- ‹‹ቅዱስነትዎ÷ ይህን ታላቅ ሓላፊነት ሲቀበሉ ቅ/ሲኖዶስ አዲስ ዋና ጸሐፊ፣ አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ሰጥዎታል፤ መምከር ያለብዎ ከእነርሱ ጋራ ነው፤ ከዚያም ካለፈ ከቋሚ ሲኖዶሱ ነው፤ አስፈላጊ ከኾነም ጠቅላላው ጉባኤው ይሰበሰባል፡፡ እርስዎ ግን ወርደው ከማን ጋራ ነው እየተማከሩ ያሉት?››
- ‹‹በአገራችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመላው ኢትዮጵያ ሲያገለግሉ ከየት መጣኽ አልተባባሉም፤ ከሥራ ወንድምችዎ ጋራ ከየት መጣኽ ሳንባባል በአንድነት እየተመካከርን ነው ማገልገል ያለብን፤ ከዚያ ወርደን መገኘት የለብንም፡፡››
- ‹‹የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በመጀመሪያ ቅዱስ ወንጌል ከዚያ የሐዋርያት፣ የሊቃውንት እያሉ ነው የሚቀጥሉት፤ እርስዎም ከብፁዕ ዋና ጸሐፊ፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከቋሚ ሲኖዶስ፣ ከምልዓተ ጉባኤ ጋራ ነው፡፡ ከዚያ ሲወርድ ግን ከሊቃውንት መጽሐፍም ወርዶ ልቦለድ መጽሐፍ እንደ ማንበብ ነው!!›› /ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/
- ‹‹እግዚአብሔር ለሚወደው ሕዝብ ነቢይ ኾኖ ትንቢት የሚነግራቸውን፣ አስተዳዳሪ ኾኖ የሚመራቸውን፣ ኖላዊ ኾኖ የሚጠብቃቸውን አባት ያዘጋጅላቸዋል፤ የዛሬው ቀን ይህን እግዚአብሔር የሚወደውን ሕዝብ ለቅዱስነትዎ ያስረከበበት ቀን ነው፡፡››
- ‹‹የዛሬው ቀን ለቤተ ክርስቲያን ችግሯን ፈቺ፣ ለዕድገቷ ፕላን አውጪ፣ ለአስተዳደሯ መመሪያ ሰጪ ለመኾን በዐደባባይ ቃል የገቡበት ቀን ስለኾነ በታላቅ አክብሮትና ደስታ እናስታውሰዋለን፡፡ ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠት በቀላል አይመጣም፤ የልብ መሻትና መሠበርን ይፈልጋል፤ ማዕርግ ከነክብሩ፣ ሥልጣን ከነእውነቱ፣ መስቀል ከነትዕግሥቱ ካልተሰጠ አይቻልም፡፡ /ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ/
- ‹‹የዛሬ ዓመት የተናርኋቸው ቃላት ኹሉ እንደጸኑ ናቸው፤ አልተበረዙም፤ አልተከለሱም፤ እንዲያውም ከቅ/ሲኖዶስ አባላት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከምእመናን ጋራ በመኾን አጠናክራቸዋለኹ፡፡››
- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ጥሪ በምድር ላይ ለመከራ መስቀል እንጂ ለተድላ ሥጋ አይደለም፤ ተድላውና ደስታው የተዘጋጀው በላይኛው ዓለም ነው፤ የቤተ ክርስቲያን መሪ፣ አገልጋይና ተከታይ የኾነ ኹሉ በውል መገንዘብ ያለበት ይህን ነው፤ የተጠራነው ለሰማያዊ ሀብትና ሹመት እንጂ እንደ ሣር ቅጠል ለጊዜው ታይቶ ለሚጠፋ ምድራዊ ሀብትና ሥልጣን አይደለም፡፡››
- ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን አሠራር እንዳይቃና እየተጠላለፉና እየተመሰቃቀሉ ብዙ እንዳንራመድ የሚያደርጉን ምክንያቶች ከማንም ይኹን ከየት ምንጫቸው ከፍቅረ ንዋይና ከፍቅረ ሢመት ውጭ ናቸው የሚል ግንዛቤ የለም፤ ለእነዚኽ ደግሞ ቁልፍ መፍትሔያቸው ራስን ክዶ መስቀልን ለመሸከም በቁርጥ ከመነሣት በቀር ሌላ ሊኾን አይችልም፡፡ እኛ የቤተ ክርስቲያናችን ተጠሪዎች ሥራችን ሊቃና፣ ተደማጭነታችን ሊሰፋ፣ ተልእኳችን ሊሠምር፣ ሕዝባችን ሊያምነንና ሊከተለን የሚችለው የጌታችንን ቃል አክብረንና ራሳችንን ክደን ለእውነት የቆምን እንደኾን ብቻ ነው፡፡››
- ‹‹ባሳለፍነው የአንድ ዓመት ጉዞ ቅ/ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያናችን በዕቅድ እንድትመራ፣ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት እንዳይባክን በዘመናዊ አያያዝ እንዲያዝ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕና ርትዕ፣ እኩልነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከመወሰን ባሻገር ይህን በሕግ ማህቀፍ፣ በደንብና በመመሪያ አጠናክራ ለመሥራት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በዕውቅ ምሁራን አማካይነት ልዩ ልዩ ጥናቶችን እያካሔደች ትገኛለች፡፡ ይህ የተጀመረው የአሠራር ለውጥ ተፈጽሞ ሲታይ ኹሉን እንደሚያስደስት ጥርጥር የለውም፤ ቤተ ክርስቲያናችን በሕግና በሥርዐት ስትመራ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ኢኮኖሚ ጠንካራ ይኾናል፤ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎታችንም ለሕዝበ ክርስቲያን በአግባቡ ተደራሽ ይኾናል፡፡ እነዚኽን ዐበይት ጉዳዮች ከሥራ ላይ ለማዋል የኹሉም ቀና መንፈስና ትብብር ያስፈልጋል፤ ራስን መካድ ያስፈልጋል፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
* * *
- ለአንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት አከባበር በእንግሊዝኛ የወጣው የመርሐ ግብሩ ዝርዝር የታየበት የአጻጻፍ ውስንነትና የእውነታ ስሕተት በታዳሚዎች ተተቸ – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን “the 1st patriarch of the Ethiopia Orthodox Tewahido Church” ያደርጋቸዋል፤ ‹‹Message from the Acting patriarch of EOTC” የሚል መርሐ ግብርም አለው! የሰዓት አገላለጹማ….
- የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የኾኑት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባለቤት ለቤተ ክርስቲያን በማይገባ አለባበስ (በአጭር ቀሚስ) የበዓለ ሢመቱ እንግዳ መኾናቸው ቅሬታ ፈጥሯል፡፡
No comments:
Post a Comment