Friday, 25 April 2014

በኢሕአዴግ የአዲስ አበባ አደረጃጀቶች ስለ አክራሪነት በተካሔደ ውይይት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተሰነዘረው ፍረጃና ክሥ ተሳታፊዎችን አስቆጣ



  • ውይይቱ ቀጣዩ የአሰላለፍ ስልትና የምት አቅጣጫ የሚወሰንበት ሊኾን ይችላል
  • ተሳታፊዎች ፍረጃዎችንና ክሦችን በመረጃና በሐሳብ የበላይነት ማጋለጥ ይገባቸዋል
AFRO TIMES TUESDAY EDITION
(አፍሮ ታይምስ፤ ቅጽ ፩ ቁጥር ፯፤ ማክሰኞ እና ረቡዕ፤ ሚያዝያ ፲፬ – ፲፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ በሃይማኖት ይኹን በማንኛውም ሽፋን የሚደረግን የፖሊቲካ ግጭት ለመመከት በሚል በአዲስ አበባ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ከታቀፉ አባሎቹ ጋራ ውይይት በማካሔድ ላይ መኾኑ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዐሥር ክፍለ ከተሞች 116 ወረዳዎች ካሉት ሰባት የግንባሩ አደረጃጀቶች ማለትም የሴቶች፣ ወጣቶች፣ መምህራን፣ የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ የአነስተኛ ጥቃቅን ተቋማት ከእያንዳንዳቸው የተውጣጡ ስድሳ፣ ስድሳ አባላትን ያሳተፈና ሦስተኛ ሳምንቱን የያዘ ውይይት በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡
‹‹የሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮች በሰላም አብሮ የመኖር ወርቃማ ተሞክሮና የማስቀጠል ፋይዳው››፣ ‹‹አዲሲቷ ኢትዮጵያና የሃይማኖት ብዝኃነት አያያዝ››፣ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ከሕገ መንግሥታችን ጋራ ያለው የማይታረቅ መሠረታዊ ቅራኔና መፍትሔው›› በሚሉ ርእሶች በቀረቡ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተው ውይይቱ ለአራት ተከታታይ ዙሮች እንደሚካሔድ ተመልክቷል፡፡
‹‹የመደማመጥ መድረክ›› የተሰኙት የመጀመሪያዎቹ ኹለት ዙሮች፣ ከቀረቡት ጽሑፎች ጋራ በተያያዘ የተዘጋጁ የመወያያ ነጥቦችን አስመልክቶ የተሳታፊዎች ግንዛቤና አቋም ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና አቋሞች በስፋት እንዲነሡና በዚህም ስልት በአባላት ውስጥ ያለውን ስሜት በቀጥታ ለማዳመጥ የታቀደበት መኾኑ ተገልጦአል፡፡
ባለፈው ሳምንት በተከናወኑት የውይይቱ ኹለተኛ ዙር መድረኰች÷ በአወያይነት በተመደቡት የወረዳ ጽ/ቤት ሓላፊዎች አማካይነት በየፈርጁ ተጠቃለው ለበላይ አመራር (ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር) ቀርበዋል ለተባሉት የተሳታፊዎች ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና አቋሞች የግንባሩና የመንግሥት አቋሞች፣ መረጃዎችና ዕቅዶች በምላሽነት እንደተሰጡ ታውቋል፡፡
በቀጣይ በሚካሔዱት ኹለት ዙሮች፣ በተናጠል ሲወያዩ የቆዩት የሰባቱ አደረጃጀቶች ስድሳ፣ ስድሳ ተሳታፊዎች በጋራ በመገናኘት በሥልጠና አመለካከታቸውንና ግንዛቤያቸውን ያስተካክሉበታል ተብሎ የሚጠበቅ የማጥራትና የመግባባት መድረክ እንደሚኾን ተጠቁሟል፡፡
በዚኽ መልኩ የሠለጠኑት የየወረዳው 420 የግንባሩ ‹‹የልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አደረጃጀቶች›› በቀጣይ በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ እንደሚጠራ በሚጠበቀው የብዙኃን መድረክ ከሕዝቡ ጋራ ተቀላቅለው በተለያዩ ስልቶች በመሳተፍ መድረኰቹ በታቀደው አቅጣጫ እንዲመሩና ወደተፈለገው መደምደሚያ እንዲደርሱ በማድረግ ድርጅታዊ ተልእኮዎቻቸውንና ስምሪቶቻቸውን እንደሚወጡ ተመልክቷል፡፡
‹‹ጠባብነት፣ ትምክህትና አክራሪነት›› የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች እንደኾኑና ከሕዝብ አቅም ግንባታ አኳያ ዋናው ርብርቡ በእነዚህ ላይ እንደኾነ መንግሥታዊ ጽሑፎች ይገልጻሉ፡፡ ሙስሊሙ ከጠባብነት፣ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑ ከትምክህት ርእዮት ጋራ የመዳበል ባሕርያት እንደሚታይባቸው የሚገልጹት የመንግሥት ሰነዶች÷ በእኒኽ ባሕርያት በተቃኙ ‹‹ሃይማኖታዊ ርእዮቶች›› ላይ የተመሠረተ ሽብርተኝነትና ሃይማኖታዊ ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ታሳቢ አድርጎ ርእዮቶቹን ‹‹በትምህርትና ሥልጠና፣ በዴሞክራሲያዊ አኳኋን›› መታገልና የለዘብተኝነትና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የተጠናከረ ሥራ መሠራት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
mahibere kidusanየመንግሥት የመልካም አስተዳደርና ልማት ጉዳዮች ተያይዘው በተነሡባቸው ባለፉት ኹለት የውይይት ዙሮች አንዳንድ የመድረክ አወያዮች ለስብሰባው አካሔድ ተቀምጧል ከተባለው ድርጅታዊና መንግሥታዊ አቋምና አቅጣጫ በተፃራሪ በኦርቶዶክሳዊው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያሰሙት ገለጻ፣ የውንጅላና የፍረጃ መንፈስ የተጠናወተው ከመኾኑም በላይ ያልተፈለገ አደገኛ ውጤት ሊያስከትልም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
በየካ፣ በቦሌ እና በልደታ ክፍላተ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች የተሳተፉ የአፍሮ ታይምስ ምንጮች ስምና ሓላፊነታቸውን ለይተው የጠቀሷቸው አወያዮች÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን መዋቅሩን አጥንቶ ፋይናንሱን እኔ ካልያዝሁትና ካልተቆጣጠርሁት ብሏል፤ ስለዚህ አክራሪ ነው››፤ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሰጠችው ደንብ ውጭ ይንቀሳቀሳል፤ ስለዚህ አክራሪ ነው››፤ ‹‹መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ለመኾኑ አስገራሚ አስገራሚ መረጃዎች አሉት›› የሚሉና የመሳሰሉ ክሦችንና ፍረጃዎችን መሰንዘራቸውን አስረድተዋል፡፡
የት/ቤት(መምህራን) አደረጃጀት አባላት እንዲሁም የስብሰባው ተሳታፊ ካህናት በበኩላቸው፣ በቅርበት ጠንቅቀው የሚያውቋቸው በርካታ የማኅበሩ አባላት መኖራቸውንና ፍረጃውና ክሡ በማስረጃ መደገፍ እንዳለበት አለበለዚያ ማኅበሩን ይኹን አባላቱን ይገልጻቸዋል ለማለት እንደሚያዳግት በመጥቀስ ተቃውመዋል፡፡
አወያዮቹ ማስረጃ እንዲያቀርቡና አነጋገራቸውን እንዲያርሙ በጥብቅ ያስጠነቀቁት ተሳታፊዎቹ፣ ውይይቱ በዚህ መንፈስ የሚካሔድ ከኾነ በተሳትፎ ለመቀጠል እንደሚቸገሩ በማሳወቅ ስብሰባውን ጥለው ለመውጣት ተነሣስተው እንደነበርና አወያዩ አካል መድረኩን መሪዎች በሌሎች በመተካት አስቸኳይ እርማት በማደረጉ በተሳትፏቸው ለመቀጠል እንደቻሉ ተጠቁሟል፡፡
ሌሎች የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ አጽድቃ በሰጠችው መተዳደርያ ደንብ መሠረት እንደሚንቀሳቀስና የፈጸማቸውን ዐበይት ማኅበራዊና የልማት ተግባራት፣ የአገልግሎቱ ዕሴቶችና ትሩፋቶች ያስገኙትን አገራዊ ጠቀሜታዎች በመዘርዘር አስረድተዋል፤ በተሰነዘሩት ፍረጃዎችና ክሦች አንጻርም እውነታውን በመግለጽ ፍረጃውና ክሡ ሕገ መንግሥታዊውን ሃይማኖት ነክ ድንጋጌ የሚጥስ ጣልቃ ገብነት ነው በሚል ኮንነውታል፤ በሕግ አውጭነት ሉዓላዊ ሥልጣኗ አገልግሎቱን የፈቀደችለት ቤተ ክርስቲያ እንኳ ያላለችውን ሕዝብን ሰብስቦ ማኅበሩን በአክራሪነት መወንጀል የማኅበሩን ገጽታ በማጠልሸት ከሕዝቡ ለመነጠልና ሕዝቡን በማኅበሩ ላይ ለማዝመት ተይዟል ብለው የሚጠረጥሩት ዘመቻ አካል ነው ብለው እንደሚያዩትም አመልክተዋል፡፡
‹‹ከመቻቻል በላይ በፍቅር እየኖርን ነው፤ ከሕጋዊነትም በላይ በፍቅር እየኖርን ነው፤›› በማለት በመድረኩ ‹መቻቻል› እና ‹የሕግ የበላይነትን ማስከበር› በሚል ከተገለጸው ባሻገር ሕዝቡ በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴቶቹን ጠብቆ በፍቅርና በመገናዘብ እየኖረ መኾኑን ይልቁንም በዚህ ረገድ ከአክራሪነትና ጽንፈኝነት ጋራ በተያያዘ የሚሰጡ ማብራሪያዎች አንዱን የድህነትና ኋላቀርነት ሌላውን የሥልጡንነት መለዮ የሚያስመስል ትርጉም እንዳያሰጡ ማስተዋልና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተመክሯል፡፡
በተያያዘም ‹‹ታሪካችን ረዥም ነው የሚለውን ትምክህት መዋጋት›› በሚል ከመጀመሪያው ምእት ዓመት (34 ዓ.ም.) አንሥቶ የሚቆጠረው የቤተ ክርስቲያኒቱ ብሔራዊ ታሪክ በቅ/ሲኖዶስ አባላት ሳይቀር የመንግሥት ሓላፊዎች የተተቹበትና እንዲታረሙም የተጠየቁበት ኾኖ ሳለ ለውይይት በቀረቡት ጽሑፎች ውስጥ በአግባቡ አለመስፈሩ የመጽሐፍ ቅዱሱን እውነታ መቆነጻጸልና ጥንታዊነቷን የማደብዘዝ ውጥን እንዳለ የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡
እስልምና በሰላም ገብቶ እንዲስፋፋ ምክንያት ኾነዋል የተባሉትን ንጉሥ አርማህ ‹‹በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ›› ከማለት በቀር ስማቸውንና ክርስቲያናዊነታቸውን በመግደፍ የቀድሞዎቹ ነገሥታት በአጠቃላይ ብዝኃነትን እንደ አደጋ የሚመለከቱና የአንድ ሃይማኖት ፖሊሲ የሚያራምዱ ነበሩ ማለትም በአነስተኛው አነጋገር ቅንነት የጎደለው እንደኾነ ተሳታፊዎቹ ለአፍሮ ታይምስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የመድረኩ አወያዮች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችና ፍረጃዎች ቅሬታ አቅራቢ ተሳታፊዎችን በግልጽ ይቅርታ መጠየቃቸው ተገልጦአል፡፡ ፍረጃውና ክሡ ለውይይቱ ከተሰጣቸው ተሰብሳቢውን የማዳመጥ አቅጣጫ አልፈው የተናገሩት መኾኑን በማመን መሳሳታቸውን የገለጹትም ‹‹ማንንም እንዳትፈርጁ፣ ‘specific’ እንዳታደርጉ ተብለናል፤ የመላእክት ስብስብ አይደለንም፤ ሰዎች ነንና እንሳሳታለን›› በማለት ነበር፡፡
ይኹንና ይህ ነው የተባለ ማስረጃ ባይጠቅሱም መንግሥት በሕግ የሚጠይቃቸው አንዳንድ ግለሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳይጠቁሙ አላለፉም፤ መንግሥት በልዩነትና ግጭት ወቅት ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ በሚል ካልኾነ በቀር በሃይማኖት ጣልቃ እንደመግባት ተደርጎ የቀረበውን አስተያየትም አልተቀበሉትም፡፡
የውይይቱ ዓላማ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከአባሉና ከአጠቃላይ ሕዝቡ አቋምና ግንዛቤ በመነሣት በትምክህትና ጠባብነት የሃይማኖት አክራሪነት ርእዮት አራማጅነት በሚፈርጃቸው ወገኖች ላይ በቀጣይ የሚይዘውን አሰላለፍና የምት አቅጣጫ ለመወሰንና ይኹንታ ለማግኘት የሚጠቅምበት ሊኾን እንደሚችል ብዙዎች ያምናሉ፡፡
በቀጣዮቹ ኹለት ውይይቶችና ከዚያም በኋላ በታቀዱ የሕዝብ መድረኮች የስብሰባ ጥሪ የተደረገላቸው ኹሉ እስከ አኹን እንደታየው መዘናጋት ሳይሆን በስብሰባ እየተገኙ አካሔዱን በሐሳብና የመረጃ የበላይነት ማጋለጥና ተገቢው አቋም ላይ እንዲደረስ መትጋት እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡

Saturday, 19 April 2014

አክራሪነትና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር – የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአክራሪነት ትርጉም የተሳሳተ ነው! የፈራጁን ማንነትም መጠራጠር ይኖርብናል!


(አዲስ ጉዳይ፤ ቅጽ ፰ ቁጥር ፪፻፲፪፤ ሚያዝያ ፳፻፮ ዓ.ም.)
Addis Guday Logoዲያቆን ዳንኤል ክብረት
  • እስከ አሁን በታተሙ ቅዱሳት መጻሕፍትም ኾነ ለጥምቀት በታተሙ ካኔቴራዎች ላይ በኤፌሶን ፬÷፬ ላይ ያለው ጥቅስ ከነመገኛው ተጠቅሶ ከመታተሙ በቀር አንድ ሀገር የሚል የለውም፡፡ ከእውነታ አንጻር ይህን ጥቅስ መጥቀስ በራሱ ስሕተት ነው፤ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ ነውና፡፡ ‹‹ጥቁር ድመትን በጨለማ ውስጥ መፈለግ አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ደግሞ ድመቷ ከሌለች›› እንደሚባለው፡፡
  • ከሃይማኖትና ከጥምቀት ጋራ በአንድ ላይ አንድ ሀገር የሚል ክርስትና ሊኖር የማይችለው ከክርስትና ዶግማ ጋራ የማይሔድ በመኾኑ ነው፡፡ ይህን ጥቅስ እስከ አሁን ፖሊቲከኞች እንጂ ሃይማኖተኞች ሲጠቅሱት አልታየም፡፡ ይህ እምነት ደግሞ የኹሉም የክርስትና አማኞች እምነት ነው፡፡ እንዴት ተነጥሎ የአንድ ማኅበር አባላትን ሊያስፈርጅ እንደቻለ የሚያውቁት ፈራጆቹ ብቻ ናቸው፡፡
  • እነዚህን ሦስት ነገሮች አንድ ላይ በማምጣት ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ አምታች እንዲኾን ተደረገ እንጂ ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ በራሱ በሕግ ወንጀል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ሁለት ዜግነትን አይፈቅድም፡፡
  • ‹‹ለአንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት›› ቢል ሌሎችን የማስወገድ ሐሳብ አለው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› ማለት ግን የሰውዬውን አንድ እምነትን መቀበሉን፣ አንድ ጥምቀት መጠመቁን፣ የአንዲት ሀገር ዜጋ መኾኑን ከማመልከት ውጭ ነውሩም፣ ኃጢአቱም ወንጀሉም ምኑ ላይ ነው፡፡ እስኪ አንቀጽ ይጥቀሱልን፤ ወይስ ትክክል የሚኾነው ስንት ሀገር ነው?
  • በቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶን መልእክት ላይ ያለው ቃል ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት›› የሚል ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊም ይኹኑ ከዚህ በፊትም ይህን የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ግን ‹‹አንድ ጌታ›› የሚለውን አውጥተው ‹‹አንድ ሀገር›› የሚል ጨምረውበታል፡፡ ለምን? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ይህ ነገር የዚህን መፈክር ምንጭ እንድንጠረጥር ያደርገናል፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ ‹‹ጌታ›› የሚለው ወጥቶ በሌላ እንዲተካ የተደረገው እነማንን ላለመቀላቀል እንደኾነም መገመት ይቻላል፡፡
  • ‹‹አንድ›› ማለት የሌላ አለመኖርን ሳይኾን ‹‹የሌላው ትክክል አለመኾንን›› የሚገልጥ ነው፡፡ አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል ‹‹አማልክት›› ተብለው የሚጠሩ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይህን መጽሐፍ ቅዱስም ‹የአሕዛብ አማልክት›› በማለት ጠርቶ የሀልዎት/ህላዌ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፤ ነገር ግን ትክክል አይደሉም ማለቱ ነው፡፡
  • ‹‹አንዲት ሃይማኖት›› እና ‹‹አንዲት ጥምቀት›› የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚቀበሉትና በሚያነቡት መጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ይገኛልና የሚኒስቴር መሥ/ቤቱ የአክራሪነት መመዘኛ ይኼ ከኾነ ነገሩ ተያይዞ የት እንደሚደርስ ማየቱ የተሻለ ይኾናል፡፡፡


Dn. Daniel Kibretባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ የሰጡትን መግለጫ አንብቤ ነበር፡፡ ከመግለጫቸው ውስጥ እጅግ የገረመኝና ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ያደረገኝም አክራሪነትን በተመለከተ የሰጡት ትርጓሜ ነው፡፡
መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት እንዳልፈረጀ ከገለጡ በኋላ፣ ‹‹ይህ ሲባል ግን እንደ ማንኛውም ተቋም የተቀደሰውን ዓላማ የሚያራክሱ፣ ማኅበሩን ወዳልኾነ አቅጣጫ የሚወስዱ ግለሰቦች አይኖሩም ማለት እንዳልኾነ ጠቅሰዋል። በተለይም ‹‹አንድ ሃይማኖት! አንድ ሀገር! አንድ ጥምቀት!›› እያሉ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በአክራሪነት ሊፈረጁ ይችላሉ›› በማለት አክራሪ የሚባሉ አባላትን አቋም ገልጠውታል፡፡
እንደ እርሳቸው፣ በእርሳቸውም በኩል እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኾነ ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› ብሎ ማመን ‹‹አክራሪ›› የሚያሰኝ ነው፡፡ እስኪ ይህን የሚኒስቴሩን መግለጫ ከእውነታ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከእምነት አቋም አንጻር እንመልከተው፡፡
‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› የሚል ጥቅስም መፈክርም እስከ አሁን ታይቶ አይታወቅም፡፡ በኤፌሶን መልእክት ፬÷፬ ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት›› የሚል ቃል ነው የሰፈረው፡፡
እስከ አሁን በታተሙ ቅዱሳት መጻሕፍትም ኾነ ለጥምቀት በታተሙ ካኔቴራዎችም ላይ ይኼው በኤፌሶን ፬÷፬ ላይ ያለው ጥቅስ ከነመገኛው ተጠቅሶ ከመታተሙ በቀር አንድ ሀገር የሚል የለውም፡፡ ከእውነታ አንጻር ይህን ጥቅስ መጥቀስ በራሱ ስሕተት ነው፤ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ ነውና፡፡ ‹‹ጥቁር ድመትን በጨለማ ውስጥ መፈለግ አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ደግሞ ድመቷ ከሌለች›› እንደሚባለው፡፡
ይህ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አባባል ከሌላው እውነት ጋራም ይጋጫል፡፡ ክርስትና ሁለት ሀገሮች እንዳሉን የሚነግረን ሃይማኖት ነው፡፡ በዚህ በምድር በሥጋ የምንኖርባትና በላይ በሰማይ ለዘለዓለም የምንኖርባት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነው››(ፊልጵ.፫÷፳) በማለት የተናገረው፡፡ ሃይማኖትና ጥምቀት ግን በዚህ በምድርም በላይ በሰማይም የማይደገሙ፣ መንትያም የሌላቸው በመኾናቸው ሁለትነት አይስማማቸውም፡፡
ከዚህም በላይ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የላከው መልእክት ክርስቲያኖች በአንድ ጊዜ በሁለት ዜግነት ውስጥ እንደሚኖሩ መግለጡን ሊቃውንት ተርጉመውታል፡፡ ‹‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን›› (ኤፌ.፩÷፩)፡፡ እነዚህ የኤፌሶን ክርስቲያኖች እንደ ሰውነታቸው ኤፌሶን በምትባል ሀገር፣ እንደ ክርስቲያንነታቸውም ክርስቶስ በሚባል ወሰንና ዘመን በሌለው ሀገር ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ሊቃውንት መንግሥተ ሰማያት ማለት ራሱ ክርስቶስ ነው፤ እርሱን ወርሰን በእርሱ እንኖራለንና፡፡
ስለዚህም ከሃይማኖትና ከጥምቀት ጋራ በአንድ ላይ አንድ ሀገር የሚል ክርስትና ሊኖር የማይችለው ከክርስትና ዶግማ ጋራ የማይሔድ በመኾኑ ነው፡፡ ይህን ጥቅስ እስከ አሁን ፖሊቲከኞች እንጂ ሃይማኖተኞች ሲጠቅሱት አልታየም፡፡ ይህ እምነት ደግሞ የኹሉም የክርስትና አማኞች እምነት ነው፡፡ እንዴት ተነጥሎ የአንድ ማኅበር አባላትን ሊያስፈርጅ እንደቻለ የሚያውቁት ፈራጆቹ ብቻ ናቸው፡፡ ምናልባትም ፈራጆቹም ይህን ማመናቸው የማይቀር ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ሦስት ነገሮች አንድ ላይ በማምጣት ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ አምታች እንዲኾን ተደረገ እንጂ ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ በራሱ በሕግ ወንጀል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ሁለት ዜግነትን አይፈቅድም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ሌላ ዜግነት ሲያገኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ወዲያው ያጣልና፡፡ (የዜግነት ዐዋጅ ቁጥር 378/96፣ ዐንቀጽ 19 – 20/1)፡፡ ይህ ማለት ሊኖርኽ የምትችለው ሀገር አንዲት ናት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎችም ዜግነታቸውን የለወጡትን ኢትዮጵያውያን ‹‹ትውልደ ኢትዮጵያውያን›› ይሏቸዋል እንጂ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› አይሏቸውም፡፡ ይህም ማለት የሀገራችን ሕግ አንድ ኢትዮጵያዊ አንድ ሀገር (እርሷም ኢትዮጵያ) ብቻ ሊኖረው እንደሚችል ይደነግጋል ማለት ነው፡፡
ከዚህም በላይ አንድ ኢትዮጵያዊ ‹‹እኔ የምትኖረኝ አንዲት ሀገር ብቻ ናት›› ቢል ችግሩ ምኑ ላይ ነው፤ ደግሞም ብዙዎቻችን እንደዚያ ነን፡፡ ትምረርም፣ ትረርም ያለችን አንዲት ሀገር ናት፤ ትመችም፣ ትቆርቁርም ያለችን አንዲት ሀገር ብቻ ናት፡፡ ስለዚህም ምን የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት ባይኾን አንድ ኢትዮጵያዊ ተነሥቶ ‹እኔ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት ብቻ እቀበላለኹ›› ቢል በሕግስ፣ በሞራልስ፣ በልማድስ ምንድን ነው የሚያስጠይቀው፡፡
‹‹ለአንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት›› ቢል ሌሎችን የማስወገድ ሐሳብ አለው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› ማለት ግን የሰውዬውን አንድ እምነትን መቀበሉን፣ አንድ ጥምቀት መጠመቁን፣ የአንዲት ሀገር ዜጋ መኾኑን ከማመልከት ውጭ ነውሩም፣ ኃጢአቱም ወንጀሉም ምኑ ላይ ነው፡፡ እስኪ አንቀጽ ይጥቀሱልን፤ ወይስ ትክክል የሚኾነው ስንት ሀገር ነው?
ይህን ሐሳብ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር ስንመረምረው አስገራሚ ነገር እናገኛለን፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶን መልእክት ላይ ያለው ቃል ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት›› የሚል ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊም ይኹኑ ከዚህ በፊትም ይህን የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ግን ‹‹አንድ ጌታ›› የሚለውን አውጥተው ‹‹አንድ ሀገር›› የሚል ጨምረውበታል፡፡ ለምን? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ይህ ነገር የዚህን መፈክር ምንጭ እንድንጠረጥር ያደርገናል፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ ‹‹ጌታ›› የሚለው ወጥቶ በሌላ እንዲተካ የተደረገው እነማንን ላለመቀላቀል እንደኾነም መገመት ይቻላል፡፡
‹‹አንድ›› የሚለውን ሐሳብ ከክርስትና አስተምህሮ አንጻር ስንመለከተው አክራሪ ሳይኾን ዐዋቂ የሚያሰኝ ኾኖም እናገኘዋለን፡፡ ‹‹አንድ›› የሚለው ሐሳብ በሦስቱም ታላላቅ የዓለም እምነቶች መሠረታዊ የእምነት ቁጥር ነው፡፡ ቁጥሮች በቅዱሳት መጻሕፍት አኃዛዊ/የብዛት ዋጋ (numerical value) ሳይኾን መንፈሳዊ ዋጋ ነው ያላቸው፡፡ ሦስት የምስጢረ ሥላሴ፣ አምስት የእምነት አዕማድ፣ ሰባት የፍጹምነት፣ ዐሥር የምሉዕነት፣ መቶ የእግዚአብሔር መንጋ፣ ሺሕ መጠንና ልክ የሌለው ዘመን እያለ ይቀጥላል፡፡
የኦሪት (ይሁዲነት) እምነት መሠረቱ በ‹‹አንድ አምላክ› ማመን ነው፡፡ በእስልምናም ከመሠረታውያኑ አምስቱ የእምነቱ አዕማድ አንዱ ‹‹በአንድ አምላክ(አላህ) ብቻ ማመን›› ነው፡፡ በክርስትናም ቢኾን በአንድ አምላክ ማመን መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ አምላክ አንድ ነው ካልን ደግሞ ሃይማኖትም አንድ ነው ማለታችን ነው፡፡
ከላይ ካነሣናቸው ታላላቅ እምነቶች አንዱም እንኳን ሃይማኖት ሁለት ነው ወይም ሦስት ነው የሚል ፈጽሞ የለም፡፡ በዚህም መሠረት ‹አንድ ሃይማኖት›› ማለት አክራሪነት ከኾነ በዓለም ላይ አክራሪ ያልኾኑት የቡድሃ፣ የኮንፊሺየስ ወይም የሌሎች የሩቅ ምሥራቅ እምነቶች ተከታዮች አለያም ደግሞ እምነት አልባ ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ከኾነ ደግሞ ከዓለም ሕዝብ ከሁለት ሦስተኛው በላይ አክራሪ ነው ያሰኛል፡፡
በክርስትና ትምህርት ‹‹አንድ›› የሚለው ቃል ከቁጥር ዋጋ በላይ አለው፡፡ የእምነት ቁጥር ነው፤ ሊደገሙ፣ ሊሠለሱ የማይችሉ ነገሮች መገለጫም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውስጥ ቢያንስ ዘጠኙ ‹አንዶች› የታወቁ የእምነት መሠረቶች ናቸው፡፡
  1. አምላክ አንድ ነው፡- ክርስትና ብዙ አማልክትን አይቀበልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም አማልክት የሚላቸው ኹለት ነገሮችን ነው፡፡ አንድም የአሕዛብን ጣዖታት (የአሕዛብ አማልክት እንዲል)፣ ያለበለዚያም ቅዱሳንን (እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ) እንዲል፡፡
  2. ሥጋዌ አንድ ነው፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ አዳምን ለማዳን ሰው ሆኗል፡፡ ዳግም አይወለድም፣ ሰውም አይሆንም፡፡
  3. ሃይማኖት አንድ ነው፡- ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የመጓዣ መንገድ፣ ፍኖተ እግዚአብሔር፣ ወይም እግዚአብሔር ዓለምን ፍለጋ ያደረገው ጉዞ በመኾኑ ምንታዌ የለውም፡፡ ወደ አንድ እግዚአብሔር የሚወስደው ትክክለኛው መንገድ አንድ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ መጽሐፍ ‹የእግዚአብሔር መንገድ› ይለዋል (ኤር. ፭÷፬)
  4. ጥምቀት አንዲት ናት፡- ጥምቀት የሞት ምሳሌ ነው፤ መጠመቅም ከክርስቶስ ጋር መሞት ነው(ሮሜ ፮÷፫)፤ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ብቻ ሞቷልና እኛም አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን፤ ሞትም አንድ ጊዜ ብቻ ነውና ጥምቀትም አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጥምቀት እንደ ቁርባንና ንስሐ አይደገምም፡፡
  5. ክህነት አንድ ጊዜ ነው፡- ክህነት እያደገ ይሄዳል እንጂ አንድ ሰው በአንድ መዓርግ ሁለት ጊዜ አይካንም፤ ክህነቱን ቢያፈርስም ምእመን ሆኖ ይኖራል እንጂ እንደገና አይካንም፡፡
  6. ፍጥረት አንድ ጊዜ ነው፡- እግዚአብሔር ፍጥረትን አንድ ጊዜ ነው የፈጠረው፤ ደግሞ የፈጠረው ፍጥረት የለም፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ፍጥረት ሲፈጸምም ከዚያ በኋላ እንደገና አይፈጠርም፡፡ ይባዛልለ፤ ይዋለዳል፤ ያረጃል፤ ይሞታል እንጂ ፍጥረት እንደገና አይፈጠርም፡፡
  7. የመጨረሻው ፍርድ አንድ ጊዜ ነው፡- የዓለም መጨረሻ አንድ ጊዜ በመጨረሻው ቀን ፍርድ የሚዘጋ ነው፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜ የሚሰጥ የዓለም የፍርድ ቀን የለም፡፡
  8. ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፡- በኒቂያ በ፫፻፳፭ ዓ.ም. የተሰባሰቡት ፫፻፲፰ ሊቃውንተ እንደ መሰከሩት ‹ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት›፡፡ ሁለትነትና ሦስትነት የለባትም፡፡
  9. ተክሊል አንድ ጊዜ ነው፡- ተክሊል የሰማያዊ አክሊል ምሳሌ ነው፡፡ ሰማያዊ አክሊል አንድ ጊዜ የሚሰጥ፣ ተሰጥቶም የሚኖር ነው፡፡ የእርሱ ምሳሌ የሆነው ተክሊልም አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ፣ ተሰጥቶም የሚኖር ነው፤ አይደገምም፡፡
መሠረታዊ የኾኑትን ዘጠኙን አነሣን እንጂ ‹አንድነት› የክርስትና ዋናው መለያ ነው፡፡ ለዚኽም ነው አንድ ሃይማኖትና አንዲት ጥምቀት የሚለው እምነት ትክክለኛ የሚኾነው፡፡ በ፫፻፹፩ ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ የተሰባሰቡ ፻፶ አባቶችም ‹‹ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት፤ ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› በማለት በማለት የደነገጉትም ለዚህ ነው፡፡ ይህን ማለት አክራሪነት ከኾነ ፍረጃው ሠለስቱ ምእትንና ፻፶ው ሊቃውንትንም ይጨምራል ማለት ነው፡፡
እነዚህን ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች በተነገሩበትና በተጻፉበት ዐውድ ውስጥ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ‹‹አንድ›› ማለት የሌላ አለመኖርን ሳይኾን ‹‹የሌላው ትክክል አለመኾንን›› የሚገልጥ ነው፡፡ አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል ‹‹አማልክት›› ተብለው የሚጠሩ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይህን መጽሐፍ ቅዱስም ‹የአሕዛብ አማልክት›› በማለት ጠርቶ የሀልዎት/ህላዌ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፤ ነገር ግን ትክክል አይደሉም ማለቱ ነው፡፡ አንድ ሰው በስሕተት ዳግም ሊያጠምቅ አይችልም እያለ አይደለም፡፡ ጥምቀቱ የተደገመ ከሆነ ስሕተት ነው እያለ ነው፡፡ ‹‹አንድ ሃይማኖት›› ሲልም ርቱዕ የኾነችው እምነት አንዲት ናት፤ ሌሎቹ የተሳሳቱ ናቸው እያለ ነው፡፡
ይህ አስተሳሰብ የእምነት አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለይም ሦስቱ የዓለማችን ታታላቅ እምነቶች ‹‹ርቱዕ፣ ትክክለኛና፣ ድኅነት የሚገኝበት ሃይማኖት›› የሚሉትን ይበይናሉ፤ በብያኔያቸውም የእነርሱ እምነት መኾኑን ይገልጣሉ፡፡ በእምነት አቋም ውስጥ ‹‹ብዙ ትክክለኛ እምነት›› ሊኖር አይችል፡፡ በሀገር ውስጥ ግን ብዙ እምነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እምነት ብዙ እምነቶችን ሊያስተናግድ አይችልም፡፡ ብዙ እምነቶችን ሊያስተናግድ የሚችለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡
ደግሞም ያኛው ስሕተት ነው እኔ ትክክል ነኝ ማለት አክራሪነት አይደለም፡፡ እምነት ነው፡፡ እንኳን አንድ እምነት፣ እን የፖለቲካ ፓርቲ እንኳን ትክክለኛው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የዕድገት መሥመር የእኔ መሥመር ነው፣ የሌላው ስሕተት ነው ብሎ አይደለም እንዴ እየተፎካከረ ያለው፡፡ ይህ በአክራሪነት ካስፈረጀ፣ እንኳን ፖሊቲከኛው በፖለቲካ የለኹበትም የሚለውም አይተርፍ፡፡ እርሱ ራሱ ‹‹ፖለቲከኛ አለመኾን ነው ትክክለኛው›› እያለ ነውና፡፡
የእኔ ትክክል ነው ማለት ሌሎች መኖር የለባቸውም፤ መጥፋትም አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ እንኳን በሥላሴ አርኣያ የተፈጠሩ ሰዎችን ቀርቶ ሰይጣንንም እንኳን እንዲጠፋ መመኘት ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡ ሰይጣንን መቃወም ሰይጣንን ማጥፋት አይደለም፡፡ መከራከርና መገዳደር እንጂ፡፡
ማጠቃለያ
ከላይ ባነሣናቸው ነጥቦች ብቻ እንኳን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰጠው የአክራሪነት ትርጉም የተሳሳተ መኾኑን ማየት ይቻላል፡፡ ‹‹አንዲት ሃይማኖት›› እና ‹‹አንዲት ጥምቀት›› የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚቀበሉትና በሚያነቡት መጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ይገኛልና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአክራሪነት መመዘኛ ይኼ ከኾነ ነገሩ ተያይዞ የት እንደሚደርስ ማየቱ የተሻለ ይኾናል፡፡

Sunday, 13 April 2014

ዋጋ የሚያሰከፍሉ ጥፋቶች!

ትዉልዱ የሚከፍለዉ ነገር ግን ሊከፍለዉ የማይገባዉ ዋጋ! ይህ ትዉልድ ስለ ሃገሩና ስለ ሃይማኖቱ የከፈለዉን ዋጋ ምንም የሚወዳደረዉ የለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከማንም ክርስቲያን ልብ ዉስጥ ከማይጠፉት ከምዕመናኖቿ ጋር የተወጣቻቸዉን ሁለት ክፉ አጋጣሚ እንመልከት፡-
. የዮዲት ጉዲት
.የግራኝ መሐመድ …. እያሉ መቀጠል ይቻላል፤
ነገሥታት እና መንግስታት በመጡ ቁጥር አንዳቸዉም አልበጇትም ሊያስብል በሚችል መልኩ ጠላቶቿ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነትና በሕዝቦቿ አንድነት ግን የተቃጣባትን መከራ ሁሉ ብዙ ዋጋዎችንም ከፍላ ቢሆን ተወጥታዉ እነሆ 21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ደርሳለች ሆኖም ግን ጠላቶቿ እየበዙ ሄዱ እንጂ ወዳጅ አላፈራችም፡፡
እንደ ግራኝ መሐመድና እንደ ዮዲት ጉዲት ቀጥታ በቤተክርስቲያን ላይ ታጥቀዉ አይምጡ እንጂ ጉዳት በማድረሱ ግን (ከሁለቱ ዘመናት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በማቃጠል፣በመዝረፍ፣በማሸሽ፣ቤተክርስቲያንን በማቃጠል፣ካህናትን በማሰር፣በማወክ፣በመግደል …. ) ከትላንት ሳይብስ አይቀርም፡፡ ትላንት ርስት ጉልት የነበራት ቤተክርስቲያን ዛሬ አጥሮቿ እየተነቀሉ ይገኛል፤ ታላላቅ ሃገራዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸዉን ሥራ የሰራች ቤተክርስቲያን ለእነሱ አካሄድ ስላልተመቸች ባሏት ልጆች ዳር ድንበሯን አናስደፍርም፣ የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም ባሉ ….ወዘተ ምክንያቶች ከአሸባሪነት እየፈረጇት ይገኛል፡፡
አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብልህነት ሳይሆን ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነዉ!
ሰዉ ለሚጠቅመዉና ለተጠቀመበት ነገር ዋጋ ይከፍላል፤ መክፈልማ አለበት ህግም ያስገድደዋልና፡፡

አዉራዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ባሳለፋቸዉ ሁለት አስርት ዓመታት ዕድሜ ዘመኑ ግን ምንም እንኳን የአንድ አፍላ ጎረምሳ ዕድሜ ቢያሳልፍም (በዛሬዉ ዘመን አቆጣጠር ከአንድ ዩኒቨርስቲ የተመረቀ ምሁር ወጣት ቢሆንም)  ስራዉ ግን ሲፈተሽ ዕቃቃ ሲጫወት የቡድኑን አባላት የጫወታ መንፈስ የሚያዉክ አንድ አስቸጋሪ ህፃን ባህሪ እየያዘ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ አካሄዱ ደግሞ ለድርጅቱ ህልዉና ብቻ ሳይሆን እንደኔ ግላዊ አመለካከት ደግሞ አገሪቱ ለተያያዘችዉ ሰላም የማስፈን፣ልማትን የማፋጠን፣ድህነትን የመዋጋት አጀንዳየሚያደናቅፍ፤ የልማት ሠራዊቱንም የሚያመናምን መስሎ ይታየኛል፡፡(የእኔ የግል አጀንዳ ምንም እንኳን ያለምንም መደራደሪያ አገር ወደ ተሻለ ሰላም እና ዕድገት ማድረስ እና ለዜጋዎቿ ሰላምን መስጠት ቢሆንም ጠንካራ እና ዓላማ ያለዉ አባል አልጠላም፤ ለእንብላዉ ያልተሰበሰበ፡፡)
ለማሳያነት ህገ-መንግሥቱን ጥሶ በሃይማኖቶች ጣልቃ በመግባት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማዋከብና አቅም ማሳነስ፣ አባላቶቹንና የፖለቲካ መሪዎቹን ሰበባሰበብ ፈልጎ በፀረ ሽብሩ አዋጅ አሳቦ የእስር ቤት ሲሳይ ማድረግ፣ማህበራትን ማፍረስ፣ አላስፈላጊ ህጎችን ለራሱ ማጥቂያነት እንዲመች አድርጎ መደንገግ….እነዚህ ሁሉ መንግስት ያለአግባብ የሚከፍላቸዉ ዋጋ እና ለራሱ እያቆየ ያለዉ ግፍ ነዉ፡፡ (እነዚህን ነገሮች ስንጠቅስ የተነሱት ነገሮች ሙሉ ለሙሉ አገርን አልጠቀመም ለማለት አልደፍርም ሚዛናዊነት የጎደለዉ ይሆንብኛልና አገርንም ከጥፋት ሃይሎች መታደጉ የማይካድ ነዉና ንፁሃንን የመበቀያ መሳሪያ የመሆኑንም ያህል ኢህአዴግ የጠላዉን አናቱን መባያ መዶሻዉ ነዉና!) 
አንድ ዓይን ያለዉ በአፈር አይጫወትም እንደሚባለዉ አሁን ባለችዉ ፀጥታና ሰላም ወቅት ልማቱን እንደማፋጠን አንዳንድ ከልማቱ ዉጭ ሆነዉ በቦዘነ/ሥራ በፈታ አዕምሮአቸዉ ነገር በሚፈጥሩ/በሚፈበርኩ (ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ወርክሾፕ ይሆናል እንዲሉ አበዉ) ሰይጣናዊ ሥራ በመሸረብ የተጠመዱ አሉ፡፡ ይህም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ሞክረዉ ያልቻሉትን ሲያገረሽባቸዉ እየቆዩ የጥፋት ስራቸዉን ማቀናበር ይጀምራሉ … … ከዚህ ቀደም ጥቃቅን ባለስልጣናትን የመንግስትን ስም ሊያጎድፉ ሲነሱ፣ህብረተሰቡን ሲበድሉ ስናይ ስንሰማ፣ መብራት ሲጠፋ፣ኔትወርክ ሲቋረጥ፣ ዉሃ ሲጠማን ….  " ይድረስ ለመንግስታችን …" እያልን አቤት! ስንል ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም በቱባ ባለስልጣናቱ የገዳማትን (እነ ዋልድባን) ይዞታ መንጠቅ እና ገዳሙን መፍታት፣ አባቶችን ለእስር በመዳረግ፣ወዘተ  የተጀመረዉ የቤተክርስቲያንዋን የጀርባ አጥንት የሆነ ማህበር "ማህበረ ቅዱሳን" አጽራረ ቤተክርስቲያንን አስርጎ ከማስገባት እስከ ለማፈራረስ እና ደብዛዉን ለማጥፋት መነሳት የጥፋት ጅማሬዎቹ ነበሩ፡፡(ያለወደደዉን የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት መበተን ስራዉ እንደሆነ ልጆች ሳለን ሰንበት ትምህርት ቤት ስንማር በነበረበት አካባቢ  ሰንበት ትምህርት ቤቱን ከመንግስት ሊሰልሉ መጥተዉ ምንም እንከን አጥተዉ ተሰብከዉ ንስሐ ገብተዉ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሆኑ ምዕመናን ምስክሮች ናቸዉ )
ይሁን እንጂ "የሲዖል ደጆች አይችሉአትም … " የተባለላት ቤተክርስቲያን ዛሬም ጸንታ ፍሬዋን እያፈራች ትገኛለች፤ ሆኖም ፍሬዋን እየተመገቡ ያደጉትም፣ በአፍኣ ያሉትም፣ በአንድነት ተባብረዉና የዉስጠኞቹ ለዉጨኞቹ ክንድ እየሆኑዋቸዉ ዛሬም በጠላትነት እየተነሱባት ግማሹ በማደስ ሰበብ፣ ግማሹ በቃ "ትጥፋ" በሚል ሰበብ፣ ግማሹ እንቆራርሳት (ወይ "ተሐድሶ" አሊያም "ተዋህዶ" እያልን እንፈርጃት በማለት ላይ ይገኛሉ፤)፡፡
ከሰሞኑም የተለያዩ ሚዲያዎች ቀድመዉ እንደሚተነብዩትም ይሁን እንደሚዘግቡት በኢቲቪ ከዚህ ቀደም እንደሚሰራዉ የዉንጀላ ቪድዮ ለዚሁ ማህበር ለማህበረ ቅዱሳን መክሰሻ እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረ ገጽ የሚጠፋበትን ሴራ (ይቅርታ ከምድረ ገጽ እንጂ ከሰዉ ልብ አላልኩም፤ እነሱም በሰዉ ልቡና ያፀኑት እንደሆነ እንጂ አያናዉፁትምና) እያዘጋጁ እንደሆነ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መንግስት ያላወቀዉ ነገር ክርስትናም ሆነ ክርስቲያን እንደ ሚስማር መከራ በበዛበት ቁጥር እየፀኑ መሄዳቸዉን አልተረዳዉም፡፡( ከመጽናት ባሻገር የመረረዉ ማህበረሰብ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ከሱ የባሰ የሚያዉቀዉ የለም ብሶት የወለደዉ "ጀግና " ነዉና!)
በማያያዝም መንግሥትን እንደዜጋ ላሳስበዉ የምወደዉ ጉዳይ እምቢኝ አልገዛም ብሎ ጫካ በገባ ጊዜ ምንም እንኳን ጥቂቶቹች ቢሆኑም ለዚህ ድል የበቃዉና ስልጣኑን ይዞ ዛሬ የደረሰዉ (በአንድም ሆነ በሌላ) በህዝብ ድጋፍ እንደሆነ ልብ ይለዋል፤ ዛሬም የሚዘነጋዉ አይመስለኝም፡፡( ይዘነጋዋል የሚልም እምነት የለኝም ከረሳዉም ላስታዉሰዉ ወዳለሁ፡፡) ይህ እንዲህ ከሆነ ዘንድ ማህበሩም (ማህበረ ቅዱሳን) የተነሳዉ እግዚአብሔርንና ህዝብን ይዞ እንደሆነ ላስገነዝበዉ ወዳለሁ፤ ማኀበሩን ለማፍረስ መነሳትም ሆነ ማሰብ አንድም ህዝብን መናቅ አንድም ከእግዚአብሔር ጋር መገዳደር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እግዚአብሔርንም ሆነ ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ የለም ደርግን ለዉድቀት ያበቃዉ የኢህአዴግ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን የህዝብ የምሬትና የሐዘን ነዉጥ ነዉ፡፡ ዛሬም እንዲሁ ይህ ህዝብ ታሪክ መድገሙ የነጠፈ አይመስለኝም ምንም እንኳን አብዛኞች ስሙን በተለያየ መንገድ ሊያጠለሹ ቢነሱም (ማኅበሩ ችግር የለበትም ማለቴ አይደለም ሊኖርበት ይችላል ግን ከሚሰጠዉ ሊተካ የማይችልና በጭራሽ የተዘነጉትን መስኮች በመስራቱ ሊበረታታ የሚገባዉ እንጂ ሊበተን ሊዘጋ የሚገባዉ ማኅበር አይደለም፤) መንግስት ሊያጠፋዉ ወይም እንቅስቃሴዉን ሊገታዉ ለሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ግን በዝምታ መንስግስትን የሚያዩት አይመስለኝም ፡፡ መንግስትም "ማኔ ቴቄል ፋሪስ" መባያ ሰዓቱ ደርሶ እንደሆን እንጂ አካሄዱን ደግሞ ደጋግሞ ፈትሾ ከሃሳቡ ቢመለስ ይሻለዉ ይመስለኛል፡፡(ይህም ደግሞ ይጠቅመዉ እንደሆነ እንጂ አይጎዳዉም እንደሚባለዉ ኢህአዴግ በሰዉ ሃሳብ መሸነፍ የማይወድ ካልሆነ በቀር፤)
አሁን ከቤተክህነቱ ጥላ ስር ሆነዉ ማኅበሩን እንደ ዕባብ በመርዛቸዉ ከሚናደፉት ዉስጥ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የሰላሌ አገረ ስብከት ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሊቀ ማዕምራን(የዛሬዉ ሊቀ ካህናት) (እሳቸዉ ሲሉት እንደነበረ ከሆነ "ታጋይ" ናቸዉ ሰዉ ምንም እንኳን ለሁለት ጌታ መገዛት ባይችልም እሳቸዉ ግን በሁለት ቢላ እየበሉ ለሁለት ጌታ እየተገዙ ይገኛሉ፡፡አንድም ከቤተክህነት ደሞዛቸዉን እየበሉ ቤተክርስቲያንን የማፈራረስ የጫካ ራዕያቸዉን ይተገብራሉ፡፡ ) እኚህ ሰዉ ሀገረ ስብከቱ ተመድበዉ እንደሄዱ በበዓለ ጥምቀት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተኮላተፈ አማርኛቸዉ ሲያስተምሩ ጨዋዉ የከተማዉ ህዝበ ክርስቲያን በእልልታና በጭብጨባ ትምህርቱን ሲያደምጣቸዉ ቆይቶ እዚያ ድረስ እንደተንሰራፋ ያላሰቡት ሊቀ ማዕምራን ማኅበረ ቅዱሳንን መወረፍ ሲጀምሩ በድምቀት ሲያዳምጣቸዉ የነበረ ህዝበ ክርስቲያን በአንድ ድምፅ ያሰማቸዉ ጉምጉምታ ሳያስቡት በድንጋጤ መናገር እስኪሳናቸዉ ድረስ ድምፅ ማጉያዉን ያስቀመጡበትና ዳግም መተንፈስ እንደተሳናቸዉ ዛሬ ድረስ የማስታዉሰዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ (ከማኅበሩ ጋር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስምምነት እንዳሌላቸዉ በልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ዛሬ ለመድረስ ችያለሁ፡፡)ዛሬም ከጠቅላይ ቤተክህነት በመሆን ይህንኑ የተለከፉበትን አባዜ ሲያካሄዱ ወደኃላ ተመልሰዉ የፍቼዉን የህዝብ ድምፅ ቢያደምጡት ይሻላቸዉ ነበር ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት አንድ ከተማ ሙሉ ድምፁን አንድ የሚያደርግለት ማኅበር ዛሬ ደግሞ ድርጅቱ ኢህአዴግ አለኝ ከሚለዉ አባላት ቁጥር በላይ ያለዉ ማኅበረ ቅዱሳንን መንካት ምን ያህል ድፍረት እንደሆነ አስቀድሞ ሊገነዘበዉ ይገባዉ ነበር፡፡ (ለነገሩ ኢህአዴግ ከማኅበሩ ጋርም ያላስማማዉና ስጋት የሆነበትም እንደ ፖለቲካ ተንታኞችም ሆነ እንደ እኔ ጥርጣሬ የማኅበሩ አባላት ቁጥር እጅግ መብዛትና የአገልግሎታቸዉ መንሰራፋት፣ ቤተክርስቲያንን ሊቀብሯታ ከነበረችበት ጉድጓድ ቀና የማስባል አካሄዳቸዉ ስላስፈራዉ ይመስለኛል፡፡ በሌላ መልኩም ካየነዉ አያድርግባቸዉና የሃይማኖት ካባቸዉን ወርዉረዉ፣ ዓላማቸዉና ግባቸዉን ቀይረዉ ማኔፌስቱ አዘጋጅተዉ ፖለቲከኞች ነን ቢሉ በዚህ ሁሉ አባላት …. የመንግሥትን ሥልጣን ለግንቦት 20 የሚያደርሱት አይመስሉም  ስለዚህ መንግሥታችን መፍራቱ ደግ አደረገ ያስብለዋል፡፡  የፈራ ደግሞ ከክፉ መንገድ ይመለስ ደግሞ መልዕክቴ ነዉ!)
(አንድ ቁም ነገር ልንገራችሁ፡- ፈርኦንን መቸስ የማያዉቅ የለም ህዝበ እስራኤልን አሳራቸዉን ያሳያቸዉ፣ ራሔልን ልጇን በግፍ ጭቃዉ ዉስጥ እንድትወልድ ያደረገና ለቤተመንግሥቱ ማሳነጫ ከሚቦካዉ የጡብ ጭቃ ጋር የጨቅላ ህጻኗ ገላ ጭቃዉን ያጠነክረዋልና አብረሽ ርገጭዉ ብሎ ያስረገጠ አረመኔዉ ፈርኦን…. እግዚአብሔር ህዝቡን ሊታደጋቸዉ ሙሴን ከአሮን ጋር ወደ ግብፅ በላከ ጊዜ ፈርኦን ባሪያዎቹ ህዝበ እስራኤልን አለቅም ባለ ጊዜ …. እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በአስር ታላላቅ ተዓምራት ግብፅን ሲመታ አርኦን ልቡ ደንድኖ ነበር በአስራ አንደኛዉ የበኩሮች ሞት የደነገጠዉ ፈርኦን ወደ መኝታ ክፍሉ ገብቶ ሚስቱን የግብፅ በኩሮች ሁሉ አለቁ እኔ ብቻ ቀረሁ እነዚህን ሰወች ላሰናብታቸዉ ብሎ አማከራት  ሁሉ መአት በአገሪቱ ላይ ሲወርድ አትልቀቃቸዉ ስትለዉ እሺ ያለ (ሴት የላከዉ እንደሚባለዉ) ፈርኦን አሁን ግን ሚስቱ ጭን ስር ገብቶ ስለፍርሃቱ ሲነግራት ከግብፅ ህዝብ እልቂት ይልቅ (ስለ ህዝቡ ሳይሆን) ባሏ እንዳይሞትባት፣ ስልጣኗን፣ ክብሯን እንዳታጣ ስትልሞት ቤታቸዉ እንዳይገባ ስትልአሁንስ ፈራሁ አለችዉ ህዝቡንም በሰላም አሰናበታቸዉ ….  ምንም እንኳን በስተመጨረሻ ትዕቢቱ አገርሽቶበት ባህረ ኤርትራ ሰጥሞ ቢሞትም፤ መፍራት ጥሩ ነዉ ጆሮ ያለዉ ይስማ! ከክፉ መንገዱም ይመለስ የእግዚአብሐየርንም ህዝብ በሰላም ያሰናብታቸዉአለበለዚያ መጥፋት እንዳለ የፈርኦን የህይወት ታሪክ ያስተምረናልና፡፡መልዕክታችን ነዉ!)
ኢህአዴግ አባላቱን በዚህም በዚያም አንድ ለአምስት እያለ ቢጠረንፋቸዉም "የፈሩት ይደርሳል: የጠሉት ይወርሳል" እንደሚባለዉ ሁሉ ኢህአዴግ የማህበሩን በሰዉ ቁጥር መብዛትና ተደማጭነት ማግኘት በአቅምም የመደራጀታቸዉ ጉዳይ ስጋቱን እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ የጥርነፋዉ አካል ከሆኑት አምስት ሰወች ያለማጋነን ሁለቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆነ ሰንበት ትምህርት ቤት የመጡ ስለሆነ የርሱ (የኢህአዴግ) አይደሉም (የሆኑትም ግዴታ ስለሆነ አንድም በቅንነት አገርን ከማገልገል አኳያ ነዉ) ሁለቱ ደግሞ ቀጥታ ጥሙቃን ካድሬዎች ሳይሆኑ እንዲሁ የተነከሩ (ጥቅመኞች፣ የደርግ ካድሬ መሰሎች)ናቸዉ፡፡ የተቀረዉ አንደኛዉ ተጠርናፊ ደግሞ ኢህአዴግ እያካሄደ ባለዉ ስርዓት ተስፋ የቆረጠ አድርባይ እንጂ የክፉ ቀን ወዳጁ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ማኅበሩን ለማፍረስ በሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ራሱን ለአደጋ ያጋልጥ እንደሆነ እንጂ ለማኅበሩ ስጋት ሊሆን አይችልም ይልቁንም የማኅበሩን እንቅስቃሴ፣ የሃይማኖት ፅናት፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ፣ መከራ የመቀበል በረከታቸዉን …. ያበዛላቸዋል የሚል ዕምነት ነዉ ያለኝ፡፡(እንዲህ ስል ግን ፍርሃት/ሽብር ለመንዛት አይደለም ምናልባት ምክሬን ሰምቶ ከመጥፎ መንገዱ ተመልሶ ወደ ልማቱ ብቻ ፊቱን ያዞር እንደሆነ የዕድሌን ልሞክር ብዬ ነዉ፤ እነሱም መንግስትን የማስፈራራት ህልም ሆነ ቅዠት የላቸዉምና አገርንና ቤተክርስቲያንን የማገልገል ራዕይ እንጂ፡፡ ምናልባት በመሃል የተሰገሰጉ የማኅበሩን ስም ለማጉደፍ የሚሯሯጡ አፅራረ ቤተክርስቲያን አይጠፉም እንዲዉም መንግስት እነዚህን ተኩላዎች ከማኅበሩ ጎን በመሆን ቢያጠራላቸዉና እነዚህን የልማት ሰራዊት በደንብ ቢጠቀምባቸዉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡)
ማኅበረ ቅዱሳን እኔ እንኳን ባለኝ ትንሽ ግንዛቤ በአራቱም ማዕዘን (በመላዉ ዓለም) እንኳን ለአንድ መንግስት ለሰይጣን የማይፈታ ጠንካራ ቤተክርስቲያንን ያሉ ፣ለእግዚአብሔር "አንለይህም!" በማለት የማሉ መከራን ስደትን፣ ወዘተ ሊቀበሉ የተዘጋጁ አባላት ያሉት ማኅበር ነዉ፡፡(እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ ሶስቴ ለመካድ ያለተዘጋጁ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ እስከ መስቀሉ ስር የማይጠፉ የቤተክርስቲያንን አደራ የሚቀበሉ ናቸዉ፡፡/የማኅበሩን አባላት እንዲህ ስል እንድትታበዩ ሳይሆን የተሸካችሁትን የክርስቶስ እረፈ መስቀል እንዳትዘነጉት ለማሳሰብ ጭምር እንጂ፤ ከአደራ ጭምር ይህንንም በማነበብ እዳትታበዩ ፡፡ አንባቢም ካብካቸዉ እንዳትሉኝ እኔ የማላዉቀዉ እግዚአብሔር የሚዉቀዉ ለዚህች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን የዋሉት ዉለታ (የተወጡት ግዴታ) አለና ነዉ! አንድም የቤተክርስቲያን አራት ዐይን የሆኑትን የቤተክርስቲያ መምህራን የቆሎ ተማሪ በመታደግ ላይ ናቸዉናወዘተ/) ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በተለየያዩ ብሔር ብሔረሰብ ጥምር ዉበትን ተላብሰዉ መገኘታቸዉና በመንግስት ዉስጥ ያለዉ የብሔርተኝነት መከፋፈል አለመታየቱ የጥንካሬአቸዉ አንዱ ማሳያ ነዉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በየዋሻዉና በየበዓቱ ያሉ ስዉራን አባቶች ፀሎትና ልመና እንዲሁ ዝም አይልም እንደከዚህ በፊቱ መልሱን እየሰጠ እንጂ፤ ትናንትም የጠበቀዉ ዛሬንም ከመከራ ከፈተና የሚከልላቸዉ የአባቶች ፀሎትና የእግዚአብሔር ቸርነት ነዉ፡፡
እንደዉ እንኳን ይህ ሁሉ አልሆነም ብንል እና የማይሳነዉ መንግሥታችን አባላቱን /መሪዎቹን በአሸባሪነት ወይም በሆነ ነገር ፈርጆ እስር ቤት ቢዶላቸዉ (አንተ ላቆምከዉ ጣዖት/ስርዓት አንገዛም/አንንበረከክም …. የምናመልከዉ አምላክ ከመታሰር ባያድነን እንኳን ለስርዓትህ አንገዛም ….ቢሉት እና እስር ቤት ቢገቡ) ሐዋርያት ከኢየሩሳሌም በተበተኑ ጊዜ መበተናቸዉ ለበጎ ሆኖ ሃይማኖት/ክርስትና  በዓለም እንደተንሰራፋ ሁሉ በማኅበሩ አባላት ክርስትና በእስር ቤትም ላሉት በሰፊዉ እንደምትሰበክ/ለተቀሩትም የነሱ መታሰር ጽናት እንደሚሆናቸዉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለመንግስት ከዘነጋዉ ላሳስበዉ የምፈልገዉ ትዉልዱ ባህሉን፣ባንዲራዉን፣እምነቱን፣ አገሩን፣ አንድነቱን ….ከማንም እና ከምንም በፊት የሚሞትለት ግንባሩን የማያሸሽበት ጉዳይ እንዳልሆነ እንዲያዉቀዉ ፈልጋለሁ፡፡ይህን መንጋ መንካት በወጣቱ የተሳሰረ ክንድ በእሳት መጫወት ይሆንበታል፤ የሚያስበዉን መጨረሻ የሌለዉ የሚመስል የስልጣን ዘመን ላይ ጠላት መግዛት ነዉ፡፡አሁን ስለፖለቲካቸዉ ተጨንቄም አይደለም፣ ስለማህበሩም ወግኜ አይደለም፣ በዚህ አጋጣሚ ስለሚጎዱት እና ጥቃት ስለሚደርስባቸዉ (ሞራላዊ ጥቃት ተስፋ የመቁረጥ ወረርሽኝ፣ አገር/መንግስት የለንም የማለት ጥቃት)ታዳጊ ህፃናት እንጂ ዝሆኖች ሲጣሉ/ሲራገጡ የሚጎዳዉ ሳሩ ነዉና፤ በፌስቡክ ላይ እንኳን ስንቱ ነዉ ስሜቱ ተነክቶ በስሜት የሚናገረዉለሃይማኖቴ ሟች ነኝ እያለ ያለዉማንንም ቢሆን በሃይማኖቴ ጉዳይ የማልደራደርበት ጉዳይ ነዉ የሚለዉእንግዲህ እንዲህ የሚሉት የማኅበሩ አባላት አይደሉም፣ሰንበት ተማሪዎችም አይደሉም ከቤተክርስቲያን ገረገራ ቆመዉ "እኔ ኃጥያተኛ ነኝ! "ብለዉ ራሳቸዉን ዝቅ ያደረጉት ከቤተክርስቲያን በዉጭ ያሉት እንጂ ….መንግስት የማኅበሩን አባላት ብዛት አይቶ አይደል እንዲህ ፍርሃት የናጠዉና ካልበተንኩት እንቅልፍ አይወስደኝም ያለዉ …. እንግዲህ እሱ ያላያቸዉ ምናልባት በመዳፌ ናቸዉ ያሉት ጭምር ሊሆኑ በሚችሉ አጋጣሚ አንተም ብትሆን በቤተክርስቲያን ላይ ከመጣህ እግርህን ላስ እያሉት ይገኛሉ፡፡ ምን ይህ ብቻ ቱባ ባለስልጣናትስ ቢሆኑ ከቤተክርስቲያን  ይልቅ ኢህአዴግን ያስቀድማሉ ትላላችሁ? እንኳን እነሱ የደርግ ባለስልጣናትም ትናንት እግዚአብሔር የለም እያሉ ዛሬ ግን ከመቅደሱ ተገኝተዉ ይቅርታ እየጠየቁ ይገኛሉ የበደሉትን አምላካቸዉን እያገለገሉት ይገኛሉ፡፡ አሁንም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለእግዚአብሔር በአስራ አንደኛዉ ሰዓት ቢቀጠሩ እግዚአብሔር ሊቀጥራቸዉና ዋጋቸዉን  ሊከፍላቸዉ ምን ይሳነዋል፡፡
መንግስት ወጣቱን ምንም እንኳን ስናየዉ ለዓይን የማይሚላ ቢመስለዉም ለእግዚአብሔር ቀናኢ ነዉ፤መንግስት ሆይ እባክህ ከጥፋት ጎዳናህ ተመለስ …. ከፍለህ የማትጨርሰዉን ዕዳ ፍዳ በራስህ ላይ አትጫን፣ግፍም አታቆይ፡፡

በፌስ ቡክ እየቀረቡ ያሉ ተቃዉሞዎች ማሳያ!