Monday, 3 February 2014

ጥንታዊው የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም ተፈታ



  • ገዳሙ ጨርሶ ሳይጠፋ ጉዳያቸው በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲታይ መናንያኑ ጠይቀዋል
  • በገዳሙ ህልውና ላይ የተጋረጠው አደጋ በሀ/ስብከቱ የተንሰራፋው ችግር የከፋ መገለጫ ነው
(አዲስ አድማስ፤ ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ አንድነት ገዳም ተፈትቶ፣ መናንያኑና መነኰሳቱ መበተናቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡
ጥንታዊውን ገዳም ለመፈታት፣ ማኅበረ መነኰሳቱንም ለመበተን ያበቃቸው፣ በአካባቢ ተወላጅነት የገዳሙን መሬት በተለያዩ ጊዜያት ተቆጣጥረው ለግላቸው ይጠቀሙ ከነበሩ ግለሰቦች ጋር ተፈጥሮ የቆየውና በተለያዩ ምክንያቶች እየተካረረ የመጣው አለመግባባት መኾኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በኅዳር ወር 2006 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ገዳሙን ለቀው የወጡት በቁጥር ከ50 – 80 የሚገመቱ መናንያኑ ከተለያዩ አህጉረ ስብከትና ክልሎች የተሰባሰቡና በጸሎት ተወስነው የራስ አገዝ ልማት እያለሙ በአንድነት የኖሩ መነኰሳትና መነኰሳዪያት ሲኾኑ በሀገረ ስብከቱ ውሳኔ ከአስተዳዳሪነት የተነሡትን አበምኔቱን መ/ር አባ ተክለ ብርሃን ሰሎሞንን ጨምሮ ከፊሎቹ በአሁኑ ወቅት በደነባ በኣታ ለማርያም ገዳም ተጠልለው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የወረዳው መንግሥታዊ አስተዳደር፣ ከእነዋሪና ደነባ ከተሞች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ገዳማውያኑንና ግለሰቦቹን በተለያየ ጊዜ በማገናኘት ለአለመግባባቱ የመፍትሔ ሐሳብ ሲሰጡና ውሳኔ ሲያሳልፉ እንደቆዩ ያስታወሱት መነኰሳቱ፤ ‹‹ተሰዳጅና መጤ›› ከሚል በቀር ግለሰቦቹ በገዳሙ አበምኔትና በመናንያኑ ላይ የሚያቀርቧቸው ክሦች መሠረተ ቢስ መኾናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
የገዳሙን ሥርዐተ ማኅበር በመጣስ የመሬት ይዞታውን፣ ቅርሱንና የልማት ቦታውን ለመከፋፈል የሚሹ ግለሰቦች በሥነ ምግባር ጉድለት ከማኅበሩ ከተወገዱ የስም መናንያን ጋራ በማበር ያቀረቡትን አቤቱታ ብቻ በመቀበል በፓትርያርክ የሚሾሙት አበምኔት፤ በሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ከሓላፊነት መነሣታቸውን ያስረዱት ማኅበረ መነኰሳቱ፣ አንዳንድ የሀ/ስብከቱን ሓላፊዎች በስም በመጥቀስ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡
ማኅበረ መነኰሳቱ እንደሚገልጹት ከሓላፊነት የተነሡት የገዳሙ አስተዳዳሪ÷ የገዳሙን መሬት ይዘውና ጋብቻ መሥርተው ከገዳማውያኑ ጋራ ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩት የአካባቢው አርሶ አደሮች ትክ መሬት አግኝተውና ካሳ ተሰጥቷቸው ከገዳሙ ክልል እንዲወጡ በማድረግ የገዳሙን ይዞታና ሥርዐተ ማኅበሩን በሕግ አስከብረዋል፤ ገዳሙንና ገዳማውያኑን ከሰብአ ዓለም ለይቶ በአግባቡ በማስተዳደር ጣልቃ ገብ ድርጊታቸውን ተከላክለዋል፤ በግብርናና በሽመና ሥራዎች፣ በንዋያተ ቅድሳት ማከፋፈያ፣ በሙዓለ ሕፃናትና በኪራይ ቤቶች ግንባታ የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት መስቀል ልመናን አስቀርተዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ አበምኔቱን ከሓላፊነት ያነሣበት ውሳኔ የገዳሙን መተዳደርያ ደንብ የሚጥስ ከመኾኑም በላይ ከጥቅመኝነት፣ ጥንቆላና ኑፋቄ ጋራ ተያይዞ በሀ/ስብከቱ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር አስከፊ መገለጫ ነው የሚሉት ማኅበረ መነኰሳቱ÷ ሥርዐተ ማኅበራቸውን ጠብቀው በገዳሙ የጀመሩትን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎት ለመቀጠል እንዲችሉ፣ የገዳሙ ቅርሶች፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲጠበቁ፣ በገዳሙ ያለጧሪ የቀሩ ድኩማን አረጋውያን ደኅንነትም እንዲታሰብበት ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የደብረ ብሥራት ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር በኾኑት ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ የተመሠረተ የ፲፪ው መቶ ክፍለ ዘመን ገዳም መኾኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
በገዳሙ ታሪክ እንደሚነገረው፣ እስከ 8000 መናንያንን እያስተዳደረ ገዳምነቱን ሳይለቅ በሥርዐተ ማኅበር በቆየው ገዳም፣ ሰበካ ጉባኤ በማቋቋም ወደ ደብርነት እንዲቀየርና በቃለ ዐዋዲ እንዲመራ ለማድረግ ተሞክሮ እንደነበር የገለጹት የዜናው ምንጮች÷ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገዳማት አስተዳደር መምሪያና የቅርስ ጥበቃ አካላት ኹሉ ከጻድቁ ዐፅም፣ የእጅና የመጾር መስቀሎች ጀምሮ በርካታ ቅርሶች ተጠብቀው የሚገኙበትን የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሥርዐተ ምንኵስናና የትምህርት ማዕከል ጨርሶ ሳይጠፋ መታደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
*                                        *                                     *
ተጉለትና ቡልጋ – ትግራይና ኤርትራ
በ፲፫ው መ/ክ/ዘ በነበረችው ኢትዮጵያ ደቡብ የምንለው የሸዋን ግዛትና ከዚያ በታች ያለውን ነው፡፡ ከዮዲት ጉዲት ጥፋት በኋላ ተዳክሞና በአረማዊነት ተውጦ በነበረው በዚኽ ግዛት በኋላ ዘመን ለተስፋፋው ገዳማዊ ሕይወትና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሠረት የኾኑት በተጉለትና በቡልጋ አካባቢ በተመሳሳይ ጊዜ የተነሡ አባቶች ናቸው፡፡
እኒኽ የተጉለትና የቡልጋ ቅዱሳን እንዲነሡ ምክንያት የኾኗቸው ሁለት ነገሮች መኾናቸውን እኛ ዘንድ የደረሱት መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው÷ ገዳማዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ካልተቋረጠበት ከትግራይ አካባቢ ጋራ በየጊዜው የነበረው ያልተቋረጠ ግንኙነት ሲኾን፤ ሁለተኛው ደግሞ በአካባቢው የነበሩ ጠንካራ መምህራን ናቸው፡፡ ይህ ኹኔታ ክርስቲያናዊ ሕይወትና ገዳማዊ ኑሮ በተጉለትና ቡልጋ አካባቢዎች እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡
በቀድሞ ጊዜ በአንድ አካባቢ ይሠፍሩ የነበሩት ዘመዳሞች ነበሩ፡፡ በዚኽም ምክንያት በተጉለትና ቡልጋ አካባቢ በተነሡ ቅዱሳን መካከል የጠበቀ ዝምድናን እናገኛለን፡፡ አንዱ አንዱን የመሳብ፣ አንዱ ለሌላው አርኣያ የመኾን ዕድልም ነበራቸው፡፡
Familial lineage of Saints in Bulga
ምንጭ፡- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ አራቱ ኃያላን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.
በተጉለትና ቡልጋ አካባቢዎች እና በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይና ኤርትራ አካባቢዎች መካከል የዘርም የእምነትም ግንኙነት እንደነበር በአካባቢው ለነበሩ ቅዱሳን የተጻፉ ገድሎቻችን ኹሉ ይመሰክራሉ፡፡ ለኑሮ ተብሎ ከትግራይና ኤርትራ ወደ ሰሜን ሸዋ መምጣት፣ ለትምህርትና ለምናኔ ተብሎ ወደ ትግራይና ኤርትራ ማምራት በሁለቱም አካባቢዎች ሲታዩ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚኽ ግንኙነቶችና ከላይ ያየናቸው መምህራን መኖራቸው በተጉለትና በቡልጋ ጠንካራ የኾኑ መንፈሳውያን እናቶችና አባቶች እንዲነሡ አድርጓል፡፡
*                                        *                                     *
ደብረ ሊባኖስ እና ደብረ ብሥራት – ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ
በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ለተመሠረተው ገዳማዊ እንቅስቃሴ መሠረት የኾኑ ሁለት ቅዱሳት መካናትና ሁለት ቅዱሳን አባቶች ነበሩ – ደብረ ሊባኖስ እና ደብረ ብሥራት፤ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ፡፡
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
St. Abune Tekle Haimanotአቡነ ተክለ ሃይማኖት በዛሬዋ ኢቲሳ ጽላልሽ በ1207 ዓ.ም. ከክርስቲያን ቤተሰብ የተወለዱ አባት ናቸው፡፡ በ15 ዓመታቸው በ1222 ዓ.ም. ዲቁናን፣ በ30 ዓመታቸው በ1237 ዓ.ም ቅስናን የተቀበሉት ከአቡነ ቄርሎስ(ጌርሎስ) መኾኑን ገድላቸው ይገልጣል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመጀመሪያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በአካባቢያቸው ተምረው በ22 ዓመታቸው በ1229 ዓ.ም. ከቤት ወጡ፡፡ በዳሞት 12 ዓመት (ከ1299 – 1241 ዓ.ም.) በሸዋ ለሦስት ዓመት (ከ1241 – 1244 ዓ.ም.) በስብከተ ወንጌል ካገለገሉ በኋላ ለበለጠው ትምህርት በዚያ ዘመን የትምህርት ማዕከላት ወደኾኑት የሰሜን ኢትዮጵያ ገዳማት ሔዱ፡፡ መጀመሪያ በአባ በጸሎተ ሚካኤል ዘአምሐራ ገዳም ዐሥር ዓመት (ከ1244 – 1254 ዓ.ም.)፣ በሐይቅ እስጢፋኖስ ዐሥር ዓመት (1254 – 1264 ዓ.ም.)፣ በደብረ ዳሞ ዐሥራ ሁለት ዓመት (ከ1264 – 1276 ዓ.ም.)፣ የትግራይን ገዳማት በመሳለምና በሑረተ ኢየሩሳሌም አንድ ዓመት(1276/77 ዓ.ም.) ቆዩ፡፡ ምንኵስናን ከሐይቅ እስጢፋኖስ አስኬማንም ከደብረ ዳሞ ተቀበሉ፡፡
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመጀመሪያውን ገዳማዊ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት በትግራይ እያሉ ነበር፡፡ በዚያ ለአያሌ ገዳማት መመሥረት ምክንያት የኾኑትን አባቶችን አመንኵሰዋል፡፡ እነ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ፣ እነ አቡነ አርኣያነ ጸጋሁ፣ እነ አቡነ በርቶሎሜዎስ እና እነ አቡነ እንድርያስ ለዚኽ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከኻያ ስምንት ዓመታት በላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ገዳማት በትምህርትና በአገልግሎት ቆይተው በ1277 ዓ.ም. ወደ ሸዋ ተመለሱ፡፡ መጀመርያ በተለያዩ ቦታዎች ለገዳም የሚኾን ቦታ ሲያፈላልጉ ቆይተው የመጨረሻው ምዕራፋቸው በግራሪያ በምትገኝ አንዲት ዋሻ ደብረ አስቦ የተሰኘውን ገዳም መመሥረት ኾነ፡፡ ደብረ አስቦ (ደብረ ሊባኖስ) ዛሬ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት የምትገኝ ገዳም ናት፡፡ የመጀመርያ ስሟ ደብረ አስቦ ይባላል፡፡ ደብረ ሊባኖስ ብሎ የሰየማት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በድላይን ድል ካደረገ በኋላ መኾኑን ዜና መዋዕሉ ይናገራል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳሙን የመሠረቱት በኋላ ካጠመቁት የአካባቢው አረማዊ ገዥ ባገኙት ቦታ በ1277 ዓ.ም. አካባቢ ነው፡፡ ገዳሟ ስትመሠረት በዋሻው ውስጥ ሲኾን ገዳማውያኑ በአካባቢው እያረሱ ይጠቀሙ ነበር፡፡ የአካባቢው ሰዎች ስለ ገዳማውያኑ የነበራቸው አመለካከት በጎ አልነበረም፡፡ አቡነ ፊልጶስ ወደ ገዳሙ ሲመጡ መንገዱን የጠየቋቸው እረኞች ‹‹መነኰሳቱ ሰው ይበላሉ›› ብለው ነው የነገሯቸው፡፡ የደብረ አስቦ መነኰሳት በተለያየ ጊዜም ከአካባቢው ተቃውሞ ይገጥማቸው ነበር፡፡ የመጀመርያዎቹ ገዳማውያን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሰሜን ገዳማት ሲመጡ አብረዋቸው የመጡና ከአካባቢው የተጨመሩ መነኰሳት ነበሩ፡፡ አቡነ አኖሬዎስ ሕግ እስኪያወጡ ድረስም የሴቶችና የወንዶች ገዳም አልተለየም ነበር፡፡
ደብረ አስቦ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እስከ 1306 ዓ.ም. ድረስ ለ29 ዓመታት ያህል አገልግለውበታል፡፡ በዚኽ ጊዜ ውስጥ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በምሥራቅ ተሠማርተው ሐዋርያዊ አገልግሎት የሰጡ፣ ገዳማትንም ያስፋፉ አባቶችን አፍርተዋል፡፡ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዜና በየአካባቢው ሲሰማ ከአራቱም አቅጣጫ ገዳማዊ ሕይወትን ፍለጋ ወንዶችና ሴቶች መጡ፡፡ ያረፉት ነሐሴ 24 ቀን 1306 ዓ.ም. በደብረ አስቦ ነው፤ የተቀበሩትም እዚያው ነበር፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም መቋቋም በሸዋ፣ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ለተስፋፋው ክርስቲያናዊና ምንኵስናዊ ሕይወት መሠረት ኾኗል፡፡ የአቡነ ፊልጶስ ደቀ መዝሙር የኾኑት አቡነ ዘካርያስ በጣና የዓባይ ወንዝ መውጫ በኩል ባለችው በገሊላ ገዳም ደሴት መሠረቱ፡፡ ሌላው ደቀ መዝሙር አባ ዘዮሐንስ በጣና ዙሪያ በሚገኙ የአገው ሕዝቦች ዘንድ ክርስትናን ካስተማሩ በኋላ በክብራን ገብርኤል ገዳም ተከሉ፡፡ እነአቡነ በርተሎሜዎስ ወደ ጃን አሞራ ተጓዙ፡፡ እነ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግም ምሥራቅ ኢትዮጵያን አስተማሩ፡፡ የአቡነ ፊልጶስ ደቀ መዝሙር አቡነ ተከሥተ ብርሃን በምሥራቅ ጎጃም አስተማሩ፤ ዲማንም አቀኑ፡፡ በኋላም በአቡነ ያዕቆብ አስተባባሪነት የተመረጡ ዐሥራ ሁለቱ ንቡረነ እድ መካከለኛውንና ደቡብ ኢትዮጵያን ተካፍለው አስተምረዋል፡፡
ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ
St. Abune Zena Markos of the Debra Bisrat Monastery
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ አራቱ ኃያላን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.
ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ የተወለዱት በመጀመሪያው የመካከለኛው ዘመን ብዙ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን በወጡበት በጽላልሽ ነው፡፡ ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ እንደሚተርከው፡- አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ አቡነ አኖሬዎስ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመዳሞች ናቸው፡፡
ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ እንደ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኹሉ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማሩት ከአካባቢያቸው ነው፡፡ ዲቁናን የተቀበሉት ከአቡነ ቄርሎስ(ጌርሎስ) ሲኾን ይህም በስምንት ዓመታቸው መኾኑን ገድሉ ይናገራል፡፡ ለዐቅመ አዳም በደረሱ ጊዜ ወላጆቻቸው ሚስት አጭተው አጋቧቸው፡፡ እርሳቸው ግን በሠርጋቸው ዕለት ከሚስትቱ ጋራ ተስማምተው ወጥተው መነኑ፡፡ ሚስታቸው በማማስ የሴቶች ገዳም ገብታ በዚያ ኖራለች፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ መጀመርያ በአካባቢያቸው እየተዘዋወሩ አስተምረዋል፤ በኋላም ጉራጌ ሀገር ወደሚገኘው ምሑር ወደተባለው ቦታ ሔዱ፡፡ በዚያም ብዙዎችን አጠመቁ፡፡ በጉራጌ ሀገር እየተዘዋወሩ አስተምረው በመንዝ ትገኝ ወደነበረችው የአባ ገብረ ናዝራዊ ገዳም ገቡ፡፡ የመነኰሱትና ሥርዐተ ምንኵስናን መጀመሪያ የተማሩት በዚያ ሳይኾን አይቀርም፡፡
ከአባ ናዝራዊ ገዳም ወጥተውም በወግዳ በሚገኝ ዋሻ በተጋድሎ ተቀመጡ፡፡ በዚያ ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መጥተው አብረው በስብከተ ወንጌል እያገለገሉ በዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም አብረው ወደ ሞረት ሔዱ፡፡ ያን ጊዜ በቦታዋ በነበረው ዋሻ እየኖሩ በአካባቢው ሰበኩ፡፡
ኹለቱ አባቶች የተወሰኑ ዓመታትን አብረው በደብረ ብሥራት ከኖሩ በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ግራርያ ሔዱ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ማእከላቸውን ደብረ ብሥራት አድርገው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ ከጉራጌ ሀገር ቀጥሎ የአቡነ ዜና ማርቆስ ሁለተኛው አገልግሎት በይፋት የሚኖሩ ቤተ አይሁድ ዘንድ ነበር፡፡ የማሕሌተ ጽጌን ደራሲ አባ ጽጌ ብርሃንን ያገኙትም ከእነዚኹ ከቤተ አይሁድ ወገን አጥምቀው ነው፡፡ አባ ጽጌ ብርሃን ከደብረ ሐንታ ገዳም መምህር ከአባ ገብረ ማርያም ጋራ በመኾን በዳዊት መዝሙር ልክ 150 አንቀጽ ያለው ማሕሌተ ጽጌ አዘጋጅተዋል፡፡ በዳግማዊ ዳዊት ዘመን በይፋት ለቤተ አይሁድ አራት አብያተ ክርስቲያናት ተተክለው ነበር፡፡
ከዚያም የሰሜን ኢትዮጵያ ገዳማት ለመሳለም ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ፣ ወሎና ጎንደር ተጓዙ፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከትግራይ አባ ገብረ ሚካኤል፣ ከላስታ አባ ዮሴፍና አባ አካለ ክርስቶስ፣ ከሸዋም አባ ገብረ መስቀል ተከተሏቸው፡፡ አባ አካለ ክርስቶስ ገዳመ ዘጋን(ደብረ ማሕውን) አቋቋሙ፡፡ አባ ገብረ መስቀልም ሀገረ ለጋሶ በሚባል ሀገር ገዳምን ተከሉ፡፡ አባ ገብረ ክርስቶስም በዳሞት ተሾሙ፡፡
በዚኽ ዐይነት ኹኔታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተውና ገዳማትን ተክለው በተወለዱ በ140 ዓመታቸው ታኅሣሥ 3 ቀን 1367 ዓ.ም. አካባቢ በዐፄ ንዋየ ማርያም ዘመን ዐርፈው በገዳማቸው በደብረ ብሥራት ተቀበሩ፡፡
ምንጭ፡- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ አራቱ ኃያላን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.፣ ገጽ 32 – 50

No comments:

Post a Comment