Thursday, 23 January 2014

የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሻረው! በርካታ ሚልዮን የምእመናን ገንዘብ የተመዘበረበት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታና ሒሳብ በብቁ እና ገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር ቅ/ሲኖዶሱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ልዩ ጽ/ቤቱ እንዲዘገይ አዘዘ – በውል ከተያዘው ገንዘብ ውጭ ከ8 ሚልዮን በላይ ብር የወጣበትና ሥራው ሳይጠናቀቅ በ6 ዓመት የዘገየው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ተሰነጣጥቋል፤ ዋናው መካከለኛ ጉልላት እንዳይወድቅ ያሰጋል



???????????????????????????????
‹‹ብፁዕ አባታችን፣ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እየተፈጸመ የሚገኘው ከባድ ወንጀል ሕዝበ ክርስቲያኑን እያስቆጣ ከመምጣቱም ባሻገር ብፁዕ አባታችን ይህን እየሰሙና እያወቁ ምነው ዝም አሉ ብሎ ሕዝቡ እንዲያስብ አድርጎታል፡፡… የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ጅምር ሥራ አልቆ ማየት እንፈልጋለን፡፡ የደብሩ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በአስቸኳይ ሕዝቡ በሚመርጣቸው የኮሚቴ አባላት ይተካልን፡፡ ይህ የማይደረግ ከኾነና ኹኔታው ባለበት ከቀጠለ ለሚፈጠረው ችግር ሓላፊነቱን የማንወስድ መኾኑን እናሳውቃለን፡፡›› /የደብሩን ወቅታዊ ጉዳይ ለማሳወቅ ምእመናኑ በኅዳር ፳፻፬ ዓ.ም. ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ከጻፉት አቤቱታ የተወሰደ/
  • የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢና ወጪ ኦዲት እስከ ግንባታው ፍጻሜ መዘግየቱ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ ተፈጻሚነት አዳጋች እንደሚያደርገውና የግንባታው ሒደት ምርመራም ከግንባታው መጠናቀቅ በኋላ እንዲኾን መታዘዙ የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ እንደሚያሥነሳ የገለጹ ምእመናን፣ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ያስተላለፈውን ትእዛዝ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
  • የኦዲት ምርመራው እንዲዘገይ ከድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ ጋራ እንደተስማሙ አስመስለው ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ያስረዱት ብርሃኔ መሐሪ፣ በአድራሻ ለፓትርያርኩ በግልባጭ ደግሞ ለድሬዳዋ ሀ/ስብከት ጽ/ቤትና ለሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በጻፉት ይዘቱ የተለያየ ደብዳቤ÷ ‹‹ማን እንደሚመራው የማይታወቅ ሲኖዶስ ግራና ቀኙን ሳያጣራ በግብር ይውጣ ያስተላለፈው ነው›› በሚል ቋሚ ሲኖዶሱ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ያስተላለፈውን ውሳኔ ማጣጣላቸው ተዘግቧል፡፡
  • የደብሩን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በብቸኝነት የሚያዝዙበት መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ፣ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የበላይ ሓላፊነት የሚመራው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ከፓትርያርኩ እንደተሰጠው በተገለጸ መመሪያ መሠረት የኦዲት ምርመራውን እስከ ግንባታው ፍጻሜ በማዘግየቱ ዝርፊያውን ያጋለጡ ተሟጋች ምእመናን ‹‹ምንም አታመጡም›› በሚል እየተሳለቁባቸው ነው፤ የደብሩ አስተዳዳሪንም ‹‹በአቋም ወደ እኛ የማትመጣ ከኾነ እናበርሃለን›› ሲሉ ዝተውባቸዋል፡፡
Lique Tiguhan Birhane Mehari00
የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ትእዛዝ ያስተጓጎሉት ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ መሐሪ
‹‹ምንም አታመጡም!››
  • መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ከጥቅመኞቹ የሕንፃው ተቋራጭ ኤፍሬም ተስፋዬ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ኢንጅነር ሰሎሞን ካሳዬ ጋራ በመኾን በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤቱ እንዲተላለፍ ያደረጉት ለሙስናና አማሳኞች ሽፋን የሚሰጠው ትእዛዝ፣ የሀ/ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አሳዝኗል፤ የከተማውን ምእመናን አበሳጭቷል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ምእመናኑን ዛሬ በጉዳዩ ላይ እንደሚያወያዩ ተጠቁሟል፡፡
  • ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ÷ ከሀ/ስብከቱ፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት በተውጣጡ ተወካዮች አማካይነት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የገቢና ወጪ ሒሳብ ኦዲትና የግንባታ ሒደቱ ምርመራ ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ለማስፈጸም ብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች የሚመረጡባቸውን አግባቦች በማዘጋጀት ላይ የነበሩ ሲኾን የምርመራ ሪፖርቶቹ እስከ ሚያዝያ ፲፱/፳፻፮ ዓ.ም. ተጠናቅቆ እንዲቀርብ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡
  • የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ማስፈጸም ያለበት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ከመዝባሪዎች ጋራ የመከረበትን ትእዛዝ ሳይኾን የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ መኾን እንደሚገባው ያሳሰቡት የደብሩ ምእመናን፣ ትእዛዙ ‹‹የፓትርያርኩ ፀረ ሙስና አቋም በተግባር የተፈተነበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
  • የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በአድራሻ ለሀ/ስብከቱ በግልባጭ ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ ትእዛዙን ያስተላለፈበት ደብዳቤ ትላንት በደብሩ አስተዳዳሪ በንባብ በተሰማበትና የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ፓትርያርኩ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ መሻር እንደማይችሉ የገለጹት ምእመናኑ እንዳስጠነቀቁት÷ የኦዲት ምርመራው በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት የማይፈጸም ከኾነ በደብሩ ሕንፃ ግንባታ ስም የሚካሔዱ ማንኛውንም የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴዎች በማገድ ለመንግሥት አቤት ይላሉ፡፡
*                         *                       *

  • በጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ዊነር ኮንስትራክሽን ከተባለው ደረጃው ከማይታወቅ የአቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ተቋራጭ ጋራ በተያዘ ውል፣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ በ2 ዓመት ጊዜና በ2‚984‚562.51 ሚልዮን ብር ወጪ መጠናቀቅ ነበረበት፡፡ ከውለታ ጊዜው ውጭ ለ6 ዓመታት የዘገየውና 8 ሚልዮን ብር የፈጀው የግንባታ ሒደት ግን ከ70 – 80 በመቶ ብቻ እንደተፈጸመ የተመለከተው፡፡
  • የግንባታ ፈቃድ እና ደረጃው በተለየ መሐንዲስ ቁጥጥር ተደርጎበት የማያውቀው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ÷ ሥራው ከዲዛየኑ ውጭ ስለመከናወኑ፣ ምእመናን በዐይነት የሚያበረክቷቸው አስተዋፅኦዎች (ቆርቆሮ፣ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ አሸዋ) በአግባቡ ተተምነው ገብተው ወጪ እንደማይደረጉ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ለቅ/ገብርኤል ክብረ በዓል በግንባታው ስም የሚሰበሰበው ከፍተኛ ገቢ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን በብቸኝነት ከሚቆጣጠሩትና የግል ኢንቨስትመንታቸውን በማጧጧፍ ላይ ካሉት ብርሃኔ መሐሪ በቀር በሚመለከተው አካል በትክክል እንደማይታወቅ በኅዳር ወር ፳፻፭ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተሠየመው አጣሪ ልኡክ ለቅ/ሲኖዶሱ ባቀረበው ሪፖርት ተረጋግጧል፡፡
Lique Tiguhan Birhane Mehari03
  • ቋሚ ሲኖዶሱ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢና ወጪ እንዲሁም የግንባታው ሒደት በብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ለሦስተኛ ጊዜ የተሠየመው የጠቅ/ቤ/ክህነቱ አጣሪ ልኡክ ባቀረበለት ሰፊ ሪፖርት ላይ የተመሠረተ ኾኖ ሳለ፣ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ከግንባታው ፍጻሜ በፊት እንዳይካሔድ ማዘዙ በርግጥም የፓትርያርኩ የፀረ ሙስና አቋም ከኹኔታዎች ጋራ የሚጋሽብ ለመኾኑ የሚያመላክትና በመግለጫዎች የሚናገሩለትን ቆራጥነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ አይቀርም፡፡
  • የድሬዳዋ ሀ/ስብከትን ከአዲስ አበባ ኾነው ለሁለት ዓመታት የመሩትና በሕንፃው ግንባታ ዙሪያ ሲቀርቡ ለቆዩት የምእመናን ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚጋፋውን የኦዲት ምርመራ የሚያዘገየውን ትእዛዝ በፊርማቸው ወጪ ያደረጉት በፓትርያርኩ መመሪያ ነው ቢባልም ወቀሳንና ተጠያቂነትን የሚያስቀርላቸው አይኾንም፡፡ – ‹‹ብፁዕ አባታችን፣ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል እየተፈጸመ የሚገኘው ከባድ ወንጀል ሕዝበ ክርስቲያኑን እያስቆጣ ከመምጣቱም ባሻገር ብፁዕ አባታችን ይህን እየሰሙና እያወቁ ምነው ዝም አሉ ብሎ ሕዝቡ እንዲያስብ አድርጎታል፡፡… ›› /የደብሩን ወቅታዊ ጉዳይ ለማሳወቅ ምእመናኑ በኅዳር ፳፻፬ ዓ.ም. ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ከጻፉት አቤቱታ የተወሰደ/
Holy Synod decision on D.D.St.Geb bld. AuditHoly Synod decision on D.D.St.Geb bld. Audit01

Wednesday, 22 January 2014

የሆሳዕና ቡሻና በዐታ ለማርያም ገዳም ተቃጠለ

     ጥር 13 ቀን 2006 ዓም.   

                        
በእንዳለ ደምስስ
በሐድያና ስልጢ ሀገረ ስብከት ጎረጎራ ወረዳ ውቅሮ ፋለታ ቀበሌ የደብረ ምጥማቅ ቡሻና በዓታ ለማርያም ገዳም ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የከተራ ዕለት መነሻው ባልተወቀ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ቢኒያም መንቻሮ ገለጹ፡፡bushana

ሥራ አስኪያጁ በሰጡን መረጃም የከተራ ዕለት የበዐታ ለማርያም ታቦት ወደ ጥምቀተ ባሕር ከወረደ በኋላ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ መቃጠሉን ገልጸው ቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅዱሳቱን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ብለዋል፡፡

በካዝና ውሰጥ የነበረው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽላት ካዝናው በእሳቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመለብለቡ ምክንያት መክፈት እንዳልተቻለና መቃጠልና አለመቃጠሉን እንዳልተረጋገጠ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ፤ ጉዳዩን ለፖሊስ በማሳወቅ የቃጠሎውን መንስኤ ለማጥራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የቡሻና በዐታ ለማርያም ገዳም ከዚህ በፊት ሥዕለ አድኅኖ በዛፎች ላይ ታይቶበት በነበረ ቦታ መቃኞ ተሰርቶለት ሐምሌ 2001 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ እንደተከበረ ይታወቃል፡፡

Friday, 17 January 2014

ታላላቅ አርቲስቶች እና ባለሃብቶች በደብረ ሊባኖሱ አስተዳዳሪ ፀባቴ አባ ወልደ ማርያም ላይ ቅሬታቸውን ገለጹ

                                                    
ከአርቲስቶቹና ባለሀብቶቸሁ ጥቂቶቹ      

            


ጥር 6/2006 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም አቶ ቁምላቸው ገ/ሥላሴ  የተባሉ አንድ ባለሃብት በግል ገንዘባቸው ያሰሩት ዕደ ጥበባት እና የቅርሳ ቅርስ ማዕከል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በመገኘት መርቀዋል ፡፡ ይህ ማዕከል ለአረጋውያን አበው መጦሪያ ይሆን ዘንድ የተሰራ ነው ያሉት አቶ ቁምላቸው  ለአረጋውያኑ  ማረፊያ ስለሌላቸው በዕለቱ ታላለቅ የኪነ ጥበብ  ባለሞያዎች  አርቲስቶች ባለሀብቶችም መገኘታቸው ከምረቃ ስነ ሥርዓቱ መበቀጠል አርቲስቶቸሁና ባለሃብቶቹ የአረጋውያን ማረፊያ ሕንጻ ለመገንባት ሚያስችል መርሃግብር ለማዘጋጀት ቢታሰብም የገዳሙ አሰተዳዳሪ አባ ወልደ ማርያም ከባህታዊ ከፊያለው ጋር በመመሳጠር በፈጠሩት አምባጓሮ አማካይነት የታሰበው መልካም ተግባር ተስተጓጉሎአል ባለሃብቶቹም ‹‹አዲስ አበባ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ሲበጠብጡን ቆይተው በመነሳታቸው እፎይ ብለን ነበር ለካ ታላቁ  ገዳማችን መጥተው አሁንም ይበጥብጡን ወዴት እንሂድ›› በማለት ቅሬታቸውን ገልጠዋል ፡፡ ባህታዊ ከፊያለው የሚባለው ሰውዬ ጫጋል መንገድ ላይ በሰራው የአረጋውያን መጦሪያ በማለት በአረጋውያን ስም የሚሰበስበው ገንዘብ ይቋረጣል የሚል ስጋት ስላደረበት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ምንም ነገር እንዳይሰራ እንደሚፈልግ የውስጥ ምንጮች ገልጠዋል፡፡ አባወልደ ማርያምም ይህንኑ ክፉ ተግባር ለመተግበር ገፋ ቀና እያሉ በመሆናቸው ለመልካም ሥራ ጊዜያቸውን፤ ጉልበታቸውን እና ሀብታቸውን ለገዳሙ ከፍተኛ ልማት ለማዋል የሄዱትን ምእመናን  ዘስቀይሞ ማባረር  የማያዛልቅ ጉዞ መበሆን በአስቸኳይ መፍትሄ እንደሚስፈልግ  በእለቱ የተገኙት ምእመናን ጠቁመዋል ይልቁንም አስተዳዳሪው ከገዳሙ ወጪ በማድረግ ትልልቅ የብር መስቀል እና የመሳሰሉትን በእለቱ ለተገኙት ጳጳሳት ሲሸልሙ መዋላቸው ህዝቡን አሳዝኖአል፡፡‹‹ እኛ ገዳምን በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለማገዝ ነው መጣነው እነሱ በሌለ ገንዘብ ወጪ እያደረጉ ይሸላለማሉ ወይ ዘመን ›› /ምእመናን ከታዘቡት የቀድሞዎቹ አባቶች ነገስታቱ ሳይቀር ለገዳማቱ ይሰጡ ነበር የዘመናችን ደግሞ መውሰድ ሆነ ፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩም በየገዳማቱ እንዲህ ያለ የዕደ ጥበባት ማእከል ሊኖር ይገባል  ያሉ ሲሆን የአረጋውያኑም ማረፊያ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል  ነገር ግን ገዳሙ አለማቀፍ እንደመሆኑ መጠን ጠንካራ እና ምእመናንን በሚገባ ማስተባበር የሚችል ለገዳሙ የሚመጥን አስተዳዳሪ ያስፈልጋል ያሉት ባለሃብቱና አርቲስቶች ያ ካልሆነ ግን ገዳሙ እየተጎዳ ስለሚሄድ ዝም አንልም ብለዋል  በእለቱ ለአረጋውያኑ መረፊያ ለመስራት ሚያስችል ገንዘብ ለመሰብሰብ ቢታቀድም በአስተዳዳሪው እና በባህታዊ ከፊያለው ክፋት ጥምረት ለጊዜው ሳይሳካ ቢቀርም ወደፊት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመወያየት ገዳሙ ችግር በዘላቂንት እንደሚፈታ እምነታችን ነው ብለዋል ምእመናኑ  በተለይ ጫጋል /ወደ ገዳሙ መዞሪያ / ያለው አረጋውን እና የአብነት ት/ቤት በሙሉ በገዳሙ አስተዳደር ሥር ተጠቃሎ ካልተዳደረ ገዳሙ መሬትና ንብረት በግለሰቦች በመበዝበዝ ላይ መሆኑን ምእመናኑ አጥብቀው ተናግረዋል በተለይ ተላላቅ ገዳማትና አድባራት ጥንታው ቅርሶች ሳይቀር በመሰረቅና በመበዝበዝ ላይ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ፈጣን እርምጃ ከሙስና የፀዳ ብቃት ያላቸው አስተዳዳሪዎች ሊመደቡና ችግር የተገኘባቸውን ደግሙ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ይህ ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን የህዝብ ስለሆነች ህዝቡ በቀጥታ ቤተ ክርስቲያኑን የማስተዳደር ስራ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው ብለዋል ምእመናኑ ፡፡                                                   
                                                


አቶ ቁምላቸው በግል ገንዘባቸው ያሰሩት የዕደ ጥበባትእና የቅርሳ ቅርስ ማዕከል

                                                          

Monday, 13 January 2014

ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅጣጫ ውጭ የአ/አ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ለመገምገም በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ በጠቅ/ቤተ ክህነቱና በሀ/ስብከቱ ችግሮች ተጠቃሽ የኾኑ ግለሰቦች መካተታቸው እንደሚያሳስባቸው የገለጹ ምእመናን አካሔዱ በጥንቃቄ እንዲጤን ጠየቁ



  • ጥናቱን የማስቆም አልያም የማዘግየት ፍላጎት ያላቸው ሙሰኛ እና ጎጠኛ ‹ተቃዋሚዎች› የመናፍቃንን ዓላማ በውስጥ አርበኝነት የማስፈጸም ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚችል በማስጠንቀቅ ሕጋዊና የሥነ ሥርዐት ርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው አመልክተዋል

*                *                *

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 
ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም 
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ 
ጉዳዩ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን አደረጃጀትና አሠራር ለማሻሻል የተጠናው ጥናት ተግባራዊ እንዲደረግ ስለ መጠየቅ

ቅዱስ አባታችን፡-
ከሁሉ አስቀድሞ እኛ ምእመናን የመንፈስ ቅዱስ ልጆችዎ በመጀመሪያው በዓለ ሢመትዎ ዋዜማ ላይ ኾነን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ው ፓትርያርክ ኾነው በመመረጥዎ የተሰማንን ደስታ እየገለጽን መልካም የሥራ ጊዜ እንዲኾንልዎት እንመኛለን፡፡ እንዲሁም ለ2006 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል እንኳን በሰላም አደረሰዎ ስንል የቅዱስነትዎ ቡራኬ እንዲደርሰን ከእግረ መስቀልዎ ሥር ኾነን በመማፀን ነው፡፡ 
ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነቷ ሥርዓቷና ትውፊቷ እንከን የማይወጣለት በዓለም ዐደባባይ ገናናነቷ ጥንታዊነቷና ድንቃድንቅ ቅርሶቿ ገዳማትና አደባራቷ ከሰው ልጆች ዓይነ ኅሊና የማይጠፋ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ያበረከተች እንደኾነች በእምነት ከማይመስሉን ወገኖች ጭምር ምስክርነት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ ሳትወሰን የመንግሥት መዋቅርና አደረጃጀት እንደዛሬው ባልተስፋፋበትና ባልተጠናከረበት ወቅት የሕዝቡ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ እንዲሻሻል፣ የአገሪቱ ሉዓላዊነት እንዲከበር፤ ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን በሕዝቡ የዕለት ተዕለት አኗኗር ሁሉ የመቻቻል መንፈስ እንዲሰፍን በማድረግ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ሥልጣኔና ዕድገት የተጫወተችውን የላቀ ሚና ታሪክ የማይረሳውና በገሓዱ ዓለምም በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ 
ቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡- ይህ በእንዲህ እንዳለ ኾኖ በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚስተዋለው የሥነ ምግባር ግድፈቶች፣ ጎጣዊ/ዘረኛ አሠራሮችና የሙስና መንሰራፋት ለምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መጉረፍ ምክንያት ከመኾናቸውም ባሻገር ፤በቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች  የተጠናና የተደራጀ በሚመስል ኹኔታ የሚፈጽሙትን የሥነ ምግባር ጉድለቶች በማየት አንዳንድ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ይርቃሉ፤ በቤታቸው ኾነው መጸለይን ይመርጣሉ፤ እነሱን አርኣያ በማድረግም ኃጢአት ለመሥራት ይደፋፈራሉ፤ ሃይማኖቱ በራሱ ሕጸጽ እንዳለበት አድርገው የሚቆጥሩም አሉ፡፡ 
የሙሰኞችና የጎጠኞች ዋነኛ ዓላማ ላይ ላዩን እንደሚታየውና እንደሚገመተው የራሳቸውን ጎጥ/ጎሳ አባላት መጥቀም ብቻ ሳይሆን በጥልቀት ሲመረመር ራሳቸውን ለመጥቀም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አውቀውም ኾነ ሳያውቁ በተዘዋዋሪ መንገድ በውስጥ አርበኝነት የመናፍቃንን ዓላማ ማስፈጸም መኾኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የውስጥ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ከውጭ ጠላቶች የበለጠ አደገኛ ናቸው፤ ከመለያቸውም መካከል፡-  
·   ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዐት ሥራ ላይ እንዳይውል በጥብቅ ይከላከላሉ፡፡
·    ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሀገረ ስብከትና እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ በተዘረጋ የሙስና መረብ ከሕጋዊ መዋቅሩ በበለጠ እርስ በርስ በመደጋገፍ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ይሸፋፈናሉ፤
·   የሥራ ዕድገት በሞያና በትምህርት ብቃት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በዘመድና በጉቦ እንዲፈጸም ያደርጋሉ፣
·       ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠ የደብር አለቃ ወይም ሓላፊ ላይ ተገቢውን የሥነ ሥርዐት ርምጃ በመውሰድ ፋንታ ወደ ሌላ የተሻለ ቦታ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል፡፡ 
በወዳጅም በጠላትም በአኩሪ ታሪክና ምግባር የምትታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን የዘመናት ስሟንና ክብሯን የማይመጥን እኩይ ተግባራት የሚፈጸምባት ቦታ፤ ከሃይማኖት ይልቅ ግላዊ ጥቅም በሚያስቀድሙ የውስጥ አርበኞች ብልሹ አሠራር ዘረኝነት፣ ሙስናና የሥነ ምግባር ጉድለት ጎልቶ የሚታይባትና ተከታዮቿን የሚያሸማቅቅ ነውር ተግባር የሚፈጽሙባት እየኾነች መጥታለች፡፡
ቅዱስ አባታችን፡- ይህን ኹኔታ በሚገባ የተገነዘቡት ቅዱስነትዎ በግንቦት 12/2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “ምእመናን በተለያየ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ስጦታ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ አያያዝና ቁጥጥር ባለመያዛችን ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ከሚውል ይልቅ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት እንደሚበዛ ፍጹም የማይካድ ሐቅ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከአድልዎና ከወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ተሰሚነትን ክፉኛ እየጎዳው መኾኑ አሌ ልንለው አይገባም” የሚለውን አባታዊ ቃልዎን በብዙኃን መገናኛ ስንሰማ እግዚአብሔር የእውነተኛ አገልጋዮቹን እንባ ተቀብሎ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር መፍትሔ የሚሰጥበት ጊዜ ደረሰ ብለን ደስ ብሎናል፤ በከፍተኛ አድናቆትም ተቀብለናል፡፡
የቅዱስ አባታችንን መንደርደሪያ ሓሳብ መሠረት አድርጎ በሰፊው  የተወያየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም በወርቅ ቀለም የተጻፈውን የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም ስምና ዝና ወደ ቀደመ የክብር ቦታው ለመመለስ የሚያስችል ጥናት የሚያጠና ኮሚቴ ማቋቋሙዎን በተለይም የቅዱስነትዎ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሠራርና አደረጃጀት የሚያጠና ኮሚቴ መዋቀሩን ስንሰማ፣ ‹‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰባት፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ትንሣኤ ሊያሳየን ነው፤›› ያላለ ምእመን አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ይፈታል ተብሎ የታመነበት ይህ ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ሰምተን ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡ ስለአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያው ጥናት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተከታታይ በተካሔዱ ውይይቶች የተሳተፉ ማኅበረ ካህናትና ምእመናንም በጥናቱ ይዘት በእጅጉ ተደስተናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ ጥናቱ ተግባራዊ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰንገው አላንቀሳቅስ ያሏት ሙስናና ጎጠኝነት ተወግደው ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያስችላል ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ በጥናቱ ያልተደሰቱ የተወሰኑ ግለሰቦች ባቀረቡት ቅሬታ ጥናቱ ተግባራዊ ከመኾን ታግዶ እንደገና በዐዲስ መልክ እንዲታይ መወሰኑን በከፍተኛ ድንጋጤ ነው የሰማነው፡፡
ይህ ለቤተ ክርስቲያን ዓበይት የአስተዳደር ችግሮች ኹነኛ መድኅን ይኾናል ተብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የታመነበት መመሪያ በተግባር ተፈትኖ በአፈጻጸም ያስከተለው ችግር ሳይመረመር ከወዲሁ በድጋሚ እንዲታይ ብሎ ማዘግየት እስካሁን የጠፋው ጥፋት አልበቃ ብሎ በሙስናው ሥራ ለተሠማሩት ወገኖች ተጨማሪ ዕድልና ጊዜ መስጠት ወይም እነሱ በሚፈልጉት ዓይነትና ሁኔታ ተቃኝቶ እንዲስተካከል ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ 
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተንሠራፍቶ የቆየው ሙስናና ብልሹ አሠራር ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ለነገ ሊባል የማይችል ባስቸኳይ ርምጃ መወሰድ ያለበት ስለኾነ የቤተ ክርስቲያቱን ሥር የሰደደና የተከማቸ ችግር ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በኾነው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው ጥናት ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
ቅዱስ አባታችን፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-የተቋማዊ ለውጡ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ማግኘቱ በራሱ ከፍተኛ ውጤት ቢኾንም አስፈላጊው የአፈጻጸም ስልትና በቁርጠኝነት ሥራ ላይ ሊያውል የሚችል ቅን ታታሪ ታማኝ ተግዳሮቶችን በከፍተኛ ጽናት መቋቋም የሚችል የሰው ኃይል ካልተመደበለት ብልጣብልጦቹ እጅ ወድቆ የታሰበውን ውጤት ሳያስገኝ ሊከሽፍ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ 
ስለዚህ ተቋማዊ ለውጡን በተሟላና በተሳካ ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋልና ዘለቄታማነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ፡ 
  1. በጥናቱ ላይ ጥያቄ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን ቢኖር ጥያቄውን በዝርዝር አቅርቦ በጥናት ቡድኑ ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚታመንበት ነገር ካለ አስፈላጊው ማሻሻያ ከሚደረግበት በስተቀር በጉጉት የምንጠብቀው የጥናት ውጤት ቢቻል ለማስቆም ካልተቻለም ለማዘግየት እንደገና በአዲስ መልክ እንዲታይ እየተደረገ ያለው አካሔድ ቆሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ልዕልና ተጠብቆ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እንዲደረግ፤
  2. የተጠናውን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥናት የሚገመግም አዲስ ኮሚቴ በተመለከተም ጥናቱን ሊያዳብር በሚችል መልኩ በፍጥነት ሠርተው ያቀርባሉ ብሎ ለማሰብ ከኮሚቴው አባላት መካከል ከአሁን ቀደም በሀገረ ስብከቱም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በተመሳሳይ ችግር ተጠቃሽ የሚኾኑ ሰዎች መካተታቸው ያሳሰበን በመኾኑ እንደገና እንዲታይልን እንዲደረግ
  3. ተቋማዊ ለውጡን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ እንዳይፈጸም በሚያውኩና በሚቃወሙ ላይ ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል ጥብቅ የሥነ ሥርዓት ርምጃ እንዲወሰድ እንደረግ፤
  4. ከቅን የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሠራተኞች፣ ከሰንበት ት/ቤት እንዲሁም ከምእመናን የተውጣጣ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ የተቋማዊ ለውጥ አስፈጸሚ አካል እንዲቋቋም
  5. ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ የፈጸሙ ሁሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተገቢው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድልን፣
  6. ስለጎጠኝነትና ሙስና አስከፊነት የሥልጠናና ትምህርት መርሐ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ እንዲደረግ፣
  7. ከሙስና የጸዱትንና የላቀ መልካም ተግባር የሚፈጸሙትን አገልጋዮች በመሸለም እንዲበረታቱ እንዲደረግ፣
  8. ቤተ ክርስቲያኒቱ ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር ራሷን እየፈተሸች፣ ችግሮቿን እየለየች መፍትሔ በማስቀመጥ ተግባራዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላት የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም እንዲደረግ፣
  9. ከመንግሥት አሠራር ልምድ በመቅሰም በስፋት የተንሰራፋውን የሙስና ተግባር መቋቋም ይቻል ዘንድ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አካል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም እንዲደረግ፤
በቅድስት ቤተክርስቲያናቸን ስም አበከረን እንጠይቃለን፡፡ 
ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-ቤተ ክርስቲያናችን የደረሰባትን የበጎች/የተከታዮች ስርቆትና ብልሹ አሠራር ለማስወገድ ብቻ ሳሆን ለህልውናዋ ስትል ከችግሩ ለመላቀቅ ጨክና (በቁርጠኝነት) ይህን መሰል ድርጊት በሚፈጽሙ ስውር የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችና የመናፍቃን ጉዳይ አስፈጻሚ ተላላኪዎች ላይ ዛሬ ነገ ሳትል በጥንቃቄ በተጠና መንገድ ጠንካራና ጠበቅ ያለ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት ይኖርባታል፡፡ 
ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲጣስ ቃለ ዓዋዲው በዘፈቀደ ሲሻር የደጋግ አባቶች አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ እንደዘበት በቸልታ ማለፍ ከክፉ ሰዎች ክፉ ተግባር ባልተናነስ ደረጃ ቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳት ላይ እየጣላት እንደኾነ ልናስተውል ይገባል፡፡ ትላንት ርምጃ መውሰድ ሲቻል ባለመወሰዱ ዛሬ መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ እየተቻለ በጥቃቅን ምክንያቶች ተግባራዊ ባለመደረጉ በዚች በዛሬዋ ዕለት እንኳ በቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ይልቁንም በቅንና እውነተኛ አባቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ኢፍትሐዊ ውሳኔ ለማዳን እየቻልን ያለማዳናቸን በታሪክና በትውልድ ይልቁንም በእግዚአብሔር ዘንድ ተወቃሽ ከመሆን ለመዳን አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እንረባረብ፡፡ 
ቅዱስ አባታችን፡- በመጨረሻም ያቀረብነው ጥያቄ በጥሞና ታይቶ ምላሽ የሚሰጥበት ቀነ ቀጠሮ እንዲያዝልን በታላቅ መንፈሳዊ ትሕትና እናሳስባለን፡፡
የቅዱስ አባታችንንና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ረድኤትና በረከት ይደርብን!  
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የአ/አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ተቃዋሚዎች ገዳማቱንና አድባራቱን አይወክሉም ‹‹ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት የተረቀቀው ሕግ ወደ ኋላ አይመለስም፤ መሥመሩን አይለቅም›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/


(አዲስ አድማስ ) ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ /ስብከት ለመዋቅርና አሠራር ለውጥ በባለሞያ ያካሔደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት እንቃወማለን የሚሉ ውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች አይወክሉንም ሲሉ የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ልዩ ልዩ አገልጋዮችና ምእመናን ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡ ለዘመናት የቆየው የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና የሥራ ሒደት ከነበረው ተስፋፍቶ፣ የወቅቱን አሠራርና ሥልጣኔ የዋጀ ኾኖ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔና በፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በባለሞያዎች መዘጋጀቱንና ረቂቁ ወደ ታች ለግምገማ ወርዶ እንደተወያዩበት አስተዳዳሪዎቹና አገልጋዮቹ ጠቅሰዋል፡፡

የግምገማው ሪፖርት በሀ/ስብከቱ ተጠናቅሮ የሚቀርብለት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ሳይታወቅ በሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ስም ‹‹በውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች›› በጥናቱ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞና በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ የሚሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ÷ ‹‹ከመሥመር የዘለለ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ አንድነትና ጥቅም እየደከሙ ያሉትን ብፁዓን አባቶች በመድፈር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰድቦ ለሰዳቢ አጋልጧታል፤›› ብለዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በአምስት ሺሕ የአስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ፊርማ አስደግፈው ማቅረባቸውን የገለጹት በመቶዎች የሚቆጠሩ እኒህ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች፣ /ስብከቱ እያካሔደው በሚገኘው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹ወሳኝ አባት›› እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡
ከቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ውጭ በኾኑ፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና ጠባየ ብልሹነት ባለባቸው ውስን ሰዎች ሳቢያ ምእመኑ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዲያመራ እየተደረገ በመኾኑ ጉዳዩ አንገብጋቢ መኾኑን በመጠቆም፣ ‹‹በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ የሚደረግ የስም ማጥፋት ዘመቻና ሰድቦ ለሰዳቢ የመስጠት ሕገ ወጥ ተግባር›› መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከማስጠበቅ ጋራ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአባቶችን ክብር ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ የሚችል ጠበቅ ያለ ሕግ ማውጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡ የጥያቄ አቅራቢዎቹን አቤቱታ ያዳመጡት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ ኹሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመኾናቸው የኹሉንም ሐሳብ የመስማት ሓላፊነት ቢኖርባቸውም በተቃዋሚዎቹ በኩል የተሰማው ሕገ ወጥና ግብረ ገብነት የጎደለው ንግግር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰዋል፤ አኹን ደግሞ በተረጋጋ መንገድ ስለቀረበው የአስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ጥያቄ አመስግነዋል፡፡
በባለሞያዎች የቀረበው የሀ/ስብከቱ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቅ ወደኋላ የሚመለስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ፓትርያርኩ ገልጸው፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና፣ ለሃይማኖት መጽናት የሚጠቅመውን ሐሳብ ኹሉ ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የዘመኑ ምሁራን የተካተቱበት በቁጥር 9 - 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቁን ዳግመኛ እንዲያዩት መቋቋሙን ለጥያቄ አቅራቢዎቹ ያስታወቁት አቡነ ማትያስ፣ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲኖራት የተዘረጋው ሕግ ረቂቅ መሥመሩን እንደማይለቅ አረጋግጠውላቸዋል፡፡