Tuesday, 25 February 2014

ወላይታ ሶዶና አቶ በጋሻው ደሳለኝ

(አንድ አድርገን የካቲት 18 2006 ዓ.ም)፡- በወላይታ ሶዶ  ኦቶና ደ/ጽ/ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከጥር 23-25 በተካሄደዉ ጉባኤ ላይ አቶ በጋሻዉ ደሳለኝ የተናገራቸው ነገሮች ብዙዎችን ያስገረመ ከመሆኑ በላይም አሁንም በሌላ የምንፍቅና ክንፍና በልዩ አስተምህሮ መመለሱን ማመስከር ችሏል፡፡ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ከስርዓተ ቤተክርስቲያን የወጣ በዜማ የታጀበና የረዘመ ‹‹አሜን›› አባባልም ለምዕመኑ አለማምደውት ታይቷል  ፤ ሊቃውንቱ ሲሰብኩ ሰው  ወደ ውስጡ እንዲመለከትና በጥሞና እና በአስተውሎ የእግዚአብሔር ቃል እንዲያደምጥ ሲያደርጉ ነበር እኛ የምናውቀው ፤ አሁን አሁን በአስር ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ከ20 ጊዜ በላይ ‹‹አሜን›› የሚያስብለውን ሆነ ‹‹አሜን›› በማያስብለው ምዕመኑን ጮኻሂ  የማድረግ አዝማሚያ እየታየ ነው ፤  ያ መናፍቃን ቤት የሚገኝው ጩኽት እኛ ቤትም ለመግባት ደጃፍ ላይ እያኮበኮበ ይገኛል፡፡ ለዚህ እማኝ ይሆን ዘንድ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን በቦታው ላይ የተከናወነውን ነገር ይመልከቱ፡፡Click here

አቶ በጋሻው ደሳለኝ በድምጽ ከተቀዳ እማኝ ማስረጃ ላይ በሶስቱ ቀናት ጉባኤ የሚቀጥሉትን መልዕክቶች አስተላልፏል (ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ የድምጽ ቅጅው ፖስት እናደርጋለን)፡፡ አሁንም ቢሆን የድፍረት ቃላቶች የእግዚአብሔር ስም በሚጠራበት ቦታ ላይ ላለመስማት አውደ ምህረት ፈቃጆች ለማን እንደምትፈቅዱ አስተውሉ፡፡


23/05/06 
.

  • ‹‹ቄስ መነኩሴ አትፈልጉ እራሳችሁ ፀልዩ፡፡››
  • ‹‹እኛ ፀልየን ሁለት ህፃናት HIV/AIDS ነፃ ሆኑ፡፡››  
  •  ‹‹ያለ ክርስቶስ ስም ፀሎት አያርግም፡፡››  
  •  ‹‹ክርስቶስ ብቻ ሙሉ ስም ነው፡፡››  
  •  ‹‹ክርስቶስን ብዙ መውደድ ነው እንጅ ብዙ መስገድ አያድንም፡፡››

24/05/06 .
  • በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ይሁዳ ብር ሲያዩ የሚጎመጁ አገልጋዮች አሉ፡፡
  • ‹‹አገልግዬ ወጣቶችን ከብዙ ነገር አስመልጫቸዋለሁ፡፡››
  • ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ለሌላ ለማንም አትስጡ፡፡››
  • ‹‹በነፃነት ለማምለክ መውጣት በክርስቶስ ስም ነው፡፡››
  • ‹‹በትናንትናው የስብከት አገልግሎታችን አንዲት በሽፍቶች ተደብድባ ዓይኗ ጠፍቶ የነበረ እህታችንእኔ እያሰብኩዋት ስለነበር ጉባኤውም እያሰባት ስለነበር ጉባኤው ሲያልቅ ዓይኗ በራ፡፡››
25/05/06 .
  • ‹‹በመዳን ህይወት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ኢየሱስ ነው፡፡››
  • ‹‹የመጣችሁ እንግዶች ካላችሁ እኛ የምንሰብከው ኢየሱስ እንደሆነ እወቁ፡፡››

Monday, 24 February 2014

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የሕንፃ ግንባታ ጥራትና ሒሳብ ምርመራ እንዲዘገይ የሰጠውን ትእዛዝ የተቃወመው የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ከሓላፊነቱ ለቀቀ: የሥራ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ የለቀቀ ኹለተኛው ሰበካ ጉባኤ ነው!


  • የቁጥጥር አገልግሎቱ የሕዝብ ገንዘብና ንብረት ይመርመር በሚል ልዩ ጽ/ቤቱን እያሳሰበ ነው
  • ልዩ ጽ/ቤቱ ከተልዕኮውና ዓላማው ውጭ የሚንቀሳቀስ አማሳኝ መዋቅር ኾኗል
  • የፓትርያርኩን አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት ለማክበር በሳምንት ርቀት ላይ እንገኛለን
???????????????????????????????ሥራው ሙሉ በሙሉ የቆመውንና በሚልዮን የሚቆጠር የምእመናን ንብረትና ገንዘብ የተመዘበረበትን የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ጥራትና ሒሳብ ምርመራ በማዘግየትና በመከላከል አማሳኞችን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ባስተላለፈው ትእዛዝ ያዘኑ የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ከሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተሰማ፡፡
በኹለተኛ የአገልግሎት ዘመኑ ላይ የሚገኘው የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ትላንት፣ የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ረፋድ ላይ ለድሬዳዋ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ÷ በግለሰብ ተጽዕኖና ቁጥጥር ሥር ያለችን ቤተ ክርስቲያን ለማስተዳደር እንደሚቸገሩ በመግለጽ ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ ከሓላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የካህናትም የምእመናም ኾና ሳለ ‹‹ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለግለሰብ አሳልፈው ሰጥተዋታል፤›› በማለት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበሩንና የሕገ ወጥ ጥቅም ተካፋዮቹን መዝባሪነት ለመሸፋፈንና ከተጠያቂነት ለመታደግ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ የሚያስተላልፈውን ተገቢነት የሌለው ትእዛዝ አባላቱ በጽኑ ተቃውመዋል፡፡
ከሒሳቡ ገቢና ወጭ በተጨማሪ ከዲዛየኑ ውጭ እንደተሠራና የግንባታው ጥራትም መፈተሽ እንዳለበት በባለሞያዎች አስተያየት እየተሰጠ መኾኑን የሚገልጹት ምእመናኑ፣ የኦዲት ምርመራው ይዘግይ ቢባል እንኳን የሕንፃ ሥራው ሳይመረመር ከተቋራጩ ተረክቦ ታቦቱን ማስገባት ስለማይቻል፣ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ደረጃ ባለውና በገለልተኛ አማካሪ መሐንዲስ ለማስመረመር ግልጽ ጨረታ ካወጡ በኋላ እያደረጉ የሚገኙት የቅድመ ምርመራ ዝግጅት ቀጥሎ ምርመራው መተግበር እንዳለበት በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡
የሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪውን ጨምሮ ካሉት ዘጠኝ አባላት መካከል በትላንትናው ዕለት መልቀቂያቸውን ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በተናጠል ያስገቡት አራት ምእመናን ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ የደብሩ አገልጋይ ካህናት ሲኾኑ ነጻ አገልግሎት እንደሚያበረክቱት ምእመናን መልቀቂያ ባያስገቡም ከምእመናኑ ጋራ የአቋም አንድነት እንዳላቸው ተገልጧል፡፡
በውል ከተያዘው ጊዜ ውጭ ለስድስት ዓመታት ከዘገየውና ከስምንት ሚልዮን ብር በላይ ለምዝበራ ከተጋለጠበት ከዚኹ የሕንፃ ሥራ ጋራ በተያያዘ ከአኹኑ በፊት የነበረውና ሕገ ወጥ አሠራርን የተቃወመው ሰበካ ጉባኤ፣ ከቃለ ዐዋዲው ውጭ ተጠሪነታቸውን ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ባደረጉት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ብርሃኔ መሐሪ ግፊትና በቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ውሳኔ የሥራ ዘመኑን ሳይጨርስ ታግዶ ከአገልግሎት ውጭ የኾነ ሲኾን ከተመሳሳይ ውዝግብ ጋራ በተገናኘ የሥራ ዘመኑን ሳይጨርስ ከሓላፊነት የለቀቀው የአኹኑ ሰበካ ጉባኤ ሁለተኛው ነው፡፡
የተሟጋች ቡድን ወገን ከኾኑና ቀደም ሲል ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በተቃውሞ ለቀው በወጡ ምእመናን ጥያቄና በቀድሞው የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፈቃድ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ኦዲት ቡድን ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. ለወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባቀረበው ሪፖርት÷ ከደንብና መመሪያ ውጭ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለተቋራጩ መከፈሉ ተረጋግጦ አፈጻጸሙ በሀ/ስብከቱና በሰበካ ጉባኤው ሕጋዊ ማስተካከያ እንዲደረግበት መመሪያ ተላልፎ ነበር፡፡
የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ባለፈው ዐርብ ምሽት ለሀ/ስብከቱ በጻፈውና በብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ በወጣው ደብዳቤ ግን፣ በዚኽ የኦዲት ሪፖርት ከተገለጹ ግኝቶች በተፃራሪ ‹‹ምንም ችግር እንደሌለ የቤተ ክህነቱ ልኡካን ማረጋገጣውቸውን›› እና ‹‹የሕንፃው ግንባታ ምርመራ ሳያስፈልገው እንዲቀጥልና ታቦቱ እንዲገባ ሒሳቡም ታቦቱ ከገባ በኋላ እንደሚመረመር›› የሚገልጽ ነው ተብሏል፡፡ ዘግይቶ እንደተሰማውም የግንባታ ጥራቱና የወጭና ገቢ ሒሳቡ በምርመራ እስኪታወቅ ድረስ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ላይ የጣለው የገቢ ማሰባሰብ እገዳም የብርሃኔ መሐሪ የጥቅም ተካፋይ እንደኾነ በሚነገረው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ደብዳቤ እንዲሻር ተደርጓል፡፡
የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በማይመለከተው ጉዳይ የሰጠው የምርመራ ማዘግየትና መከላከል ትእዛዝ አግባብ እንዳልኾነና ተመዝብሯል የተባለ የሕዝብ ገንዘብ ቋሚ ሲኖዶሱ መስከረም ፱ ቀን ፳፻፮ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት መመርመር እንዳለበት የገለጸው የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ኹኔታው ከአቅሙ በላይ እንደኾነ በአዲስ አበባ ለሚገኙት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ማስታወቁ ተነግሯል፡፡
ሊቀ መንበሩ አቶ ብርሃኔ መሐሪ ከሦስት ተቀጣሪ ሠራተኞቻቸው ጋራ ብቻ በቀሩበት በዚኽ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የሚፈጸመው ሕጉንና ደንቡን የጣሰ አሠራር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ኦዲት ቡድን ከሦስት ዓመት በፊት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ በተሰጠው የብፁዕ ዋ/ሥ/አስኪያጁ መመሪያ ሳይስተካከል አኹንም ቀጥሎ በአነስተኛ ስሌት ከብር ስምንት ሚልዮን ግምት ያለው የሕዝብ ገንዘብና ንብረት መመዝበሩን የምእመናን ተሟጋች ቡድን በ፳፻፬ ዓ.ም.፣ የቋሚ ሲኖዶስ ልኡክ በ፳፻፭ ዓ.ም. ባደረጓቸው ክትትሎች መረጋገጡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ቅድስና የሚመኙ፣ በተግባርም ለመደገፍና በነጻ ለማገልገል የሚፋጠኑ፣ የተለያዩ ሞያዎች ያሏቸው ምእመናን ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ጀምሮ ወሳኝ መዋቅሮችን በተቆጣጠሩ አማሳኞችና ጎጠኞች የጥቅም ሰንሰለት ተማረው ከአገልግሎት ውጭ መኾናቸው እስከ መቼ???
His Holiness Abune Mathias briefing the pressብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁለተኛው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ያሰሙትን አስቸኳይ የእርምት ርምጃ ጥሪ መሠረት አድርጎ በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተቋቋመው የፀረ ሙስናና መልካም አስተዳደር ዐቢይ ኮሚቴ ለጥቅምቱ ፳፻፮ ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤ ባቀረበው የመሪ ዕቅድ ማህቀፍ ከቤተ ክርስቲያናችን ዕሴቶችና መርሖዎች አንጻር የሙስና ትርጉም፣ ሃይማኖታዊ አስተዳደራዊና ሞያዊ ሥልጣንንና ሓላፊነትን አላግባብ በመገልገል የግል ጥቅምን በማካበት ብቻ ሳይኾን ምእመናን በመከፋፈልና በማጋጨት፣ ፍትሕን በማሳጣትና በማዘግየት ተነሣሽነታቸውን መጉዳት፣ ከአገልግሎት ማራቅንና ከሃይማኖታቸው እንዲወጡ መንሥኤ መኾንን ያጠቃልላል፡፡
ቃል የገቡበትንና በሓላፊነት የተረከቡትን ወይም የተሾሙበትን አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣን እና የሞያ ሓላፊነት በመፃረር ንብረትንና ገንዘብን ማባከን ወይም ለግል ጥቅም ማዋል ወይም ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መሳካት ውጤት ያመጣሉ ተብለው ለአገልግሎት የተነሣሱና የተሰለፉ አገልጋዮችና ሠራተኞች ውጤታማ እንዳይኾኑ ግልጽ በኾኑ የተለያዩ መንገዶች ማሰናከል፣ ዕውቀታቸውን ማባከን ኹሉ ሙስና ነው፡፡
ሙስናን በመግታት የቤተ ክርስቲያናችንን መሠረታዊ ተልእኮ ለማስፈጸም የግለሰቦችን ወይም የቡድንን ወይም የአንድን ተቋም አሠራር፣ ጠባይና አስተምህሮ ያጤነ ግንዛቤ መወሰድ እንደሚገባው የሚያሳስበው ገለጻው÷ የተለያዩ የለውጥ አማራጮችን ለመተግበር በታሳቢነት ሊያዙ ይገባል ካላቸው የምእመኑ ክርስቲያናዊና ተጨባጭ ኹኔታዎች መካከል የሚከተለው ሐተታ ይገኝበታል፡-
  • ሙስና የሰለቸው፣ ፍትሕ የተጠማ፣ በሃይማኖቱ  ስም ያሉ ምግባረ ብልሹ አገልጋዮች ያስመረሩት ሕዝብ ነው፡፡ በመኾኑም ፍትሕና ርትዕ በአስቸኳይ ተግባራዊ ኾነው ማየት ይፈልጋል፡፡ ይህን ኹኔታ የሚያሰፍኑ ተግባራዊ ርምጃዎችን ሁሉ ከልቡ ይደግፋል፤ ይሳተፋልም፡፡ ተሳትፎው አሉታዊ እንዳይኾንና በሌሎች ኢ-ክርስቲያናዊ አጀንዳ ባላቸው ኃይሎች እንዳይጠለፍ ጥበቃ፣ መረጃና፣ ሰፋ ያለ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
  • መንፈሳዊና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሕዝብ ነው፡፡ በመኾኑም ከላይ የተከበሩና ከሐሜት ነጻ በኾኑ አባቶች የሚነገረውን በተግባር ተፈጽሞ እስከተመለከተ ድረስ ያለማወላወል ገንዘቡን፣ ጊዜውነና ዕውቀቱን ለመስጠት የተዘጋጀ ሕዝብ ነው፡፡ በመኾኑም በለውጡ የሚነገሩ ዜናዎችና የታወጁ የለውጥ አቅጣጫዎች ኹሉ እየተፈጸሙ የሚታዩ መኾን ይገባቸዋል፤ የማይደረግ መነገር የለበትም፤ እምነት ያጎላልና፡፡
የስድስተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት ለማክበር በሳምንት ርቀት ላይ እንገኛለን፡ ከቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣመውን የቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ ብልሽት በሥር ነቀል የማስተካከያ ርምጃዎች ማረም ፓትርያርኩ ከበዓለ ሢመታቸው ቀን ጀምሮ ቀዳሚ ትኩረት የሰጡት አጀንዳ ነው፡፡
አማሳኝነትና ጎጠኝነት መገለጫው ያደረገ ቢሮክራሲን መስተካከል በአጭር ጊዜ ለማምጣት አዳጋች ቢኾንም የቤተ ክህነቱን የተቋማዊ ለውጥ መሠረት ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ እጅግ አስፈላጊ፣ እጅግ አስቸኳይ መኾኑን ቅዱስነታቸው በመግለጫዎቻቸው አሳስበዋል፡፡ በቆሙባቸው መድረኮች ኹሉ ሓላፊነት፣ ሐቀኝነትና ተጠያቂነት የተሞላበት መልካም አስተዳደር ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ እንዲሰፍን ደጋግመው ተናግረዋል፤ እንዲያውም ‹‹መልካም አስተዳደር ከሌለ ኹሉም ነገር ከንቱ እንደኾነ እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡
ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ እንደተነሣው ኹሉ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ምዕራፍ ከፋች በኾነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ልናደርግ የሚገባንን ምግባረ ሠናይ ኹሉ በመፈጸምና በማስፈጸም በያለንበት ደጀንነታችንን ለማረጋገጥ መነሣሣት እንደሚጠበቅብን አባታዊ ትምህርት፣ መመሪያና ቃለ በረከት ሰጥተውናል፡፡
ከቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልዕኮ ጋራ የሚጣጣም ሥር ነቀል የለውጥ ርምጃ በቆራጥነት ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ በፓትርያርኩ ፊታውራሪነትና በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በተቋቋሙት የፀረ ሙስና፣ የአስተዳደር መሻሻል እና የገንዘብ አያያዝ ሥርዐት ማሻሻያ ዐበይት ኮሚቴዎች ተደራጅቷል፡፡ ዛሬ ከአንድ ዓመት በኋላ የት ነን? ከቃለ ነቢብ(rhetoric) ውጭ ምን የተግባር ርምጃ አስመዘገብን? ምን ውጤት አገኘን?

Wednesday, 19 February 2014


አባ ሰረቀ ብርሃን ‹‹በታቦት ዝርፊያ›› ክስ ብጹዕ አቡነ ማትያስ ዘንድ ቀርበው ነበር


  • ‹‹ለዚህ መረጃ አቡነ ማትያስ ቀድሞ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በአሁን ሰዓት 6ተኛው ፓትርያርክ፣ አቡነ ሣሙኤልና አቡነ ኢሳይያስ ህያው ምስክሮች ናቸውና›› መረጃውን የላኩልን የሎሳንጀለስ ምዕመን
  • ‹‹አባ›› ሰረቀ ታቦት ሰርቀው ተይዘዋል፡፡ ከገዛናቸው 12 ጸናጽል ያስረከቡን ስድስቱን ሲሆን 12 መቁዋሚያም 6ቱን ይዘውብን ሄደዋል፡፡
  • ‹‹አቡነ አረጋዊም የሚባል ቤተክርስቲያን የለም፡፡›› ‹‹አባ›› ሰረቀ ብርሃን በአንድ ወቅት የሰበኩት ስብከት
  •  ‹‹በወቅቱ የአሜሪካ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት አቡነ ማትያስ ማኅተም ወስደው በነጭ ወረቀት ላይ እያተሙ የኔን ፊርማ እያስቀመጡ ሰዎችን ብር እየተቀበሉ ከኢትዮጵያ ወደዚህ ሲያመጡ ተደርሶባቸው..........››
    በወቅቱ አባ ሰረቀ ከጓደኛቸው ጋር ሲሰሩት የነበረ ሥራ የምዕመኑ ቃል
ከአንድ የሎስ አንጀለስ ምዕመን የደረሰን መልዕክት 

(አንድ አድርገን የካቲት 11 2006 ዓ.ም)፡- በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት ሊካሄድ የታሰበው የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ በአባ ሰረቀ ብርሃን አማካኝነት ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተሰጠ መመሪያ መሠረት ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል፡፡ የአባ ሰረቀን  የቀድሞ ተግባር በርካታ ምዕመን ቢያውቀውም  ብጹዕ አቡነ ማትያስ የሚያውቁትን እና በሎስአንጀለስ ምዕመናን ላይ ያደረሱትን በደል የደረሰንን መልዕክት ለእናንተው ለማድረስ ወደድን፡፡ ‹አባ› ሰረቀን ከአመታት በፊት በታቦት ሌብነት ብጹዕ አቡነ ማትያስ ዘንድ ቀርበውም እንደነበርም መረጃው ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ቅዱስነታቸው አሁን እየሰሩ የሚገኙት ቀድሞ  ለሰሚ ጆሮ የሚከብድ ዝርፊያ በቤተ ክርስቲያን ላይ ካደረገ ሰው ጋር መሆኑን ነው፡፡ እስኪ በወቅቱ የነበሩ ህያው ምስክሮች የላኩልንን መረጃ ይህን ይመስላል፡፡

አባ ሰረቀ ማን ናቸውከዚህ በፊት ያልተሰሙ ወሬዎችን ያንብቡት
ምንም እንኳን የሰሩት ሥራ ያደረጉት አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር አንቱ ለማለት ቢያስቸግርም የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ፣  የሀገራችን ባህል አስገድዶኝ  አንቱ  በማለቱ እቀጥላላልሁ  አባ ሰረቀ ብርሃን (እዚህ ባለሁበት ሎሳንጀለስ ከተማ) ታቦታቸውንና ንዋያት ቅዱሳታቸውን ዘርፈው ስለሄዱ አባ ሰራቂ በማለት ይጠሯቸዋል አንዲት የቤተክርስቲያናችን አዛውንት ስማቸው እንኳን ሲጠራባቸው  የሚያንገሸግሻቸው አውቃለሁ። 
ወደ ዋናው ቁም ነገር ልግባና አባ ሰረቀ  በሎሳንጀለስ እንዴት ነበሩ የሚለውን እስኪ እንመልከት፦ 
አባ ሰረቀ ብርሃን 1993 መስከረም ላይ ከኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ይህንን መረጃ የሰጡን አባት እንዲህ ያጫውቱናል። ‹‹አባ ሰረቅ ብርሃንን ለማስመጣት ሂደቱን የጀመእኩት እኔ ነኝ። 1993 ... የእህቴን ባል እባክህ ጥሩ ካህን የተማረና ሰዎችን የሚያስተምር ሰው ፈልግልን ብዬ ነገርኩት። እርሱም ወዲያው አንድ በጣም የተማሩ ሰው አግኝቸልሃልሁ ብሎ አጫወተኝና (በኢትዮጵያም ክረምት አካባቢ ነው) ደስ አለኝ። ደውዬም እንዳነጋግራቸው አመቻቸልኝና አባ ሰረቀን ድውዬ አገኘኋቸው። እርሳቸውም ለመምጣት እፈልጋለሁ ግን ለመጉዋጓዣ 2000 ዶላር ያስፈልገኛል ብለው ነገሩኝ። እኔም ቦርዱን አስፈቅጀ የመምጫቸውን ሁኔታ ጀመርን።2000 ዶላርም ተላክላቸው። ››
በኋላም ስለመምጫቸው ተነጋግረን ንዋያተ ቅዱሳት (ጽናጽልና መቋሚያ ) እንዲሁን ጽላትም ጭምር እንደሌለን ስነግራቸው፤ ሁሉንም ማግኘት እንደሚችሉ፤ ነገር ግን ተጨማሪ 1000 ዶላር እንደሚያስፈልግ ነገሩኝ። ያንንም ቦርዱን አስፈቅጀ ላኩላቸው።  መስከረም 1993 ... 12 ጸናጽል፣ 12 መቋሚያና ጽላት ይዘውልን ሎሳንጀለስ ገቡ። እኛም አባት ናፍቆን ስለነበረ ምንም እንኳን ያወጣነው ወጭ ብዙ ቢሆንም በደስታ ተቀበልናቸው። ስላሁሰንና ዌስት (between Slauson and West) ላይ አንድ የአድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ተከራይትን አገልግሎት ማግኘት ጀመርን። 
ትንሽ ቆይቶም አባ ተከስተ የሚባሉ መነኩሴ (የዛሬው ብጹእ አቡነ ሣᎀኤል) ወደዚህ እነደሚመጡ ተነገረንና እኔው ተቀብዬ አብረው መኖር ጀመሩ። የሚገርመው ግን አባ ሰረቀ ከሰው ጋር ተስማምቶ መኖርን ስለማይፈልጉ፤ አባ ተከስተ ጋር አለመግባባት ፈጠሩና አባ ተክስተ ወደ ሌላ ስቴት ሄዱ። 
ከዚያም እርሳቸውም ብቻቸውን እንዳይሆኑ በማለትሳንሆዜ የነበረ አንድ ይሥሐቅ የሚባል አገልጋይ ልናመጣልዎት ነበር” ብንላቸው ያሉንን እስከ አሁን አስታውሰዋለሁ ‹‹እኔ ቤት አንድ ሰው አይገባም›› ነበር  በወቅቱ ያሉት። ያን ጊዜ ነበር አባ ሰረቀ ላይ የነበረው እምነታችን እየተሸራረፈ የመጣው። እንደምንም አግባብተን ልጁን ብናመጣውም አሁንም እርሱም የአባ ተክስተ እጣ ደርሶት አባረሩትና ሄደብን። 
መቼም የኛ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ ነችና ከአሪዞና አባ ወልደ ሰንበት የሚባሉ አንድ መነኩሴ ደግሞ አስመጣንላቸው። ለካስ ሁለቱም መሰሪ ነበሩና የሚከተለውን ምእመናን የማይረሱትን አሳዛኝ ሥራ ሰሩ። 
‹‹ቀኑ እሁድ ነው አስታውሳለሁ አባ ስረቀና አባ ወልደ ሰንበት ቅዳሴ ቀድሰው ሲያበቁ አባ ሰረቀ ለእኔና ለጓደኞቸአባ ወልደ ሰንበት ወንድሙ ስላረፈ ልናረዳው ነው ምን ትላላችሁአሉ። እኛም አዝነን አሁን ቅዳሴ ቀድሰው ከምንነግራቸው ለምን ሳምንት ወይንም ነገ አንነግራቸውም አልናቸው። እርሳቸውም እሺ ብለው እኛን ከላኩ በኋላ ረድተዋቸው ነበርና ወዲያው ደውለው አርድቻቸዋለሁና ተባልን በጣም ሁላችንም ተመልሰን መጣን እውነት መስሎን በጣም አዝነን አባ ወልደ ሰንበትንም አጽናንተን ተመለስን። ከዚያም ወደ ሀገራቸ መመልስ እንደሚፈልጉ አባ ሰረቀ ነገሩን እኛም አዝነን ያለንን አዋጥተን ላክናቸው። ትዝ የሚለኝ ለቤተሰቦቻቸውም አምነዋቸው ብር አድርሱልንም ያሉ ሰዎች ነበሩ። ግን አባ ወልደ ሰንበት ሳያደርሱላቸው ብራቸውን በዚያው በልተው ቀርተዋል። 
ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ የአባ ወለደ ሰንበትን እህት ወይዘሮ አብርኸትን የሚያውቅ አንድ የቤተ ክርስቲያናችነ አባል፤ አዲስ አበባ ሄዶ ወይዘሮ አብርኸትን ያገኝና ‹‹እባክሽ የወንድማችሁን መሞት ሰምተን እኮ አባን አጽናናቸው ቢሏት››  የምን ወንድም ነው የምታወራው? ትለዋለች። ለካስ አባ ወልደ ሰንበት ወድማቸው ሞተ ትብሎ የተነገረው የውሸት ኑሯል። አባ ሰረቀና እርሳቸው የፈጠሩት ውሸት መሆኑን አወቅን። ከዚያ በኋላ ይኸው አባ ወልደ ሰንበት በወቅቱ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ እንደዘገበው በወቅቱ የአሜሪካ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት አቡነ ማትያስ ማኅተም ወስደው በነጭ ወረቀት ላይ እያተሙ የኔን ፊርማ እያስቀመጡ ሰዎችን ብር እየተቀበሉ ከኢትዮጵያ ወደዚህ ሲያመጡ ተደርሶባቸው መጀመርያ ወደ ጀርመን አሁን ደግሞ መቼም ጅብ በማያውቁት ሀገር እንደሚባለው በገለልትኞች ሲኖዶስ ጳጳስ ሆነው ካናዳ ይኖራሉ። 
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ ሰረቀ አባ ወልደ ሰንበትን እንዲህ አድርገው ከአጠገባቸው ካራቁ በኋላ ከቤተ ክርስቲያን አባልት ጋር መግባባት አልቻሉም። ከእለታት አንድ ቀን እንደውም ‹‹ቤተክርስቲያን የለችም አቡነ አረጋዊም የሚባል ቤተክርስቲያን የለም ›› በማለት ሲስብኩ አስታውሳለሁ። ይህ በእምነታችን የሌለ ኑፋቄ ነው። ከዚያም በኋላ ከቤተክርስቲያናችን ተለይተው ‹‹የአቡነ ጳውሎስ እንደራሴ ነኝ እኔ ማንንም መነኩሴ ጳጳስ እንዲሆን አስደርጋለሁ››  ከሚለውና እዚሁ ሎሳንጀለስ ከሚኖረው ቄስ ጋር ገጠሙና ከእኛ ጋር መጣላት ጀመሩ። ከዚያም አቡነ ማትያስ ለጥቅምት አቡነ አረጋዊ ሲመጡ ምእመናን ክስ አቀረቡ። ውይይቱ የተደረገው በወዳጃችን በ አቶ ዕቁበ ጽዮን ቤት ነበር። ብጹእ አባታችንም ቢመክሩዋቸው አልሰማ አሉ። አባ ሰረቀንም ብጹእ አቡነ ማትያስ ምእመናኑ ምንም አልበደሉምና ‹‹ተሳስባችሁ አብራችሁ ኑሩ›› ቢሉዋቸው አባ ሰረቀ ‹‹ከአሁን በኋላ እዚህ አላገለግልም›› ብለው ካበቁ በኋላ ትንሽ ቆይተው ለአቡነ ማትያስብርሌ ከነቃ…” የሚል መልስ ሰጧቸው። 
ብጹእ አቡነ ማትያስም ‹‹እንግዲያውስ እናንተም ሌላ ካህን ፈልጉ እርሳቸውንም መጓጓዣ ከፍላችሁ ላኳቸው ፤ እርሳቸውም ንዋያተ ቅዱሳቱን ፤ ታቦቱን ጭምር ያስረክቧችሁ›› ተባለ  (ይህንንም በዚያን ጊዜ አባ ኢሳይያስ- የሳንዲያጎ ገብርኤል አስተዳዳሪ የነበሩ- የአሁኑ ብጹእ አቡነ ኢሳይያስ ያረካክቡዋችሁ ተባለ)  እኛም አዝነን እሺ ብለን 700 ዶላር ከምዕመናን ሰበሰብንና / ኃይሉ አቶ ጥላሁንና አንድ ሌላ ሰው ወክለን አባ ኢሳይያስን ይዘው እንዲረከቡ ላክናቸው። 
ከዚያም አባ ሰረቀ በለመዱት አንደበታቸው የተወከሉ ምእመናንን ታቦቱን ነው የያዝኩት ብለው ብሪፍ ኬዝ ይዘው መጡና ይህንን ለመነኩሴው ለአባ ኢሳይያስ ብቻ ነው የማስረክበው በማለት ወደ ውስጥ ሁለቱ ብቻ ገቡ። ብዙ ቆይተው ሲወጡ አባ ኢሳይያስን የተወከሉት ሰዎች ‹‹ታቦቱን ተረከቡ ወይ?›› ሲሉዋቸው ታቦት ተረከብኩም አልተረከብኩም አይባልም አሏቸው። 
ተወካዮችም ግራ ግብቷቸው ሲመለሱ አባ ኢሳይያስም ለብጹእ አቡነ ማትያስ ደውለው ታቦቱን እንዳልተረከቡ እንደውም ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ አባ ሰረቀ ብሪፍ ኬዙን ሳይከፍቱ ይረከቡ ይሏቸዋል። አባ ኢሳይያስም ‹‹ይክፈቱት እንጂ እንዴት ዝም ብዬ እረከባለሁ›› ይሉና ተቀብለው ቢከፍቱት የተገኘው ታቦት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ፤ ከዚያም አባ ሰረቀ እግራቸው ላይ ወድቀው ‹‹እባክዎን አልተቀበልኩም ብለው ለተወካዮች አይንገሩብኝ ፤ ታቦቱን ዲሲ ልኬዋለሁ እዚያ ሄጄ ለአቡነ ማትያስ እሰጣለሁ ወይንም እልከዋለሁ›› ብለዋል ይሏቸዋል። 
ይህንን ነገር አቡነ ማትያስ ሲሰሙ በጣም አዝነውና ተናድደው ነገሩን ምእመናን እንዲሰሙ ያደርጋሉ። ሁለቱም አባቶች (አቡነ ማትያስና አቡነ ኢሳይያስ በሕይዎት ስላሉ ህያው ምሥክር ናቸውና ስለ እውነትነቱ እነሱው ሊጠየቁ ይችላሉ።ከገዛናቸው 12 ጸናጽል ያስረከቡን ስድስቱን ሲሆን 12 መቁዋሚያም 6ቱን ይዘውብን ሄደዋል። ምእመናንም በዚህ ተናድደን ያዋጣነውን ገንዝብ ሳንሰጣቸው ቀርተናል። ከሁሉ የሚገርመኝ ሲሄዱ አንዲት ምዕመን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሰንና ብርን ይስጡን ብለን ስንጠይቃቸው ፤  ‹‹መልሳ ወስዳዋለች›› አሉን። ይህ ሁሉ እንግዲህ በሎሳንጀለስ የነበራቸው ታሪክ ነው። 
አንድ መነኩሴ ከሰረቀ ፤ ከዋሸ ፤ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ስልጣን ፤ ገንዝብና ክብርን ከፈለገ እንዴት መነኩሴ ይሆናል። በአሁኑ ሰዓት የሚያደርጉት ብጥብጣ እኔ ከአባ ሰረቀ የማልጠብቀው አይደለም። እርሳቸው፤ ከሰው ጋር ተስማምተው የማይሰሩ ፣ የሚዋሹና በሃሰት ማንኛውንም ኃጢያት ሁሉ ሊሰሩ የሚችሉ ሰው ናቸው። ለዚህ ደግሞ አቡነ ማትያስ ቀድሞ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ አሁን 6ተኛው ፓትርያርክ ፣ አቡነ ሣሙኤል፤ አቡነ ኢሳይያስ ህያው ምስክሮች ናቸውና ፡፡ እነሱን በመጠየቅ ወይንም ለእኔም በመደወል የበለጠ መረጃ ማግኝት ይቻላል ብለውናል። 
በአጠቃላይ አባ ሰረቀ ማለት  ለእምነታቸው ሳይሆን ለሆዳቸውና ለገንዘብ የሚኖሩ ፤ ካለ ፍርኃት የሚዋሹ ፤ ካለ ሃፍረት የሚሰርቁ ፤ ከሰው ጋር ተባብረውና ተግባብተው መኖርን የማያውቁ ሰው ናቸው። 
እርሳቸው ከሄዱ በኋላ ስድስት ወራት ሙሉ ካለ ካህን እሁድ እሁድ ምእመናን ብቻችንን ተሰብስበን አቶ እቁባይ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡልን እንበተን ነበር። በኋላ ይኼው እስከ አሁን የሚያገለግሉንን ታላቅ አባቶች አግኝተን እንገለገላለን፡፡ እንደውም ባለፈው ዓመት ቤተ ክርስቲያን ገዝተን ገብተናል። በአሁኑ ሰዓትም ከልብ የሚያገለግሉ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ታላላቅ ምእመናን ያላት ቤት ክርስቲያን በማግኘታችን ደስትኞች ነን። በማለት አባ ሰረቀ ቤተክርስቲያን ላይ ያደረሱትን በደል ከብዙ በጥቂቱ እንዲህ አቅርበውልናል፡፡
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን