ትዉልዱ የሚከፍለዉ ነገር ግን ሊከፍለዉ የማይገባዉ ዋጋ! ይህ ትዉልድ ስለ ሃገሩና ስለ ሃይማኖቱ የከፈለዉን ዋጋ ምንም የሚወዳደረዉ የለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከማንም ክርስቲያን ልብ ዉስጥ ከማይጠፉት ከምዕመናኖቿ ጋር የተወጣቻቸዉን ሁለት ክፉ አጋጣሚ እንመልከት፡-
ሀ. የዮዲት ጉዲት
ለ.የግራኝ መሐመድ
…. እያሉ መቀጠል ይቻላል፤
ነገሥታት እና መንግስታት በመጡ ቁጥር አንዳቸዉም አልበጇትም ሊያስብል በሚችል መልኩ ጠላቶቿ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነትና በሕዝቦቿ አንድነት ግን የተቃጣባትን መከራ ሁሉ ብዙ ዋጋዎችንም ከፍላ ቢሆን ተወጥታዉ እነሆ ለ21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ደርሳለች ሆኖም ግን ጠላቶቿ እየበዙ ሄዱ እንጂ ወዳጅ አላፈራችም፡፡
እንደ ግራኝ መሐመድና እንደ ዮዲት ጉዲት ቀጥታ በቤተክርስቲያን ላይ ታጥቀዉ አይምጡ እንጂ ጉዳት በማድረሱ ግን (ከሁለቱ ዘመናት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በማቃጠል፣በመዝረፍ፣በማሸሽ፣ቤተክርስቲያንን በማቃጠል፣ካህናትን በማሰር፣በማወክ፣በመግደል ….
) ከትላንት ሳይብስ አይቀርም፡፡ ትላንት ርስት ጉልት የነበራት ቤተክርስቲያን ዛሬ አጥሮቿ እየተነቀሉ ይገኛል፤ ታላላቅ ሃገራዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸዉን ሥራ የሰራች ቤተክርስቲያን ለእነሱ አካሄድ ስላልተመቸች ባሏት ልጆች ዳር ድንበሯን አናስደፍርም፣ የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም ባሉ ….ወዘተ ምክንያቶች ከአሸባሪነት እየፈረጇት ይገኛል፡፡
አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብልህነት ሳይሆን ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነዉ!
ሰዉ ለሚጠቅመዉና ለተጠቀመበት ነገር ዋጋ ይከፍላል፤ መክፈልማ አለበት ህግም ያስገድደዋልና፡፡
አዉራዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ባሳለፋቸዉ ሁለት አስርት ዓመታት ዕድሜ ዘመኑ ግን ምንም እንኳን የአንድ አፍላ ጎረምሳ ዕድሜ ቢያሳልፍም (በዛሬዉ ዘመን አቆጣጠር ከአንድ ዩኒቨርስቲ የተመረቀ ምሁር ወጣት ቢሆንም)
ስራዉ ግን ሲፈተሽ ዕቃቃ ሲጫወት የቡድኑን አባላት የጫወታ መንፈስ የሚያዉክ አንድ አስቸጋሪ ህፃን ባህሪ እየያዘ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ አካሄዱ ደግሞ ለድርጅቱ ህልዉና ብቻ ሳይሆን እንደኔ ግላዊ አመለካከት ደግሞ አገሪቱ ለተያያዘችዉ ሰላም የማስፈን፣ልማትን የማፋጠን፣ድህነትን የመዋጋት አጀንዳ …የሚያደናቅፍ፤ የልማት ሠራዊቱንም የሚያመናምን መስሎ ይታየኛል፡፡(የእኔ የግል አጀንዳ ምንም እንኳን ያለምንም መደራደሪያ አገር ወደ ተሻለ ሰላም እና ዕድገት ማድረስ እና ለዜጋዎቿ ሰላምን መስጠት ቢሆንም ጠንካራ እና ዓላማ ያለዉ አባል አልጠላም፤ ለእንብላዉ ያልተሰበሰበ፡፡)
ለማሳያነት ህገ-መንግሥቱን ጥሶ በሃይማኖቶች ጣልቃ በመግባት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማዋከብና አቅም ማሳነስ፣ አባላቶቹንና የፖለቲካ መሪዎቹን ሰበባሰበብ ፈልጎ በፀረ ሽብሩ አዋጅ አሳቦ የእስር ቤት ሲሳይ ማድረግ፣ማህበራትን ማፍረስ፣ አላስፈላጊ ህጎችን ለራሱ ማጥቂያነት እንዲመች አድርጎ መደንገግ….እነዚህ ሁሉ መንግስት ያለአግባብ የሚከፍላቸዉ ዋጋ እና ለራሱ እያቆየ ያለዉ ግፍ ነዉ፡፡ (እነዚህን ነገሮች ስንጠቅስ የተነሱት ነገሮች ሙሉ ለሙሉ አገርን አልጠቀመም ለማለት አልደፍርም ሚዛናዊነት የጎደለዉ ይሆንብኛልና አገርንም ከጥፋት ሃይሎች መታደጉ የማይካድ ነዉና ንፁሃንን የመበቀያ መሳሪያ የመሆኑንም ያህል ኢህአዴግ የጠላዉን አናቱን መባያ መዶሻዉ ነዉና!)
አንድ ዓይን ያለዉ በአፈር አይጫወትም እንደሚባለዉ አሁን ባለችዉ ፀጥታና ሰላም ወቅት ልማቱን እንደማፋጠን አንዳንድ ከልማቱ ዉጭ ሆነዉ በቦዘነ/ሥራ በፈታ አዕምሮአቸዉ ነገር በሚፈጥሩ/በሚፈበርኩ (ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ወርክሾፕ ይሆናል እንዲሉ አበዉ) ሰይጣናዊ ሥራ በመሸረብ የተጠመዱ አሉ፡፡ ይህም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ሞክረዉ ያልቻሉትን ሲያገረሽባቸዉ እየቆዩ የጥፋት ስራቸዉን ማቀናበር ይጀምራሉ … … ከዚህ ቀደም ጥቃቅን ባለስልጣናትን የመንግስትን ስም ሊያጎድፉ ሲነሱ፣ህብረተሰቡን ሲበድሉ ስናይ ስንሰማ፣ መብራት ሲጠፋ፣ኔትወርክ ሲቋረጥ፣ ዉሃ ሲጠማን …. " ይድረስ ለመንግስታችን …" እያልን አቤት! ስንል ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም በቱባ ባለስልጣናቱ የገዳማትን (እነ ዋልድባን) ይዞታ መንጠቅ እና ገዳሙን መፍታት፣ አባቶችን ለእስር በመዳረግ፣ … ወዘተ የተጀመረዉ የቤተክርስቲያንዋን የጀርባ አጥንት የሆነ ማህበር "ማህበረ ቅዱሳን" አጽራረ ቤተክርስቲያንን አስርጎ ከማስገባት እስከ ለማፈራረስ እና ደብዛዉን ለማጥፋት መነሳት የጥፋት ጅማሬዎቹ ነበሩ፡፡(ያለወደደዉን የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት መበተን ስራዉ እንደሆነ ልጆች ሳለን ሰንበት ትምህርት ቤት ስንማር በነበረበት አካባቢ ሰንበት ትምህርት
ቤቱን ከመንግስት ሊሰልሉ መጥተዉ ምንም እንከን አጥተዉ ተሰብከዉ ንስሐ ገብተዉ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሆኑ ምዕመናን ምስክሮች ናቸዉ )
ይሁን እንጂ "የሲዖል ደጆች አይችሉአትም … " የተባለላት ቤተክርስቲያን ዛሬም ጸንታ ፍሬዋን እያፈራች ትገኛለች፤ ሆኖም ፍሬዋን እየተመገቡ ያደጉትም፣ በአፍኣ ያሉትም፣ በአንድነት ተባብረዉና የዉስጠኞቹ ለዉጨኞቹ ክንድ እየሆኑዋቸዉ ዛሬም በጠላትነት እየተነሱባት ግማሹ በማደስ ሰበብ፣ ግማሹ በቃ "ትጥፋ" በሚል ሰበብ፣ ግማሹ እንቆራርሳት (ወይ "ተሐድሶ" አሊያም "ተዋህዶ" እያልን እንፈርጃት በማለት ላይ ይገኛሉ፤)፡፡
ከሰሞኑም የተለያዩ ሚዲያዎች ቀድመዉ እንደሚተነብዩትም ይሁን እንደሚዘግቡት በኢቲቪ ከዚህ ቀደም እንደሚሰራዉ የዉንጀላ ቪድዮ ለዚሁ ማህበር ለማህበረ ቅዱሳን መክሰሻ እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረ ገጽ የሚጠፋበትን ሴራ (ይቅርታ ከምድረ ገጽ እንጂ ከሰዉ ልብ አላልኩም፤ እነሱም በሰዉ ልቡና ያፀኑት እንደሆነ እንጂ አያናዉፁትምና) እያዘጋጁ እንደሆነ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መንግስት ያላወቀዉ ነገር ክርስትናም ሆነ ክርስቲያን እንደ ሚስማር መከራ በበዛበት ቁጥር እየፀኑ መሄዳቸዉን አልተረዳዉም፡፡( ከመጽናት ባሻገር የመረረዉ ማህበረሰብ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ከሱ የባሰ የሚያዉቀዉ የለም ፤ ብሶት የወለደዉ
"ጀግና
" ነዉና!)
በማያያዝም መንግሥትን እንደዜጋ ላሳስበዉ የምወደዉ ጉዳይ እምቢኝ አልገዛም ብሎ ጫካ በገባ ጊዜ ምንም እንኳን ጥቂቶቹች ቢሆኑም ለዚህ ድል የበቃዉና ስልጣኑን ይዞ ዛሬ የደረሰዉ (በአንድም ሆነ በሌላ) በህዝብ ድጋፍ እንደሆነ ልብ ይለዋል፤ ዛሬም የሚዘነጋዉ አይመስለኝም፡፡( ይዘነጋዋል የሚልም እምነት የለኝም ከረሳዉም ላስታዉሰዉ ወዳለሁ፡፡) ይህ እንዲህ ከሆነ ዘንድ ማህበሩም (ማህበረ ቅዱሳን) የተነሳዉ እግዚአብሔርንና ህዝብን ይዞ እንደሆነ ላስገነዝበዉ ወዳለሁ፤ ማኀበሩን ለማፍረስ መነሳትም ሆነ ማሰብ አንድም ህዝብን መናቅ አንድም ከእግዚአብሔር ጋር መገዳደር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እግዚአብሔርንም ሆነ ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ የለም ፤ ደርግን ለዉድቀት
ያበቃዉ የኢህአዴግ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን የህዝብ የምሬትና የሐዘን ነዉጥ ነዉ፡፡ ዛሬም እንዲሁ ይህ ህዝብ ታሪክ መድገሙ የነጠፈ አይመስለኝም ምንም እንኳን አብዛኞች ስሙን በተለያየ መንገድ ሊያጠለሹ ቢነሱም (ማኅበሩ ችግር የለበትም ማለቴ አይደለም ሊኖርበት ይችላል ግን ከሚሰጠዉ ሊተካ የማይችልና በጭራሽ የተዘነጉትን መስኮች በመስራቱ ሊበረታታ የሚገባዉ እንጂ ሊበተን ሊዘጋ የሚገባዉ ማኅበር አይደለም፤) መንግስት ሊያጠፋዉ ወይም እንቅስቃሴዉን ሊገታዉ ለሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ግን በዝምታ መንስግስትን የሚያዩት አይመስለኝም ፡፡ መንግስትም "ማኔ ቴቄል ፋሪስ" መባያ ሰዓቱ ደርሶ እንደሆን እንጂ አካሄዱን ደግሞ ደጋግሞ ፈትሾ ከሃሳቡ ቢመለስ ይሻለዉ ይመስለኛል፡፡(ይህም ደግሞ ይጠቅመዉ እንደሆነ እንጂ አይጎዳዉም እንደሚባለዉ ኢህአዴግ በሰዉ ሃሳብ መሸነፍ የማይወድ ካልሆነ በቀር፤)
አሁን ከቤተክህነቱ ጥላ ስር ሆነዉ ማኅበሩን እንደ ዕባብ በመርዛቸዉ ከሚናደፉት ዉስጥ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የሰላሌ አገረ ስብከት ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሊቀ ማዕምራን(የዛሬዉ ሊቀ ካህናት) (እሳቸዉ ሲሉት እንደነበረ ከሆነ "ታጋይ" ናቸዉ ሰዉ ምንም እንኳን ለሁለት ጌታ መገዛት ባይችልም ፤ እሳቸዉ ግን
በሁለት ቢላ እየበሉ ለሁለት ጌታ እየተገዙ ይገኛሉ፡፡አንድም ከቤተክህነት ደሞዛቸዉን እየበሉ ቤተክርስቲያንን የማፈራረስ የጫካ ራዕያቸዉን ይተገብራሉ፡፡ ) እኚህ ሰዉ ሀገረ ስብከቱ ተመድበዉ እንደሄዱ በበዓለ ጥምቀት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተኮላተፈ አማርኛቸዉ ሲያስተምሩ ጨዋዉ የከተማዉ ህዝበ ክርስቲያን በእልልታና በጭብጨባ ትምህርቱን ሲያደምጣቸዉ ቆይቶ እዚያ ድረስ እንደተንሰራፋ ያላሰቡት ሊቀ ማዕምራን ማኅበረ ቅዱሳንን መወረፍ ሲጀምሩ በድምቀት ሲያዳምጣቸዉ የነበረ ህዝበ ክርስቲያን በአንድ ድምፅ ያሰማቸዉ ጉምጉምታ ሳያስቡት በድንጋጤ መናገር እስኪሳናቸዉ ድረስ ድምፅ ማጉያዉን ያስቀመጡበትና ዳግም መተንፈስ እንደተሳናቸዉ ዛሬ ድረስ የማስታዉሰዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ (ከማኅበሩ ጋር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስምምነት እንዳሌላቸዉ በልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ዛሬ ለመድረስ ችያለሁ፡፡)ዛሬም ከጠቅላይ ቤተክህነት በመሆን ይህንኑ የተለከፉበትን አባዜ ሲያካሄዱ ወደኃላ ተመልሰዉ የፍቼዉን የህዝብ ድምፅ ቢያደምጡት ይሻላቸዉ ነበር ፤ ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት አንድ ከተማ ሙሉ ድምፁን አንድ የሚያደርግለት ማኅበር ዛሬ ደግሞ ድርጅቱ ኢህአዴግ አለኝ ከሚለዉ አባላት ቁጥር በላይ ያለዉ ማኅበረ ቅዱሳንን መንካት ምን ያህል ድፍረት እንደሆነ አስቀድሞ ሊገነዘበዉ ይገባዉ ነበር፡፡ (ለነገሩ ኢህአዴግ ከማኅበሩ ጋርም ያላስማማዉና ስጋት የሆነበትም እንደ ፖለቲካ ተንታኞችም ሆነ እንደ እኔ ጥርጣሬ የማኅበሩ አባላት ቁጥር እጅግ መብዛትና የአገልግሎታቸዉ መንሰራፋት፣ ቤተክርስቲያንን ሊቀብሯታ ከነበረችበት ጉድጓድ ቀና የማስባል አካሄዳቸዉ ስላስፈራዉ ይመስለኛል፡፡ በሌላ መልኩም ካየነዉ አያድርግባቸዉና የሃይማኖት ካባቸዉን ወርዉረዉ፣ ዓላማቸዉና ግባቸዉን ቀይረዉ ማኔፌስቱ አዘጋጅተዉ ፖለቲከኞች ነን ቢሉ በዚህ ሁሉ አባላት …. የመንግሥትን ሥልጣን ለግንቦት 20ም የሚያደርሱት አይመስሉም ስለዚህ መንግሥታችን
መፍራቱ ደግ አደረገ ያስብለዋል፡፡ የፈራ ደግሞ
ከክፉ መንገድ ይመለስ ደግሞ መልዕክቴ ነዉ!)
(አንድ ቁም ነገር ልንገራችሁ፡- ፈርኦንን መቸስ የማያዉቅ የለም ህዝበ እስራኤልን አሳራቸዉን ያሳያቸዉ፣ ራሔልን ልጇን በግፍ ጭቃዉ ዉስጥ እንድትወልድ ያደረገና ለቤተመንግሥቱ ማሳነጫ ከሚቦካዉ የጡብ ጭቃ ጋር የጨቅላ ህጻኗ ገላ ጭቃዉን ያጠነክረዋልና አብረሽ ርገጭዉ ብሎ ያስረገጠ አረመኔዉ ፈርኦን…. እግዚአብሔር ህዝቡን ሊታደጋቸዉ ሙሴን ከአሮን ጋር ወደ ግብፅ በላከ ጊዜ ፈርኦን ባሪያዎቹ ህዝበ እስራኤልን አለቅም ባለ ጊዜ …. እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በአስር ታላላቅ ተዓምራት ግብፅን ሲመታ አርኦን ልቡ ደንድኖ ነበር በአስራ አንደኛዉ የበኩሮች ሞት የደነገጠዉ ፈርኦን ወደ መኝታ ክፍሉ ገብቶ ሚስቱን የግብፅ በኩሮች ሁሉ አለቁ እኔ ብቻ ቀረሁ እነዚህን ሰወች ላሰናብታቸዉ ብሎ አማከራት
ያ ሁሉ መአት በአገሪቱ ላይ ሲወርድ አትልቀቃቸዉ ስትለዉ እሺ ያለ (ሴት የላከዉ እንደሚባለዉ) ፈርኦን አሁን ግን ሚስቱ ጭን ስር ገብቶ ስለፍርሃቱ ሲነግራት ከግብፅ ህዝብ እልቂት ይልቅ (ስለ ህዝቡ ሳይሆን) ባሏ እንዳይሞትባት፣ ስልጣኗን፣ ክብሯን እንዳታጣ ስትል … ሞት ቤታቸዉ እንዳይገባ ስትል … አሁንስ ፈራሁ አለችዉ ህዝቡንም በሰላም አሰናበታቸዉ …. ምንም እንኳን
በስተመጨረሻ ትዕቢቱ አገርሽቶበት ባህረ ኤርትራ ሰጥሞ ቢሞትም፤ መፍራት ጥሩ ነዉ ጆሮ ያለዉ ይስማ! ከክፉ መንገዱም ይመለስ የእግዚአብሐየርንም ህዝብ በሰላም ያሰናብታቸዉ …አለበለዚያ መጥፋት እንዳለ የፈርኦን የህይወት ታሪክ ያስተምረናልና፡፡ … መልዕክታችን ነዉ!)
ኢህአዴግ አባላቱን በዚህም በዚያም አንድ ለአምስት እያለ ቢጠረንፋቸዉም "የፈሩት ይደርሳል: የጠሉት ይወርሳል" እንደሚባለዉ ሁሉ ኢህአዴግ የማህበሩን በሰዉ ቁጥር መብዛትና ተደማጭነት ማግኘት በአቅምም የመደራጀታቸዉ ጉዳይ ስጋቱን እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ የጥርነፋዉ አካል ከሆኑት አምስት ሰወች ያለማጋነን ሁለቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆነ ሰንበት ትምህርት ቤት የመጡ ስለሆነ የርሱ (የኢህአዴግ) አይደሉም (የሆኑትም ግዴታ ስለሆነ አንድም በቅንነት አገርን ከማገልገል አኳያ ነዉ)፤ ሁለቱ ደግሞ
ቀጥታ ጥሙቃን ካድሬዎች ሳይሆኑ እንዲሁ የተነከሩ (ጥቅመኞች፣ የደርግ ካድሬ መሰሎች)ናቸዉ፡፡ የተቀረዉ አንደኛዉ ተጠርናፊ ደግሞ ኢህአዴግ እያካሄደ ባለዉ ስርዓት ተስፋ የቆረጠ አድርባይ እንጂ የክፉ ቀን ወዳጁ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ማኅበሩን ለማፍረስ በሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ራሱን ለአደጋ ያጋልጥ እንደሆነ እንጂ ለማኅበሩ ስጋት ሊሆን አይችልም ፤ ይልቁንም የማኅበሩን እንቅስቃሴ፣ የሃይማኖት ፅናት፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ፣ መከራ የመቀበል በረከታቸዉን …. ያበዛላቸዋል የሚል ዕምነት ነዉ ያለኝ፡፡(እንዲህ ስል ግን ፍርሃት/ሽብር ለመንዛት አይደለም ምናልባት ምክሬን ሰምቶ ከመጥፎ መንገዱ ተመልሶ ወደ ልማቱ ብቻ ፊቱን ያዞር እንደሆነ የዕድሌን ልሞክር ብዬ ነዉ፤ እነሱም መንግስትን የማስፈራራት ህልም ሆነ ቅዠት የላቸዉምና አገርንና ቤተክርስቲያንን የማገልገል ራዕይ እንጂ፡፡ ምናልባት በመሃል የተሰገሰጉ የማኅበሩን ስም ለማጉደፍ የሚሯሯጡ አፅራረ ቤተክርስቲያን አይጠፉም እንዲዉም መንግስት እነዚህን ተኩላዎች ከማኅበሩ ጎን በመሆን ቢያጠራላቸዉና እነዚህን የልማት ሰራዊት በደንብ ቢጠቀምባቸዉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡)
ማኅበረ ቅዱሳን እኔ እንኳን ባለኝ ትንሽ ግንዛቤ በአራቱም ማዕዘን (በመላዉ ዓለም) እንኳን ለአንድ መንግስት ለሰይጣን የማይፈታ ጠንካራ ቤተክርስቲያንን ያሉ ፣ለእግዚአብሔር "አንለይህም!" በማለት የማሉ መከራን ፣ ስደትን፣ ወዘተ
ሊቀበሉ የተዘጋጁ አባላት ያሉት ማኅበር ነዉ፡፡(እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ ሶስቴ ለመካድ ያለተዘጋጁ ፤ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ እስከ መስቀሉ ስር የማይጠፉ የቤተክርስቲያንን አደራ የሚቀበሉ ናቸዉ፡፡/የማኅበሩን አባላት እንዲህ ስል እንድትታበዩ ሳይሆን የተሸካችሁትን የክርስቶስ እረፈ መስቀል እንዳትዘነጉት ለማሳሰብ ጭምር እንጂ፤ ከአደራ ጭምር ይህንንም በማነበብ እዳትታበዩ ፡፡ አንባቢም ካብካቸዉ እንዳትሉኝ እኔ የማላዉቀዉ እግዚአብሔር የሚዉቀዉ ለዚህች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን የዋሉት ዉለታ (የተወጡት ግዴታ) አለና ነዉ! አንድም የቤተክርስቲያን አራት ዐይን የሆኑትን የቤተክርስቲያ መምህራን ፣ የቆሎ ተማሪ በመታደግ ላይ ናቸዉና …ወዘተ/) ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በተለየያዩ ብሔር ብሔረሰብ ጥምር ዉበትን ተላብሰዉ መገኘታቸዉና በመንግስት ዉስጥ ያለዉ የብሔርተኝነት መከፋፈል አለመታየቱ የጥንካሬአቸዉ አንዱ ማሳያ ነዉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በየዋሻዉና በየበዓቱ ያሉ ስዉራን አባቶች ፀሎትና ልመና እንዲሁ ዝም አይልም እንደከዚህ በፊቱ መልሱን እየሰጠ እንጂ፤ ትናንትም የጠበቀዉ ዛሬንም ከመከራ ከፈተና የሚከልላቸዉ የአባቶች ፀሎትና የእግዚአብሔር ቸርነት ነዉ፡፡
እንደዉ እንኳን ይህ ሁሉ አልሆነም ብንል እና የማይሳነዉ መንግሥታችን አባላቱን /መሪዎቹን በአሸባሪነት ወይም በሆነ ነገር ፈርጆ እስር ቤት ቢዶላቸዉ (አንተ ላቆምከዉ ጣዖት/ስርዓት አንገዛም/አንንበረከክም …. የምናመልከዉ አምላክ ከመታሰር ባያድነን እንኳን ለስርዓትህ አንገዛም ….ቢሉት እና እስር ቤት ቢገቡ) ሐዋርያት ከኢየሩሳሌም በተበተኑ ጊዜ መበተናቸዉ ለበጎ ሆኖ ሃይማኖት/ክርስትና
በዓለም እንደተንሰራፋ ሁሉ በማኅበሩ አባላት ክርስትና በእስር ቤትም ላሉት በሰፊዉ እንደምትሰበክ/ለተቀሩትም የነሱ መታሰር ጽናት እንደሚሆናቸዉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለመንግስት ከዘነጋዉ ላሳስበዉ የምፈልገዉ ትዉልዱ ባህሉን፣ባንዲራዉን፣እምነቱን፣ አገሩን፣ አንድነቱን ….ከማንም እና ከምንም በፊት የሚሞትለት ግንባሩን የማያሸሽበት ጉዳይ እንዳልሆነ እንዲያዉቀዉ ፈልጋለሁ፡፡ይህን መንጋ መንካት በወጣቱ የተሳሰረ ክንድ በእሳት መጫወት ይሆንበታል፤ የሚያስበዉን መጨረሻ የሌለዉ የሚመስል የስልጣን ዘመን ላይ ጠላት መግዛት ነዉ፡፡አሁን ስለፖለቲካቸዉ ተጨንቄም አይደለም፣ ስለማህበሩም ወግኜ አይደለም፣ በዚህ አጋጣሚ ስለሚጎዱት እና ጥቃት ስለሚደርስባቸዉ (ሞራላዊ ጥቃት ፣ ተስፋ የመቁረጥ
ወረርሽኝ፣ አገር/መንግስት የለንም የማለት ጥቃት)ታዳጊ ህፃናት እንጂ ዝሆኖች ሲጣሉ/ሲራገጡ የሚጎዳዉ ሳሩ ነዉና፤ በፌስቡክ ላይ እንኳን ስንቱ ነዉ ስሜቱ ተነክቶ በስሜት የሚናገረዉ … ለሃይማኖቴ ሟች ነኝ እያለ ያለዉ … ማንንም ቢሆን በሃይማኖቴ ጉዳይ የማልደራደርበት ጉዳይ ነዉ የሚለዉ …እንግዲህ እንዲህ የሚሉት የማኅበሩ አባላት አይደሉም፣ሰንበት ተማሪዎችም አይደሉም ፣… ከቤተክርስቲያን ገረገራ ቆመዉ "እኔ ኃጥያተኛ ነኝ! "ብለዉ ራሳቸዉን ዝቅ ያደረጉት ከቤተክርስቲያን በዉጭ ያሉት እንጂ ….መንግስት የማኅበሩን አባላት ብዛት አይቶ አይደል እንዲህ ፍርሃት የናጠዉና ካልበተንኩት እንቅልፍ አይወስደኝም ያለዉ …. እንግዲህ እሱ ያላያቸዉ ምናልባት በመዳፌ ናቸዉ ያሉት ጭምር ሊሆኑ በሚችሉ አጋጣሚ አንተም ብትሆን በቤተክርስቲያን ላይ ከመጣህ እግርህን ላስ እያሉት ይገኛሉ፡፡ ምን ይህ ብቻ ቱባ ባለስልጣናትስ ቢሆኑ ከቤተክርስቲያን ይልቅ ኢህአዴግን
ያስቀድማሉ ትላላችሁ? እንኳን እነሱ የደርግ ባለስልጣናትም ትናንት እግዚአብሔር የለም እያሉ ዛሬ ግን ከመቅደሱ ተገኝተዉ ይቅርታ እየጠየቁ ይገኛሉ የበደሉትን አምላካቸዉን እያገለገሉት ይገኛሉ፡፡ አሁንም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለእግዚአብሔር በአስራ አንደኛዉ ሰዓት ቢቀጠሩ እግዚአብሔር ሊቀጥራቸዉና ዋጋቸዉን ሊከፍላቸዉ ምን
ይሳነዋል፡፡
መንግስት ወጣቱን ምንም እንኳን ስናየዉ ለዓይን የማይሚላ ቢመስለዉም ለእግዚአብሔር ቀናኢ ነዉ፤… መንግስት ሆይ እባክህ ከጥፋት ጎዳናህ ተመለስ …. ከፍለህ የማትጨርሰዉን ዕዳ ፍዳ በራስህ ላይ አትጫን፣ግፍም አታቆይ፡፡
በፌስ ቡክ እየቀረቡ ያሉ ተቃዉሞዎች ማሳያ!
No comments:
Post a Comment