Monday, 7 July 2014

ሰበር ዜና – የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የተፃረረው የፓትርያርኩ የአድባራት አለቆች ዝውውር ቁጣ ቀሰቀሰ፤ አዲሱ የደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል አስተዳዳሪ በሕዝቡ ተቃውሞ አቀባበል ሳይደረግላቸው ተመለሱ


  • ቋሚ ሲኖዶሱ የካህናቱንና ምእመናኑን አቤቱታ በመቀበልና የፓትርያርኩ ጥያቄ እንዲጣራ በማዘዝ፣ በሓላፊነታቸው እንዲቀጥሉ የወሰነላቸው ውጤታማው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ፣ ውሳኔውን የሚፃረር የዝውውር ደብዳቤ በአባ ማትያስ ትእዛዝ ተጽፎባቸዋል፡፡
  • የፓትርያርኩን አግባብነት የሌለው ትእዛዝ በመቃወም የደብሩን ሀብት ከአማሳኞች ሰንሰለታዊ ምዝበራ ለመከላከል እንዲሁም የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ በማስከበር የደብሩን ሰላም ለማስጠበቅ መንፈሳዊነት በተሞላው አኳኋን የሚንቀሳቀሱ የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን በኃይል ለማስፈራራት ሙከራ እየተደረገ ስለመኾኑ ተመልክቷል፡፡
  • የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን፡- ውጤታማው አስተዳዳሪ አግባብነት በሌለው የፓትርያርኩ ትእዛዝ መነሣታቸውን በመቃወም ስላቀረቡት አቤቱታ፣ ለቦሌ ክ/ከተማ ካራማራ ንኡስ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ለክፍለ ከተማው አዛዥና ለጸጥታ ሰዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
  • ጥያቄአቸው÷ በሕጋዊ ውሳኔ ተመድበው በሰላማዊ መንገድ እየመሯቸው የሚገኙት ውጤታማው አስተዳዳሪ ስለተነሡበት የፓትርያርኩ ትእዛዝ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ እንዲሰጣቸው መኾኑን አመልካቾቹ ገልጸዋል፡፡
  • ፀረ – የአማሳኞች ሰንሰለታዊ ምዝበራ የኾነውን ሰላማዊ እንቅስቃሴአቸውን ግለሰባዊና ፖለቲካዊ በማስመሰል ከመንግሥት ለማጋጨትና የኃይል ርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረግ ግፊት እንዳለ የጠቀሱት የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን÷ ‹‹ወደ ፖሊቲካ ይቀይሩብናል፤ እኛ ግን ፖሊቲከኞች አይደለንም›› ብለዋል፡፡
  • የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በሚፃረረው የፓትርያርኩ ትእዛዝ ከሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የተመደቡት አለቃ፣ ‹‹ወደ ደብሩ መሔድ የሚገባቸው ከሰበካ ጉባኤው አስተዳደር ጋራ አስቀድመው ከተነጋገሩና ከተግባቡ ብቻ እንደኾነ›› በትላንት ዕለት ከፖሊስ ተነግሯቸው እንደነበር ተገልጧል፡፡፡
*                   *                  *
  • የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን የደብሩን ሰላምና ሀብት ከአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ለመጠበቅና የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለማስከበር የሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት÷ ከቋሚ ሲኖዶሱ፣ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎችና ከሌሎችም አጥቢያዎች ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት ነው፡፡
  • ውጤታማና የብዙኃን ተቀባይነት ያላቸውን አለቆች፣ በጥቅመኝነት በታወረው የአማሳኞች ምክር ማዘዋወርን የመረጡት አባ ማትያስ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ያልተቀበለውን የዝውውር አቋማቸውን በባለሥልጣናት ጉልበት እና በአማሳኞች ተንኰል ለማስፈጸም መንቀሳቅሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
  • ፓትርያርኩ÷ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገው ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ እየተወያዩ ከመሥራት ይልቅ ‹‹አለቆችን በራሴ ፍላጎት ብቻ የማዘዋወር ሥልጣን ከሌለኝ ፓትርያርክነቴ ምንድን ነው?›› ሲሉ ለባለሥልጣናት አቤቱታ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
  • ለአቋማቸው ተቀባይነት አለማግኘትና ላስከተለው ከፍተኛ ተቃውሞ ማኅበረ ቅዱሳንን ተጠያቂ ለማድረግ በአማሳኞች አመቻችነት ከሚገናኟቸው ባለሥልጣናት ጋራ መክረዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ኾነው አላሠራ አሉኝ፤›› በሚል በማኅበሩ ላይ ጫናቸውን ለማጠናከርም እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡
*                   *                  *
St. Urael parish head row02በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ዛሬ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከእሑድ ሰንበት ጸሎተ ቅዳሴ መጠናቀቅ በኋላ የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና በርካታ ምእመናን ውጤታማው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ ወደ ሌላ ደብር መዛወራቸውን በተመለከተ ተቃውሟቸውን ሰላማዊነት በተሞላው አኳኋን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡
በተቃውሞው እንደተገለጸው÷ ከሐምሌ ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ካህናትና ምእመናን በአንድ ቃል በሚመሰክሩለት የተሟላ ክህነታዊ አገልግሎትና ብቃት ያለው አስተዳደራዊ ክህሎት ደብሩን የመሩትና በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ፋይናንሳዊ ሀብቱን ከአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ጠብቀው ከፍተኛ የልማት አቅም በመፍጠር መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ እስከ ዛሬ ከታዩት አለቆች ኹሉ ይልቅ ውጤታማ ኾነዋል፡፡
ውጤታማው አስተዳዳሪ፣ ከሰበካ ጉባኤው ጋራ በመተባበር÷ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደር እና በልማት መስኮች ያሳዩት የአገልግሎት ፍሬ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ጭምር መረጋገጡን በተቃውሞው ተመልክቷል፡፡
ውጤታማው አስተዳዳሪ ዓመት ሳይሞላቸው ለደብሩ በፈጠሩት ከፍተኛ አቅም የያዟቸውን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል ሊሰጣቸው የሚገባ እንጂ የአጥቢያውን ሀብት እንደለመዱት ለመቀራመት ባሰፈሰፉና በፓትርያርኩ ዙሪያ በተሰለፉ አማሳኞች ምክር ሊነሡ እንደማይገባ በብርቱ ተጠይቋል፡፡
በፓትርያርኩ ዙሪያ የተሰለፉ አማሳኞች ከደብሩ ልማደኛ መዝባሪዎች ጋራ ሰንሰለታዊ ግንኙነት በመፍጠር የፈበረኩት ክሥ፣ ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ በፓትርያርኩ አማካይነት እንዲያው በደፈናው ቀርቦ እንደነበር ተገልጧል፡፡
ይኹንና ክሡ አንድም ፓትርያርኩ በደፈናው ተቀበሉኝ ያሉትን የፈጠራ ክሥ በማስረጃ ማስደገፍ ባለመቻላቸው፣ በሌላም በኩል ከፓትርያርኩ የስማ በለው ክሥ ይልቅ የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱ አጋር የኾኑት አስተዳዳሪ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ስላደረጉት ውጤታማ ጥረት በቅርበት የሚያውቀው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በቃለ ጉባኤ አስደገፎ ከሰጠውና ቅ/ሲኖዶሱ በንባብ ካዳመጠው ምስክርነት ጋራ በቀጥታ የሚፃረር በመኾኑ በተባበረ ድምፅ ውድቅ ተደርጓል፡፡
የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ለቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መነሻ እንዲኾን በፓትርያርኩ ትእዛዝ ሠርቶ ያቀረበው የዝውውር ቃለ ጉባኤ÷ አጥቢያው ከኹለ ገብ ሕንጻው የኪራይ ውል፣ ከሙዳይ ምጽዋትና ሌሎች በርካታ የገቢ ምንጮቹ በተጭበረበሩ ሰነዶች ከ22 ሚልዮን ብር በተመዘበረበትና ሰላሙ በታወከበት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ከደብረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው የተመደቡት መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ፣ ደብሩን ከማረጋጋትም በላይ በአጭር ጊዜ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት እንዳስመዘገቡት የዘረዘረው የሥራ ፍሬ የሚያስመሰግን እንጂ ከሓላፊነት የሚያሥነሳ ኾኖ እንዳላገኘው ቋሚ ሲኖዶሱ መወያየቱ ተጠቅሷል፡፡
አቡነ ማትያስ÷ አለቃውን በማንሣትና በቀጣይ በሚካሔደው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ምርጫ አጋጣሚ አስተዳደሩን በመቆጣጠር በጥንቃቄ የተጠበቀውን የአጥቢያውን ቅምጥ ሀብት የመቀራመት ዕቅድ ያላቸው የደብሩ ልማደኛ መዝባሪዎች፣ በዙሪያቸው ከተሰለፉ አማሳኞች ጋራ የሸረቡትን ተንኰል ከመቀበላቸው በፊት በሐሰት ተከሣሹን አስተዳዳሪ በሚገባ አቅርበው ያውቋቸው እንደኾነ በቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ጥያቄ እንደቀረበላቸውም ተዘግቧል፡፡
አለቃው እንዲነሡ በፓትርያርኩ የተያዘው አቋም ተቀባይነት የሚኖረው በበቀልና በጥቅመኝነት ስሜት መቅረቡ የታመነው የአማሳኞች ክሥ ልዩ ሀገረ ስብከቴ ነው ከሚሉት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ከቀረበው የአስተዳዳሪው ዘርፈ ብዙ የውጤታማነት ምስክርነት ጋራ ተነፃፅሮ ሐቀኝነቱ ሲረጋገጥ ብቻ መኾኑን ቋሚ ሲኖዶሱ በውሳኔው አመልክቷል፤ እስከዚያው ድረስ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለቋሚ ሲኖዶሱ ቀርበው በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የተመደቡት ውጤታማው አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ በምደባቸው ጸንተው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ፓትርያርኩ ግን በውሳኔው የተስማሙ መስለው በወጡ ማግሥት፣ አስተዳዳሪው ወደ ሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን እንዲዛወሩና አዛውንቱ የሳሪስ አለቃም ወደ ደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲሔዱ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፤ ትእዛዙም በልዩ ጽ/ቤታቸው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ፊርማ ለየአለቆቹ በተከታታይ ቀናት መድረሱ ተገልጧል፡፡
St. Urael parish head row01
ተዋሕዶ ሃይማኖቴ የጥንት ነሽ የናትና አባቴ፤ ማዕተቤን አልበጥስም ትኖራለች ለዘላለም፤ አንመካም በጉልበታችን እግዚአብሔር ነው የኛ ኃይላችን፡፡
ደብዳቤው ለበርካታ የመንግሥት አካላት ግልባጭ መደረጉ የተገለጸ ሲኾን ይህም ፓትርያርኩ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ተደግፎ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ እየተወያዩ የተስማሙበትን ውሳኔውን ከማስፈጸም ይልቅ በጥቂት አማሳኞች የክፋት ምክር መመራትንና በባለሥልጣናት ጉልበት መመካትን መምረጣቸውን እንደገፉበት ያጠይቃል ብለዋል፤ ምእመናኑ በተቃውሟቸው፡፡
አኹንም ጥያቄአቸው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ማስከበርና አስተዳዳሪው ከሓላፊነታቸው አላግባብ የሚነሡበት ምክንያት ግልጽ እንዲደረግልን ነው የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፣ አለቃውን በሥራቸው ከሚያውቋቸውና በውጤታማነታቸው ከሚደግፏቸው በቀር ግለሰባዊ ጉዳይ እንደሌላቸው ገልጸዋል፤ እንቅስቃሴቸው ፀረ ሰላምና ፖለቲካዊ ነው በሚል ከመንግሥት ጋራ ለማጋጨት የሚሰነዘረው ትችትም አገልጋዩና ምእመኑ መብቱን እንዳይጠይቅና እናት ቤተ ክርስቲያኑን እንዳይጠብቅ ለማሸማቀቅ ያለመ የአማሳኞች የተለመደ ተንኰል ነው ብለዋል፡፡
አስተዳዳሪው በማስረጃ ተደግፎ የሚቀርብ ጥፋት ካለባቸው፣ በአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለታዊ አሠራር እንደተለመደው፣ ከደብር ደብር ከማዘዋወር ይልቅ በሓላፊነት ቦታ ከመቀመጥ ታግደው በሕግ መጠየቃቸውን እንደሚመርጡ፣ ይህም በደብሩ መዋቅር በተለያየ የሓላፊነት ደረጃ የመሸጉና በዓይነ ቊራኛ የሚከታተሏቸውን ልማደኛ መዝባሪዎችን ጭምር ማካተት እንደሚኖርበት ለዚኽም በግንባር ቀደምነት እንደሚሰለፉ ተናግረዋል፤ ምእመኑ በየአጥቢያው ምዝበራን ለመዋጋት ከአማሳኞች ጋራ የሚፈጥረውን ግጭት ለመፍታት በሚል እንደፈሊጥ የተያዘው ያለተጠያቂነት የማዘዋወር አሠራርም መታረም እንዳለበት አሳስበዋል – ‹‹ሌላውስ ደብር የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል አይደለም ወይ? ለዘራፊዎች ለምን ተጨማሪ ዕድል ይሰጣቸዋል?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡
St. Urael parish head row00ካህናቱ፣ የጽ/ቤት ሠራተኞቹና ምእመናኑ በዛሬው የእሑድ ሰንበት ረፋድ ተቃውሞው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በሚፃረረው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ደብዳቤ መነሻነት በተላለፈላቸው ሕገ ወጥ የዝውውር ትእዛዝ ማልደው የመጡትን አረጋዊውን የሳሪስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባትነት አክብሮ ነገር ግን መመደባቸውን ሳይቀበል በጨዋነት መልሷቸዋል፤ የሚከተለውን ማሳሰቢያም ከዐውደ ምሕረቱ ተሰጥቷል – ‹‹ጥያቄአችን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይከበር የሚል እንጂ የአንድ አለቃ መነሣት አይደለም፤ እርስዎን አባታችንን እናከብርዎታለን፤ ጥያቄአችን በአግባቡ እስኪመለስ ድረስ ግን እንዳይመጡ፡፡››
ከቁጥሩ ብዛት ጋራ መንፈሳዊነትና ሰላማዊነት የታየበት የአገልጋዩና ምእመናኑ የተቀናጀ የተቃውሞ ሥርዓት በደብሩ የተገኙትን ስቭል ለባሽ የጸጥታ ሰዎችና የፖሊስ ኃይሎች ጭምር ያስደመመ ነበር፡፡ የአማሳኞች መቅሠፍት፣ የመናፍቃን ውጋት በመኾን የታወቁት የአጥቢያው ወጣቶችና ወላጆች ምእመናን በወቅቱ በኅብረት ካሰሟቸው መዝሙራት መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፤
ተዋሕዶ ሃይማኖቴ፣
የጥንት ነሽ የናትና አባቴ፤
ማዕተቤን አልበጥስም፣
ትኖራለች ለዘላለም፤
አንመካም በጉልበታችን
እግዚአብሔር ነው የኛ ኃይላችን፡፡
ይኹንና ዘግይተው የደረሱ በቁጥር እስከ አርባ የሚገመቱ የፌዴራል ፖሊሶች ሦስቱንም የቤተ ክርስቲያኑን በሮች በመዝጋት ዙሪያውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ የክ/ከተማው ኮማንደር ናቸው በተባሉና በደብሩ ውስጥ በስቭል ልብስ በቆዩ አዛዥ ትእዛዝ እንዲመለሱ መደረጋቸው ታውቋል፡፡
በፓትርያርኩ የተመደቡት አስተዳዳሪ በመጡበት አኳኋን ተቀባይ ሳያገኙ መመለሳቸውን ተከትሎ ከሠርሆተ ሕዝብ ከተደረገ በኋላ ሰባት ያህል ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ምእመናን ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ካራማራ ንኡስ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርተው መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
ለሰላም ሲባል አስተዳዳሪው ለዛሬው አቀባበል ከመሔዳቸው በፊት ከሰበካ ጉባኤው ጋራ አስቀድሞ መነጋገርና መግባባት እንደሚጠበቅባቸው ትላንት ማምሻውን ከፖሊስ ማሳሳቢያ ደርሷቸው እንደነበር በንግግሩ ተጠቅሷል፤ የዝውውር ውሳኔው በፓትርያርኩ እንደታዘዘ በመጥቀስ አስተዳዳሪውን እንዲቀበሉ ለማድረግ ከፖሊስ በኩል የተደረገው ሙከራ ግን ትእዛዙ አግባብነት እንደሌለው በሚገልጽና እንቅስቃሴው ተገቢ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ መንፈሳዊነቱንና ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንደሚቀጥል በሚያመለክት ማብራሪያ ምላሽ እንደተሰጠበት ታውቋል፡፡s

Wednesday, 2 July 2014

ፓትርያርኩ ከጥቂት አማሳኞች ምክር ይልቅ የብዙኃኑን ካህናትና ምእመናን ድምፅ ሰምተው ተገቢ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠየቁ፤ ‹‹አለዚያ ውሳኔዎ ደብሩ በአንድ ዓመት ያገኘውን ሰላም ያውከዋል፤ እኛም ልጅ እርስዎም አባት አይኾኑንም››



St.Urael church bld complex
የደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንና ኹለገብ ሕንፃ

ቋሚ ሲኖዶስ ዛሬ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ትላንት ጥዋት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለተሰለፉ ከአንድ ሺሕ ለማያንሱ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት፣ የካህናት፣ የሰንበት ት/ቤትና የምእመናን ተወካዮች አስታውቀዋል፤ የዛሬው የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የካህናቱንና ምእመናኑን ቀጣይ ርምጃ ይወስናል፡፡


  • ፓትርያርኩ በጥቂት አማሳኞች ምክር ላይ የተመሠረተ የሙስና ክሣቸውን በማስረጃ አስደግፈው እንዲገልጹላቸው የተማፀኗቸውን፤ ለአቤቱታ በሕዝብ ማመላሻ አውቶቡሶች፣ ታክሲዎችና የቤት መኪናዎች ተጓጉዞ የመጣውን ምእመንም በአባታዊ መልእክት እንዲያሰናብቱ የጠየቋቸውን አምስት ተወካዮች በግቢ ጥበቃ፣ በፖሊስና በጸጥታ ኃይል ለማስወጣት ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡
  • ፓትርያርኩ የደብሩን አስተዳዳሪ በሙሰኛነት በመክሠሥ የጠቀሱት ምክንያት፣ ሀገረ ስብከቱ የአስተዳዳሪውን ውጤታማ አመራር በመመስከር ካቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ጋራ መለያየቱና መፃረሩ፣ ጉዳዩ በርግጥም ቅን መነሻ የሌለውና በጥቅም ትስስር ላይ የተመሠረተ መኾኑን አጋልጧል፡፡
  • በፓትርያርኩ እንደ ሙስና የተጠቀሱት የገንዘብ ወጪዎች÷ በሀገረ ስብከቱ የታዘዙ፣ የሰበካ ጉባኤው ውሳኔ ዐርፎባቸው በሕጋዊ ሰነዶች የተደገፉና ፓትርያርኩም በቀጥታ የሚያውቋቸው እንደኾኑ ተመልክቷል፤ የፓትርያርኩን የቢሮ ዕቃዎች ለማሟላት ከደብሩ ወጪ የተደረገው አራት መቶ ሺሕ ብር ይገኝበታል፡፡
  • ከደብሩ ከ22 ሚልዮን ብር በመመዝበር የተጠረጠሩ አማሳኞች ተጋልጠው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረጋቸውን ያስታወሱት የምእመናን ተወካዮቹ፣ ክሡ በአሳማኝ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ከኾነ አስተዳዳሪው ከሓላፊነታቸው መነሣት ብቻ ሳይኾን በሕግ የማይጠየቁበት ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል፤ አካሔዱም በደብሩ ልማደኛ አማሳኞችና በሙስና ከተጨማለቁ በኋላ ያለተጠያቂነት በሚዘዋወሩ ሌሎች አለቆች ላይም ተፈጻሚ እንዲኾን ጠይቀዋል፡፡
  • ‹‹አለቃው ቅዱስ ናቸው ብለን አይደለም፤ ሊያጠፉ ይችላሉ፤ እስከ አኹን ከተመደቡት ግን እንደ እርሳቸው ያሉ አላየንም፤ ቆጠራው በይፋ ነው፤ የገባና የወጣውን ማንም በይፋ ያውቀዋል፤ ገቢው ኻያ ሚልዮን ብር ደርሷል፤ አገልግሎቱ ሥርዓት ይዟል፤ አገልጋዩ ቦታውን አግኝቷል፤ ሰዓታት ቆመው፣ ኪዳን አድርሰው፣ ቀድሰውና አቊርበው፣ ካህኑን ከምእመኑ አስማምተው ሕዝቡን አንድ አድርገው የሚመሩ እንደ እርሳቸው አይተንም አናውቅ፡፡››
  • ‹‹እስከ አኹን ገንዘባችን ተዘርፏል፤ እስከ አኹን ዑራኤል ተሽጧል፤ ከአኹን በኋላ አንድ ሌባ እዚያች ደጅ አይደርሳትም፤ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናችኹን አጥራችኹ ጠብቁ፡፡›› /የአካባቢውን ወጣቶች ያበረታቱ የአጥቢያው ተሰላፊ እናቶች/
About these ads

የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱን የደገፉ አለቆች በቀል እየተፈጸመባቸው ነው፤ የደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ፣ ካህናትና ምእመናን ዛሬ ለቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት አቤቱታቸውን ያቀርባሉ



St.Urael church bld00
የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን


ፓትርያርኩ እና አማሳኝ አማካሪዎቻቸው÷ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የመልቀቂያ ጥያቄ ካቀረቡት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጋራ የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱን በመደገፍ በቅርበት የሠሩት ውጤታማው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ክብሩ ገብረ ጻድቅ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ላይ ግፊት አድርገዋል – ‹‹ታዝዤ ነው፤ የፓትርያርኩ ጭቅጭቅ አላስቀምጥ አለኝ፡፡›› (ዋ/ሥ/አስኪያጁ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን)

  • የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ይኹንታ የሰጠው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት በቅ/ሲኖዶሱ በተላለፈው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት እንዳይከናወን ተቃዋሚ ነን ባይ አማሳኞችን ያስተባበሩት ዘካርያስ ሐዲስና ኃይሌ ኣብርሃ በውጤታማው አስተዳዳሪ ላይ ‹‹አንተን ባንሠራልኽ›› በሚል ሲዝቱባቸው ቆይተዋል፡፡
  • በተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው እና የአመራር ክህሎታቸው በካህናቱ፣ በሰንበት ት/ቤቱ፣ በአካባቢው ወጣቶችና በአጠቃላይ ምእመኑ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙት ውጤታማው አስተዳዳሪ÷ አንድ ዓመት ባልሞላ ቆይታቸው ከሙስናና ምዝበራ እንዲጠበቅ ያደረጉት የደብሩ ተቀማጭ ገንዘብ ከኻያ ሚልዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
  • በውጤታማው አስተዳዳሪ ምትክ ለመመደብ የታቀደው፣ ‹‹በተቃውሟችን አብረኽን ካልተሰልፍኽ›› በሚል በመልአከ ብርሃናት ክብሩ ገብረ ጻድቅ ላይ ዛቻ ሲሰነዝሩባቸው ከቆዩት አማሳኞች አንዱ የኾነውን ኃይሌ ኣብርሃን ነው፡፡
  • አማሳኙ ኃይሌ ኣብርሃ÷ በውጤታማው አስተዳዳሪ ከምዝበራ ተጠብቆ ከፍተኛ አቅም የፈጠረውን የደብሩን ተቀማጭ በልማት ስም ለመመዝበር፣ በድጋፍ ሰጭነት ከሚሠሩና በስም ተለይተው ከሚታወቁ የደብሩ ልማደኛ ጥቅመኞች ጋራ ቁርኝት በመፍጠር ሲነጋገርበት እንደቆየ ተጠቁሟል፡፡
  • አማሳኙ÷ ከደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከ13.3 ሚልዮን ብር በላይ በመመዝበር በፈጸመው የከፋ ሙስና ከእልቅና ከተወገደ በኋላ ወደ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያለተጠያቂነት ቢዛወርም የአስተዳደር ሓላፊነቱን ትቶ የግል ቢዝነሱን በማጧጧፍ ላይ እንደኾነ ነው የሚነገረው – ‹‹ሳይገባው በውዝግብ የተመደበበትን የአስተዳደር ሓላፊነት እየበደለ ራሱ በሚሾፍረው ሚኒባስ ታክሲ ከመገናኛ – ጣፎ – ሰንዳፋ እየሸቀለ ያመሻል፡፡›› /ታዛቢዎች/
  • የመልአከ ብርሃናት ክብሩ ገብረ ጻድቅ አላግባብ ከሓላፊነት የመነሣት ጉዳይ ነገ በሚካሔደው ሳምንታዊው የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ በፓትርያርኩ አማካይነት በአጀንዳነት እንደሚቀርብ ተጠቅሷል፡፡
  • የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በፓትርያርኩ ግፊት አቅርቤዋለኹ በሚሉት የውሳኔ መነሻ መሠረት፣ ዝውውሩ የሚፈጸመው በደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል እና በሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አድባራት አለቆች መካከል ቢኾንም አካሔዱ የኃይሌ ኣብርሃ ቀጥተኛ ምደባ የሚፈጥረውን ቁጣ ለመከላከል የተቀየሰ ስልት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡
  • ከሐምሌ ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከውጤታማው አስተዳዳሪ ጋራ በመግባባት ሓላፊነቱን በአግባቡ የተወጣውና የአገልግሎት ዘመኑን እያጠናቀቀ የሚገኘው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ባለፈው እሑድ በተከበረው የቅዱስ ዑራኤል ወርኃዊ በዓል ላይ ባቀረበው ዝርዝር ሪፖርት፣ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በርካታ ተግባራት በስኬት መከናወናቸውን ከመግለጹም በላይ የአለቃውን መነሣት በይፋ ተቃውሟል፡፡
  • ልማደኛ አማሳኞች በውጤታማው አስተዳዳሪ የተገታባቸውን ሕገ ወጥ ጥቅም ለማስቀጠል አለቃውን በፓትርያርኩ ግፊት ከሓላፊነት ከማሥነሳት ባሻገር፣ እስከ ልዩ ጽ/ቤት በተዘረጋውና 22 ሚልዮን ያኽል ብር በዘረፉበት የምዝበራ ኔትወርካቸው አማካይነት ቀጣዩን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የምርጫ ሒደት ለመቆጣጠር ቋምጠዋል፡፡
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን በመዋጋት በአዲስ አበባ ደረጃ ለተቋቋመው የማኅበራት ኅብረት ምሥረታ ቀዳሚ አስተዋፅኦ ያደረገው የቅዱስ ዑራኤል አካባቢ መንፈሳዊ ጎልማሶችና ወጣቶች ማኅበር ውጤታማው አስተዳዳሪ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸውን ተቃውሟል፡፡
  • በዐሥራ ኹለት ቀበሌዎች የተቋቋሙ ማኅበራት አንድነት የኾነውና ከኹለት ሺሕ በላይ ወጣቶችን ያቀፈው ማኅበሩ÷ ለአማሳኞች መቅሰፍት፣ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ውጋት መኾኑን በመቀጠል አጥቢያውን ከአማሳኞች ኔትወርክና ከልማደኛ መዝባሪዎች ለመጠበቅ ተዘጋጅቷል፡፡
About these ads

Sunday, 15 June 2014

አባ ማትያት ፡- ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ

     
     

 

 

 

 

ከታደሰ ወርቁ
  • አቡኑ ጉዱ ካሳን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ የለውጥ አባት ተደርገው ተወሰዱ ፤ በቤተ ክርስያኒቱ ምሁራን ልጆች ተሳትፎ እየፈራረስ የነበረውን ጽመታዊ ቡድንን ከያለበት እየፈለጉ በማሰባሰብ ነፍስ ዘሩበት፡፡ቅዱስነታቸው ፤ ራሳቸውን ለአላስፈላጊ ተጽህኖ ያጋለጡበት ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ቄሳራዊው ወገን ብቻ ሳይሆን ጽምታዊውም ቡድን ያልጠበቀው ምርኮ ኾነለት፡፡
  • ፓትያርኩ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ ተቋምነቷ የሚመጥኑ ሰዎች ሊመደቡላት እንደሚገባ ቢናገሩም በቅዱስነታቸው የሚታየው አቋም የለሽነትና አቅመ ቢስነት ከፍቶ አደባባይ ወጥቶ አሸማቃቂ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
  • ቅዱስነታቸውን በክብረ-ክህነት ላይ አመንዝረው ፤ ከአባቶቻችን አዋራጆች ፤ ምሁራን ልጆቻቸውን በጠራራ ጸሀይ ለማስገደል ጭምር ከሚያሴሩ ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን በግላጭ ከሚዘርፉና ከሚመዘብሩ እንዲሁም ለመሰረተ እምነቷ  ፤ ለሥርዓቷ ፤ ለትውፊቷና  ታሪኳ ግድ ከማይላቸው አማሳኞችና ጽልመታዊ ኃይሎች ጋር የተሰለፉት ሕለተ ሙሴን ጠልተው ሕለተ ወርቅን በማፍቀር አባዜ ነው፡፡

(አንድ አድርገን ሰኔ 7 2006 ዓ.ም)፡-በአዲስ ፓትርያርክ ፤ ዋና ጸሐፊ እና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሥራውን የጀመረው ቤተ ክህነት ባሳለፍነው ወርሀ ግንቦት አንደኛ አመቱን ይዟል፡፡ ይህው የአንድ ዓመት የሥራ ዘመን ገና ከጅምሩ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ለውጥ ብዙ የተለፈለፈበት ቢኾንም መሠረታዊ ችግሮቿን መፍታት ይቅርና አንዲት ክንድ አንኳን ፈቅ አላደረገውም፡፡ ዓመቱ ፤ በመልካም አስተዳዳር እጦት መንስኤ የኾኑት ብልሹ አሰራር - ሙስና- ጎጠኝነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ጎልተው የታዩበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ኻያ አንድ አመታት በርዕሰ አበውነት ‹ሲገዙ› የነበሩትን የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ሞትን አስከትሎ ስድስተኛውን ዘመነ ፕትርክና  የምደባ ያህል  የተረከቡት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀናኢ ሊቃውንትና ምእመናን ለዘመናት ሲያንገሸግሽ የቆየውን አድሏዊ አሠራር ፤ ጎጠኝነትና ሙስና በመጠኑም ቢኾን ይፈታሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡


ይህም ያለምክንያት የተሰጠ ቅድመ ግምት አይደለም፡፡ ቅዱስነታቸው በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ፕትርክና ይታዩ የነበሩትን  እነዚህን ችግሮች በማንሳት እንዲሁም በአቡነ ጳውሎስ ዘመን  ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ለሚጠይቋቸው የመብትም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ማግኝት አለመቻላቸውን በየብዙኃን መገናኛ ማጋለጣቸው የመጀመሪያው  የቅድመ ነገር ምክንያት ነበር፡፡

በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ንግግር ሲያደርጉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንትና ምእመናን ብሶትና የዕለት ከዕለት ምሬት የተሰማቸው በሚመስል ሁኔታ  ትኩረት ሰጥተው ከሚንቀሳቀሱባቸው  የሥራ ዘርፎች  መካከል ፤ በዋነኝነት ሙስናንና ጎጠኝነትን መዋጋት እንደሚሆን መጥቀሳቸው ኹለተኛው የቅድመ ነገር ምክንያት ነበር፡፡

በዚህ ንግግራቸው ሳይወሰኑ ያስቀመጧቸውን ነጥቦች በቁርጠኝነት ወደ ስራ ለመለወጥ የተነሱ በመሚመስል አኳኋንና  በአምስተኛው ዘመነ ፕትርክና  ባልተለመደ ግለት ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ብልሹ አሠራርን ለማረምና ለማስወገድ የጸረ- ሙስና አብይ ኮሚቴ ፤ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀር የአስተዳደር ማሻሻያ አብይ ኮሚቴ ፤ የፋይናንስ አሠራር ስርዓት ለመዘርጋት ደግሞ የገንዘብ አያያዝ ማሻሻያ አብይ ኮሚቴ ፤ እንዲቋቋም የብዙኃን መገናኛ ጠርተው ማወጃቸው ሦስተኛ ቅድመ ነገር  ምክንያት ነበር፡፡ ቅዱስነታቸው በዚያ ታሪካዊ በሚመስል በኋላ ግን በብዙዎች ዘንድ ራስን ማስተዋወቂያ ተደርጎ በተወሰደው ስልታዊ ንግግራቸው ‹‹እነዚህን ሦስት መሰረታዊ እርምጃዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሂደት የሚወስኑ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ርምጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀረበው ሀሳብ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ቆራጥ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል›› ካሉ በኋላ ‹‹ሥር ሰዶ የሚታየው አሳፋሪና አሳዛኝ አሠራር ሳይታረም ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምትወድቅ እኛንም በአመራር ላይ ያለነውን ብልሹነት ታሪክ እንዲወቅሰንና እንዲፈርድብን የሚያደርግ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል›› ሲሉም አስጠንቅቀው ነበር፡፡ አክለውም ‹‹በርምጃው ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቆራጥነት ይጠይቃል ፤ በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚዳግት ቢሆንም የለውጡን መሠረት በአስቸኳይ ማስቀመጥና  አቅጣጫውን መቀየስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል›› ብለውም ነበር፡፡

ይህ አፍዓዊ መግለጫቸው ተከትሎም በቤተክህነቱ መዋቅራዊ ለውጥ ተደርጎ የአገልግሎት አሰጣጡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዋንኛ ተልእኮ ማስፈጸም የሚያስችል ይሆናል የሚል ግምት በብዙዎች  ዘንድ ተወሰደ፡፡ ቅዱስነታቸውም  በአንድ አመት በዓለ ሲመት አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይም ‹‹የዛሬ ዓመት የተናገርኳቸው ቃላት ኹሉ እንደጸኑ ናቸው ፤ አልተበረዙም ፤ አልተከለሱም ፤ እንዲያውም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምእመናን ጋር በመሆን አጠነክራቸዋለሁ›› ከማለት አልፈው ለተቋማዊ ለውጡ በቁርጠኝነት የተነሱ በሚመስል ሁኔታ  በለውጡ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች  ላይ የተለያዩ የጥናት ቡድኖች እንዲቋቋሚ በጎ ፍቃዳቸውን ያሳዩ መስለው ‹ተወኑ› ፡፡ በአንዶቻችን ዘንድ አቡኑ ጉዱ ካሳን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ የለውጥ አባት ተደርገው ተወሰዱ፡፡

በኋላ ግን ኾነው የተገኙት መስለው የተናገሩትን ሳይሆኑ ከቅድስት ሀገር እየሩሳሌም እስከ አሜሪካ ኖረውታል የሚባለውን ምንነታቸውንና ማንነታቸውን ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በማስፈን ኾነ ጎጠኝነትን ኾነ ጥቅመኝነትን መሠረት ያደረጉ አድሏዊ አሠራሮችን በማስቀረት ፤ ሙስናን በመዋጋትም ኾነ በቤተ ክህነቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሊቃውንቱንና  የምእመኑን ቅሬታ የሚፈቱና አመኔታቸውን ያተረፉ ኾነውና በቅተው አልተገኙም፡፡

ይባስ ብለው ሞያዊ እውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ደህንነት አስራት አድርገው ያቀረቡ ሙያተኞችን አግልለው ድጋፍ ነስተው ፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ከሚያስቀድሙና  ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድገትና ለውጥ የዘመናት እንቅፋቶች የሆኑ አማሳኞችና አድር-ባር ፖለቲከኞች ጋር ማኅበርተኝነት መስርተው ተገኙ፡፡ ርእሰ አበውነታቸውን ዘንግተው የስርዓቱ ጭቃ ሹምና ምስለኔ በመሆን የማይገባቸውን ሥልጣን ከሚገባቸው ነጥቀው  ከያዙት ፤ ድኻውን ካህን ባለፉት 23 ዓመታት ሲበዘብዙ እና ሲያሰቃዩት ከኖሩት ፤ የካህኑን ቤተ-ሰብእ ለዘመናት ከእጅ ወደ አፍ የሠቆቃ ኑሮ እንዲገፋ ካደረጉት ፤ ሊቃውንቱን በተዋራጅነት ፤ በድህነት ፤ በእርዛትና በበሽታ እየተሰቃዩ እና እየተጎሳቀሉ አስከፊ ኑሮ እንዲያሳልፉ ያደረገውን አማሳኝና አድር ባይ  ቡድን ጠባቂ ሆነው አረፉት፡፡

ከመንበረ ፕትርክና እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት  ድረስ ያለውን አገልጋይ ጭሰኛ አድርገው ያለዋስትና ከሥራው ሲያፈናቅሉት ከኖሩት ከመንበረ ፓትርያርክ ጅራፍ አውራጆችና በእልቅና ወንበር ከተቀመጡ የአጥቢያ ምሽሮዎች ጋር በመሆን ፤ የብዝበዛውን መረብ ይበልጥ ለማጠናከርና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው የሚያስችላቸውን የስልጣን ከለላ በመስጠት ፤ የእነርሱ አገልጋይ እና የብዝበዛው ተባባሪ ሆነው እንዲታዩ አደረጓቸው፡፡ እውነተኛው አገልጋይ በዚህ የዘመናችን መልከኞች መብቱን ተገፎ ለብዝበዛ በመጋለጡ ከመላ ቤተሰቡ ጋር በችግር ሲማቅቅ ፤ እነርሱ የመዘበሩትን የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማተራመስ ከሚጠቀሙት ጋር  ግንባር ፈጥረው ተገኙ፡፡

እንደ አምስተኛው ዘመነ ፕትርክና ሁሉ በስድስተኛው ዘመነ ፕትርክና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና ክብር የደከሙላትን መስዋዕትነት የከፈሉ ሊቃውንት ፤ ቢያንስ ፍትሀዊ አስተዳደር ሲጠብቁ ፤ የቤተ ክህነቱ የዘመናት አድ-ባይ ቡድንና የአጥቢያ አማሳኞች ግንባር ፈጥረው የፓትርያርክ አባ ማትያስ የአስተዳደራቸውን ባለሟልና ባለጊዜዎች በመሆን ለሹመት ፤ ለሽልማቱ እና ለጥቅማ ጥቅሙ በመጀመሪያ ረድፍ ተሰለፉ፡፡ ሊቃውንቱ ለቤተ ክህነቱ ባይተዋርና የበይ ተመልካች እንዲሆኑ የሚያደርጉ ጸረ-ምሁራን ፤ ጸረ-ሊቃውት አስተሳሰቦች ፤ አቋሞችና ድርጊቶች መታየታቸው ቀጥሏል፡፡

በቤተ ክርስያኒቱ ምሁራን ልጆች ተሳትፎ እየፈራረስ የነበረውን ጽመታዊ ቡድንን ከያለበት እየፈለጉ በማሰባሰብ ነፍስ ዘሩበት፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በመተባበር የካቲት 21 እና 22 በአዘጋጁት ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል የምክክር ጉባኤ ወቅት ቅዱስነታቸው አድርገውት በነበረው ንግራቸው ላይ ‹‹ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቤተ ክርስቲያንን እንምራ እያሉ ነው ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ስርዓት አላት ፤ እንዲህ ማለት አይችሉም ፤ በባይሎጂ እና በኬሚስትሪ እንቀድስ ይላሉ›› የሚለውን ክሥና ወቀሳም ይህንን ያረጋገጠ ነበር፡፡

ይኽውም ከመንፈሳዊነትና ሞያዊነት ይልቅ በጥቅመኝነትና ጎሰኝነት የተሳሰሩ አማሳኞች በፓትርያርኩ አስተሳሰብ ላይ የፈጠሩት የጸረ መንፈሳዊነትና የጸረ ምሁርነት ተጽህኖም የተጋለጠበት ከመሆኑም በላይ ‹‹ቤተ ክርስያኒቱን በሰለጠ እና በተማረ ኃይል አንቀሳቅሳለሁ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን አስተካክላለሁ ፤ ታማኝነት ፤ አቀኝነትና  ተጠያቂነትን አሰፍናለሁ›› ዓይነቱና የመሳሰለው ንግግራቸውም ‹‹ሥር በሰደደ ችግር መፍትሄ አማራጭ መስለው ራሳቸውን ያስተዋወቁበት ፤ ከውስጥ እምነታቸው ያልመነጨና የተጫናቸው›› መሆኑም የተረጋገጠበት ኾኗል፡፡

‹‹ቅዱስ ሲኖዶስም ከምንም በላይ በራሱ መተማመን አለበት ፤ ከእግዚአብሔር በታች  እምነቱ እና ትውክልቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ መሆን አለበት ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም ነቅቶ እና ተግቶ የመጠበቅ ሓላፊነት አለበት››  ብለው በዓለ ሲመታቸውን የመከሩት ቅዱስነታቸው ፤ ራሳቸውን ለአላስፈላጊ ተጽህኖ ያጋለጡበት ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ቄሳራዊው ወገን ብቻ ሳይሆን ጽምታዊውም ቡድን ያልጠበቀው ምርኮ ኾኖለታል፡፡ በርዕሰ መንበርነት ለሚመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ እና በብዙ ሚሊየን የሚልቁ አገልጋዮችና ምዕመናን በርእሰ አበውነት የተሰየሙበት መንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ከውስጣዊ እና ውጫዊ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ  ጣልቃ ገብነትን ተከላክለው መመሪያውንና ውሳኔውን በማስፈጸም ልዕልናውን ማስከበት ተስኗቸው እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡

ቅዱስነታቸው ግንቦት 21 2005 ዓ.ም በመጀመሪያ ጊዜ ለመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግር ፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር  ሒደት ሲመረመር ግን  እጅግ የተንዛዛ ቢሮክራሲ የሰፈነበትና  የሰው ኃይል አመዳደቡም ከመሠረታዊ  ተልእኮ ፤ ተግባርና እቅድ ጋር ያልተቀናጀ ከመሆኑ በላይ የሰራተኛው አቀጣጠርና የስራ ችሎታ ፤ ዕውቀትንና ልምድን እንደ መስፈርት ወስዶ የተፈጸመ ባለመሆኑ የሰራተኛው ቁጥር ከሚያስፈልገው በላይ ወጥቶ ይታያል ፤ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ሲመረመርም በወገንተኝነትና በሙስ የተቀጠረ መሆኑንና እንዲሁም አፈጻፀሙ የተለያዩ የስነ ምግባር ብልሹነት በስፋት የሚያንጸባርቅ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ይህ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና ቅድስና ጋር የማይጣጣም ሂደት በመሆኑ ሁኔታው ለማረም ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን ፤ በዚህ መልኩ በራሳቸው አንደበት የጠቀሷውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መሰረታዊ የአስተዳደር ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የተቋማዊ ለውጥ ግስጋሴ በአማሳኙ ቡድን አባላት ጎትጓተኝነት ፤ በሙሰኛ የደኅንንት  ነን ባይ ግለሰባዊ አጋፋሪነትና የራሳቸው የቅዱስነታቸው ሽንፍ ስነ ልቦና በወለደው  ተንበርካኪነት የተነሳ የተገታ መስሎ ይታያል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋማዊ ለውጥ ጥናቶች የሰጠውን ይሁንታንና የአፈጻጸም አቅጣጫዎች በአማሳኞቹ ምክር ማገት ሳይበቃቸው ይባስ ብለው የቤተ ክርስቲያኒቱን የተቋማዊ ለውጥ እድሎችና ተስፋዎች ሲያመክን ከኖረው ጽልመታዊ ሃይል ጋር  በጎጠኝነት ተሰልፈዋል፡፡  በዚህም ሳቢያ በአመራራቸው ላይ ቅሬታና እምነት ማጣት እየተባባሰ ሲሄድ ይታያል፡፡ ፓትያርኩ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ ተቋምነቷ የሚመጥኑ ሰዎች ሊመደቡላት እንደሚገባ ቢናገሩም በቅዱስነታቸው የሚታየው አቋም የለሽነትና አቅመ ቢስነት ከፍቶ አደባባይ ወጥቶ አሸማቃቂ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጥቂት በማይባሉ ሰራተኞችና አገልጋዮች ዘንድ ደግሞ አቅመ ቢስነቱ እና አቋመ ቢስነቱ ንቀትና ጥላቻን ከማስከተሉም በላይ ፤ የቀድሞውን ፓትርያርክ በደል አስረስቶ ዘመነ ፕትርክናቸውን ብዙዎች እንደ መልካም ትዝታ የሚያወጉትና የሚጨዋወቱበት ኾኗል፡፡        

በዘንድሮ የግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ስብሰባ ቅዱስነታቸው ከምልዓተ ጉባኤው ቁጥጥር ውጪ የሆኑበት  አግባብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ  የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞች ጋር የፈጠሩት ቁርኝት በገሐድ  ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ  ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ  ውላጤ የማድረጋቸው ትእምርት  ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡  የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ አቡነ ኤጲፋንዮስ በምልዓተ ጉባኤው መካከል ቆመው ቅዱስነታቸውን  ‹‹ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላዎት  ለምነው አብረው ይስሩ ያሏቸውን  ሊቀጳጳስ በመገፍተር  ኃይልዎን ማሳየትዎ እንዴት ነው ? ሥራ ሆኖ የሚቀጥለው ከወዲሁ እንዴት ነው ? የሚገፋው ? ›› ብለው መናገራቸው በራሱ በእውንነት  ከወሰድነው  ፓትርያርክ አባ ማትያስ ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ መሸጋገራቸውን ያረጋግጥልናል፡፡
በዚህ አውድ ሕለተ ሙሴ የእወነተኛና ቸር እረኝነት ትእምርት ሲሆን ሕለተ ወርቅ ደግሞ የአጤያዊ አምባገነንነት ትእምርት ነው፡፡ በመጀመሪያው ራስን ስለመንጋው አሳልፎ መስጠት  ፤ ራስን መካድና መስቀል መሸከም ፤ ስለ ቤተክርስቲያን ክብርና ልዕልና መስዕዋት መሆን  ፤ ስለገቡት ቃልና ሃላፊነት ፤ ስለ ስርዓተ አበውና ቀኖና መታመን ፤ በራስ ቅድስና ሌሎችን መቀደስ  ፤ በመልካም አርአያነት በምእመናን ዘንድ መታፈር ፤ በጥብአት አጥፊ ሹማምንትን መገሰጽ ፤ በብሔራዊ በአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተደማጭነት ሲኖርበት  በሁለተኛው ደግሞ ስለ መንበር መንጋውን አሳልፎ መስጠት ፤ ለራስ አጤያዊ ስርዓት መቆርቆርና መስቀሉን ከባሕርያዊ እሴቱ አርቆ እና አውጥቶ በጌጥነት መጠቀም  ፤ ስለ ራስ ክብርና ዝና መጨነቅ ፤ ቃለ-አባይ ሆኖ መገኝት ፤ ከስርዓተ አበውና ቀኖና ቤተ ክርስቲያ በላይ ግላዊ ደማዊ እና  ሥጋዊ ፍቃዳትን አግዝፎ መታየት ፤ ተኣምኖን በቤተ መንግሥቱ ማድረግ ፤ የቅጥረኝነትንና የተላላኪን አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡
ቅዱስነታቸው ፤ ከሕለተ መሴ ወደ ሕለተ ወርቅ ውላጤ አድርገዋል ስንል  በመጀመሪያ የዘረዘርናቸውን የሕለተ ሙሴ መገለጫዎችን በፈቃዳቸው ትተው በሁለተኝነት የዘረዘርናቸውን የሕለተ ወርቅ  መገለጫዎችን ገንዘብ አድርገዋል ማለታችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአምልኮተ እግዚአብሔር  ወደ አምልኮተ ጣኦት መሔድ በአመንዝራነት የማስቆጠሩን ያህል ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ ውላጤ ማድረግ በክብረ ክህነት እንደማመንዘር ይቆጠራል፡፡
በታሪካችን እንኳን ሰማዕተ ጻድቅ ብጹዕ አቡነ ጰጥሮስና ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ሕለተ ወርቅን ተጸይፈው ሕለተ ሙሴን አፍቅረው ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ልዕልና ፤ ለአገርና ለሕዝብ ነጻነት በኦርቶዶክሳዊ ጥብዐት ሰማዕት ሲኾኑ  ፤ ሕለተ ሙሴን ትተውና ቀብረው ፤ ሕለተ ወርቅን ወድደውና አፍቅረው የአገር ዳር ድንበር የደፈረውን ፤ ሉአላዊ ክብራችንና ልዕልናችንን የገፈፈውን ፤ ሕዝባችንን በቦንብ ያቃጠለውን ፤ ገዳማትንና አድባራትን ያጋየውን የፋሽስት ጦርን ያስተናገዱ ሌሎችም ነበሩ፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እየኾነ ያለው በቅርጽ ሳይሆን በይዘት አንድ ነው፡፡
ቅዱስነታቸውን በክብረ-ክህነት ላይ አመንዝረው ከአባቶቻችን አዋራጆች ፤ ምሁራን ልጆቻቸውን በጠራራ ጸሀይ ለማስገደል ጭምር ከሚያሴሩ ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን በግላጭ ከሚዘርፉና ከሚመዘብሩ እንዲሁም ለመሰረተ እምነቷ  ፤ ለሥርዓቷ ፤ ለትውፊቷና  ታሪኳ ግድ ከማይላቸው አማሳኞችና ጽልመታዊ ኃይሎች ጋር ተሰልፈው በመጀመሪያዎቹ ገጾች የጠቀስናቸውን የድፍረት ጥፋቶች እንደፈጸሙና ከገቡት ቃል በተቃራኒው እንዲቆሙ ኃይልና ብርታት የሆናቸው ይህው የትላንት ደዌያችን ፤ ሕለተ ሙሴን ጠልቶ ሕለተ ወርቅን በማፍቀር አባዜ ነው፡፡
የቅዱስነታቸው በዚህ አሳዛኝና አሳፋሪ ኹኔታዎች ውስጥ መገኝት ቤተ ክርስቲያናችን ተዘርዝረው በማያልቁ  ከተከማቹ አስተዳደራዊ ችግሮች  ጋር እንድትተበተብ እንድትቀጥል እያደረገ መኾኑ እሙን ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች እንዲቃለሉ ሳይሆን እንዲወሳሰቡና እንዲጠልቁ ከአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የሚመጋገበው ቅዱስነታቸው ሕለተ ወርቅነትን  ብቻ ሳይሆን የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላትና አሠራር በመቆጣጠር ቤተ ክርስያኒቱን የቆብ ደሴት ለማድረግ የተያያዘው አቅጣጫ ጭምር ነው፡፡    
በዚህም የተነሳ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ከቀናነትና ከጽናት እየራቀ እንጂ እየቀረበ የሚሄድ አልሆነም፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ሕይወት  ፤ ይህን አቅም በተግባር ላይ ለማዋል በሚችሉ ኃይሎች እጅ እንዲሆን አላበቃውም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን የላዕላይና ታህታይ መዋቅር ሥልጣን የተቆጣጣሩት ጥቁር ራሶችም ፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም በፊት የራስን ስልጣን ለማስቀጠልና ከዚህ ስልጣን የሚገኝ ጥቅም በሙሉ እያግበሰበሱ ለመኖር ቆርጠው የተነሱ ኃይሎች በመሆናቸው ፤ ሕለተ ወርቅነትንም ሆነ የቆብ ደሴትነትን መግራት አልቻሉም፡፡ ለዚህ እንዴት እንደበቃን በሚገባ መረዳት ተመሳሳይ የሆነ ወይም የከፋ ውድመት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዳይደርስ ለመከላከል ያስችለናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የሥርዓትና የትውፊት ግምጃ ቤት እያሉ ፤ ያለፈውን ዘመን ታላቅነቷን እና ልዕልናዋን ብቻ እየተረኩ ፤ ነገር ግን ቤተክህነቱ ያለበትን ድቅድቅ ጨለማ እና ስልጣኔ አልባ ሕይወት ፤ የመንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ልዕልና መላሸቅ  እንዳለዩ ሆኖ ማለፍ የሚቻልባቸው ዘመናት ያበቃ ይመስለናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከረጅም ውጣ ውረድ ፤ ብዙ ችግርና ፈተና ከሞላው ታሪኳ በእነዚህም ታሪኮች ውስጥ አባቶች ያሳዩት ተጋድሎና  ለሀገሪቱ ከከፈሉት መስዋዕትነት ጋር የማይመጥን አስተዳደራዊ እና ልማታዊ ደረጃ ላይ መገኝቷ  ፤ እጅግ የሚያንገበግበው ልሂቃዊው ትውልድ መምጣቱንም ማጤን ያስፈልጋል፡፡  ይህ ትውልድ በአንድ በኩል በሀገሩ እና በቤተ ክርስቲያኑ የቀደመ ታላቅነት እና ነጻነት የሚኮራ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክህነቱ የሚታየውን የጎጠኝነት ፤ ብኩንነት ፤ ብልሹ አሰራር እና ምዝበራ በመሳቀቅ ለመፍትሄ እየተጋ ያለ ትውልድ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው በጎሳዊ ፤ ጥቅማዊ እና ፖለቲካዊ ተዛምዶ ለሕለተ ወርቅ ያስገበረው የአማሳኞች ስብስብ ተቋማዊ ለውጥን ከጎጠኝነትና ጥቅመኝነት ጋር እያገናኝ የጸረ ሙስና ትግል አንድነት ለመከፋፈል ቢጥርም እነዚህ ኦርቶዶክሳዊያን ኃይሎች ከየትኛውም ጎሳ ሊመዘዝ የሚችል የትውልድ ታሪክ ያላቸው መኾኑ ፤ ኹሉም በጋራና በአንድነት ቤተ ክርስቲያናቸውን ከተጋረጡባት አደጋ ለመጠበቅ በቅተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ይቻላል ፤ ጎጠኞችና ስግብግቦች ዛሬ ፓትርያርኩን ከብበው ሕለተ ሙሴነታቸውን አውርደው ለሕለተ ወርቅ የዳረጓቸውና  የቤተ ክርስቲያናችንን የትርምስ አጀንዳ የሚቀርጹት አማሳኞች ከሀዲነታቸውንና ሌብነታቸውን ለመሸፈን የሚጠቀሙበት የጎሳ ፖለቲካ  ማጭበርበር በዝምታ የማይታለፍበት ዘመን እየቀረበ ስለመኾኑ!!

በመጨረሻም ለቅዱስነታቸው ግንዛቤ አንድ ነገር ላስቀምጥ፡፡ ፀሮቻቸው በሕይወት አሉ፡፡ ግን በቤተመቅደስ አይኖሩም፡፡ ልጆቻቸው ግን በቤተመቅደሱ በሕይወት ልዕልና የድኾች ከተማ በሚሉት ዓይነትና ኹኔታ በእውነትና በትሩፋት አጊጠው ይኖራሉ፡፡


ቸር ሰንብቱ
ቅዳሜ ሰኔ 7 2006 ዓ.ም ፋክት መጽሄት የተወሰደ 

‹‹አንድ ሚሊዮን ወጣትም ቢሆን የፈለገበት ይድረስ ፤ ምንጣፍ አነጠፈም አላነጠፈም የፈለገበት ይድረስ›› የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ


  •  " ገመድ የምትበላ ብትሄድ ጠፍር የምትበላ ትመጣለችሀገርኛ ብሂል

(ፋክት ቅዳሜ ግንቦት 7 2006 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ወጣቶች ማኅበራት ሕብረት ፍቃድ መሰረዙ ተሰማ፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ግንቦት 8 ቀን 2006 ዓ.ም ለሕብረቱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው ፤ ሕብረቱ ከሕገ-ቤተክርስቲያን እና ከቃለ አዋዲው ሕግጋት ፍቃድ መሰረዙን ገልጿል፡፡

86 ማኅበራትን ያቀፈው እና ከ200ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እንደያዘ የሚነገረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  መንፈሳዊ ወጣቶች ማኅበር ሰብሳቢ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን ለዝግጅት ክፍላችን ‹‹የማኅበራቱ ሕብረት ፍቃድ እንዲያገኝ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጠየቅነው መሰረት  ያገኝነው ፍቃድ ፤ ቋሚ ሲኖዶስ ሀገረ ስብከቱን ፍቃዱን እንዲሰርዝ ሲያዝ ፤ ሕብረቱ ስለጉዳዩ ሳያውቅና ሳይጠየቅ ፤ ሕብረቱም ለምን እንደታገደ ሳናውቅ ነው ደብዳቤ የደረሰን›› ስትል ጉዳዩን ገልጻለች፡፡

ሀገረ ስብከቱ ፍቃዱን የሰረዘው ሕብረቱ ‹‹ከሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ከቃለ ዓዋዲው ሕግጋት ውጪ›› እንደሆነ ቋሚ ሲኖዶሱ በማዘዙ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ‹‹ቃለ ዓዋዲው መሻሻል ይችላል›› የምትለው ሰብሳቢዋ በብጹዕ አቡነ ጳውሎስ ጊዜ ቃለ ዓዋዲው ይሻሻላል ተብሎ እንደነበር ገልጻለች፡፡ሕብረቱ  ፍቃዱ እንዲመለስለትና እያከናወነ ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲቀጥል በተደጋጋሚ ፓትርያርኩን ለማግኝትና ጉዳያችን እንዲታይ ለማድረግ ያደረግነው ጥረት ሊሳካ አልቻለም ብላለች፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ ተመላልሰን  ያገኝናቸው የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማትያስም ‹‹አንድ ሚሊየን ወጣትም ቢሆን የፈለገበት ይድረስ ፤ ምንጣፍ አነጠፈም አላነጠፈም የፈለገበት ይድረስ›› ብለውናል የምትለው ወ/ሪት ፌቨን ‹‹በየአካባቢው የተደራጁ ማኅበራት እውቅና ካላገኙ ለቤተክርስቲያኒቱ ጉዳት ›› እንደሆኑ ገልጻ ‹‹ቤተ ክርስቲያን መጥቶ እውቅና ያላገኝው ወጣትን ለመቆጣጠር እና ለመምራት አዳጋች ይሆናል›› ስትል የሁኔታውን አሳሳቢነት ትገልጻለች፡፡

ከ6ተኛው ፓትርያርክ ጋር መጪ  ዘመናችንን ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም ፤ የሀገሬ ሰው “ገመድ የምትበላ ብትሄድ ጠፍር የምትበላ ትመጣለች” ይላል፡፡

Saturday, 14 June 2014

ፓትርያርኩ ከመንግሥት ጥገኝነት ነፃ ለመኾን እንደማይችሉ ያምናሉ



  • በአብዮቱ መባቻ ዓመታት ከደርጉ ‹‹የለውጥ ሐዋርያት›› ጋራም በቁርኝት ሠርተዋል
  • ከደርግ ጋራ አብሮ በመሥራትና ደርግን በማውገዝ መካከል የሚታዩት የፓትርያርኩ የአቋም ጽንፎች ፀረ አማሳኝ መስሎ የአማሳኞች ከለላ ኾኖ የመገኘት ፍፃሜ ነው!!
(ፋክት መጽሔት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፵፱፤ ግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም.)
ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቤተ ክርስቲያኒቱና መሪዎቿ ከመንግሥት ጥገኝነት ነፃ ሊኾኑ እንደማይችሉና መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቷ የአስተዳደር ጉዳይ ጣልቃ ቢገባ ሕገ መንግሥቱን እንደማይፃረር አቋም ይዘው መከራከራቸው ተገለጸ፡፡
የፓትርያርኩ አቋም የተንጸባረቀው፣ ከአንድ ሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ለቀናት ውይይት ባደረገበት ወቅት እንደነበር የስብሰባው የፋክት ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ማሻሻያ ለካህናት ስለተከለከሉ ተግባራት አስመልክቶ፣ ጳጳሳትና በቤተ ክርስቲያኒቱ በሓላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ካህናት ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ አባልነት ወይም አራማጅነት ነፃ መኾን እንደሚገባቸው ይደነግጋል፡፡
ስለ አንቀጹ አግባብነትና አስፈላጊነት በተሰጠ ማብራሪያ፣ ‹‹እስከመቼ ድረስ አንድ ላይ ተጣብቀን እንኖራለን፤ ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው ነፃ መኾን አለብን፤ ነፃ መኾናችንን ለማረጋገጥ ጳጳሳትና በሓላፊነት ደረጃ ያሉ ካህናት ከፖሊቲካ እንቅስቃሴ አባልነትና አራማጅነት ነፃ እንዲኾኑ መከልከል አለብን፤›› መባሉ ተዘግቧል፡፡
ፓትርያርኩ አንቀጹን በመቃወም ‹‹ከመሐንዲስ፣ ከዶክተር ነፃ ልንኾን እንደማንችለው ከመንግሥት ጥገኝነትም ነፃ ልንኾን አንችልም፤›› የሚል አስተያየት መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡ አያይዘውም በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ እንጂ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጣልቃ ቢገባ ድንጋጌውን እንደማይፃረር የሚያሰማ አቋም አራምደዋል ተብሏል፡፡
አቡነ ማትያስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የመጨረሻ ወሳኝና ላዕላይ የሥልጣን መዋቅር ከኾነው ከቅ/ሲኖዶሱና አባላቱ ይልቅ ከመንግሥት ጋራ አላቸው የሚባለው ያልተገራና ያልተገደበ ግንኙነት የሊቃነ ጳጳሳቱን ቁጣ ቀስቅሷል በተባለበት ኹኔታ ይህን አቋም ማራመዳቸው እያነጋገረ እንደሚገኝ ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
Patriarch Abune Mathias formerly known as Aba Teklemariam with Dergue's Renewal committee membersሌሎች የፋክት ምንጮች በበኩላቸው፣ ፓትርያርኩ ከመንግሥት ጋራ አላቸው በሚል በተቺዎቻቸው የሚጠቀሰው ልክ ያልኾነና ያልተገራ ግንኙነት ጵጵስና ከመሾማቸው አስቀድሞ የሦስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ በነበሩባቸው የአብዮቱ መባቻ ዓመታትም፣ የወቅቱን የሥርዓት ለውጥ በቤተ ክህነቱ ለማሥረጽና ተቃዋሚዎች (በተለይ ኢዲዩ) የሕዝብ ተቀባይነት እንዳያገኙ ወደ ስሜን ኢትዮጵያ ተጉዘው የፈጸሙትን ተግባር በአስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡*
›››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››
*YeTahisas Girgir ena Mezezuበግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከ፲፱፻፵፰ – ፶፫ ዓ.ም. በአገር ግዛት ሚኒስቴር የሕዝብ ፀጥታ ጥበቃ መምሪያ ሓላፊ ሌተና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ልዩ ረዳት የነበሩት አቶ ብርሃኑ አስረስ ‹‹ማን ይናገር የነበረ… የታኅሣሥ ግርግርና መዘዙ›› በሚል ርእስ በቅርቡ ለኅትመት ባበቁት መጽሐፍ፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የፊት ስማቸው አባ ኃይለ ማርያም እንደነበር የጠቀሱት በስሕተት ይመስላል፡፡
በ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. በወልቃይት፣ በፀገዴና በአርማጭሆ ቆላ ደርግን በመቃወም የተንቀሳቀሰውን የኢዲዩ ኃይል ለማቆምና ደገኛው ከቆለኛው ጋራ እንዳይተባበር ለመምከር በደርግ ተመልምለው ወደ በጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ካቀኑት መካከል በወቅቱ አባ ተክለ ማርያም ዓሥራት አኹን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አንዱ የቡድኑ አባል እንደነበሩ የመጽሐፉ አዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
አባ ተክለ ማርያም በወቅቱ ‹‹የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አቡነ ቀሲስ፣ በኋላ አቡነ ማትያስ ናቸው›› የሚሉን ጸሐፊው፣ ከአባ ተክለ ማርያም ጋራ አለቃ ቀለመ ወርቅ(የቤተ ክህነት ደብተራ ይሏቸዋል) በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት ‹‹ለሃይማኖት ነክ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደነበር›› አስፍረዋል፡፡
የሕዝብ ተሰሚነት አላቸው በሚል ከጠቅላይ ግዛቱ ሰባት አውራጃዎችና የጎንደርን ከተማ በመወከል ከተመረጡት መካከል በወቅቱ የደብረ ታቦር አውራጃ ተወካይ አቶ(በኋላ ሊቀ ማእምራንና ደርግ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር በኅብተረሰብ ተሳትፎ ላይ መመሥረት በሚል ሐዋርያዊ አገልግሎቷን በሶሻሊስታዊ መንፈስ ለመቃኘት ያቋቋመው ጊዜያዊ ጉባኤ ጸሐፊ) አበባው ይግዛው አንዱ እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡
Patriarch Abune Mathias with renewal committeesከዘመቻው ጉዳይ ጋራ በተያያዘ ስብሰባ የተደረገው በጎንደርና ደብረ ታቦር ላይ ብቻ እንደነበር የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ ‹‹ኢዲዩ እየበረታ መጥቷል፤ እኛም በሰላም ተነጋግረን ደገኛውንና ቆለኛውን እንዳይተባበር ማድረግ አልቻልንም፤›› በማለት ዘመቻው ስኬታማ እንዳልነበር ጠቅሰዋል፤ አያይዘውም ‹‹ኹለቱ የሃይማኖት ሰዎች የተመለሱት አንድም አስተያየት ወይም ማብራሪያ ሳይሰጡ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ (ገጽ 400 – 421)
***************************************************
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ ካሱ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ በሠሩት ጥናት፣ የሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ቀሲስ የነበሩት አባ ተክለ ማርያም ዓሥራት (በኋላ ብፁዕ አቡነ ማትያስ) ደርግ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የለውጥ ጊዜያዊ ጉባኤ›› (the EOC provisional council or Renewal Council) በሚል ያቋቋመው ጊዜያዊ ጉባኤ አባል የነበሩ ባይኾኑም የምክር ቤቱ ሊቀ መንበር ከነበሩት ዶ/ር ክነፈ ርግብ ዘለቀ ጋራ በጥብቅ ቁርኝት መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጊዜያዊ ጉባኤው በነሐሴ ወር ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ምክትል ሊቀ መንበር ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ቀጥተኛ መመሪያና ቁጥጥር የተቋቋመ ነበር፡፡ ከኹለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጋራ ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ የገባው ጊዜያዊ ጉባኤው፣ ቅዱስነታቸው በአራት መዋቅሮች(የፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ የስብከተ ወንጌልና ማስታወቂያ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ፣ የውጭ ጉዳይና ልማት ኮሚሽን) የቤተ ክህነቱን አስተዳደር ለማጠናከር ያቋቋሙትን ኮሚቴ በመጋፋት ለውጥና መሻሻል ያመጣል ያለውን የራሱን ባለአምስት ኮሚቴዎች (የሕግና አስተዳደር፣ የስብከተ ወንጌልና ትምህርት፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የታሪክና ባህል ጉዳዮች እና የአቤቱታ ሰሚ) መዋቅር ዘርግቷል፡፡
ጊዜያዊ ጉባኤው ጋራ ያልተግባቡትና የማሻሻያ መዋቅሩን ያልተቀበሉት ቅዱስነታቸው በወርኃ የካቲት ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. ጊዜያዊ ጉባኤው ለደርጉ ባቀረበው የክሥ ሪፖርት ‹‹ሲጠበቅ የቆየ ፍርድ›› በሚል ዐዋጅ ከመንበረ ፕትርክናው ተገፉ፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱና በጊዜያዊ ጉባኤው መካከል ሽኩቻ የተካሔደበት ቀጣዩ የፕትርክና ምርጫ በጊዜያዊ ጉባኤው በኩል ታጭተው የቀረቡትን ሐዋርያዊውን ባሕታዊ አባ መላኩ ወልደ ሚካኤል – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመንበሩ ሠየመ፡፡
ጊዜያዊ ጉባኤው በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና ሹመት፣ በአህጉረ ስብከት ዝውውር እንዲሁም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሹመት በቀጥታ ይቆጣጠር የነበረ ከመኾኑም በላይ ከደርጉ ጋራ እጅና ጓንት ኾነው በአባልነት የሠሩ አባላቱ በዋና ሥራ አስኪያጅነትም ተቀምጠው ነበር፡፡ ጵጵስና እስኪሾሙ ድረስ የቅዱስነታቸው አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ የነበሩት አባ ተክለ ማርያም ዓሥራት ጊዜያዊ የሃይማኖት ጉባኤው ጋራ በጥብቅ ቁርኝት መሥራት ብቻ ሳይኾን ወደ ስሜን ኢትዮጵያ ተነቃንቀው ስለ አብዮቱ ካስተማሩና የሥርዓት ለውጡን የሚቃወሙ እንደ ኢዲዩ ያሉ ኃይሎች የሕዝብ ተቀባይነት እንዳያገኙ ከቀሰቀሱ የደርጉ ‹‹የለውጥ ሐዋርያት› አንዱ ነበሩ፡፡

Saturday, 31 May 2014

የቤተ ክህነቱ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ ፡ Cynical Intellectual Atmosphere

                                                              
                                                              በታደሰ ወርቁ ተጻፈ
  • ዛሬ ሊቃውንቱ የቤተክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና ቤተክርስቲያን አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች፡፡

(አንድ አድርገን ግንቦት 23 2006 ዓ.ም)፡- በዚህ ዐውድ(Context)ምሁር የምለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሊቅነታቸውን ያስመሰከሩ ፤ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጥናትና ምርምር አድርገው የጥናት ወረቀቶቻቸውን ያበረከቱ ፤ መጻሕፍትን ያሳተሙትን ጭምር ነው፡፡ በጥቅሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በአዕምሮ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ነው፡፡

በዚህ መልኩ ያስቀመጥናቸው ሊቃውንት ቁጥር በአንጻራዊነት እያደገ ቢሄድም በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመኑ ውስጥ ቀድሞ የነበራቸው ቦታና የኑሮ ደረጃ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹም ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያኒቱ  አገልግሎታቸውን እየሰጡ ቢሆኑም  በአሁን ጊዜ በቤተ ክርስቲኒቱ ውስጥ እንደሚታየው የቀድሞውን የመንፈስ ልዕልና እና ሐሳባዊ መሪነት አጥተዋል፡፡ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ከማድረግ በተረፈ ምሁር የሚያሰኛቸውን ተግባር የሚፈጽ አሉ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡

በተለያዩ አዝማናት የቀሰሙትን በጎ እውቀት ከምእመኑ ሕይወትና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ግንኙነት ያለው ፤ የምእመኑንና የቤተ ክርስቲያኒቱን የአግልግሎት ሕይወት ለመቀየር የሚውል መሆኑ ቀርቶ ዝም ብሎ የኑሮ መደጎሚያ ብቻ አድርጎ መውሰድ በእጅጉ ይታይባቸዋል፡፡ይህ ደግሞ እውቀትን ለእውነትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረት እምነት ፤ ቀኖናና ትውፊት ወገንተኛ መሆን ቀርቶ የበለጠ ዋጋ ለከፈለ የጥፋት ኃይል ሁሉ በሚፈለገው ዓይነት ተለክቶና ከሐሰት ጋር ተለውሶ የሚሸጥ ሸቀጥ አድርታል፡፡


ሊቃውንቱ ‹‹እኔ ንጹሕ ነኝ ፤ ምንም አልሆንም ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሙያተኛ ነኝ ፤ ሥራዬን እየሠራ ነው” በሚል ራሳዊ አቋም መንጋውን የተኩላ ሲሳይ አድርገውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የ‹‹አጉራ ዘለሎችና ጆቢራዎች›› መፈልጫ እንድትሆን ፈቅደዋል የሚሉ ወቀሳዎችም ይቀርቡባቸዋል፡፡ ወቀሳውም የደረት ንግግር አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሁኔታውን ክፉና ጨለማ የሚያደርገው ምሁራኑ አሁን ያሉበት ደካማ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማሻሻል ያላቸው ወኔ እና የሌሎች እህት አብያተ-ክርስቲያናት ምሁራን አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድባቸው ጊዜ ስናሰላ ነው፡፡

በቤተክርስቲያኒቱ ትምህርተ መሠረት የሊቃውንት ድርሻ ‹‹የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው›› መሆንም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ታላቅነት በድርሻቸው ሲታደሉት በደካማነታቸውና በሓላፊነት ሽሽታቸው ብርሃንነታቸውን ወደ ጨለማ ፤ ጨውነታቸውን ወደ አልጫነት በመለወጣቸው ኃላፊነታቸውንና ብርኩናቸውን አውጥነው የጣሉ ይመስላሉ፡፡

በእርግጥ ብዙዎች የምሁርነታቸውን ሚና በሚገባ መደላደል(Stabilization) እንዳልተጫወቱ አሳምረው ያውቁታል፡፡ዕውቀታቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔ ሰጪ አካል ለመምከር አለመቻሉንም ሁሉም ይረዱታል፡፡ ውሳኔ ሰጪዎቹም የ‹‹ሊቃውንት ምክር›› ብለው ሲጠይቁ የሚያገኙት እውነቱን ሳይሆን ሊቃውቱ ውሳኔ ሰጪውን አካል ያስደስተዋል ብለው የሚያስቡትን ‹‹እውነት›› ብቻ እንደሆነም ይገነዘባሉ፡፡
አሁን ባለው የቤተ-ክህነቱ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝነው የእነኚህ ኃይሎች(የውሳኔ ሰጪው እና የምሁራን) በተናጠል መዳከም ብቻ ሳይሆን ይህንን ድክመት በመገንዘብ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲባል በጋራ ለመሥራት አለመቻላቸውና የመሥራም ፍላጎት ፍንጭ አለመታየቱ ነው፡፡

የሁለቱም ኃይሎች እርስ በእርስ የጎሪጥ መተያየት ፤ ቅንነት በተሞላውና ገንቢ በሆነ መልኩ መተቻቸት አለመቻል ወይም ለመደጋገፍ አለመመሞከር ተቋሟን ‹‹የነጋ አድርሶች›› ስብስብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ሕግ የሚጣስላቸውና ሕግ የሚጣስባቸው ሰዎች ጥርቅምም እንድትሆን አብቅቷታል፡፡

ይልቁንም በጽንፈኛነት የአንዱን ድክመት ማጉላትና ይህን የጽንፈኛነትን አቋም በየጎራው በማስተጋባት ‹‹እኔ የበለጠ አሳቢ ፤ ከእኔ የተለየው ሁሉ ግን የቤተክርስቲያ አጥፊ ነው›› ብሎ በመኩራራት እና በዚህም እንጀራ ለመጋገር መሞከር በእጅጉ የሚዘወተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቢያንስ በግል ደረጃ የግብዝነትና የአድርባይነት (Opportunist) መገለጫ ፤ ሲያልፍ ደግሞ ቤተ ክርስቲያቱን ሊጎዳ የሚችል እኩይ ድርጊት ነው፡፡  

ይህ ሁሉ የእውቀትና የሞራል ተገናኝ ቀጠናዎች(Inter-Zone) የሚያመጡትን የሥነ ልቡና ቀውስ ለመከላከል በሚመስል ሁኔታ በቤተ-ክህነቱ ሊቃውንተ ዙሪያ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ(Cynical Intellectual Atmosphere) የተንሰራፋ ይመስላል፡፡ 

ነገሮችን በዕውቀትና በሃይማኖት ከመጋፈጥ ይልቅ ፍጹም ሥር በሰደደ ወሬና ሐሜት ማለፍ ፤ አጥፊ የቤተ-ክህነቱን ሹማምንት እነርሱ ሳያውቁ በየመሸታ ቤቱ ወይም አንድ አይነት ሀሳብ በሚያስቡ ቡድኖች  መካከል ማማት ፤ የሚደረጉ ጥረቶች መጨረሻ መጥፎ ይሆናሉ ብሎ ማመን ፤ ለለውጥ ሳይጥሩ ሌላው የሚያደርገውን የለውጥ ጥረት ማጣጣል ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ክፉና ጎጂ ክስተት እንዳይመጣ ‹‹ አኔ ምን ማድረግ አለብን?›› ብሎ በመጠየቅ በምሁርነት ማድረግ የሚገባቸውን ከማድረግ ይልቅ ክፉ ነገር ሲመጣ ‹‹አላልኳችሁም›› ብሎ በጨለምተኛ ምሁርነት መመጻደቅ የቤተ-ክህነቱ ምሁራዊ ድባብ የሆነ ይመስላል፡፡በቤተ ክርስያኒቱ ደረጃ ውድቀት ሊያመጡ የሚችሉ መሠረታዊ ችግሮችን እያዩና እየተገነዘቡ  ለምእመኑ እይታና ውይይት ማቅረብ ምሁራዊ ግዴታ ከመሆኑ በላይ የኦርቶዶክሳዊነት ግዴታ ሳይሆን እንደ የዋህነትና አላዋቂነት የሚቆጠሩበት ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ ያለበት ቤተክህነት ባለፉት በ22 ዓመታት ውስጥ ያፈራን ይመስላል፡፡

ከዚህ ቢብስም በምዕመኑ ፊት ትክክለኛ የሆነውንና የሚመስለን ነገር መናገር በተለይም ይህን ነገር መንግሥትን የሚጎነትል ከሆነ አንድም የተናገርነው ጀብደኝነት አሊያም ‹‹ ሰውየው የመንግሥት ሰላይ ሳይሆን አይቀርም›› ተብሎ የሚያስጠረጥር ደረጃ ላይም እየተደረሰ ነው፡፡

እንዲህ አይነቱን ምሁራዊ ጨለምተኝነት ለተጣለባቸው ፍርሃትና ስንፍና መደበቂያ የሚያደርጉት ብዙዎች ናቸው፡፡በዚህ ምክንያት እውነተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቅነት ስሜት ጠፍቶ ምሁርነቱ ርካሽና የማይከበር እየሆነ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል የምሁርነቱ ደረጃ እየወረደ ፤ በሌላ በኩል የቆራጦቹ ቤትና የነጻዎቹ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን እየተዋረደች ትገኛለች፡፡ እነዚህ ምሁራን ‹‹ሆዷን ለቆረጣት የራስ ሕመም መድኃኒት የማዘዝ›› ያህል እየታየባቸው ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተደራርቦ የፈጠረው ‹‹የምሁራዊ ቅሌት›› ስሜት ሊቃውንቶቻችን በቤተ-ክህነቱ ውስጥ በጉልህ የሚታዩትን መሠረታዊ ችግሮች(የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ፤ የቤተሰብ አስተዳደር እጦት ፤ ሙስናና ጎጠኝነት) የሚያሳዩ መስታወቶች ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት ፤ ሥርዓተ አምልኮ ሐዋርያዊ ትውፊትና አስተዳደራዊ ድርጁነት ቀጣይነት የሚጠቁሙ ዘመን ተሻጋሪ ኃይል መሆናቸው ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡

እንደ ማኛው ተራ ምዕመን በቤተ-ክህነቱ ‹‹ገዥ መደቦች›› አድርጉ የተባሉትን ሁሉ በተንበርካኪነት (submissive) የሚያደርጉ ፤ ባሳለፍነው ዘመነ ፕትርክና እንደታየው የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት በቤተ-ክህነቱ ‹‹ገዥ መደብ›› ጎን የመቀመጥ ክብር መቀዳጀትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ ለራሳቸውና ለሊቅነታቸው ብዙ ክብር የሌላቸው ፤ አቅመ ቢስ የቀንድ አውጣ ኑሮ ነዋሪዎች ናቸው የሚለው የብዙዎች አስተያየት እየሆነ ይገኛል፡፡

ሊቃውንቶቻችን የቤተ-ክህነቱ ፖለቲካ ሳበዳቸው ‹ገዥዎች› ጋር ሲርመጠመጡ መቃናት የሚገባው ሁሉ ይበልጥ እየጎበጠ መሄዱና ቤተ-ክርስቲያኒቱም የምትተማመንበት የታሪክ ምስክርና ታጋይ መጥፋቱም በጉልህ ታይቷል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ‹‹ነጻ የወጣ ነፍስ›› የሌላቸው እስኪመስል ድረስ ሕሊናው ላይ አንጥፈው ተቀምጠዋል፡፡

እርግጥ ከላይ የጠቀስኳቸው በሊቃውንቶቻችን ዘንድ የሚታዩት ምሁራዊ ጨለምተኝነት እና ክትያው(Consequences) እነዚህ ሊቃውት በሚኖሩባቸውና በሚሠሩባቸው አካባቢዎች በሚደርስባቸው ቤተ-ክህነታዊ ‹‹ገዥ መደብ›› እና ‹‹መንግሥታዊ›› ገዥ መደቦች ነን ባዮች ተጽዕኖ ምክንያት የመጡና ከፍተኛ አስዋጽኦ ያደረጉባው እንደሆኑ አይካድም፡፡

ይሁንና እንደ ጥንቶቹ ሊቃውንት ነጻ ምሁራዊ ድባብ በሌለበትም የቤተ ክርስቲያቱ ማኅጠነ ልቦና(Think Thank) በመሆን ምእመኑን በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሐሳብ መርተው በሚፈለገው የሞራልና የመንፈስ ልዕልና ማብቃት ባለመቻላቸው ከወቀሳ አይድኑም፡፡

ዛሬ ቤተ ክርስቲያ ከእነሱ የበለጠ አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና፡ ለዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰረታዊ ችግሮች ‹‹ ያለ አቡነ ተክለሃይማኖት ያለ አቡነ ፍሊጶስ ደብረ ሊባኖስ ምንድን ነች ? ያለ አቡነ እየሱስ ሞዐ ያለ አቡነ ክርስቶስ ሞዐ ደብረ ሀይቅ ምንድን ነች ? ያለ አቡነ ኤዎስጣቲዎስ ያለ አቡነ ፊሊጶስ ደብረ ባዚን ምንድን ነች ? ›› ያሰኙንን አይነት ሊቃውንት አጥብቀን እንፈልጋለን ፡፡ 
ሊቀ ካህናት ማንትሴን ፤ ሊቀ ስዩማን እገሌን ፤ መጋቢ ሐዲስ ፤ መጋ ብሉይና ሊቀ ማእመራንን እንትናን እናከብራቸዋለን ፡፡ ለዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን ደዌ መድኀኒት መሆን ካልቻሉ ክእነርሱ ይልቅ መድኀኒት መሆን የቻለውን ጨዋን እንመርጠዋለን፡፡
እንዲህ ካለ ምሁራዊ ጨለምተኝነት ወጥታችሁ በቦታሁ ተገኝታችሁ ቢሆን ኖሮ ያልጠገገውንና ከቶውንስ በላይ በላዩ የሚጨማመርበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁስል እኛም በየጋዜጣው ፤ በየመጽሔቱና በየብሎጉ የምንሞጫጭር የቤተ ክርስቲያን ልጆች በየብዕራችን ባንጓጉጠው ደስ ይለን ነበር፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ውኃንም ድንጋዩ ስለሚያጮኽው›› ጥሩ ትንፋሽ ለመሳብ ፋታ አልተገኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያቱና ምእመኑ ተራ በተራ አንድ ጊዜ በመሐል አገር ፤ ሌላ ጊዜ በደቡብ ፤ አንድ ጊዜ በሰሜን ሌላ ጊዜ በምእራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በገዛ እረኞቻቸው ሲወጉና ሲደሙ ብዕር አብሮ ይጮኻል፡፡ ያ የእረኞች አጥቂነት የባለቅኔውን ፤ የደራሲውን ፤ የፖለቲከኛውን ፤ የምሁሩን አንጀት ያላውሳል፤ ሐሞቱን ፤ የቀረች ውሳኔን ይነካካል፡፡ ያስጮኻል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱን እያጠፋ ያለው መዋቅር አርበድባጅ (Shock detachment) ቡድንም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ፤ ክብርንና ሉዓላዊነት  እየተፈታተነና ከዚህ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ (አንዳንዶችን) ያደረሰው ቤተ ክርስቲያቱን ለመጠበቅ ፤ ለመንከባከብ ፤ ለማዳን የምሁራን ቆራጥነት የማጣት ጉዳይ ነው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ጥንካሬና ችሎታ ላይ እንዳንተማመን በብዛት የምናየው በሲኖዶስ በኩል ችሎታ ማጣትንና ችሎታ ካላቸው የሊቃውንት ኃይል ጋር የበለጠ እየተለያየ መሄዱን ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውጪ ባሉ አደረጃጀቶች ላይ እምነታችንን እንዳናሳርፍ የቤተ-ክህነቱን አርበድባጅ ቡድን መቋቋም ቀርቶ በራሱ ለመቆም የሚችል አደረጃጀት ያለበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ይህን ሁኔታ ለማስቀረት የቤተ-ክህነቱ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ መቀየሩ ወሳኝነት አለው፡፡ መቀየር ማለት ሊቃውንቱ በቤተ- ክርስቲያኒቱ የመሠረተ እምነት ፤ የሥርዓተ አምልኮና ትውፊት መፋለሶች ላይ እውቀትን መሠረት ያደረገ ሂሳዊ አስተሳሰብ በነጻነት ማራመድ ፤ የቤተክህነቱን መዋቅራዊ አርበድባጅ ቡድን ያለ አንዳች መሸማቀቅ መገሰጽ ፤ ቤተ ክርስያኒቱ ያለችበት ነባራዊ እውነታ ከአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ተገንዝቦ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ማለት ነው፡፡
እናም በዚህ መልኩ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባቡ እንዲለወጥ ከተፈለገ ቅዱስ ሲኖዶስ ይከተል የነበረውን ኋላ ቀር አሰራር ለውጦ ፤ ከትንሽ ቡድን ጉጠኝነት (Sectarianism) ወጥቶ ፤ የተለያዩ ምሁራን አቅፎ እና የፖሊሲ ማውጣት ላይ አማክሮ ምእመኑን ለሚፈልገውበጎ አላማ የሚያነሳሳበት መንገድ መቀየስ አለበት ፡፡ ይህ ነው ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቀው ‹‹ኦርቶዶክሳዊነት››፡፡
በሊቃውንት በኩል ደግሞ ከላይ የጠቀስኩትን ፤ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ከልቡ ወስዶ ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ በድብቅና በሹክሽክታ ሳይሆን በግልጽና ሓላፊነት በሚሰማው መልክ በመሳተፍ ፤ ያሉትን መንፈሳዊ የትምህርት ተቋሞቻችንን እያጠናከረ ፤ የሌሉና የሚያስፈልጉትን እየፈጠረ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት መብቱን በቀናኢነት የሚጠብቅ ፤  ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣ መሆን ይገባዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት ልንማጸን የምፈልገው ወደ ኋላ ተመልካችነቱን አቁመውና ረስተው በወደፊቱ ላይ ያተኩሩ ዘንድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሲባል ካለፈው ታሪካችን ሳንማርና ሳንታረም ዘግቶና ለማኅደር አስረክቦ አይደለም፡፡
ባለፉት 22 ዓመታት የሚያሳፍርና ለአድማጭ ግር የሚያሰኝ የታሪክ ሸክም የተፈጸመ ይመስለናል፡፡ የወደፊቱን ተመልካች (Future Oriented) ሊቃውንቶቻችን እነዚህን የታሪክ ሸክም ነቁጥ በምራዊ ቅኝት ሊያሳዩን ይገባል፡፡ በጥናትና ምርምር ታግዘው ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል ? የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁኔታዎች አሁን ባሉበት አቅጣጫ ከቀጠሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምን መልክ ይኖራቸዋል? በጎ ለውጥ ለማጣት ቅዱስ ሲኖዶስ ካህናቱና ምእመኑ አንዳድ የአቅጣጫ ማስካካከያዎችን በአንድት ቢያደርጉ በቤተ ክርስቲያቱ የሚታየው ለውጥ ምንድነው? ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ ከሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን ፤ ከአገልጋዮችና ምዕመናን ምን ይጠበቃል ? ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ፤ ቤተ ክርስቲያቱ ካለችበት አዙሪት ለመውጣት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚዘጋጅ እውነተኛ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ››  ምሁራዊ መኅበረሰብ እንዲዳብር መታገል የሚጠበቅባቸው ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡