Tuesday, 31 December 2013


የአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ካህናቱንና ምእመናኑን እያነጋገረ ነው

  • ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲያገልግሉ ብቻ ሳይሆን በትምህርትና በተግባራዊ ልምምድ ለከፍተኛ ክብርና ማዕርግ እንዲበቁም ትሠራለች
  • ገዳማት እና አድባራት የልማት ፈንድ ያቋቁማሉ
/ምንጭ፡- ኢትዮ – ምኅዳር፤ ቅጽ 02 ቁጥር 51፤ ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 ቀን 2006 ዓ.ም./
Addis Abeba diosces facebook profile picበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰሞኑን ለሀ/ስብከቱ ባለድርሻ አካላት ለውይይት ያቀረበው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ካህናቱንና ምእመናኑን እያነጋገረ ነው፡፡ የጥናት ሰነዱን እንደማይቀበሉት የሚገልጹ ወገኖች፡- ‹‹ጥናቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያልተሳተፉበትና በውይይት ያልዳበረ በመኾኑ በገለልተኛና ልምድ ባላቸው ምሁራን ይሰናዳ፤ ከነባሩ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዐዋዲ ጋራ የሚጋጭና የሚጣረስ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ጥናቱ ‹‹ነባሩን ሠራተኛ በማፈናቀል በስመ ዲግሪና ዲፕሎማ ዕውቀት የሌለውን በመዋቅሩ ውስጥ በመሰግሰግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር ያለመ ነው፤›› የሚሉት እኒሁ ወገኖች፣ ‹‹የአጥኚው አካል ማንነት በግልጽ አይታወቅም፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ሥልጣን ያለውን የፓትርያርኩን ሥልጣን ይጋፋል፤›› የሚሉ ተቃውሞዎችን በመዘርዘር አቤቱታቸውን ለፓትርያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አቅርበዋል፡፡
ተቃዋሚዎቹ በአደረጃጀትና አሠራር ትግበራው በሚመጣው ለውጥ ተጠቃሚ የኾኑትን ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደማይወክሉ ለኢትዮ – ምኅዳር የተናገሩ የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች በበኩላቸው፣ የተጀመረው የለውጥ ሒደት በሐቅ ላይ ባልተመሠረተ፣ ቅንነት በጎደለውና ደረጃውን ባልጠበቀ የአቋም መግለጫ ወደኋላ እንደማይመለስ በመግለጽ ተቃውሞውን አስተባብለዋል፡፡
የጥናቱ መነሻ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኃይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ የተሰጠው ውሳኔ መኾኑን ሓላፊዎቹ አስታውሰዋል፤ጥናቱን ያካሄደው የባለሞያ ቡድንም በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በኾኑት አቡነ እስጢፋኖስ መዋቀሩንና ሥራውን ከመጀመሩ በፊትም በፓትርያርኩ ፊት ቀርቦ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አልፎ ለሌሎች አህጉረ ስብከትም የሚያገልግል የአሠራር ጥናት በማድረግ አደረጃጀቶችንና መመሪያዎችን እንዲያዘጋጅ አባታዊ መመሪያ መቀበሉን ገልጸዋል፡፡
His Holiness meglecha 11ሀገረ ስብከቱ በአንድ ሀገረ ስብከትና በአንድ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ከተወሰነ በኋላ ከሐምሌ 2005 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለሦስት ወራት የተመራበትንና ቋሚ ሲኖዶስ ያጸደቀውን ጊዜያዊ መዋቅር የሠራው የባለሞያ ቡድኑ፣ በፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ ላይ ተመሥርቶ በረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው የቅርብ ክትትል እየተደረገለት በቀጣይ ባከናወነው ጥናት÷ ክህነታዊ አገልግሎትንና ስብከተ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ፣ ወጥነት ያለው የሰው ሀብት አስተዳደርና ዘመኑን የዋጀ የፋይናንስ አሠራር ለመዘርጋትና በልማት ራስን ለመቻል የሚያበቃ 13 ጥራዞች ያሉት ሀገረ ስብከት አቀፍ መዋቅርና አደረጃጀት ሰነድ አርቅቆ ጥቅምት 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ማቅረቡ ተገልጦአል፡፡
ጥናቱ በባለሞያ ቡድኑ ገለጻ ታግዞ በስላይድ የቀረበለት የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም ዐይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውለው ይኹንታና የአፈጻጸም አቅጣጫ እንደሰጠበት ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት ቁጥራቸው ከ2700 በላይ የኾኑ የሀ/ስብከቱ የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ የሰባት ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ መሪዎች፣ የ169 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና ምእመናን ተወካዮች ከኅዳር 17 – ታኅሣሥ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. በተለያዩ ዙሮች በንቃት እንደተወያዩበት ሓላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ የውይይት መድረኮቹ፣ ‹‹ጥናቱ በይዘቱ እንዲዳብርና በአቀራረቡ እንዲስተካከል ግብአት የሚኾኑ ትችቶችና አስተያየቶች የተገኙበት አሳታፊ ብቻ ሳይሆን ሳይዘገይ ጸድቆ እንዲተገበር ብዙኃኑ አገልጋይና ሠራተኛ በአማካይ እስከ 96 በመቶ ድጋፍ በመስጠት ግፊት ያደረገበትም ነበር፤›› ብለዋል፡፡
his grace abune estifanosበሕገ ቤተ ክርስቲያኑም ይኹን በቃለ ዐዋዲ ደንቡ፣ የሁሉም አህጉረ ስብከት ማዕከል የኾነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው ልዩ ደንብና መመሪያ እንደሚተዳደር መደንገጉን የጠቀሱት ሓላፊዎቹ የጥናት ሰነዱን በሲኖዶሱ አባላት እየታየ ከሚገኘው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ጋራም ለማገናዘብ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ኹሉ አኳያ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ወሳኝ አካል የኾነው ሲኖዶሱ በምልአተ ጉባኤ ስብሰባው ባስተላለፈው ውሳኔና የውሳኔው አስፈጻሚ የኾኑት ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ መሠረት÷ ዕውቅና ባለው፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በተውጣጣና ቤተ ክርስቲያኒቱን በጥልቀት በሚያውቅ የባለሞያ ቡድን አዲስ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነድ መዘጋጀቱ የሚጥሰው ሕግና ደንብ የለም በማለት የሕግና ደንብ ጥሰት እንዳለ የተሰነዘረውን ተቃውሞ ተከራክረዋል፡፡
የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጡ ‹‹ነባሩን ሠራተኛ በማፈናቀል በስመ ዲግሪና ዲፕሎማ ዕውቀት የሌለውን በመዋቅሩ ውስጥ በመሰግሰግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር ያለመ ነው፤›› ስለሚለው ተቃውሞ ኢትዮ – ምኅዳር የጠየቃቸው የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች÷ ‹‹በጥናቱ የሀ/ስብከቱ የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ችግሮች መነሻ ተደርገዋል፤ ዋና ተልዕኮውና መሠረታዊ ተልዕኮውን የሚደግፉ ተግባራት በዝርዝር ተለይተዋል፤ መዋቅሩ ከዚህ አንጻር ያሠራል ወይስ አያሠራም በሚል አመቺነቱና እንከኑ ተገምግሞ በስምምነት የሚወሰን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሰነዱ የሚታየው ተቋማዊ መዋቅር የመጨረሻ መልክ ከመያዙ በፊት ብዙ አማራጮች እየቀረቡ መፈተሹን ያስረዱት ሓላፊዎቹ ለውይይት የቀረበው መዋቅር የቤተ ክርስቲያናችን ዋነኛ ተልዕኮ የኾነው ሐዋርያ አገልግሎትዋ እየሰፋ እንዲሄድ፣ የተሻለ የልማት ዕድል ተፈጥሮ የበለጠ ገቢ በማግኘት ሐዋርያዊ አገልግሎትዋን ለማስፋፋትና ለማጠናከር እንዲቻል የተመቻቸበት በመኾኑ ከፍተኛ የአገልጋይ ቁጥር እንደሚያበቃ የተናገሩት ሓላፊዎቹ÷ ያለውን አገልጋይ በሥልጠና የማብቃት፣ በትምህርት ራሱን እንዲያሳድግ የማበረታታት፣ የመደልደልና የማሸጋሸግ ሥራ ይሠራል እንጂ ትርፍ ነው ተብሎ የሚፈናቀል ሰው አይኖርም ብለዋል፡፡
ሀ/ስብከቱ በጥቅምት ወር መጨረሻ ባካሄደው የሦስት ወራት የጊዜያዊ መዋቅሩ አፈጻጸም ግምገማ በየገዳማቱና አድባራቱ ካለው ከፍተኛ የሰው ኃይል ክምችት አንጻር በተለያየ ምክንያት ከሥራ ተፈናቅለው ካልተመደቡ ሠራተኞች በስተቀር ላልተወሰነ ጊዜ የአዲስ ሠራተኛ ቅጥር እንዲቆም መወሰኑም በሥራ ላይ ያለውን አገልጋይ ሰፊ የሥራ ዕድል በሚፈጥረው በአዲሱ ተቋማዊ መዋቅር አደረጃጀትና የሥራ መደብ ዝርዝር መሠረት በመለስተኛ ሥልጠና ጭምር እያበቁ ለመደልደል ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳለ ሓላፊዎቹ በምላሻቸው ጠቅሰዋል፡፡
የሀ/ስብከቱ ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በአገልግሎት ስፋትና በልማት አቅም እርስ በርስ እየተወዳደሩ ወደ ደረጃ አንድ የሚያድጉበት አምስት ደረጃዎችና ደረጃዎቹ የሚለዩባቸው መመዘኛዎች መዘጋጀታቸው ተገልጧል፤ አምስቱም ደረጃዎች የየራሳቸው መዋቅር፣ በሞያና በቁጥር የተለያየ የሰው ኃይል ምደባና የደመወዝ ስኬል ያላቸው ሲኾን ቤተ ክርስቲያኑ እንደሚገኝበት ደረጃና እንደሚሰጠው የአገልግሎት ስፋት የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ትመና የቤተ ክህነቱን ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጋራ በአቻ ንጽጽር በመመዘን ተገቢው ትኩረትና ደረጃ እንዲሰጠው ተደርጎ መሠራቱም ተመልክቷል፡፡
‹‹የሰው ኃይል ትመናው÷ ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት የሥራን ጥራት ከማሳደግ አንጻር የአገልጋዩ ዝቅተኛ የትምህርት፣ የሥራ ልምድና የክሂሎት ዝግጅት የታየበት ነው፤ የደመወዝ ስኬል ጥናቱ÷ ከቢሮ ሥራ ይልቅ ለካህናቱ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት የካህናቱን ኑሮ ለማሻሻል፣ ሊቃውንቱ ትኩረት አግኝተው ተተኪ ለማፍራት እንዲችሉ በልዩ ኹኔታ የሚበረታቱበት ነው፤›› ይላሉ ለኢትዮ – ምኅዳር አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የባለሞያ ቡድኑ አባል፡፡
ባለሞያው አያይዘውም ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲያገልግሉ ብቻ ሳይሆን በትምህርትና በተግባራዊ ልምምድ ለከፍተኛ ክብርም እንዲበቁ እንደምትሠራ ገልጸዋል፤ ከዚህም አንጻር ልዩ ተሰጥኦና ላቅ ያለ ችሎታ ያላቸው አገልጋዮች ወደ ታችና ወደ ጎን ለተሻለ ዕድል የሚበቁበትና የሚበረታቱበት የደረጃ ዕድገት፣ የዝውውርና ሹመት፣ የክፍያና ምዘና፣ የጤና ክብካቤ ሽፋንና የጡረታ ዋስትና ሥርዐት የሚወሰንበት የአገልጋዮች ማስተዳደርያ ፖሊሲ፣ መመሪያና ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ለየዘርፉ የተጠኑት የሥራ ማኑዋሎች መለስተኛ ክሂል (semi-skilled) ያለው አገልጋይ በቀላል ሥልጠና ሊተገብራቸው የሚችላቸው ናቸው፤›› ያሉት ባለሞያው፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የለውጥ አመራር ዕቅድና በአገልጋዩ አቅም መካከል የሚታዩ ክፍተቶች በየጊዜው እየተለዩ የሚሞሉባቸው የአቅም ግንባታዎች(የሥልጠና) ዐይነቶች ከማስፈጸሚያ መመሪያው ጋራ በሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲው በዝርዝር መቀመጣቸውን አብራርተዋል፡፡

የገዳማትና አድባራት የልማት ፈንድ
በተያያዘ ዜና÷ የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራት ልማትን በማስፋፋት ሐዋርያዊ አገልግሎትን በዘላቂነት ለማከናወን የሚያስችል ሀብትና ንብረት የሚያፈሩበት የልማት ፈንድ ሊያቋቁሙ መኾኑን የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሰበካ ጉባኤ ከሚሰበስቡት አስተዋፅኦ ጋራ በልማት መስኮች ለሚያገኙት ገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ለኢትዮ ምኅዳር ያስታወቁት የሀ/ስብከቱ ምንጮች÷ ገዳማትና አድባራት በአንድ የበጀት ዓመት መጨረሻ ለመደበኛ አገልግሎት ከሚመደበው በጀትና መጠባበቂያው ከሚተርፈው ገንዘብ ስድሳ በመቶውን (60%) የልማት ፈንድ እንዲያቋቁሙበት የሚያስችል ጥናት በሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
እንደምንጮቹ ገለጻ በጥናቱ መሠረት፣ ሀገረ ስብከቱና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ካለው የተጣራ የባንክ ሒሳብ ተቀማጭ ገንዘብና የአጭር ጊዜ ተሰብሳቢ ገንዘብ ውስጥ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት መደበኛ ወጭዎችን ለመሸፈን የሚያስፈልገውን ገንዘብ መጠባበቂያ አድርገው ካስቀመጡ በኋላ ከሚተርፈው ዓመታዊ ቀሪ ገንዘብ ውስጥ ስድሳ በመቶውን የልማት ፈንድ እንዲያቋቁሙበት ታስቧል፡፡
የልማት ፈንዱ÷ የልማት ተቋማትን በማቋቋምና በማስፋፋት የካህናትንና ሊቃውንትን የኑሮ ኹኔታ የማሻሻልና አብያተ ክርስቲያናቱን ከልመና የማውጣት፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ከመደገፍ ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የምግባረ ሠናይ ድርጅቶች በቋሚ የገንዘብ ምንጭነት በማገልገል የምግባረ ሠናይ ተግባራትን በስፋት የማከናወን በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮ የኾነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በከተማና በገጠር የማስፋፋትና የማጠናከር አስፈላጊነት እንዳለው የሀ/ስብከቱ ሌላው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ አካል የኾነው የልማት ሥራዎችና የምግባረ ሠናይ ተግባራት ፖሊሲና መመሪያ ረቂቅ ያስረዳል፡፡
ፖሊሲው ለልማት ተቋማቱ ባስቀመጣቸው መርሖዎች መሠረት÷ በተቋማቱ ምሥረታና ማስፋፋት ወቅት ለቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊ አገልግሎት እንደ ግብዓት የሚያገልግሉ ዕቃዎችን ለማምረትና ለማከፋፈል ቅድሚያ መሰጠት ይገባዋል፡፡ ተቋማቱ የሚያመርቷቸውና የሚያከፋፍሏቸው ንዋያተ ቅድሳት፣ የኅትመት ውጤቶች፣ የምስል ወድምፅ ሥራዎችና የመሳሰሉት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ሥርዐት፣ ከማኅበረሰቡ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ትውፊት አንጻር ታሳቢ መደረጋቸው መፈተሽና መረጋገጥ እንደሚኖርበትም ተመልክቷል፡፡
ፖሊሲው ‹‹የተፈቀዱ›› የሚላቸው የልማት ተቋማት ለብዝኃ ሕይወት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ በዕውቀቱ የበለጸገ፣ በሥነ ምግባሩ የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው በመርሖው አስቀምጧል፡፡ ከተቋማቱ ዝርዝር ውስጥም፡- ኮሌጆችና ማሠልጠኛዎች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅት በማቋቋም የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት መስጠት፣ ክሊኒኮችንና ፋርማሲዎችን በማቋቋም የሕክምና አገልግሎት መስጠትና መድኃኒቶችን ማከፋፈል፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ ለአገልግሎትና ኪራይ የሚውሉ ሕንጻዎችን መገንባትና ማከራየት፣ ከውጭ የሚገቡ ንዋያተ ቅድሳትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማዳንና ሥርዐትና ትውፊት የጠበቁ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ የግብርና ውጤቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ፣ የፋይናንስ ተቋም አክስዮን፣ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድና ቦንድ መግዛት የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ገዳማትና አድባራት በራሳቸው አልያም በመቀናጀት ተቋማቱን መመሥረት እንደሚችሉ በመርሖው የተገለጸ ሲኾን ቅንጅቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አጥቢያዎች ጋራ፣ አጥቢያዎች ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጋራ እንዲሁም ሀ/ስብከቱና አጥቢያዎቹ ከሌሎች አህጉረ ስብከትና አጥቢያዎቻቸው ጋራ ሊከናወን የሚችልበት የፕሮጀክት አጸዳደቅና አተገባበር ሥርዐት መካተቱ ተገልጧል፡፡ የልማት ተቋማቱ የሚተዳደሩት በቦርድ ሲኾን የቦርዱ ተጠሪነትም ላቋቋማቸው አካል (በአጥቢያ ደረጃ ከኾነ ለአጥቢያው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ) እንደኾነ ታውቋል፡፡
በልማት ፈንዱ የሚቋቋሙና የሚስፋፉ ተቋማት፣ ካህናትና ሊቃውንት ከመደበኛ ተግባራቸው  በተጨማሪ እንደየዝንባሌያቸው በተለያዩ ክሂሎቶች እየሠለጠኑ እንዲሠማሩ በማስቻል የሥራ ዕድል እንደሚፈጠሩላቸው፣ በአገልግሎታቸውም እንዲበረቱ ተገቢውን በማሟላት አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉላቸው ታምኖባቸዋል፡፡ የልማት ተቋማቱ ወደፊት ሀገረ ስብከቱ ከምእመናን አሰፋፈር አኳያ እንደአስፈላጊነታቸው እያየ ከሚተክላቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋራም አንጻራዊ መስፋፋት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በቁጥር 169 ለሚደርሱት የመዲናዪቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሰራጨው ቅጽ እየሰበሰበው የሚገኘው የአገልጋዮች ጠቅላላ መረጃ÷ ገዳማቱና አድባራቱ ልዩ ልዩ ክህሎት ያላቸው አገልጋዮች እንዳሉባቸው በምንጮቹ መረጃ ተመልክቷል፡፡ ይህም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በየደረጃቸው ከተዘረጋላቸው ተቋማዊ መዋቅርና አደረጃጀት አኳያ የተሠራላቸው የሥራ መደቦች መዘርዝር መንፈሳዊ ዕውቀትን ከዘመናዊው ሞያ ጋራ በአቻ ንጽጽር በማስቀመጥ ከሚያቅፈው በርካታ የሰው ኃይል በተጨማሪ በሒደት አገልጋዮችን በብዛት ለማፍራትና ለማሰማራት ያስችላል የሚል እምነት እንደተጣለበት ተዘግቧል፡፡

Monday, December 30, 2013

ፓትርያርኩ ስለ እምነታቸው የከፈሉት ዋጋ


(አንድ አድርገን ታህሣሥ 21 2006 ዓ.ም)፡- ኢትዮጵያ ብዙ መከራዎችን አሳልፋለች ፤ ብዙዎቹ መከራዎች ከውጭ ወራሪዎች ቢደረሱም ከውስጥ ሀይሎችም ከደረሰው ጥቃት ያልተናነሰ መከራ በቤተክርስትያንና በሀገር  ላይ ብዙ መከራ ደርሷል ፤ ይህች ቤተክርስቲያን ከዘመነ አክሱም ጀምሮ አሁን እስካለንበት የኢህአዴግ ዘመን ድረስ ብዙ መንግስታትን አሳልፋለች ፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ነገስታት ለቤተክርስትያን እና ለህዝበ ክርስትያን በርካታ መልካም ተግባሮችን አከናውነው ወደማይቀረው አለም አልፈዋል ፤ ስማቸውም በየዘመኑ በመልካም እየተጠራ ትውልድም የሚዘክራቸው እስከ አሁን ድረስ አሉ ፤ ሌሎች ደግሞ የምትጠፋ መስሏቸው ጦር መዘውባታል ፤ በዘመናቸው ቤተክርስትያኒቷን ለማፍረስ ድንጋይ  አንስተውባታል ፤ አሳት ለኩሰውባታል  ፤ እርሷ ግን የመጣውን መከራ ተቋቁማ እጃቸውን ያነሱባትን ወደ ኋላ ትታ አሁን እኛ ትውልድ ላይ ደርሳለች፡፡
በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እውነተኛ ጠበቃ የሆኑ አባቶች ላይ ጫና ሲፈጥር ኖሯል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ከደርግ አምባገነናዊ ከሆነው ስርዓት እስከ አሁኑ ጊዜ ድረስ ከመንግሥት ተጽህኖ ስር ወጥታለች የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ዘወትር መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚሰማውና የሚታየው ነገር የቤተክርስቲያኒቱን ሕልውና የሚያናጋ ክብሯንም የሚቀንስ ነገር እየሆነ መጥቷል ፡፡ በ2001 ዓ.ም በጥቂት ጥቁር ለባሾች ብጹአን አባቶች ላይ በውድቅት ለሊት ሊደረግ የታሰበው ድብደባ እና የአባቶችን ማረፊያ መግቢያ በር በጥቁር ለባሾች የተሰበረው ድርጊት ተደባብሶ ማለፉ ከጀርባው ማን እንዳለ ለማወቅ የስለላ ምሁር መሆን አያስፈልገውም፡፡ አሁንም እየተሰማ ያለው ነገር ደርግ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት  በሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የደረሰውን ነገር እንድናስታውስ ግድ ይለናል፡፡ ብጹዕነታቸው ስለ ቤተክርስቲያን በነበራቸው አቋም ምክንያት በግፈኞች ሕይወታቸውን በግፍ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡ አባቶቻችን ለዚች ቤተክርስቲያን የከፈሉትን ዋጋ ማወቅ በየዘመኑ እግዚአብሔር በጎቹን እንዲጠብቁ ለመረጣቸው አባቶች ቤተክርስቲያኒቱ በምን አይነት ዋጋ ከእነርሱ ትውልድ እንደደረሰች ትልቅ ትምህርት ይሰጣቸዋል ብለን እናምናለን፡፡
አወይ ጊዜ አወይ ጊዜ
ጊዜ ነቃሽ ፤ጊዜ ወቃሽ
መንገደኛ ሁሉን ታጋሽ

 አባታችን ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከደርግ መንግሥት የደረሰባቸው ፈተና እና ስለ ከፈሉትን ዋጋ ለትውልዱ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው ብለን ስላመንን አቅርበነዋል፡፡
 
ኢትዮጵያውያን አብዮትን የምናወቀው በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሳይሆን በውስጡ አልፈን በቃጠሎው ተገርፈን ወላፈኑን ቀምሰን ነው፡፡ በዛን ወቅት የነበረው የሶሻሊስት ርዕዮት አለም አብዮታዊነትን እንደ ታላቅ ነገር ሲሰብክ የነበረ በመሆኑ ብዙ ወጣቶች አብዮተኛ ተብለው ሀገሪቱንም አብዮታዊት ኢትዮጵያ አስብለዋታል፡፡ በዚህች ተአምረኛ ሃገር አብዮታውያን ወንድሞቻችን ጸረ አብዮተኛ የተባሉ ወንድሞችቻቸውንና እህቶቻቸውን ቅርጥፍ አድርገው በልተዋል፡፡ በዚያ ክፍለ ዘመን ‹‹አብዮት ልጆቿን›› ትበላለች በሚል ፈሊጥ ብዙዎች ወጣቶች ጸረ-አብዮት፤ ጸረ ህዝብ ተብለው አይሆኑ ሆነዋል..ጊዜው ጥቁር ጠባሳውን ጥሎ ያለፈው ሁሉም ላይ በመሆኑ የጊዜው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን 2ኛ ፓትርያልክ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የደረሰው በደል ግን ለየት ያደርገዋል፡፡
በዚያ ወቅት ደርግ ቤተክርስቲያኒቱ ጳጳስ እንዳትሾም ትእዛዝ አውጥቶ ነበር። በወቅቱ አቡነ ቴዎፍሎስ የደርግን ትእዛዝ ሽረው ሦስት ጳጳሳትን ሾሙ።ደርግም ትእዛዜን አልሰሙም ብሎ ፓትሪያርኩንና ሦስቱን ተሿሚ ጳጳሳት እስር ቤት ጨመራቸው። በወቅቱ የተሾሙት ጳጳሳት አቡነ ባስልዮስ፤አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ጳውሎስ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ሦስቱ ጳጳሳት ከእስር ሲፈቱ ፓትሪያሪኩ ብቻ በዚያው ቀሩ።
አቡነ ቴዎፍሎስ በእስር ቤት ደረሰባቸውን ፀዋትወ መከራ በዓይን ያዩ በታላቁ ቤተመንግስት አብረዋቸው ታስረው የቆዩ በአፄ /ስላሴ ዘመን በስልጣን ላይ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ የአይን ምስክሮች በተገኝው የቃል መረጃ መሰረት ቅዱስነታቸው መጀመሪያ የታሰሩት ለብቻቸው በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ነበር፡፡ በዚህ ቦታ ጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ ........
በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ አስገብተው እጃቸውንና እግራቸውን ከአልጋ ጋር ጠፍረው አሰሯቸው ፡፡ ቀንም ሆነ ማታ ለሽንት ሲወጡ ካልሆነ በስተቀር ሰንሰለቱ አይፈታላቸውም ነበር በዚህ አይነት ለአራት ቀናት እንዲሰቃዩ ከተደረገ በኋላ ባለስልጣኖች ታስረውበት ወደነበረው ቁጠር አንድ እስር ቤት ወሰዷቸው
ወቅቱ አብይ ፆም ነበር ከጎፋ ገብርኤል ተይዘው ከመጡበት ቀን ጀምሮ ለአርባ ቀናት ያህል እህል የሚባል ነገር አልቀመሱም ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጣታቸውን በውሀ ውስጥ በመንከር ከንፈራቸውን ከማርጠብ በስተቀር ጥም የሚቆርጥ ውሀ እንኳን አልጠጡም፡፡ ምግብ እንዲበሉ አንዳንድ ደርግ ባለስልጣናት እና አብረዋቸው ታስረው የነበሩ አዛውንቶች ለምነዋቸው ነበር ነገር ግን ለመብላት ፍቃደኛ አልነበሩም  እስከ ፋሲካ ማግስት ድረስ ምንም ሳይቀምሱ ቆይተዋል ፡፡ ለፋሲካ ማግስት ግን እስረኞች መካከል አረጋውያኑ አጥብቀውና አስጨንቀው ስለለመኗቸው እህል ሊበሉ ችለዋል፡፡


በወቅቱ ከነበሩ ሰዎች መረጃ መሰረት ደርግ አቡነ ቴዎፍሎስን በእስር ቤት ስቃይ ካሳዩአቸው ሰዎች መካከል አንድ ሻለቃ የፈፀመባቸው ግፍ ሳይቀስ አይታለፍም ፡፡ ይህ ሰው እርሳቸውን የማበሳጨት ተልዕኮ ስለነበረው በንቀትአባ መልአክቱ›› እያለ ይጠራቸው ነበር፡፡ ሞራልም የሚነካ አነጋገርም ይናገራቸው ነበር፡፡ ከወርቅ የተሰራ የእጅ መስቀላቸውን ቀምቶ እስከ መውሰድ ደርሶም ነበር፡፡ ከሚተኙበት ትንሽ ክፍል ውስጥ ሰቅለውት የነበረውን የጌታችን እና የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስዕልም በስልጣኑ አውርዶ ወስዶባቸዋል፡፡ የዚህ ሰው ድርጊት ከበስተኋላው የሚገፋፋው ጠላት እንዳለ ያመላት ነበር፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ የነበራቸው አነስተኛ ግላዊ ነፃነት እንኳን እስከዚህ ድረስ ተገፍፎ እንደነበር የሻለቃው ድርጊት ያሳያል፡፡
‹‹ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።›› የማቴዎስ ወንጌል 5፤ (11-12)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በብዙ ስቃይ እያዩ በእስር ቤት የቆዩት እስከ  ሐምሌ 7 1971 . ነበር፡፡ በዚህ ቀን እስረኛው እንዲሰበሰብ ታዞ ሲሰበሰብ አንድ ዘበኛ መጣና የሁለት እስረኞችንና የብፁዕነታቸውን ስም ጠርቶ ብርድ ልብሳቸውን እና የሽንት ቤት ወረቀታቸውን ይዘው እንዲወጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ክፍላቸው ገብተው አጭር ፀሎት ካደረጉ በኋላ ጥቁር ቀሚሳቸውን ለብሰው ነጠላ ጫማ አድርገው ቆባቸውን ደፍተውና ከእንጨት የተሰራ የእጅ መስቀላቸውን ይዘው እስረኞችን ካፅናኑ እና መስቀል ካሳለሙ በኋላ ‹‹ እግዚአብሔር ያስፈታችሁ›› በማለት ተሰናብተዋቸው ወጡ፡፡..
‹‹ጊዜው ክረምት ነበር አባታችን አቡነ ቴዎፍሎስ ተይዘው ወደ ራስ አስራት ካሳ ግቢ አዲስ አበባ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ተይዘው ሄዱ በወቅቱ የለበሱት ጥቁር የሐር ቀሚስ ጥቁር ነጠላ ጫማ ጥቁር የመነኩሴ ቆብ ነበር፡፡ እንደ ወትሮ በአንገታቸው ያጠለቁት ወይም በእጃቸው የያዙት መስቀል ግን አልነበረም ፡፡ በተጠቀሰው ግቢ ውስጥ ወዳለው ቤት እንዲገቡ ሲደረግ ከውስጥ የተደበቁ ኮማንዶዎች ባዘጋጁት ገመድ በድንገገት አንገታቸውን ሸምቀቅ አድርገው በማነቅ ገደሏቸው፡፡ወዲያውም አስከሬን የሚያነሱ ሌሎች ሰራተኞች አስከሬናቸውን አንስተው ከቤቱ ውጪ ባለው ግንብ ስር በስተ ምዕራብ በኩል በተቆፈረው እና በርካታ ሬሳ በተጣለበት ጉድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት››    (በጊዜው ከነበረ ወታደር የዓይን እማኝ የሰጠው ቃል)
ከዚህ በኋላ ቅዱስነታቸው የት እንደደረሱ ምን አይነት ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሳይታወቅ ለ13 ዓመት ተዳፍኖ ቆየ፡፡ ነገር ግን ‹‹ የማይገለጥ የተከደነ ፤ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም›› ማቴ 16፤26 እንደተባለው ጊዜ ሲደርስ በምን አኳኋን እንደሞቱና አስከሬናቸው የት ቦታ እንደተጣለ ሊታወቅ በመቻሉ በእንጦጦ አውራጃ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ከሚገኝው ከራስ አስራት ካሳ ግቢ አስከሬናቸው ተቆፍሮ ወጥቶ በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን በክብር አረፈ፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከአሜሪካ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ በቴዎሎጂ የክብር ዶክትሬት ድግሪ አግኝተዋል ፤  24 ሺህ ሰው በማሳመንና በማጥመቅ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አድርገዋል ፤ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማቋቋም እንደ አንድ መምህር ከክፍል እየገቡ በማስተማር ምሳሌነታቸውን አሳይተዋል ፤  የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ድርጅት መስርተዋል ፤  ቤተ ክርስቲያን ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር ጎን ለጎን መራመድ ትችል ዘንድ ሰባኪያን ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሰለጥኑባቸው የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትን በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ አድርገዋል ፤ አሜሪካ ከሚገኝው  ብሔራዊ የሰብአዊ ጥናቶች መርጃ ድርጅት  የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ በመጠየቅ የብራና መጻህፍት  የማይክሮ ፊልም ድርጅት አቋቁመዋል(አሁን በመንግስት የተወረሰ) ፤ የዘመን ጥርስ የበላቸው በርካታ  በሺህ የሚቆጠሩ የብራና መጻህፍት ጨርሰው ሳይጠፉ ከየገዳማቱና ከየአድባራቱ በማሰባሰብ በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አድርገዋል ፤ ቤተክርስቲያን በራሷ ገቢ የምትተዳደርበት የሰበካ ጉባኤ ሃሳብ በማቅረብ አደራጅተው  በቃለ አዋዲ እንዲመራ አድርገዋል ፤ የሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲቋቋም አድርገዋል ፡፡  አቡነ ቴዎፍሎስ በጠቅላላ ቤተክርስቲያን ያፈራቻቸው አለም አቀፋዊ ብቁ ዲፕሎማት መሆናቸውን ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡
ለብጹዕ አባታችን ለአቡነ ማቲያስ የአቡነ ቴዎፍሎስን ሥራ እና ምግባር እግዚአብሔር አብዝቶ ያድልልን፡፡ አሜን