Wednesday, 2 July 2014

የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱን የደገፉ አለቆች በቀል እየተፈጸመባቸው ነው፤ የደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ፣ ካህናትና ምእመናን ዛሬ ለቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት አቤቱታቸውን ያቀርባሉ



St.Urael church bld00
የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን


ፓትርያርኩ እና አማሳኝ አማካሪዎቻቸው÷ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የመልቀቂያ ጥያቄ ካቀረቡት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጋራ የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱን በመደገፍ በቅርበት የሠሩት ውጤታማው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ክብሩ ገብረ ጻድቅ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ላይ ግፊት አድርገዋል – ‹‹ታዝዤ ነው፤ የፓትርያርኩ ጭቅጭቅ አላስቀምጥ አለኝ፡፡›› (ዋ/ሥ/አስኪያጁ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን)

  • የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ይኹንታ የሰጠው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት በቅ/ሲኖዶሱ በተላለፈው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት እንዳይከናወን ተቃዋሚ ነን ባይ አማሳኞችን ያስተባበሩት ዘካርያስ ሐዲስና ኃይሌ ኣብርሃ በውጤታማው አስተዳዳሪ ላይ ‹‹አንተን ባንሠራልኽ›› በሚል ሲዝቱባቸው ቆይተዋል፡፡
  • በተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው እና የአመራር ክህሎታቸው በካህናቱ፣ በሰንበት ት/ቤቱ፣ በአካባቢው ወጣቶችና በአጠቃላይ ምእመኑ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙት ውጤታማው አስተዳዳሪ÷ አንድ ዓመት ባልሞላ ቆይታቸው ከሙስናና ምዝበራ እንዲጠበቅ ያደረጉት የደብሩ ተቀማጭ ገንዘብ ከኻያ ሚልዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
  • በውጤታማው አስተዳዳሪ ምትክ ለመመደብ የታቀደው፣ ‹‹በተቃውሟችን አብረኽን ካልተሰልፍኽ›› በሚል በመልአከ ብርሃናት ክብሩ ገብረ ጻድቅ ላይ ዛቻ ሲሰነዝሩባቸው ከቆዩት አማሳኞች አንዱ የኾነውን ኃይሌ ኣብርሃን ነው፡፡
  • አማሳኙ ኃይሌ ኣብርሃ÷ በውጤታማው አስተዳዳሪ ከምዝበራ ተጠብቆ ከፍተኛ አቅም የፈጠረውን የደብሩን ተቀማጭ በልማት ስም ለመመዝበር፣ በድጋፍ ሰጭነት ከሚሠሩና በስም ተለይተው ከሚታወቁ የደብሩ ልማደኛ ጥቅመኞች ጋራ ቁርኝት በመፍጠር ሲነጋገርበት እንደቆየ ተጠቁሟል፡፡
  • አማሳኙ÷ ከደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከ13.3 ሚልዮን ብር በላይ በመመዝበር በፈጸመው የከፋ ሙስና ከእልቅና ከተወገደ በኋላ ወደ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያለተጠያቂነት ቢዛወርም የአስተዳደር ሓላፊነቱን ትቶ የግል ቢዝነሱን በማጧጧፍ ላይ እንደኾነ ነው የሚነገረው – ‹‹ሳይገባው በውዝግብ የተመደበበትን የአስተዳደር ሓላፊነት እየበደለ ራሱ በሚሾፍረው ሚኒባስ ታክሲ ከመገናኛ – ጣፎ – ሰንዳፋ እየሸቀለ ያመሻል፡፡›› /ታዛቢዎች/
  • የመልአከ ብርሃናት ክብሩ ገብረ ጻድቅ አላግባብ ከሓላፊነት የመነሣት ጉዳይ ነገ በሚካሔደው ሳምንታዊው የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ በፓትርያርኩ አማካይነት በአጀንዳነት እንደሚቀርብ ተጠቅሷል፡፡
  • የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በፓትርያርኩ ግፊት አቅርቤዋለኹ በሚሉት የውሳኔ መነሻ መሠረት፣ ዝውውሩ የሚፈጸመው በደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል እና በሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አድባራት አለቆች መካከል ቢኾንም አካሔዱ የኃይሌ ኣብርሃ ቀጥተኛ ምደባ የሚፈጥረውን ቁጣ ለመከላከል የተቀየሰ ስልት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡
  • ከሐምሌ ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከውጤታማው አስተዳዳሪ ጋራ በመግባባት ሓላፊነቱን በአግባቡ የተወጣውና የአገልግሎት ዘመኑን እያጠናቀቀ የሚገኘው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ባለፈው እሑድ በተከበረው የቅዱስ ዑራኤል ወርኃዊ በዓል ላይ ባቀረበው ዝርዝር ሪፖርት፣ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በርካታ ተግባራት በስኬት መከናወናቸውን ከመግለጹም በላይ የአለቃውን መነሣት በይፋ ተቃውሟል፡፡
  • ልማደኛ አማሳኞች በውጤታማው አስተዳዳሪ የተገታባቸውን ሕገ ወጥ ጥቅም ለማስቀጠል አለቃውን በፓትርያርኩ ግፊት ከሓላፊነት ከማሥነሳት ባሻገር፣ እስከ ልዩ ጽ/ቤት በተዘረጋውና 22 ሚልዮን ያኽል ብር በዘረፉበት የምዝበራ ኔትወርካቸው አማካይነት ቀጣዩን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የምርጫ ሒደት ለመቆጣጠር ቋምጠዋል፡፡
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን በመዋጋት በአዲስ አበባ ደረጃ ለተቋቋመው የማኅበራት ኅብረት ምሥረታ ቀዳሚ አስተዋፅኦ ያደረገው የቅዱስ ዑራኤል አካባቢ መንፈሳዊ ጎልማሶችና ወጣቶች ማኅበር ውጤታማው አስተዳዳሪ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸውን ተቃውሟል፡፡
  • በዐሥራ ኹለት ቀበሌዎች የተቋቋሙ ማኅበራት አንድነት የኾነውና ከኹለት ሺሕ በላይ ወጣቶችን ያቀፈው ማኅበሩ÷ ለአማሳኞች መቅሰፍት፣ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ውጋት መኾኑን በመቀጠል አጥቢያውን ከአማሳኞች ኔትወርክና ከልማደኛ መዝባሪዎች ለመጠበቅ ተዘጋጅቷል፡፡
About these ads

No comments:

Post a Comment