Saturday, 15 March 2014

የድሬዳዋ ምእመናን በጥረታቸው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ አስከበሩ! የቅ/ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሒሳብና የግንባታ ጥራት ምርመራ እንዲዘገይ ኹለት ጊዜ ያዘዙት ፓትርያርኩ ምርመራው እንዲቀጥል መመሪያ ሰጡ! መዝባሪዎቹ ምርመራውን ለሦስተኛ ጊዜ ለማስተጓጎል በአዲስ አበባ ይገኛሉ


  • ምርመራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተባርኮ ታቦቱ ከመግባቱ በፊት ይከናወናል
  • የጠ/ቤ/ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ከምእመናኑ ጥረት ጎን በመቆም ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል
  • በሀ/ስብከታቸው አስተዳደር ጣልቃ መገባቱን ሊቀ ጳጳሱ ለቋሚ ሲኖዶስ አባላት አስታውቀዋል
  • መዝባሪዎቹ ‹‹አንመረመርም›› በሚል በሊቀ ጳጳሱና በደብሩ አስተዳዳሪ ላይ እየዛቱ ናቸው
  • የጠ/ቤ/ክቱ ምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ኢ/ር ሰሎሞን ካሳዬ ብቃት እንዲመረመር ተጠይቋል
Private Secretariat office of His Holiness on D.D.Gab Audit Row
ፓትርያርኩ በተሟጋች ምእመናን ጥያቄ ምርመራው እንዲቀጥል ያዘዙበትና የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ያስከበረው ደብዳቤ
ለቤተ ክርስቲያናችን የታቀደውን የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥረት የሚቃወሙ አማሳኝና ጎጠኛ አስተዳዳሪዎችና ተባባሪዎቻቸው በእብሪትና በስሜታዊነት ሲለፍፉ እንደሰነበቱት፣ ምእመኑ የሚሰጠውን ሰጥቶ ዘወር ማለት አለበት እንጂ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሚያገባው ነገር የለም፤ በእነርሱ እምነት ‹‹ነጠላ ለባሽ›› አቶና ወይዘሪት የሚያጠኑት ጥናትና ድጋፍ ሰጭ ጥረቶቻቸው ኹሉ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም አይደለም፤ እንዲያውም ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባላት እንጂ አካላት አለመኾናቸው ታውቆ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ሊተላለፍበት ይገባል፡፡››
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ግን፣ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንና በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌዎች ለጾታ ምእመናን ከተሰጠው ድርሻ አንጻር ይህ ዐይነቱ የአማሳኞች የእብሪት አነጋገር ቦታ እንደሌለው የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ የተሟጋች ምእመናን ቡድን በተግባር አረጋግጠዋል!!
በሚልዮኖች የሚቆጠር የምእመናን ገንዘብና ንብረት በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ለምዝበራ የተጋለጠበትና ከውለታ ጊዜው በላይ በእጅጉ የዘገየው የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ጥራት እንዲመረመር በቋሚ ሲኖዶሱ የተላለፈውን ውሳኔ በመጋፋት፣ ምርመራው ቤተ ክርስቲያኑ ተባርኮ ታቦተ ሕጉ እስኪገባ ድረስ እንዲዘገይ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ያስተላለፈውን ትእዛዝ በጽናት ሲቃወሙ የቆዩት ምእመናኑ፣ ጥረታቸው ሠምሮና ተቀባይነት አግኝቶ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ምርመራው እንዲቀጥል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ ተሰጥቶላቸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ምርመራው እንዲቀጥል መመሪያውን ለመስጠት የተገደዱት÷ ከድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤት፣ የስብከተ ወንጌል እና ልማት ኮሚቴዎች የተውጣጡ 12 አባላት ያሉት የተሟጋች ምእመናን ቡድን በመንበረ ፓትርያርኩ በአካል ተገኝተው ጉዳዩን ለቅዱስነታቸውና ለሚመለከታቸው አካላት ኹሉ በሚገባ በማስረዳት ባደረጉት ጥረት ነው፡፡
ተጋድሎውን በ፳፻፫ ዓ.ም. የጀመረውና በመላው ምእመን የሚደገፈው ተሟጋች ቡድኑ ከየካቲት ፳፬ – መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርኩ ባደረገው ቆይታ፣ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ስም በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሊቀ መንበርና የጥቅም አጋሮቻቸው የተፈጸመውንና በምርመራ የተረጋገጡ ጉድለቶችን በማስረጃ አስደግፎ ማጋለጡና ማስረዳቱ ታውቋል፡፡
pvt sec office of His Holiness 03
ፓትርያርኩ በመዝባሪዎች የተሳሳተ መረጃ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመጋፋት ምርመራው እንዲዘገይ ያዘዙበት ደብዳቤ
የሕንፃ ሥራው የገቢና ወጪ ሒሳብ እንዲኹም የግንባታ ጥራቱ ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች መመርመር ያለበት ቤተ ክርስቲያኑ ተባርኮ ታቦተ ሕጉ ከመግባቱ በፊት መኾን እንደሚገባው የተከራከሩት ምእመናኑ፣ ‹‹ምርመራው በማንኛውም ጊዜ ሊካሔድ ይችላል›› በሚል ለማዘግየት የሚደረግ ጥረት አንድም ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚጥስ በሌላም በኩል መዝባሪዎቹንና ተባባሪዎቻቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን የሚደረግ ሙከራ ነው ብለዋል፡፡
ሒሳቡን መመርመርና የግንባታ ጥራቱን ማረጋገጥ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ሥራ ከማቀላጠፍ ጎን ለጎን ሊፈጸም እንደሚችል የገለጹት የተሟጋች ቡድኑ አባላት፣ የሕዝብ ገንዘብ እንዲመረመር የሚያደርጉት ጥረት ግንባታውን በማጓተት ቀውስ ለመፍጠር ከመሻት ጋራ ፈጽሞ ሊያያዝ እንደማይገባውና ይህ ፍላጎት፣ ግንባታውን በማጓተት ሕገ ወጥ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚማስነው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሊቀ መንበርና የጥቅም ተጋሪው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ለምርመራው ዝግጅት እንዲደረግ ለደብሩ አስተዳደር መመሪያ የሰጡበት ደብዳቤ
ተሟጋች የምእመናን ቡድኑ ባቀረቧቸው ማስረጃዎችና በሰጧቸው ማብሪራሪያዎች ላይ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ከቋሚ ሲኖዶስ አባላትና ከሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ጋራ ውይይት መደረጉ ተገልጧል፡፡ በውይይቱ ላይ ብፁዕነታቸው በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት የሕዝብ ገንዘብ እንዲመረመር አማካሪ ድርጅት በግልጽ ጨረታ ተለይቶ ሥራው እንዲጀመር መመሪያ ቢሰጡም የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ለመዝባሪዎች በማድላትና ጥያቄያቸውን በመቀበል ከአንድም ኹለቴ በጻፈው ምርመራው እንዲዘገይ የሚያዝ ደብዳቤ ሳቢያ መጓተቱት አስረድተዋል፤ ድርጊቱንም በጣልቃ ገብነት ኮንነዋል፡፡
የተሟጋች ቡድኑን ድካም መና ለማስቀረት በአዲስ አበባ የሚገኘው የሕንፃው ተቋራጭ ኤፍሬም ተስፋዬና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ አቶ ሰሎሞን ካሳዬ በድሬዳዋ ኾኖ ከሚፎክረው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ብርሃኔ መሐሪ ጋራ በመተባበር የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እገዛ ቢሚፀኑም እንዳልተሳካላቸውና ‹‹አሳሳቾች›› ተብለው በልዩ ጽ/ቤቱ ሓላፊ አቡነ ገሪማ መባረራቸው ተጠቁሟል፡፡
በውጤቱም ፓትርያርኩ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል በሰጡትና በቁጥር ል/ጽ/299/66/2009 በቀን 2/7/2006 ዓ.ም. በወጣ መመሪያ መሠረት÷ የሕንፃው የገቢና ወጭ ሒሳብና የግንባታው ጥራት ምርመራ ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ መሠረት በገለልተኛ ኦዲተርና በመንግሥት የሥራና ከተማ ልማት ባለሞያዎች እንዲጣራ፣ ቀሪው የሕንፃ ግንባታም ጎን ለጎን እንዲጠናቀቅ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ይኸው መመሪያ የተላለፈበት የፓትርያርኩ ደብዳቤ ጥር 9 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥር ል/ጽ/114/66/2006 እና የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥር ል/ጽ/263/2006 ዓ.ም. ምርመራው ቤተ ክርስቲያኑ ተባርኮ ታቦቱ ከገባ በኋላ እንዲካሔድ የሰጡት ትእዛዝ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ያላገናዘበ መኾኑን በግልጽ ከማስቀመጡም በላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖረውም ተመልክቷል፡፡
ተሟጋች ምእመናኑ ጉዳያቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ለማስረዳት ያደረጉትን ጥረት ከመደገፍ ጀምሮ መመሪያ የተሰጠበትን የፓትርያርኩን ደብዳቤ በማርቀቅ ረገድ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊ መ/ር ኤርሚያስ ተድላ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተገልጦአል፡፡
ዋና ሓላፊው፣ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔና በሐምሌ ወር ፳፻፫ ዓ.ም. የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያው በኦዲት ቡድኑ ባደረገው ማጣራት ከደንብና አሠራር ውጭ ከ1.8 ሚልዮን ብር በላይ ለተቋራጭ ክፍያ እንደተፈጸመ የተረጋገጠበትን ሪፖርት መሠረት በማድረግ በጉዳዩ ተጠያቂ የኾኑት አካላት አስተያየት ውድቅ ተደርጎ የምእመናኑ አቤቱታ ተቀባይነት ማግኘት እንዳለበት ለፓትርያርኩና ለልዩ ጽ/ቤታቸ ማብራሪያ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡
ከዚኹ ጋራ በተያያዘም ያለበቂ ጥናት በተካሔዱና እየተካሔዱ በሚገኙ የቤተ ክህነቱ የግንባታ ፕሮጀክቶች የደረሱትንና በመድረስ ላይ ያሉትን ብክነቶችና ምዝበራዎች በመጥቀስ ፕሮጀክቶቹን በዘፈቀደ በማጽደቅ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ኾነዋል የተባሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ኢ/ር ሰሎሞን ካሳዬ ብቃትና በግለሰቡ ብቻ የሚመራው የዘርፉ የግንባታ ቁጥጥር አግባብነት እንዲገመገም በዋና ሓላፊው መጠየቁ ተገልጦአል፡፡
ምንጮች እንደሚያስረዱት፣ ፓትርያርኩ በአማካሪነት ካስጠጓቸውና ለስሕተቶቻቸውም ተጠያቂ ከሚደረጉት ግለሰቦች አንዱ የኾኑት ኢ/ር ሰሎሞን ካሳዬ፣ በመንግሥት የሥራና ከተማ ልማት መሥ/ቤት ባልደረባ የነበሩ፣ በአቅም ማነስና ሙስና ከመባረራቸውም በላይ በየትኛውም ተቋም በሞያቸው እንዳሠሩ እገዳ የተጣለባቸው ናቸው፡፡
ፓትርያርኩ ምርመራው እንዲቀጥል የሰጡት ትእዛዝ እንደተሰማ፣ በድሬዳዋ የሚገኘው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ‹‹የተጻፈልኝን ደብዳቤ ማንም አያሻራትም›› በሚል የደብሩን አስተዳዳሪና የሀ/ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ከሓላፊነታቸው የሚያሥነሳበትን ደብዳቤ ይዞ እንደሚመጣ በተመልካቾች ፊት ከመዛቱም ባሻገር ትእዛዙን ለማስገልበጥ ከኻያ ሺሕ ብር በላይ ወጭ ከሕንፃ ኮሚቴው ገንዘብ አውጥቶና የሐሰት የአቤቱታ ፊርማ አዘጋጅቶ ወደ አዲስ አበባ መጓዙ ተሰምቷል፡፡ ይህ መረጃ በሚጠናቀርበት ሰዓትም ግለሰቡ በአዲስ አበባ እንደሚገኝ የተመለከተ ሲኾን ምርመራው እንዲቀጥል በፓትርያርኩ የተላለፈውን ትእዛዝ በለመደው መንገድ ያስገለብጠው እንደኾነ በቅርበት የምንከታተለው ይኾናል፡፡
የድሬዳዋ ሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግንባታ በዕሥራ ምእቱ መባቻ ከተገባለት የውለታ ጊዜ ውጭ ለስድስት ዓመት የተጓተተና በውል ስምምነት ተይዞ ከነበረው ሦስት ሚልዮን ብር በላይ በሚልዮኖች የሚገመት የምእመናን ብርና የዐይነት አስተዋፅኦ ለዝርፊያ የተጋለጠበት እንደኾን ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በአዲስ አበባስ??
ከዘገባው እንደምንረዳው በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችን የሚያሸማቅቁት ብልሹ አሠራር የሚመቻቸውና ይኸው ብልሽት በግልጽነትና ተጠያቂነት መርሕ እንዳይታረም የሚሹ አማሳኞች ብቻ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ለቤተ ክርስቲያናችን የታቀደው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት በዐጸደ ሥጋም በዐጸደ ነፍስም ያሉ በርካታ ምእመናን የጸሎት ውጤትና የቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ለመቃረቡ ምልክት መኾኑን ማኅበረ ምእመናንና ሌሎችም የተቋማዊ ለውጥ ኃይሎች ከመናገራቸውም በላይ ዓይናቸው፣ ጆሯቸውና ልባቸው በለውጡ ተግባራዊነት ላይ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

ፓትርያርኩም የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጡን ተግባራዊ በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከብዝበዛ እንዲያድኑ ማኅበረ ምእመናኑ በእንባ ጭምር ተማፅነዋቸዋል፡፡ ንግግር፣ ገለጻና ተማኅፅኖ ግን ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው እንደ ድሬዳዋ ምእመናን በጽናት የሚዘልቅ፣ በተግባር የታገዘ ኹለንተናዊ መተባበር ሲኖር ነው፡፡
በአኹኑ ወቅት የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተቃዋሚዎች ለውጡን በመደገፍ የተንቀሳቀሱ አስተዳዳሪዎችን ‹‹ጥናቱ ከሽፏል፤ የት ትገባላችኹ!›› በሚል ከማስፈራራትም አልፈው የጥናት ሰነዱን ዳግመኛ እንዲገመግሙ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስም ከተሠየሙትና በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ዙሪያ በአማካሪነት ስም ከከተሙት የሙስና ጌቶች ጋራ ጥዋት ማታ ጥብቅ ግንኙነት ፈጥረው ይታያሉና ምእመኑ ሒደቱን በንቃት በመከታተል እንደ ድሬዳዋ ምእመናን የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የማስከበር ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment