Monday, 24 March 2014

‹‹ፓትርያርኩ ይደግፉናል መንግሥት ያግዘናል›› ያሉ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞች ማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ሀብትና ንብረቱ ታግዶ በፀረ ሽብር ሕጉ መሠረት እርምትና ርምጃ እንዲወሰድበት ጠየቁ



  • በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ያልታወቀውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የአዳራሽ ፈቃድ የተነፈጋቸው አማሳኞቹ ትላንት መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ረፋድ ላይ ተጀምሮ እስከ እኩለ ቀን በዘለቀው ስብሰባቸው፣ በሌላቸው ሕጋዊነትና ውክልና ‹‹የአዲስ አበባ አገልጋዮች ማኅበር›› መሥርተው ማኅበረ ቅዱሳንን መቃወማቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
  • ‹ውሳኔያቸውና የአቋም መግለጫቸው› ተቀባይነት አግኝቶ ተፈጻሚ ካልኾነና የማስወጣት ርምጃ ከተወሰደባቸው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቃውሟቸውን ለማጠናከር የዛቱ ተሰብሳቢዎችም አሉባቸው! - ‹‹ከዚኽ እንኳ ቢያስወጡን መንግሥታችን ቸር ነው፤ ቦታ ተቀብለን የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን ሠርተን ለምን አንቀጥልም?››
  • የአቋም መግለጫቸውን በተለያዩ መሸኛዎች አዘጋጅተው ከሚያደርሷቸው አካላት መካከል÷ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የመ/ፓ/ጠ/ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ለየብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚገኘበት ሲኾን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡
  • ፓትርያርኩየተዘጋባቸው አዳራሽ እንዲከፈትላቸው ከማዘዝ ጀምሮ በተቃውሟቸው ሳቢያ ከሥራቸው እንደማይፈናቀሉና መፍራት እንደሌለባቸው በመግለጽ አበረታተውናል ያለው ኃይሌ ኣብርሃ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በፊዚክስና ኬሚስትሪ አትመራም›› በማለት በአንድ ስብሰባ ላይ መናገራቸው እነርሱን ለማበረታታት መኾኑን በመጥቀስ አወድሶላቸዋል፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅም በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ደብዳቤ ለመጻፍ በመድፈራቸው ‹‹ልናደንቃቸው ይገባል›› ብሏል፤ ደብዳቤዎቹም በንባብ ተሰምተዋል፡፡
*   *   *
  • ማኅበረ ቅዱሳን ‹‹በሀገር አቀፍ ደረጃ ንጹሕ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለአድማ በማነሣሣት በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከትና ሽብር እንዲፈጠር ሰላም እንዲደፈርስ ያደርጋል›› ያሉትና የደኅንነቱ ኃይል በእጃቸው እንደኾነ የተናገሩት አማሳኞቹ እርስ በርሱ በሚምታታውና በሚገባ ባልተደራጀው መግለጫቸው፣ ‹‹መንግሥት ለሽብር ተግባር እንደሚውል ዐውቆ በፀረ ሽብር ሕጉ ታሳቢነት ማኅበሩ በገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ስም ከምእመናን በሚሰበስበው ዓሥራት በኩራት ያፈራውን ጠቅላላ ሀብትና ንብረት ቁጥጥር በማድረግ የተለመደ እገዛው እንዳይለየን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤›› ብለዋል፡፡
  • አማሳኞቹ በቅ/ሲኖዶስ በኩል ለሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲተላለፍላቸው የጠየቁት የጠቅላላ ሀብትና ንብረት እገዳ ደብዳቤ ደግሞ÷ ት/ቤቶች፣ ሕንፃዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች፣ የአክስዮን ተቋማትና የባንክ አካውንቶች የሚመለከት ነው፡፡ አማሳኞቹ ከቀደመው ንግግራቸው ጋራ በሚጋጭ አኳኋን እንደተናገሩት፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሀብቶችና ንብረቶች ምንጭ አይታወቅም፤ ባለቤትም የላቸውም፤ ኦዲት ተደርገውም አያውቁም፤ ዓመታዊ ሪፖርት አቅርቦ አያውቅም፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሞዴልም ተገልግሎ አያውቅም፡፡
  • በቅ/ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት ለዓላማው ተግባራዊነት በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው የሚራዱ አባላት ያሉት ማኅበረ ቅዱሳን እንደየገቢያቸው መጠን በየወሩ ቢያንስ ከመቶ አንድ እጅ(1%) የአባልነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ አባላት አሉት፤ ለማኅበሩ አገልግሎት አስፈላጊ የኾኑ አዳዲስ የልማትና ተራድኦ ተቋማት እንዲቋቋሙ ወይም እንዲዘጉ የመወሰን ተግባርና ሓላፊነት ያለው የሥራ አመራር ጉባኤ አለው፡፡
  • ማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ዕቅድ ዝግጅቱንና የአፈጻጸም አጠቃላይ ዘገባውን በየስድስት ወሩ አንድ ጊዜ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያቀርባል፤ በዘመናዊ የፋይናንስ አሠራርና የንብረት አስተዳደር መመሪያ የያዘውን የአባላቱን ሀብት አጠቃቀም በተመሰከረለት የውጭ ኦዲተር ያስመረምራል፤ የኦዲት ሪፖርቱንም በየዓመቱ ያቀርባል፤ መመሪያም ይቀበላል፡፡
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የነጠላ ሒሳብ ሥርዓት አዝማናት የተሻገሩትና ከማንኛውም የአካውንቲንግ ሶፍትዌሮች ጋራ የማይጣጣም ከሊትሬቸሩም የጠፋ ነው፤ ለቁጥጥር የሚያመች የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር መመሪያ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አልተተከለም፤ ሞዴላሞዴሎቹ ምስጢራዊ ኅትመት (security features) የሌላቸው፣ የሀብት፣ ንብረትና ዕዳ መጠን በተመለከተ ተፈላጊውን መረጃ የማይሰጡ በምትኩ ለአማሳኞች ማጭበርበርያ አመቺ ኾነው እንዳሉ በተለያዩ መድረኮች ሲገለጽ የቆየ ነው፡፡
  • ከዚኽ አኳያ የማኅበሩ ጥያቄ ቤተ ክህነቱ አይቆጣጠረኝ ሳይኾን ለቁጥጥር አመች(audit-able) የኾነ ነባራዊ ኹኔታ(ለምሳሌ፡- ጠቅ/ቤተ ክህነቱ ኅትመቱን የፈቀደውና ቁጥሩን የመዘገበው፣ ከሒሳብ ሥርዐቱ ጋራ የሚስማሙ ደረሰኞች ኅትመት) የመፍጠር ጥያቄ እንደኾነ በየጊዜው እንደሰጣቸው የሚታወቁ ገለጻዎች ሰሚ ጆሮ አስተዋይ አእምሮ ቢያገኙ መልካም ነው፡፡
  • በስተቀር የማኅበሩ አባላት በድካማቸው ያፈሩትን ሀብት ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ እንጂ የማይቀበሉ (አማሳኞቹ እንዳሉት የዓለም የኑሮ ውድነት አባሯቸውና መንግሥት የሚከፍላቸው ደመወዝ አላረካ ብሏቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርገው የገቡ) እንዳልኾኑ፣ ማኅበረ ቅዱሳንም በማዕከላዊ የቤተ ክህነት መዋቅር ውስጥ ኾኖ የድርሻውን በመወጣት ላይ የሚገኘው፣ በአባቶች የታመነበትን ክፍተት የመሙላት አገልግሎቱን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመከታተል እንደኾነና ይህን የአገልግሎት ድርሻውን ለመወጣት በበጎ ፈቃድ የተሰበሰቡ አባላቱ ማኅበር በመኾኑ ለሥራው የሚመደብለት በጀት ይኹን ከእርሱም የሚጠበቅ የገቢ ፈሰስ እንደሌለ ሊያዝ ይገባል፡፡
*   *   *
  • መንግሥት ባጋመስነው የ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት በትኩረት እረባረብበታለኹ በሚል በያዘውና በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር አስተባባሪነት እንደሚመራ በገለጸው የፀረ አክራሪነት ዕቅድ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በማኅበራት ጥላ ሥር ይካሔዳል ያለውን ‹የአክራሪነት አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ› የምዝገባ፣ የክትትልና የመረጃ ሥርዐቱን አጠናክሮ የፋይናንስ ዝውውራቸውንና አጠቃቀማቸውን ግልጽነት በማረጋገጥ እንደሚፈተሽ አስፍሯል፡፡
  • የፀረ አክራሪነት ትግል አስተዳደራዊና የጸጥታ ሥራ ብቻ ሳይኾን ቁልፍ ፖሊቲካዊ ትግልም እንደኾነ የሚገልጸው መንግሥት፣ ፖሊቲካዊ ትግሉ የሴኩላር መንግሥትን ሚና ጠብቆ በንቃት ሊመራ እንደሚገባውና ከዚኽ አኳያ በገዛ መዋቅሩ ውስጥ መሽገው የትግሉን አቅጣጫ የሚያስቱ፣ የሚያደበዝዙና ሽፋን የሚሰጡ፣ የሕዝብን እይታ የሚያዛቡና ለተለያዩ ጥርጣሬዎች መንገድ የሚከፍቱ ያላቸው የመንግሥትና የድርጅት አካላትና አባላት ቁመና መፈተሽ እንደሚገባው ያሳስባል፡፡
  • እናስ? የቤተ ክርስቲያናችን ማኅበራት አፈራረጅ ይቆየንና ከእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ጋራ ጥብቅ ቁርኝት ፈጥረው በመንቀሳቀስ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ የሚሰናከልበትን አሻጥር እየሠሩ የሚገኙት አማሳኞቹ እነ ኃይሌ ኣብርሃ ‹‹በእጃችን ናቸው›› ያሏቸው ‹‹የቤተ ክህነት ደኅንነቶች›› የትግሉ አያያዝና የቁመና ጥራት መፈተሽ አይኖርበትምን?
*   *   *
  • አማሳኞቹ ተጽዕኖ ለመፍጠር አልመው እንዳስወሩት፣ ፓትርያርኩ በስብሰባው ላይ ባይገኙም ቅዱስነታቸው የቅ/ሲኖዶሱን ጽ/ቤት እና የሌሎች ብፁዓን አባቶችን ምክር ወደ ጎን በማለት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አዳራሽ ሓላፊ ቀጥተኛ የቃል ትእዛዝ በማውረድ ለአማሳኝ ተቃዋሚዎች ቁልፍ እንዲሰጥ በማድረግ ነበር ስብሰባው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብሰባ አዳራሽ የተካሔደው፡፡
the corrupt parish head haile abreha
በልማታዊነት ስምና በእልቅና ካባ በሚልዮኖች የተመዘበሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ሀብት (ከደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ብቻ 13.3 ሚልዮን ብር መኾኑ ተጠቁሟል) ፣ የግል ሚኒባስ፣ የግል መኖሪያ ቤቶች ይዞታና ድልብ የባንክ ተቀማጭኽ ጉዳይ ይቆየንና በ1.3 ሚልዮን ብር የተገዛውና በወር 70‚000 ብር የኪራይ ገቢ የሚገኝበት ሲኖ ትራክ ገልባጭ መኪና ባለቤትነትኽ ምንጩ ምን ይኾን?
  • እነኃይሌ ኣብርሃ ባስተባበሩትና በዘካርያስ ሐዲስ በተመራው ቅጥፈትና ያላዋቂነት እብሪት (arrogance of ignorance) በተሞላበት ስብሰባ ከተገኙት በደግ ግምት 200 ያኽል በሚኾኑ ተሰብሳቢዎች መካከል ኹለቱን ቀንደኛ አማሳኞች ጨምሮ አስተዳዳሪዎቹ ስምንት ብቻ ናቸው፡፡
  • ከ169 በላይ በኾኑ የሀገረ ስብከቱ ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት ካሉ 14 ሺሕ ያኽል ሠራተኞች መካከል አማሳኞቹ በጎጥና ጥቅም ከሳቧቸውና በሥልጣናቸው ካስፈራሯቸው በቀር የተገኙት አስተዳዳሪዎችና አጠቃላይ ተሳታፊዎች ቁጥር ማነስ አማሳኞቹን ክፉኛ አሳስቧቸዋል፡፡
  • ኹኔታውም አንዱ ተናጋሪ ‹‹ሴት ያወጣውን ሕግ አንቀበልም›› እንዳለው ሳይኾን የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ትግበራው እንዲፋጠን እየተጠየቀ ያለውና 96 በመቶ የሀገረ ስብከቱን ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች የተረጋገጠ ድጋፍ ያስገኘው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ሰፋኒነትና ኃያልነት የተመሰከረበት ኾኗል፡፡
  • የሕግና የሥርዓት ምንጭ የኾነችውን ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሚመራው ቤተ ክህነታችን ባለቤት የሌለው ይመስል የግለሰቦችና ቡድኖች መፈንጫ መምሰሉ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ተሻሽሎ ማየት የማይሹ አማሳኞች መንበረ ፓትርያርኩን ከበው የፓትርያርኩን የለውጥ ተነሣሽነት ሲያግቱት ማየቱም ያስቆጣል፡፡ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔዎች የማስፈጸም ሓላፊነት ያለበት ቋሚ ሲኖዶስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአጠቃላይ እየኾነ ያለውን ነገር በዝምታ ሊያዩት አይገባም፡፡ በሃይማኖት ተቋማት ለልዩነት፣ ግጭትና ቅስቀሳ ምቹ ኹኔታዎች እንዳይፈጠሩ እሠራለኹ የሚለው መንግሥትም ነገሩን በጥንቃቄ ሊያጤነው ያስፈልጋል፡፡

No comments:

Post a Comment