Sunday, 13 April 2014

ዋጋ የሚያሰከፍሉ ጥፋቶች!

ትዉልዱ የሚከፍለዉ ነገር ግን ሊከፍለዉ የማይገባዉ ዋጋ! ይህ ትዉልድ ስለ ሃገሩና ስለ ሃይማኖቱ የከፈለዉን ዋጋ ምንም የሚወዳደረዉ የለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከማንም ክርስቲያን ልብ ዉስጥ ከማይጠፉት ከምዕመናኖቿ ጋር የተወጣቻቸዉን ሁለት ክፉ አጋጣሚ እንመልከት፡-
. የዮዲት ጉዲት
.የግራኝ መሐመድ …. እያሉ መቀጠል ይቻላል፤
ነገሥታት እና መንግስታት በመጡ ቁጥር አንዳቸዉም አልበጇትም ሊያስብል በሚችል መልኩ ጠላቶቿ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነትና በሕዝቦቿ አንድነት ግን የተቃጣባትን መከራ ሁሉ ብዙ ዋጋዎችንም ከፍላ ቢሆን ተወጥታዉ እነሆ 21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ደርሳለች ሆኖም ግን ጠላቶቿ እየበዙ ሄዱ እንጂ ወዳጅ አላፈራችም፡፡
እንደ ግራኝ መሐመድና እንደ ዮዲት ጉዲት ቀጥታ በቤተክርስቲያን ላይ ታጥቀዉ አይምጡ እንጂ ጉዳት በማድረሱ ግን (ከሁለቱ ዘመናት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በማቃጠል፣በመዝረፍ፣በማሸሽ፣ቤተክርስቲያንን በማቃጠል፣ካህናትን በማሰር፣በማወክ፣በመግደል …. ) ከትላንት ሳይብስ አይቀርም፡፡ ትላንት ርስት ጉልት የነበራት ቤተክርስቲያን ዛሬ አጥሮቿ እየተነቀሉ ይገኛል፤ ታላላቅ ሃገራዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸዉን ሥራ የሰራች ቤተክርስቲያን ለእነሱ አካሄድ ስላልተመቸች ባሏት ልጆች ዳር ድንበሯን አናስደፍርም፣ የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም ባሉ ….ወዘተ ምክንያቶች ከአሸባሪነት እየፈረጇት ይገኛል፡፡
አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብልህነት ሳይሆን ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነዉ!
ሰዉ ለሚጠቅመዉና ለተጠቀመበት ነገር ዋጋ ይከፍላል፤ መክፈልማ አለበት ህግም ያስገድደዋልና፡፡

አዉራዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ባሳለፋቸዉ ሁለት አስርት ዓመታት ዕድሜ ዘመኑ ግን ምንም እንኳን የአንድ አፍላ ጎረምሳ ዕድሜ ቢያሳልፍም (በዛሬዉ ዘመን አቆጣጠር ከአንድ ዩኒቨርስቲ የተመረቀ ምሁር ወጣት ቢሆንም)  ስራዉ ግን ሲፈተሽ ዕቃቃ ሲጫወት የቡድኑን አባላት የጫወታ መንፈስ የሚያዉክ አንድ አስቸጋሪ ህፃን ባህሪ እየያዘ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ አካሄዱ ደግሞ ለድርጅቱ ህልዉና ብቻ ሳይሆን እንደኔ ግላዊ አመለካከት ደግሞ አገሪቱ ለተያያዘችዉ ሰላም የማስፈን፣ልማትን የማፋጠን፣ድህነትን የመዋጋት አጀንዳየሚያደናቅፍ፤ የልማት ሠራዊቱንም የሚያመናምን መስሎ ይታየኛል፡፡(የእኔ የግል አጀንዳ ምንም እንኳን ያለምንም መደራደሪያ አገር ወደ ተሻለ ሰላም እና ዕድገት ማድረስ እና ለዜጋዎቿ ሰላምን መስጠት ቢሆንም ጠንካራ እና ዓላማ ያለዉ አባል አልጠላም፤ ለእንብላዉ ያልተሰበሰበ፡፡)
ለማሳያነት ህገ-መንግሥቱን ጥሶ በሃይማኖቶች ጣልቃ በመግባት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማዋከብና አቅም ማሳነስ፣ አባላቶቹንና የፖለቲካ መሪዎቹን ሰበባሰበብ ፈልጎ በፀረ ሽብሩ አዋጅ አሳቦ የእስር ቤት ሲሳይ ማድረግ፣ማህበራትን ማፍረስ፣ አላስፈላጊ ህጎችን ለራሱ ማጥቂያነት እንዲመች አድርጎ መደንገግ….እነዚህ ሁሉ መንግስት ያለአግባብ የሚከፍላቸዉ ዋጋ እና ለራሱ እያቆየ ያለዉ ግፍ ነዉ፡፡ (እነዚህን ነገሮች ስንጠቅስ የተነሱት ነገሮች ሙሉ ለሙሉ አገርን አልጠቀመም ለማለት አልደፍርም ሚዛናዊነት የጎደለዉ ይሆንብኛልና አገርንም ከጥፋት ሃይሎች መታደጉ የማይካድ ነዉና ንፁሃንን የመበቀያ መሳሪያ የመሆኑንም ያህል ኢህአዴግ የጠላዉን አናቱን መባያ መዶሻዉ ነዉና!) 
አንድ ዓይን ያለዉ በአፈር አይጫወትም እንደሚባለዉ አሁን ባለችዉ ፀጥታና ሰላም ወቅት ልማቱን እንደማፋጠን አንዳንድ ከልማቱ ዉጭ ሆነዉ በቦዘነ/ሥራ በፈታ አዕምሮአቸዉ ነገር በሚፈጥሩ/በሚፈበርኩ (ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ወርክሾፕ ይሆናል እንዲሉ አበዉ) ሰይጣናዊ ሥራ በመሸረብ የተጠመዱ አሉ፡፡ ይህም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ሞክረዉ ያልቻሉትን ሲያገረሽባቸዉ እየቆዩ የጥፋት ስራቸዉን ማቀናበር ይጀምራሉ … … ከዚህ ቀደም ጥቃቅን ባለስልጣናትን የመንግስትን ስም ሊያጎድፉ ሲነሱ፣ህብረተሰቡን ሲበድሉ ስናይ ስንሰማ፣ መብራት ሲጠፋ፣ኔትወርክ ሲቋረጥ፣ ዉሃ ሲጠማን ….  " ይድረስ ለመንግስታችን …" እያልን አቤት! ስንል ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም በቱባ ባለስልጣናቱ የገዳማትን (እነ ዋልድባን) ይዞታ መንጠቅ እና ገዳሙን መፍታት፣ አባቶችን ለእስር በመዳረግ፣ወዘተ  የተጀመረዉ የቤተክርስቲያንዋን የጀርባ አጥንት የሆነ ማህበር "ማህበረ ቅዱሳን" አጽራረ ቤተክርስቲያንን አስርጎ ከማስገባት እስከ ለማፈራረስ እና ደብዛዉን ለማጥፋት መነሳት የጥፋት ጅማሬዎቹ ነበሩ፡፡(ያለወደደዉን የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት መበተን ስራዉ እንደሆነ ልጆች ሳለን ሰንበት ትምህርት ቤት ስንማር በነበረበት አካባቢ  ሰንበት ትምህርት ቤቱን ከመንግስት ሊሰልሉ መጥተዉ ምንም እንከን አጥተዉ ተሰብከዉ ንስሐ ገብተዉ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሆኑ ምዕመናን ምስክሮች ናቸዉ )
ይሁን እንጂ "የሲዖል ደጆች አይችሉአትም … " የተባለላት ቤተክርስቲያን ዛሬም ጸንታ ፍሬዋን እያፈራች ትገኛለች፤ ሆኖም ፍሬዋን እየተመገቡ ያደጉትም፣ በአፍኣ ያሉትም፣ በአንድነት ተባብረዉና የዉስጠኞቹ ለዉጨኞቹ ክንድ እየሆኑዋቸዉ ዛሬም በጠላትነት እየተነሱባት ግማሹ በማደስ ሰበብ፣ ግማሹ በቃ "ትጥፋ" በሚል ሰበብ፣ ግማሹ እንቆራርሳት (ወይ "ተሐድሶ" አሊያም "ተዋህዶ" እያልን እንፈርጃት በማለት ላይ ይገኛሉ፤)፡፡
ከሰሞኑም የተለያዩ ሚዲያዎች ቀድመዉ እንደሚተነብዩትም ይሁን እንደሚዘግቡት በኢቲቪ ከዚህ ቀደም እንደሚሰራዉ የዉንጀላ ቪድዮ ለዚሁ ማህበር ለማህበረ ቅዱሳን መክሰሻ እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረ ገጽ የሚጠፋበትን ሴራ (ይቅርታ ከምድረ ገጽ እንጂ ከሰዉ ልብ አላልኩም፤ እነሱም በሰዉ ልቡና ያፀኑት እንደሆነ እንጂ አያናዉፁትምና) እያዘጋጁ እንደሆነ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መንግስት ያላወቀዉ ነገር ክርስትናም ሆነ ክርስቲያን እንደ ሚስማር መከራ በበዛበት ቁጥር እየፀኑ መሄዳቸዉን አልተረዳዉም፡፡( ከመጽናት ባሻገር የመረረዉ ማህበረሰብ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ከሱ የባሰ የሚያዉቀዉ የለም ብሶት የወለደዉ "ጀግና " ነዉና!)
በማያያዝም መንግሥትን እንደዜጋ ላሳስበዉ የምወደዉ ጉዳይ እምቢኝ አልገዛም ብሎ ጫካ በገባ ጊዜ ምንም እንኳን ጥቂቶቹች ቢሆኑም ለዚህ ድል የበቃዉና ስልጣኑን ይዞ ዛሬ የደረሰዉ (በአንድም ሆነ በሌላ) በህዝብ ድጋፍ እንደሆነ ልብ ይለዋል፤ ዛሬም የሚዘነጋዉ አይመስለኝም፡፡( ይዘነጋዋል የሚልም እምነት የለኝም ከረሳዉም ላስታዉሰዉ ወዳለሁ፡፡) ይህ እንዲህ ከሆነ ዘንድ ማህበሩም (ማህበረ ቅዱሳን) የተነሳዉ እግዚአብሔርንና ህዝብን ይዞ እንደሆነ ላስገነዝበዉ ወዳለሁ፤ ማኀበሩን ለማፍረስ መነሳትም ሆነ ማሰብ አንድም ህዝብን መናቅ አንድም ከእግዚአብሔር ጋር መገዳደር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እግዚአብሔርንም ሆነ ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ የለም ደርግን ለዉድቀት ያበቃዉ የኢህአዴግ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን የህዝብ የምሬትና የሐዘን ነዉጥ ነዉ፡፡ ዛሬም እንዲሁ ይህ ህዝብ ታሪክ መድገሙ የነጠፈ አይመስለኝም ምንም እንኳን አብዛኞች ስሙን በተለያየ መንገድ ሊያጠለሹ ቢነሱም (ማኅበሩ ችግር የለበትም ማለቴ አይደለም ሊኖርበት ይችላል ግን ከሚሰጠዉ ሊተካ የማይችልና በጭራሽ የተዘነጉትን መስኮች በመስራቱ ሊበረታታ የሚገባዉ እንጂ ሊበተን ሊዘጋ የሚገባዉ ማኅበር አይደለም፤) መንግስት ሊያጠፋዉ ወይም እንቅስቃሴዉን ሊገታዉ ለሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ግን በዝምታ መንስግስትን የሚያዩት አይመስለኝም ፡፡ መንግስትም "ማኔ ቴቄል ፋሪስ" መባያ ሰዓቱ ደርሶ እንደሆን እንጂ አካሄዱን ደግሞ ደጋግሞ ፈትሾ ከሃሳቡ ቢመለስ ይሻለዉ ይመስለኛል፡፡(ይህም ደግሞ ይጠቅመዉ እንደሆነ እንጂ አይጎዳዉም እንደሚባለዉ ኢህአዴግ በሰዉ ሃሳብ መሸነፍ የማይወድ ካልሆነ በቀር፤)
አሁን ከቤተክህነቱ ጥላ ስር ሆነዉ ማኅበሩን እንደ ዕባብ በመርዛቸዉ ከሚናደፉት ዉስጥ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የሰላሌ አገረ ስብከት ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሊቀ ማዕምራን(የዛሬዉ ሊቀ ካህናት) (እሳቸዉ ሲሉት እንደነበረ ከሆነ "ታጋይ" ናቸዉ ሰዉ ምንም እንኳን ለሁለት ጌታ መገዛት ባይችልም እሳቸዉ ግን በሁለት ቢላ እየበሉ ለሁለት ጌታ እየተገዙ ይገኛሉ፡፡አንድም ከቤተክህነት ደሞዛቸዉን እየበሉ ቤተክርስቲያንን የማፈራረስ የጫካ ራዕያቸዉን ይተገብራሉ፡፡ ) እኚህ ሰዉ ሀገረ ስብከቱ ተመድበዉ እንደሄዱ በበዓለ ጥምቀት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተኮላተፈ አማርኛቸዉ ሲያስተምሩ ጨዋዉ የከተማዉ ህዝበ ክርስቲያን በእልልታና በጭብጨባ ትምህርቱን ሲያደምጣቸዉ ቆይቶ እዚያ ድረስ እንደተንሰራፋ ያላሰቡት ሊቀ ማዕምራን ማኅበረ ቅዱሳንን መወረፍ ሲጀምሩ በድምቀት ሲያዳምጣቸዉ የነበረ ህዝበ ክርስቲያን በአንድ ድምፅ ያሰማቸዉ ጉምጉምታ ሳያስቡት በድንጋጤ መናገር እስኪሳናቸዉ ድረስ ድምፅ ማጉያዉን ያስቀመጡበትና ዳግም መተንፈስ እንደተሳናቸዉ ዛሬ ድረስ የማስታዉሰዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ (ከማኅበሩ ጋር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስምምነት እንዳሌላቸዉ በልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ዛሬ ለመድረስ ችያለሁ፡፡)ዛሬም ከጠቅላይ ቤተክህነት በመሆን ይህንኑ የተለከፉበትን አባዜ ሲያካሄዱ ወደኃላ ተመልሰዉ የፍቼዉን የህዝብ ድምፅ ቢያደምጡት ይሻላቸዉ ነበር ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት አንድ ከተማ ሙሉ ድምፁን አንድ የሚያደርግለት ማኅበር ዛሬ ደግሞ ድርጅቱ ኢህአዴግ አለኝ ከሚለዉ አባላት ቁጥር በላይ ያለዉ ማኅበረ ቅዱሳንን መንካት ምን ያህል ድፍረት እንደሆነ አስቀድሞ ሊገነዘበዉ ይገባዉ ነበር፡፡ (ለነገሩ ኢህአዴግ ከማኅበሩ ጋርም ያላስማማዉና ስጋት የሆነበትም እንደ ፖለቲካ ተንታኞችም ሆነ እንደ እኔ ጥርጣሬ የማኅበሩ አባላት ቁጥር እጅግ መብዛትና የአገልግሎታቸዉ መንሰራፋት፣ ቤተክርስቲያንን ሊቀብሯታ ከነበረችበት ጉድጓድ ቀና የማስባል አካሄዳቸዉ ስላስፈራዉ ይመስለኛል፡፡ በሌላ መልኩም ካየነዉ አያድርግባቸዉና የሃይማኖት ካባቸዉን ወርዉረዉ፣ ዓላማቸዉና ግባቸዉን ቀይረዉ ማኔፌስቱ አዘጋጅተዉ ፖለቲከኞች ነን ቢሉ በዚህ ሁሉ አባላት …. የመንግሥትን ሥልጣን ለግንቦት 20 የሚያደርሱት አይመስሉም  ስለዚህ መንግሥታችን መፍራቱ ደግ አደረገ ያስብለዋል፡፡  የፈራ ደግሞ ከክፉ መንገድ ይመለስ ደግሞ መልዕክቴ ነዉ!)
(አንድ ቁም ነገር ልንገራችሁ፡- ፈርኦንን መቸስ የማያዉቅ የለም ህዝበ እስራኤልን አሳራቸዉን ያሳያቸዉ፣ ራሔልን ልጇን በግፍ ጭቃዉ ዉስጥ እንድትወልድ ያደረገና ለቤተመንግሥቱ ማሳነጫ ከሚቦካዉ የጡብ ጭቃ ጋር የጨቅላ ህጻኗ ገላ ጭቃዉን ያጠነክረዋልና አብረሽ ርገጭዉ ብሎ ያስረገጠ አረመኔዉ ፈርኦን…. እግዚአብሔር ህዝቡን ሊታደጋቸዉ ሙሴን ከአሮን ጋር ወደ ግብፅ በላከ ጊዜ ፈርኦን ባሪያዎቹ ህዝበ እስራኤልን አለቅም ባለ ጊዜ …. እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በአስር ታላላቅ ተዓምራት ግብፅን ሲመታ አርኦን ልቡ ደንድኖ ነበር በአስራ አንደኛዉ የበኩሮች ሞት የደነገጠዉ ፈርኦን ወደ መኝታ ክፍሉ ገብቶ ሚስቱን የግብፅ በኩሮች ሁሉ አለቁ እኔ ብቻ ቀረሁ እነዚህን ሰወች ላሰናብታቸዉ ብሎ አማከራት  ሁሉ መአት በአገሪቱ ላይ ሲወርድ አትልቀቃቸዉ ስትለዉ እሺ ያለ (ሴት የላከዉ እንደሚባለዉ) ፈርኦን አሁን ግን ሚስቱ ጭን ስር ገብቶ ስለፍርሃቱ ሲነግራት ከግብፅ ህዝብ እልቂት ይልቅ (ስለ ህዝቡ ሳይሆን) ባሏ እንዳይሞትባት፣ ስልጣኗን፣ ክብሯን እንዳታጣ ስትልሞት ቤታቸዉ እንዳይገባ ስትልአሁንስ ፈራሁ አለችዉ ህዝቡንም በሰላም አሰናበታቸዉ ….  ምንም እንኳን በስተመጨረሻ ትዕቢቱ አገርሽቶበት ባህረ ኤርትራ ሰጥሞ ቢሞትም፤ መፍራት ጥሩ ነዉ ጆሮ ያለዉ ይስማ! ከክፉ መንገዱም ይመለስ የእግዚአብሐየርንም ህዝብ በሰላም ያሰናብታቸዉአለበለዚያ መጥፋት እንዳለ የፈርኦን የህይወት ታሪክ ያስተምረናልና፡፡መልዕክታችን ነዉ!)
ኢህአዴግ አባላቱን በዚህም በዚያም አንድ ለአምስት እያለ ቢጠረንፋቸዉም "የፈሩት ይደርሳል: የጠሉት ይወርሳል" እንደሚባለዉ ሁሉ ኢህአዴግ የማህበሩን በሰዉ ቁጥር መብዛትና ተደማጭነት ማግኘት በአቅምም የመደራጀታቸዉ ጉዳይ ስጋቱን እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ የጥርነፋዉ አካል ከሆኑት አምስት ሰወች ያለማጋነን ሁለቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆነ ሰንበት ትምህርት ቤት የመጡ ስለሆነ የርሱ (የኢህአዴግ) አይደሉም (የሆኑትም ግዴታ ስለሆነ አንድም በቅንነት አገርን ከማገልገል አኳያ ነዉ) ሁለቱ ደግሞ ቀጥታ ጥሙቃን ካድሬዎች ሳይሆኑ እንዲሁ የተነከሩ (ጥቅመኞች፣ የደርግ ካድሬ መሰሎች)ናቸዉ፡፡ የተቀረዉ አንደኛዉ ተጠርናፊ ደግሞ ኢህአዴግ እያካሄደ ባለዉ ስርዓት ተስፋ የቆረጠ አድርባይ እንጂ የክፉ ቀን ወዳጁ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ማኅበሩን ለማፍረስ በሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ራሱን ለአደጋ ያጋልጥ እንደሆነ እንጂ ለማኅበሩ ስጋት ሊሆን አይችልም ይልቁንም የማኅበሩን እንቅስቃሴ፣ የሃይማኖት ፅናት፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ፣ መከራ የመቀበል በረከታቸዉን …. ያበዛላቸዋል የሚል ዕምነት ነዉ ያለኝ፡፡(እንዲህ ስል ግን ፍርሃት/ሽብር ለመንዛት አይደለም ምናልባት ምክሬን ሰምቶ ከመጥፎ መንገዱ ተመልሶ ወደ ልማቱ ብቻ ፊቱን ያዞር እንደሆነ የዕድሌን ልሞክር ብዬ ነዉ፤ እነሱም መንግስትን የማስፈራራት ህልም ሆነ ቅዠት የላቸዉምና አገርንና ቤተክርስቲያንን የማገልገል ራዕይ እንጂ፡፡ ምናልባት በመሃል የተሰገሰጉ የማኅበሩን ስም ለማጉደፍ የሚሯሯጡ አፅራረ ቤተክርስቲያን አይጠፉም እንዲዉም መንግስት እነዚህን ተኩላዎች ከማኅበሩ ጎን በመሆን ቢያጠራላቸዉና እነዚህን የልማት ሰራዊት በደንብ ቢጠቀምባቸዉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡)
ማኅበረ ቅዱሳን እኔ እንኳን ባለኝ ትንሽ ግንዛቤ በአራቱም ማዕዘን (በመላዉ ዓለም) እንኳን ለአንድ መንግስት ለሰይጣን የማይፈታ ጠንካራ ቤተክርስቲያንን ያሉ ፣ለእግዚአብሔር "አንለይህም!" በማለት የማሉ መከራን ስደትን፣ ወዘተ ሊቀበሉ የተዘጋጁ አባላት ያሉት ማኅበር ነዉ፡፡(እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ ሶስቴ ለመካድ ያለተዘጋጁ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ እስከ መስቀሉ ስር የማይጠፉ የቤተክርስቲያንን አደራ የሚቀበሉ ናቸዉ፡፡/የማኅበሩን አባላት እንዲህ ስል እንድትታበዩ ሳይሆን የተሸካችሁትን የክርስቶስ እረፈ መስቀል እንዳትዘነጉት ለማሳሰብ ጭምር እንጂ፤ ከአደራ ጭምር ይህንንም በማነበብ እዳትታበዩ ፡፡ አንባቢም ካብካቸዉ እንዳትሉኝ እኔ የማላዉቀዉ እግዚአብሔር የሚዉቀዉ ለዚህች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን የዋሉት ዉለታ (የተወጡት ግዴታ) አለና ነዉ! አንድም የቤተክርስቲያን አራት ዐይን የሆኑትን የቤተክርስቲያ መምህራን የቆሎ ተማሪ በመታደግ ላይ ናቸዉናወዘተ/) ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በተለየያዩ ብሔር ብሔረሰብ ጥምር ዉበትን ተላብሰዉ መገኘታቸዉና በመንግስት ዉስጥ ያለዉ የብሔርተኝነት መከፋፈል አለመታየቱ የጥንካሬአቸዉ አንዱ ማሳያ ነዉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በየዋሻዉና በየበዓቱ ያሉ ስዉራን አባቶች ፀሎትና ልመና እንዲሁ ዝም አይልም እንደከዚህ በፊቱ መልሱን እየሰጠ እንጂ፤ ትናንትም የጠበቀዉ ዛሬንም ከመከራ ከፈተና የሚከልላቸዉ የአባቶች ፀሎትና የእግዚአብሔር ቸርነት ነዉ፡፡
እንደዉ እንኳን ይህ ሁሉ አልሆነም ብንል እና የማይሳነዉ መንግሥታችን አባላቱን /መሪዎቹን በአሸባሪነት ወይም በሆነ ነገር ፈርጆ እስር ቤት ቢዶላቸዉ (አንተ ላቆምከዉ ጣዖት/ስርዓት አንገዛም/አንንበረከክም …. የምናመልከዉ አምላክ ከመታሰር ባያድነን እንኳን ለስርዓትህ አንገዛም ….ቢሉት እና እስር ቤት ቢገቡ) ሐዋርያት ከኢየሩሳሌም በተበተኑ ጊዜ መበተናቸዉ ለበጎ ሆኖ ሃይማኖት/ክርስትና  በዓለም እንደተንሰራፋ ሁሉ በማኅበሩ አባላት ክርስትና በእስር ቤትም ላሉት በሰፊዉ እንደምትሰበክ/ለተቀሩትም የነሱ መታሰር ጽናት እንደሚሆናቸዉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለመንግስት ከዘነጋዉ ላሳስበዉ የምፈልገዉ ትዉልዱ ባህሉን፣ባንዲራዉን፣እምነቱን፣ አገሩን፣ አንድነቱን ….ከማንም እና ከምንም በፊት የሚሞትለት ግንባሩን የማያሸሽበት ጉዳይ እንዳልሆነ እንዲያዉቀዉ ፈልጋለሁ፡፡ይህን መንጋ መንካት በወጣቱ የተሳሰረ ክንድ በእሳት መጫወት ይሆንበታል፤ የሚያስበዉን መጨረሻ የሌለዉ የሚመስል የስልጣን ዘመን ላይ ጠላት መግዛት ነዉ፡፡አሁን ስለፖለቲካቸዉ ተጨንቄም አይደለም፣ ስለማህበሩም ወግኜ አይደለም፣ በዚህ አጋጣሚ ስለሚጎዱት እና ጥቃት ስለሚደርስባቸዉ (ሞራላዊ ጥቃት ተስፋ የመቁረጥ ወረርሽኝ፣ አገር/መንግስት የለንም የማለት ጥቃት)ታዳጊ ህፃናት እንጂ ዝሆኖች ሲጣሉ/ሲራገጡ የሚጎዳዉ ሳሩ ነዉና፤ በፌስቡክ ላይ እንኳን ስንቱ ነዉ ስሜቱ ተነክቶ በስሜት የሚናገረዉለሃይማኖቴ ሟች ነኝ እያለ ያለዉማንንም ቢሆን በሃይማኖቴ ጉዳይ የማልደራደርበት ጉዳይ ነዉ የሚለዉእንግዲህ እንዲህ የሚሉት የማኅበሩ አባላት አይደሉም፣ሰንበት ተማሪዎችም አይደሉም ከቤተክርስቲያን ገረገራ ቆመዉ "እኔ ኃጥያተኛ ነኝ! "ብለዉ ራሳቸዉን ዝቅ ያደረጉት ከቤተክርስቲያን በዉጭ ያሉት እንጂ ….መንግስት የማኅበሩን አባላት ብዛት አይቶ አይደል እንዲህ ፍርሃት የናጠዉና ካልበተንኩት እንቅልፍ አይወስደኝም ያለዉ …. እንግዲህ እሱ ያላያቸዉ ምናልባት በመዳፌ ናቸዉ ያሉት ጭምር ሊሆኑ በሚችሉ አጋጣሚ አንተም ብትሆን በቤተክርስቲያን ላይ ከመጣህ እግርህን ላስ እያሉት ይገኛሉ፡፡ ምን ይህ ብቻ ቱባ ባለስልጣናትስ ቢሆኑ ከቤተክርስቲያን  ይልቅ ኢህአዴግን ያስቀድማሉ ትላላችሁ? እንኳን እነሱ የደርግ ባለስልጣናትም ትናንት እግዚአብሔር የለም እያሉ ዛሬ ግን ከመቅደሱ ተገኝተዉ ይቅርታ እየጠየቁ ይገኛሉ የበደሉትን አምላካቸዉን እያገለገሉት ይገኛሉ፡፡ አሁንም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለእግዚአብሔር በአስራ አንደኛዉ ሰዓት ቢቀጠሩ እግዚአብሔር ሊቀጥራቸዉና ዋጋቸዉን  ሊከፍላቸዉ ምን ይሳነዋል፡፡
መንግስት ወጣቱን ምንም እንኳን ስናየዉ ለዓይን የማይሚላ ቢመስለዉም ለእግዚአብሔር ቀናኢ ነዉ፤መንግስት ሆይ እባክህ ከጥፋት ጎዳናህ ተመለስ …. ከፍለህ የማትጨርሰዉን ዕዳ ፍዳ በራስህ ላይ አትጫን፣ግፍም አታቆይ፡፡

በፌስ ቡክ እየቀረቡ ያሉ ተቃዉሞዎች ማሳያ!
 


Wednesday, 9 April 2014

መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት አልፈረጅኹም አለ



  • እንደ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ገለጻ በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ በአክራሪነት የተፈረጁት ‹አንዳንድ ግለሰቦች›÷ ‹‹አንዲት ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት›› የሚሉቱም ናቸው፡፡ ታዲያ ምን ይበሉ?!
  • ‹‹በይፋ አክራሪ ናችኹ ያለን አካል የለም፡፡›› /ተስፋዬ ቢኾነኝ፤ የማኅ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ/
  • ‹‹በጉዳዩ ላይ የጠራ ነገር የለም፤ ነገር ግን ጢስ አለ፡፡ ከጢሱ በስተጀርባ ያለው እሳት ይኹን እሳተ ገሞራ ባይታወቅም ለጊዜው ግን ማኅበሩን በተመለከተ ግልጽ የኾነ ነገር የለም።›› /ዲ.ን ዳንኤል ክብረት/
/ሰንደቅ፤ ፱ ቁጥር ፬፻፵፰፤ ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም./Sendek Miyazeya 2006
ዘሪሁን ሙሉጌታ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት የተቋቋመውን ማኅበረ ቅዱሳንን የኢትዮጵያ መንግሥት በአክራሪነት አለመፈረጁን አስታወቀ፤ ማኅበረ ቅዱሳንም በበኩሉ በይፋ በአክራሪነት የፈረጀው አካል እንደሌለ ገልጦአል።
በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ አበበ ወርቁ እና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንን መንግሥት በአክራሪነት ፈርጆ ሊያፈርሰው ነው፤›› የሚለውን አስተያየት በተመለከተ ተጠይቀው እንደመለሱት፣ ማኅበሩ በአክራሪነት በይፋ መፈረጁን እንደማያውቁ ተናግረዋል።
‹‹የአክራሪነት ፍረጃው ጉዳይ ከምን አንጻር እንደተነሣ ግልጽ አይደለም። በየትኛውም መድረክ ላይ ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ነው ተብሎ የተነሣበት ኹኔታ የለም። ማኅበረ ቅዱሳንን የማሳደግ፣ የመደገፍ ሓላፊነት የራሱ የሃይማኖቱ ተቋም እንጂ የመንግሥት ጉዳይ አይደለም፤ የማፍረስ ዓላማ አለው የተባለውም ስሕተት ነው፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ ‹‹መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ ሕገ መንግሥቱም አይፈቀድለትም፤ የመንግሥትም ባሕርይ አይደለም፤›› ብለዋል።
‹‹የመንግሥት ፍላጎት ሃይማኖት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ በአግባቡ በዚህች ሀገር ላይ ሰላማዊ የአምልኮ ሥርዓት እንዲፈጸም እንጂ በሲኖዶሱ የተደራጀን ተቋም ሊያፈርስ የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የለውም፤›› ሲሉ አቶ አበበ ጨምረው ገልጸዋል።
‹‹መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን ሊያፈርስ ነው፤›› የሚለው ጉዳይ የተለያየ መነሻ እንደሚኖረው የጠቀሱት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው፣ ጉዳዩ ከግንዛቤ እጥረት ወይም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የአክራሪነት አስተሳሰብን የማስፋፋት ፍላጎት ባላቸው አካላት የተነሣ ሊኾን እንደሚችል ገምተዋል።
‹‹ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ የሚካሔድን እንቅስቃሴ ሊሸከም የሚችል ትከሻ እንደሌለው በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ ትልቅ ትግልም አካሒዷል፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ የአሉባልታው ምንጭ አክራሪነትን በማስፈንና አክራሪነትን በመዋጋት መካከል ባለው ፍልሚያ የተቀሰቀሰ አሉባልታ ነው ብለዋል።
‹‹ጉዳዩ በሬ ወለደ ነው፤›› የሚሉት ሕዝብ ግንኙነቱ፤ ‹‹ከዚኹ አካባቢ[ከማኅበረ ቅዱሳን] አክራሪነትን ሊደግፉ የሚችሉ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፤›› ብለዋል። ‹‹የሰላማዊው አምልኮ ሥርዓት እየጠነከረ በሄደ ቁጥር የአክራሪው መድረክ እየጠበበ ስለሚመጣ ከሕዝብ ልንነጠል ነው በሚል ፍራቻ ልክ በሕዝበ-ሙስሊሙ አካባቢ የሐሰት ወሬ ተዘርቶ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል እንዳሉት ኹሉ አሁን ደግሞ ወደ ሕዝበ-ክርስቲያኑ በማሰራጨት በባዶ ጩኸት ሕዝቡን ለማሳሳት የታለመ ነው፤›› ብለዋል።
‹‹መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ምንም ዓይነት ስጋት የለውም፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከመንፈሳዊ ሥራው ጎን ለጎን እያካሄደ ያለው የልማት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲ ሥራ ስለሚሠራ፣ መንግሥት ከያዘው አጀንዳ ጋር ስለሚጣጣም በአጋዥነት ስለሚያየው ይደግፈዋል እንጂ አያፈርሰውም ብለዋል። ይህ ሲባል ግን እንደ ማንኛውም ተቋም የተቀደሰውን ዓላማ የሚያራክሱ፣ ማኅበሩን ወዳልኾነ አቅጣጫ የሚወስዱ ግለሰቦች አይኖሩም ማለት እንዳልኾነ ጠቅሰዋል። በተለይም ‹‹አንድ ሃይማኖት! አንድ ሀገር! አንድ ጥምቀት!›› እያሉ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በአክራሪነት ሊፈረጁ ይችላሉ ብለዋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው፣ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና አግኝቶ መተዳደርያ ደንብ ተቀርፆለት የሚተዳደር ማኅበር እንደኾነ አስታውሰው፤ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኗ ሥር የሚያገለግል ማኅበር በመኾኑ ከአክራሪነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤›› ብለዋል።
‹‹ክርስትናችን አክራሪነትን የሚያስተምር አይደለም። የማኅበሩም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከአክራሪነት ጋር ምንም የሚያገናኝ ሥራ የለውም። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየሰጠ ያለ ማኅበር ነው፤ በጉዳዩም ላይ በይፋ የደረሰን የተጻፈ፣ በቃልም የተባልነው ነገር የለም። ካለም ልንወያይ፣ አስፈላጊውን ነገር ልንተባበር እንችላለን፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ ከአክራሪነት ፍረጃ ጋር በተያያዘ በይፋ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፤ ማኅበሩም የተለመደ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።
ማኅበሩን በተመለከተ እየተነሣ ያለው የፍረጃ ሐሳብ ምንጩ ምን እንደኾነ አናውቅም ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ምንጩን ሊያውቁ ይችላሉ ብለን የምንገምተው ሚዲያዎቹ ናቸው። እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። እንደማንኛውም ጉዳዩን እንደሚከታተል አካል ነው የምናየው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ በወጡ ሰነዶች ላይ ማኅበሩ መጠቀሱን በተመለከተ አቶ ተስፋዬ ተጠይቀው፣ በማኅበር ደረጃ በይፋ በግልጽ የተጠቀሰ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ማኅበሩን በቀጥታ የሚመለከት በደብዳቤም ኾነ በሌላ መንገድ የተባለ ነገር የለም ብለዋል።
Dn. Daniel Kibretአንዳንድ የማኅበሩ ምንጮች በመጋቢት ፳፻፭ ዓ.ም. ‹‹የፀረ አክራሪነት ትግል የወቅቱ ኹኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች››* በሚል ርእስ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና መድረክ የአክራሪነት አደጋ ያለው በሃይማኖት ሽፋን በሚንቀሳቀሱና የከሰሩ ፖሊቲከኞች ምሽግ በመኾን ያገለግላሉ በተባሉ ማኅበራት ውስጥ ነው መባሉ፤ በቅርቡም በሐዋሳ ከተማ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ችግሮቹና መፍትሔዎቹ››** በሚል ርእስ በቀረበ ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአክራሪዎች ምሽግ የኾኑት የወጣት ማኅበራት አደረጃጀቶች መኾናቸውንና እኒህም ማኅበራት በሃይማኖት ተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ይኹንታ ያላቸው ከመኾኑም በላይ ማኅበራቱ ከጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ጋራ ግንኙነት እንዳላቸው መጠቀሱ እንዲሁም ከፓትርያርክ ምርጫው፣ ከቀድሞ ፓትርያርክ ጋር ዕርቅ ለመፍጠር የተደረገውን ጥረት ማኅበሩን ከከሰሩ ፖለቲከኞች ጋር ለማስተሳሰር መሞከሩና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች የማኅበሩ አባላት መንግሥትን በጥርጣሬ እንዲያዩት መደረጉን ይገልጻሉ።
በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ከነበራቸው አመራሮች አንዱ የነበሩት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በግል ስለ ኹኔታው ተጠይቀው፣ በጉዳዩ ላይ የጠራ ነገር አለመኖሩን፣ ነገር ግን ጢስ መኖሩን ገልጸዋል። ከጢሱ በስተጀርባ ያለው እሳት ይኹን እሳተ ገሞራ ባይታወቅም፤ ለጊዜው ግን ማኅበሩን በተመለከተ ግልጽ የኾነ ነገር የለም ብለዋል።
በግላቸው መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን በማፍረስ ስሕተት ይሠራል ብለው እንደማይገምቱና ምናልባትም ለማኅበሩ ያሰቡ ሰዎች መስለው ለማኅበሩ የተሳሳተ መረጃ ያቀበሉ እንዲሁም በመንግሥት በኩል ማኅበሩን በተመለከተ አፍራሽ አቋም ሊያንጸባርቁ የሚችሉ አንዳንድ ግለሰብ ባለሥልጣናት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያላቸውን ጥርጣሬ ተናግረዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን በ፲፱፻፹፬ ዓ.ም በዋናነት በእምነቱ ተከታዮች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተመሠረተ ሲኾን፤ የአባልነት መዋጮ በመክፈልና ከፍተኛ አገልግሎት በማበርከት ተሳትፎ ያላቸው ከ፴ ሺሕ በላይ አባላትና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተባባሪ አባላት አሉት፤ ማኅበሩ በስብከተ ወንጌል ረገድ ከሚያከናውነው ዓበይት መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርቲስያናት በልማት ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የአብነት ት/ቤቶች እንዲጠናከሩና እንዲጎለብቱ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው።
>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>> 
በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት የአክራሪነትና የከሰሩ ፖሊቲከኞች ምሽግ በመኾን መገልገል ከጀመሩ ውሎ አድሯል፡፡ ከ፮ው ፓትርያርክ ምርጫ ጋራ በማያያዝ የየራሳቸው ፍላጎት የሚያሳኩ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍና አሜሪካ ከሚገኘው ስደተኛው ሲኖዶስ ከሚባለው ቡድን ጋራ የዕርቅ ኹኔታ በሚል እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡
በዚኽ በራሳቸው በፈጠሩት ትርምስ ውስጥ መንግሥት እጁን አስገብቷል ወዘተ እያሉ የኦርቶዶክስ አማኞችን ለማወናበድ ይሞክራሉ፡፡ በራሳችንም እንደሌላው ኃይል ሰልፍ ልንወጣ ይገባል በሚል የዐመፅና የሁከት ቅስቀሳ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
በተለይም ሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ራሱን ስደተኛው ሲኖዶስ ብሎ የሚጠራው አካል ሰላማዊ፣ አሳታፊና ግልጽ ኾኖ የተካሔደውን የ፮ው ፓትርያርክ ምርጫ አውግዘናል በማለት መግለጫ ሲሰጥ የሰነበተ ቢኾንም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዩ ሕዝብ ጆሮውን ሳይሰጠው አልፏል፡፡ በሒደትም ይህ ኃይል ሰላም እንዳልኾነ፣ የሰላም ጥረቶችን በሙሉ ሲያሰናክል የሰነበተ፣ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ሳይኾን የከሰሩ ፖሊቲከኞች እንቅስቃሴ መኾኑን ግንዛቤ ይዟል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች አካል በመኾን በጋዜጣና በመጽሔት ሕዝባችንን ለዐመፅና ሁከት ለማነሣሣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በስደተኛው ሲኖዶስ በመሸፈንም እያንዳንዱ ሌላ ቀን ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሌለች አስመስለው የግንቦት ሰባትን ከበሮ ሲመቱ ከርመዋል፡ (የፀረ አክራሪነት ትግል የወቅቱ ኹኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች፤ መጋቢት ፳፻፭ ዓ.ም.)
** slide presentation by Dr. Shiferaw000

Tuesday, 8 April 2014

ማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች

Sunday, April 6, 2014

 የግል ምልከታ
(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)
ይህ ጽሑፍ የእኔን የግል ምልከታና አስተያየት ብቻ የሚመለከት እንጂ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰውን ማኅበርም ሆነ ከእርሱ ጋር የአገልግሎት ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት የማይመለከት መሆኑን አበክሬ በመግለጽ ልጀምር።
አንድ ብሒል አለ። ውሸትን ደጋግመው ቢናገሩት እንደ እውነት የሚቀበለው ሰው መፍጠር ይቻላል። ስለዚህም ሐሰተኞች ሐሰታቸውን ሳያሰልሱ በተናገሩት መጠን፦ አንደኛ ራሳቸውንም በሐሰታቸው እውነትነት ያሳምናሉ፤ ብሎም ሌሎችን ማሳመን ይችላሉ። ደጋግሞ የመናገር ጥቅሙ ይኼው ነው።

አንዳንድ እውነት የያዙ ሰዎች ደግሞ “እውነት እስከያዝን ድረስ ደጋግሞ መናገር ለምን ይገባል?” ብለው ያቀርባሉ። እውነት አላቸው። ፀሐይ ሲወጣ ጨለማ መሸሹ፣ ሻማ ሲለኮስ ብርሃን መፈንጠቁ ላይቀር “ጨለማን ማውገዝ ምን ጥቅም አለው?” ይላሉ። ይህም እውነት ነው። “ጨለማን ደጋግሞ ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት” እንደተባለው። ነገር ግን ሐሰት ተደጋግማ በመነገሯ ተከታይ መፍጠር እስከቻለች ድረስ እውነትን ደጋግሞ በመናገር የሚመጣ ምን ችግር አለ? ሻማውንም እየለኮሱ እውነቱንም ደጋግሞ መናገሩስ? ስለዚህ በእውነት ተደጋግሞ መነገር፣ በሻማ መለኮስም አምናለኹ። ደጊመ ቃል እንዲሉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት።
እንኳን አገር ቤት ያለው አንባቢ ይቅርና እኛ ከአገራችን በብዙ ሺህ ማይሎች ርቀን የምንገኘው ሳንቀር በየዕለቱ የምንኮመኩመው አዲሱ ትኩስ ዜና የማኅበረ ቅዱሳን እና “የተጠመደለት ወጥመድ” ጉዳይ ነው። በማኅበራዊ ድረ ገጾች እና በጡመራ መድረኮች፣ እንዲህ በሕትመት ውጤቶች በሰፊው ሽፋን ያገኘ ጉዳይ ሆኗል። ብዙ ኢትዮጵያውያን (እምነት ሳይለይ) ይህንን ጣልቃ ገብነት በጽኑዕ እየተቃወሙት እያወገዙት ነው። “ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ የሚባል ከሆነ እኔም አክራሪነትን እወደዋለኹ” የሚሉ ሐሳቦች በብዛት ተጽፈው ተመልክቻለኹ።
“የአክራሪነቱ ነገር”፣ ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ በፓርላማ ተናግረውት በነበረ ጊዜ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ፀሐፍት አስተያየታቸውን የሰጡበት ከመሆኑ አንጻር ወደዚያ መመለስ አይገባ ይሆናል። ማኅበሩ ከፓርቲ ፖለቲካ ጋር ግንኙነት እንዳለው በመንግሥት ሰዎች እና በደጋፊዎቻቸው የሚነሣውን ሐሳብ በተመለከተ ግን የግል አስተያየቴን ላሰፍር እወዳለኹ።
ማኅበሩ ፖለቲካ ውስጥ አለበት? ለመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ መግባት/ አለመግባት ምንድነው? ማንኛውም ሰው የተባለ ፍጡር ፖለቲካዊ አመለካከት አለው። ፖለቲካ አልወድም የሚሉ ሰዎች ራሳቸው እንኳን ፖለቲካዊ አቋም አላቸው። ልዩነቱ እያወቁ ማወቅ እና ሳያውቁ መኖር ናቸው። የተለያዩ ሐሳቦች እስካሉ ድረስ፣ አስተዳደሮች፣ ገዢዎችና ተገዢዎች እስካለን ድረስ ፖለቲካዊ አመለካከቶች መኖራቸው ግድ ይመስለኛል። “ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቅ” የሚለው ሰው ራሱ በኮረንቲ ከመጠቀም፣ ሕይወቱ በፖለቲካ ተጽዕኖ ሥር መውደቁ እስካለ ድረስ ፖለቲካ የማይነካው ኢትዮጵያዊ አይኖርም።
ይኼ በፖለቲካ ምሁራን ሳይሆን እኔን በመሳሰሉ ለፖለቲካው ዕውቀት ተርታ በሆንን ሰዎች ቋንቋ “ፖለቲካ ውስጥ መግባት ወይም አለመግባት” የምንለው የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ማለታችን እንደሆነ ይሰማኛል። ፖለቲከኞች የምንላቸው እንደዚያ ያሉ ሰዎችን ነውና። ማኅበረ ቅዱሳን “ፖለቲካ ውስጥ ገባ/ አልገባም” የሚለውንም የምፈታው በዚሁ አንድምታውና አገባቡ ብቻ ነው።
ማኅበሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት አሉት። አባላቱ ሰዎች እንደመሆናቸው ፖለቲካዊ አመለካከት አላቸው። ማኅበሩን በአባልነት ለመቀላቀል የሚያበቃቸው ግን ይህ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው አይደለም። የአባላቱ የዓላማ አንድነትና መሠረቱ ማኅበሩ የሚያራምደው ቤተ ክርስቲያናዊ አቋም ብቻ ነው። በሃይማኖትና በአገልግሎት ዓላማ አንድ ናቸው እንጂ በፖለቲካ ርዕዮት የተሰባሰቡ አይደሉም። ሲጀመርስ ስለ ፖለቲካ አመለካከታቸው የት ተጠያይቀው? የት ተገማግመው? የት ተለካክተው? በየትኛው ጊዜ?
ስለዚህም ማኅበሩ አንድ ሃይማኖታዊ አቋም ያራምዳል እንጂ “አንድ ፖለቲካዊ አቋም” የሚባል የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ለምን? ምክንያቱም “ፖለቲካዊ አቋምን ለማራመድ” መጀመሪያ ፖለቲካዊ አቋም መያዝ ያስፈልገዋል። ያንን ለማድረግ ደግሞ አባላቱን በሙሉ በዚህ ፖለቲካዊ አቋም ማሳመን ያስፈልጋል፤ ያንን ማድረግ ደግሞ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ማኅበሩ የያዘውን ሃይማኖታዊ አቋም የሚጻረርና ማንም ሳይነካው እንዲፈርስ የሚያደርገው ድማሚት ነው።
እዚህ ላይ መነሣት ያለበት ቁምነገር፤ የማኅበሩ አባላት በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው ራሳቸውን የቻሉ (ማለትም ማመዛዘን የሚችሉ) ክርስቲያኖች እንጂ የአንድ ቡድን ጀሌዎች አለመሆናቸውን ነው። ራሱን የቻለ አስተሳሰብ ያለው ማንኛውም ሰው፣ አባል የሚሆንበትን ድርጅት ያያል፤ ይመዝናል፣ ያስባል። እንደማይጠቅመውና እንደማይስማማበት ከተረዳ ይተወዋል። ጀሌ ግን የተነገረውን ተቀብሎ እንደ በቀቀን ያስተጋባል፤ ሳያውቅ አባል ይሆናል፤ በጥቂት ጥቅም ይደለላል፣ የሚኖርለትም-የሚሞትለትም ቋሚ መርሕ አይኖረውም።
ማኅበረ ቅዱሳንን እና አባላቱን በአገራችን ላለፉት 40 ዓመታት በጠነነው የፖለቲካ ድርጅት ጀሌነት መገምገም ትክክል የማይሆነው ለዚህ ነው። አባላቱ አገልጋዮች እንጂ ካድሬዎች አይደሉም። አመራር ላይ የሚቀመጡት ሰዎች በተራቸው ለማገልገል እንጂ ከሌላው አባል የተለየ መርሕ ለማራመድ አይችሉም። እናራምድ ቢሉም አባላቱ ጀሌዎች ስላልሆኑ ሊከተሏቸው የሚችሉበት ምንም መንገድ አይኖርም። የአባላቱ አንድነት በሃይማኖት እና በሃይማኖት ብቻ ነው። በበሰለ ሚዛን የሚለካቸው ቢኖር ኖሮ በዘር፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በትምህርት ደረጃ፣ በዕውቀት፣ በዕድሜ ወዘተ ወዘተ የተለያዩ እንጂ እንደ ሜዳ አህያ አንድ ወጥ እና ልሙጥ አለመሆናቸውን ይገነዘባል።
ስለዚህ አንድ አባል በግልጽ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ የዜግነት ድርሻውን መወጣት ቢፈልግ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በማኅበሩ ውስጥ ያለውን የአመራር ኃላፊነት ማስረከብ ይኖርበታል። በዚህ ደረጃ በይፋ ከአመራርነታቸው በሰላም ተሰናብተው ወደፈቀዱት ይፋዊ የፖለቲካ መስመር መጓዝ የቻሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ማኅበሩንም የፖለቲካ ድርጅታቸውንም መምራት የሚችሉበት መንገድ አይኖርም። እነርሱ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸውን በማኅበሩ ላይ ለመጫን ቢፈልጉም እንኳን “የፍላጎት መላተም” ("conflict of interests") ስለሚኖር ሊሳካላቸው አይችልም። የማኅበሩ አባላት በፖለቲካ መሳተፍ የዜግነት መብታቸው ሲሆን በማኅበሩ አገልግሎት መሳተፍ ደግሞ ሃይማኖታዊ የትሩፋት ሥራ እንደመሆኑ ማቻቻል የአባሉ ፈንታ ነው።
ማኅበሩ በፖለቲካ ውስጥ ገብቷል የሚለው (በተለይ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች) ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሲያዜሙት የነበረ የሰለቸ ዜማ ነው። የሚነቅፉት ግን ማኅበሩ “ኢሕአዴግን አይደግፍም” ብለው ስላሰቡ እንጂ “ተቃዋሚ ነው ብለው ስላመኑ” ብቻ አይደለም። ለነገሩ እነዚህ መንግሥትን በዱላነት ለመጠቀም የሚፈልጉ፣ በመንፈሳዊም በዓለማዊም ሚዛን ቢመዘኑ ውኃ የማያነሱ ደመናዎች “ፖለቲካ” የሚሉት አጎብዳጅነትን ነው። መንግሥት እነሱን ይጠቀማል። እነሱም በአቅማቸው በመንግሥት ይጠቀማሉ።
ታዲያ ማኅበሩ የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት እንደማይደግፍ ነገሩን ሥራዬ ብሎ ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሆኖ ሳለ በዚህ ጉዳይ መወንጀሉ ለምን አስፈለገ? ክርስቶስ አምላካችን ራሱ “ግብር አትክፈሉ ይላል? ለቄሳር አትገዙ ብሏል፤ ንጉሣችን ሳይሆን ንጉሥ ነኝ ብሏል” የሚል ፖለቲካዊ ክስ እንደቀረበበት ሃይማኖትን ብለው የሃይማኖት አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ሰዎች በየዘመኑ የሚከሰሱበት ጉዳይ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልገናል።
ቅዱስ ሉቃስ “ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር” ሲል እንደጻፈው (ሉቃስ 23፥2)። በሌላው ዓለም ያለውን እንኳን ትተን በአገራችን ያለውን ብናስታውስ፣ ነገር ሰሪዎች በየዘመኑ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን ከነገሥታቱ ጋር በማጋጨት በአደባባይ እስከመገረፍ ያደረሱበት ጊዜ፣ በግዞት በእስር እንዲማቅቁ ያደረጉበት ወቅት እንዳለ ታሪክ ያስተምረናል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን እና የደብረ ሊባኖስ እጬጌ ጻድቁ አባ ፊሊጶስን ለአብነት ብናንሣ አባ ጊዮርጊስ እንደተጋዘ፣ አባ ፊሊጶስ በአደባባይ ራቁቱን እንደተገረፈ እናነባለን።
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ ያለ ማኅበር ትናንት እንደፈላ እንደ ክረምት አግቢ ሊታይ አይችልም። መንግሥት ይኼ ሁሉ ሐቲት አይጠፋውም። ማኅበሩ ተቃዋሚም ደጋፊም እንዳይደለ መግለጹ እስካሁን ጉንጭ አልፋ ከመሆን አልዘለለም። መደገፍ የማይችል አካል፣ ባይቃወምም እንኳን ገለልተኛ መሆኑ ለአደጋ ያጋልጠናል በሚል “ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው” የዶሮ ፍልስፍና የተቃኘ ነው።
ከዚህም ባሻገር አባላቱ ከአንድ ዘርና ቋንቋ፣ ባህልና ፖለቲካዊ አቋም የመጡ አለመሆናቸው፤ ይልቁንም ሕብረ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እንቅልፍ የሚነሣቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው። “አዳሜ በየቅርጫትህ ግባ” ሲባል አንድ ቅርጫት ውስጥ የማይጨመሩ፣ ከሌላውም ቅርጫት ካለው ጋር ዝምድናና ፍቅር ያላቸው፤ ከቅርጫታቸው ውጪ የሚያስቡ ሰዎች ያሉበት ማኅበር መሆኑ የሚያስፈራቸው አሉ።
በውጪ አገር ባሉ የተለያዩ የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ሲጠረጠር እንደኖረ እነርሱም በፈንታቸው “ማኅበረ ቅዱሳን የኢሕአዴግ ደጋፊ መሆን አለበት” ሲሉ ኖረዋል። ለምን እንዲህ አላችሁ ሲባሉ ምክንያቱም “ይህንን የሚያህል ትልቅ ተቋም እንዴት ነጻና ፍፁም ሃይማኖታዊ ብቻ ሊሆን ይችላል? ጠርጥር ጠርጥር” የሚል ጥርጣሬ ያቀርባሉ።
ማኅበሩ አብሯቸው ጀብ ጀብ ላለማለቱ ምክንያቱ ዓላማውና ተፈጥሮው መሆኑን ለመቀበል የአገር ውስጡም የዳያስጶራውም ቡድን፣ እነዚያም እነዚያም ይኸው እንደተቸገሩ አሉ። እነዚያ “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት፣ እነዚያም “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት። ማኅበሩ ደግሞ “አነ ዘክርስቶስ፣ አነ ዘቤተ ክርስቲያን፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ፣ እኔ የቤተ ክርስቲያን ነኝ” እንዳለ አለ። መጨረሻውን ደግሞ ዕድሜ ይስጠን እንጂ፣ እናየዋለን።
     

ይቆየን - ያቆየን 

Tuesday, 1 April 2014

አማሳኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በአሸባሪነት የፈረጁበት ስብሰባና መግለጫ ሊቃነ ጳጳሳቱን አስቆጣ



  • ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ገልጸዋል
  • የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉና በጀቷን አውጥታ እያስተማረቻቸው የሌላ እምነት በሚያራምዱ የስም ደቀ መዛሙርት ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፵፩፤ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
Admas logoየኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የኾኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዐት እንዲማሩ፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን በማቀናጀት ሞያዊ ድጋፍ እንዲያበረክቱ በማስተባበር ላይ የሚገኘውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአሸባሪነት በመፈረጅ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት ጠቅላላ ሀብቱና ንብረቱ የሚታገድበት ውሳኔ እንዲተላለፍ በመንግሥትም በኩል እርምትና ርምጃ እንዲወሰድበት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአድባራት አስተዳዳሪዎች መግለጫ አውጥተውበታል በተባለው ስብሰባ ጉዳይ ኹለት ሊቃነ ጳጳሳት ለከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች ቅሬታቸውን ማሰማታቸው ተገለጸ፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን በስም የጠቀሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች፣ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች እንደኾነ ቢገልጹም የሓላፊዎቹን ስም ከማሳወቅ ተቆጥበዋል፡፡
Lukas
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በክልል ትግራይ የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ቤተ ክርስቲያኒቱ በፀረ ሙስናና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከመንግሥት ጋራ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወሰኗን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ በዚህም መሠረት ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን ለማረምና ለማስተካከል ጥረት እያደረገች ቢኾንም ባለሥልጣናቱ ከማን ጋራ መሥራት እንዳለባቸው በትክክል አለመለየታቸውንና ግንኙነቱም አማሳኞችን በአይዟችኹ ባይነት የሚያበረታታ እንደኾነ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን በዚህ መልኩ ለባለሥልጣናቱ ለማቅረብ ያስገደዳቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎቹ፣ ‹‹ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለአድማ ያነሣሣል፤ በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከትና ሽብር እንዲፈጠርና ሰላም እንዲደፈርስ ያደርጋል›› ባሉት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚወሰደው አስተዳደራዊ ርምጃ በፀረ ሽብር ሕጉ መሠረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁበት መግለጫቸው ነው፡፡
የመንግሥት የተለመደ እገዛ እንዳላቸው በአጽንዖት የጠቀሱት አስተዳዳሪዎቹ በዚኹ መግለጫቸው፣ መንግሥት በፀረ ሽብር ሕጉ ታሳቢነት ገለልተኛ ኦዲተር መድቦ በማኅበሩ ላይ የሀብትና ንብረት ቁጥጥር የማካሔድ ድጋፉ እንዳይለያቸው ያስተላለፉት ጥሪ በሌላቸው ሕጋዊነትና ውክልና የቀረበ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ መንገድ ማከናወን በሚገባት ተግባር ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝና ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
በመንበረ ፓትርያርኩ ከተገኙት የመንግሥት ሓላፊዎች ጋራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንደተካሔደ በተገለጸው የኹለትዮሽ ውይይት፣ ማኅበረ ቅዱሳንን በመቃወም አድርጎ (በመቃወም ሰበብ) የወጣው የአስተዳዳሪዎቹ መግለጫ ዋነኛ ዓላማ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ወስና የምታካሒደውን የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ሒደት መጋፋት ነው ተብሏል፡፡
መላውን የሀገረ ስብከቱን አድባራት ለመወከል የማይበቁ ጥቂት ግለሰቦችን በመያዝ ይደረጋል የተባለው ይኸው ተቋማዊ ለውጡን ኾነ ብሎ የመጋፋት እንቅስቃሴም ‹‹የት እንደሚያደርስ እናየዋለን!›› የሚሉ ንግግሮች ጭምር ከሊቃነ ጳጳሳቱ የተሰሙበት እንደነበር ምንጮቹ አስታውቀዋል፤ ጉዳዩም በመጪው ግንቦት በሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዓቢይ መነጋገርያ መኾኑ እንደማይቀር ጠቁመዋል፡፡
ከሀገረ ስብከቱ አድባራት የተውጣጡ ናቸው የተባሉ አስተዳዳሪዎች ያደረጉት ስብሰባ፣ አስተባባሪዎቹ ከፓትርያርኩ ተሰጥቶናል ከሚሉት ፈቃድ በቀር በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዘንድ በይፋ የታወቀና የተፈቀደ እንዳልነበረ ምንጮቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንን በሁከትና ሽብር ለሚከሱ በቂ ሕጋዊነትና ውክልና የላቸውም ለተባሉ አካላት ፓትርያርኩ የሰጡትን የስብሰባ ፈቃድ፣ በቅርቡ ማኅበሩ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውን ሀገር አቀፍ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ እንዳያካሒድ ከተጣለበት እገዳ ጋራ ያነፃፀሩ ታዛቢዎች፣ ኹኔታው የፓትርያርኩን ርምጃዎች መርሕ አልባነት የሚያጋልጥ ነው ይላሉ፡፡ ከዚኽም ባሻገር መተዳደርያ ደንብ ያለውና ግልጽ ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ማኅበር ህልውናና አገልግሎት በግልጽ አስተዳደራዊ ጫና ውስጥ መግባቱን እንደሚያመለክት ታዛቢዎቹ ያምናሉ፡፡
ከመዋቅር፣ ከሀብትና ንብረት ቁጥጥር ጋራ በተያያዘ በማኅበሩ ላይ የሚቀርቡት ውንጀላዎች፣ በፀረ አክራሪነት ስም የሚናፈስበትን ፕሮፓጋንዳ በማጠናከር ፖሊቲካዊ ርምጃ እንዲወሰድበት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ምኞት በጉልሕ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ሃይማኖቱን የሚጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያኑን የሚከባከብና ሀገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያለውን ዓላማ የሚረዱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የመንግሥት አካላትም የተቃዋሚዎቹን አቋምና መግለጫ በጥንቃቄ እንዲመለከቱትም አሳስበዋል፡፡
Emblem of Holy Trinity Theological collegeበሌላ በኩል፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ትውፊት ውጭ ነው በተባለ የሌላ እምነት አስተምህሮ ምክንያት በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት መካከልና በደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት አባላት ውስጥ ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየተገለጸ ነው፡፡
ከኮሌጁ ውጭ ከሚገኙና በቅ/ሲኖዶስ ከተወገዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋራ የዓላማና የጥቅም ግንኙነት መሥርተዋል በተባሉ ጥቂት ደቀ መዛሙርት አማካይነት በኮሌጁ ውስጥ ከመንጸባረቅ አልፎ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው የተባለው ይኸው የኑፋቄ አስተምህሮ፣ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲበጅለት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኮሌጁ አስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ እስከ አሁን ምላሽ አለመሰጠቱ ውጥረቱን የበለጠ እንዳባባሰው ለአዲስ አድማስ የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡
የአስተምህሮው ውዝግብ አፋጣኝ መፍትሔ አለማግኘቱ ከደቀ መዛሙርቱ አልፎ የደቀ መዛሙርቱን ምክር ቤት አባላት ለሁለት እንደከፈለ ተገልጧል፡፡ ኮሌጁንና ደቀ መዛሙርቱን በቅንነትና በትጋት ለማገልገል በደቀ መዛሙርቱ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠውና ከፍተኛ ሓላፊነት የተጣለበት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት ‹‹ከልማቱ ጥፋቱ አመዝኗል›› ያሉት ጸሐፊውና አንድ የአመራር አባሉም ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል፡፡
‹‹ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ትውፊት ውጭ የኾነ የኑፋቄ ትምህርት ሲዘራ ድምፀ ተዓቅቦ ከማድረግ ባሻገር ችግር አለባቸው ከሚባሉት ደቀ መዛሙርት ጎን ተሰልፈው ኮሌጁንም ኾነ ሓላፊነት የሰጠንን ደቀ መዝሙር በቅንነት እንዳናገለግል የአንዳንድ መማክርት አባላት ተግባር አግራሞትን ፈጥሮብናል›› ያሉት ሁለቱ አባላት፣ በዚህ ሳምንት ለኮሌጁ ዋና ዲን ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ የችግሩ ተባባሪ በመኾኑ ከሓላፊነቱ ታግዶ ጉዳዩ እንዲጣራና እምነታቸውና ሥነ ምግባራቸው በተመሰከረላቸው ደቀ መዛሙርት እንዲተካ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉና በጀቷን አውጥታ እያስተማረቻቸው የሌላ እምነት የሚያራምዱ›› ያሏቸውን አጥብቀው እንደሚቃወሙ የገለጹ የደቀ መዛሙርት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ኮሌጁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት ለመጠበቅና ለማስፋፋት ከየአህጉረ ስብከታቸው ተልከው የመጡበት በመኾኑ አስተዳደሩ ኹኔታውን አስመልክቶ በቃል፣ በድምፅና በጽሑፍ የሚቀርቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡Letter of Holy Trinity Theological college disciple's council to the adminLetter of Holy Trinity Theological college disciple's council to the admin00