ መንፈሳዊ ቅንአት ያላቸው መንፈሳዊ መሪዎች እንዲኖሩና እንዲበዙ መጸለይና መሥራት ነው፡፡  
የፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ሙሰኞችንና ጎጠኞችን የማጥራት ዘመቻው ፍሬያማ እንዲኾንና ለዚሁ የለውጥ ዘመቻ ትግበራም ያግዛል ተብሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች/ምሁራን የቀረበው የጥናት ሰነድ ተግባራዊ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ መቅደም ያለበት አማራጭ ይህ ነው ሲሉም ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም ይላሉ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፣ የቤተ ክህነቱ ተቋም ማስቀደም ያለበት ዋነኛው ዕርምጃ መሆን ያለበት መንፈሳዊነትን ያስቀደሙ የእግዚአብሔርና የቤቱ ቅናት የሚያቃጥላቸው፣ መመሪያቸውና መለያቸው ፍቅር የኾነ፣ ሰላምንና ዕርቅን የሚሰብኩ፣ ለእውነትና ለፍትሕ የቆሙና የሚከራከሩ መሪዎችና አባቶች እንዲኖሩና እንዲበዙ መሥራትና መትጋት የግድ ይላል በማለት አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
እነዚህ ትችቶች፣ መከራከሪያዎችና አስተያየቶች እንዳሉ ኾነው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የጀመሩት የቤተ ክህነቱን ተቋም ከሙሰኞችና ከጎጠኞች የማፅዳት ዘመቻቸውን አጥብቀው እንዲገፉበት የሚመኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን ድምፅ አሁንም ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ በመጨረሻ አንድ ነገር ለማለት እወዳለኹ፡፡ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፕትርክና ዘመናቸው የተከፋፈለችውን ቤተ ክርስቲያን አንድነት በማስጠበቅ፣ የቤተ ክህነቱን ተቋም ከሙሰኞች፣ ከአስመሳዮችና ከጎጠኞች የፀዳች በማድረግ አዲስ ታሪክ ያስመዘግቡ ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡

1 comment:

  1. Heya i'm for the first time here. I found this board and I find It really useful & it helped me out a lot. I hope to give something back and help others like you helped me.





    ranjang pasien

    ReplyDelete