መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሹመት ገ/እግዚአብሔር
በደሴ ማእከል ከወረኢሉ ወረዳ ማእከል
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በወረኢሉ ወረዳ የምትገኘው የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች ተመዘበረች፡፡
የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከወረኢሉ ከተማ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከጧቱ 4፡00 ሰዓት ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ንዋየ ቅድሳቷ የመዘረፍና የመውደም አደጋ ደርሶባታል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው የቤተ ክርስቲያኒቱን በርና መስኮት ሰብሮ በመግባት ሲሆን፤ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የቅዳሴ መጽሐፍ ባለምልክቱ፣ ሰባት የቤተ ክርስቲያን መጋረጃ፣ ሰባት መቋሚያ፣ ሦስት ምንጣፍ እና አምስት መሶበ ወርቅ ተሰርቋል፡፡ ትልቅ የመፆር መስቀል እና የእጅ መስቀሎች የተፈላለጡ ሲሆን መንበሩ ተገነጣጥሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗንና መንበሩን ሳርና ስዕለ አድህኖ በመሰብሰብ ለማቃጠል የተደረገው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
መጽሐፈ ክርስትና፣ ሥርዓተ ተክሊልና መጽሐፈ ግፃዌ ሙሉ በሙሉ ተቀዳደው፤ ሻኩራ፣ ፃህል፣ እርፈ መስቀል፤ ሻማዎች፣ የተቀጠቀጡ አንድ ሺህ ጧፎች፤ አስር ኪሎ እጣን፤ ጥላዎች ተቀዳደው፤ 15 ባለ መስታወት ፍሬም ስዕለ አድህኖዎች ተሰባብረው፤ ከፍሬም ውጭ የሆኑ 88 ስዕለ አድኅኖዎች ተቀዳደው ጫካ ውስጥ የተጣሉ ሲሆን፤ መቋሚያዎችና አምፖሎች ከነማቀፊያቸው ተሰባብረው ገደል ውስጥ ተጥለዋል፡፡ 6 ትላልቅ ሥዕለ አድኅኖዎችም ተቃጥለዋል፡፡
ይህንን ልብ የሚያደማና የሚያሳዝን ድርጊት የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ቦታው ድረስ በመሄድ የተመለከቱ ሲሆን፤ ድርጊቱን የፈፀሙትን ወንጀለኞች ለመያዝ የወረዳው ፖሊስ አስፈላጊውን ክትትልና ምርመራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በግራኝ አህመድ ከመቃጠሏና ከመውደሟ በፊት “ቀርቀሬ ማርያም” በሚል ስያሜ ትጠራ የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ጦር ሜዳ በሔዱ ጊዜ “ያገሬ ታቦት ወይ በይኝ፣ ከዚህ ጦርነት በሰላም ከመለሺኝ ስመለስ ስዕለቴን አገባለሁ” ብለው በመሳላቸውና ሥዕለታቸውም በመድረሱ ሲመለሱ “ወይብላ ማርያም” በሚል ስያሜ እንደተጠራች ይነገራል፡፡ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗ እንደገና ታንፆ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበረች፡፡
No comments:
Post a Comment